ስፖርት በዘመናችን ከውድድርነት አልፎ ሁሉም ነገር ሆኗል ማለት ይቻላል። ስፖርት በታወቁ ዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች ተሳትፎ የአገርን ስም ከማስጠራት ባለፈ ለስፖርተኛውና ለአገር ያለው የምጣኔ ሃብት ጥቅም ቀላል የሚባል እንዳልሆነ ከአገራችን ብርቅዬ አትሌቶች ተሞክሮ በመነሳት እንኳን ብዙ ማሳያዎችን መዘርዘር ይቻላል።
ስፖርት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአንድ አገር፣ግለሰብ፣ አካባቢ፣ፖለቲካዊ፣ማህበራዊና መሰል ጉዳዮች ላይ ያለው ተጽእኖ እየጎላ መጥቷል።
በተለይም የተለያዩ አገራት ስፖርትን በመጠቀም የገጽታ ግንባታ ስራዎችን ለመስራት ሲረባረቡ ማየት በስፋት እየተለመደ መጥቷል።
ለዚህም ሳውዲ ዓረቢያና ኳታርን የመሳሰሉ በነዳጅ ሃብት ኪሳቸው ያበጠ አገራት ገጽታቸውን ለመገንባት ታላላቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ለማዘጋጀት ከሚገቡበት ፉክክር ባለፈ ታላላቅ የስፖርት ክለቦችን በቢሊየን ዶላሮች አውጥተው ለመግዛት ሲረባረቡ ይስተዋላል።
በአገራችንም እንደ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ያሉ ስፖርታዊ ኩነቶች የፈጠሩት የማህበረሰብ ንቅናቄና በጎ ተግባራት ተጽኗቸው ምን ያህል የጎላ እንደሆነ ይታወቃል። የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽንም ሰሞኑን ስፖርትን ለመልካም አላማ ተጠቅሞ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ የመታበትን የተሳካ የጎዳና ላይ ውድድር አከናውኗል።
ኮሚሽኑ ከሪያ ስፖርትስ ኢትዮጵያ እንዲሁም ከሌሎች ባለድርሻ ተቋማት ጋር በመተባበር የደንበል ሃይቅ አስር ኪሎ ሜትር ሩጫን ባለፈው እሁድ በባቱ ከተማ ደንበል ሃይቅ ዳርቻዎች አካሂዷል። “እየሮጥን የደንበል ሃይቅ ዳርቻን እናጽዳ” በሚል መሪ ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ በስምጥ ሸለቆዋ ባቱ ከተማ የተካሄደው ውድድር አንድ ሺ አምስት መቶ ሰው ተሳትፎበታል።
የውድድሩ ዋና አላማ በባቱ ከተማ የሚገኘው ደንበል ሃይቅ ዳርቻ በቆሻሻ ምክንያት ካንዣበበት አደጋ ለመታደግና የከተማዋን የቱሪስት መስህብነት ለማሳደግ ነው። የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ነጋ ወዳጆ፣ የውድድሩ ዋና አላማ የባቱ ከተማን በተለይም በደንበል ሃይቅ ዳርቻ የተከማቸው ቆሻሻ በማጽዳት የቱሪስት መስህብነቱን ለማሳደግና በውሃው ላይ ሊፈጠር የሚችለውን ብክለት ለመከላከል መሆኑን ከውድድሩ አስቀድሞ በተሰጠው መግለጫ ተናግረዋል። ውድድሩ በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ግንዛቤ ለመፍጠር ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው በመግለጽ የከተማውን ሕዝብ በከፍተኛ ሁኔታ እንዳነሳሳም አቶ ነጋ አክለዋል።
ውድድሩን በቀጣይነት በየዓመቱ በማካሄድም የአካባቢው ማህበረሰብ እየተዝናና የከተማውንና የሃይቁን ጽዳት በመጠበቅ ያለውን የተፈጥሮ ሃብት እንዲጠቀምበት ከባለድርሻ አካላት ጋር አብሮ የመስራት ጥረቱን በማጠናከር ይህ መልካም ተሞክሮ በሌሎች ከተሞችም እንደሚቀጥል አስረድተዋል።
የባቱ ከተማ ከንቲባ ገዛኸኝ ደጀኔ በበኩላቸው፣ የደንበል ሃይቅ በኦሮሚያ ክልል ከሚገኙ ውብ የተፈጥሮ ሃብቶች አንዱ ብቻ ሳይሆን በርካታ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊቶች የሚከወኑበት ስፍራ መሆኑን በመጥቀስ ያለው ትልቅ የቱሪዝም አቅም በመገናኛ ብዙሃን በበቂ ሁኔታ እንዳልተዋወቀ ተናግረዋል።
ይህንን ለመቀየርም የሩጫ ውድድሩ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው አስረድተዋል። የሃይቀለ ዳርቻ ከሃያ ሺ ሄክታር በላይ ያለማ ክፍት ቦታ ስላለው የጎዳና ላይ ሩጫው ማህበረሰቡ ቆሻሻን በማጽዳት የአገር ውስጥና የውጪ ኢንቬስተሮችን በመሳብ ትልልቅ የልማት ስራዎች እንዲሰሩ ያግዛል የሚል እምነት እንዳላቸውም ከንቲባው ተናግረዋል።
የሩጫ ውድድሩን ያስተባበረው ሪያ ስፖርትስ ኢትዮጵያ ስራ አስኪያጅ ቃለአብ ጌታነህ፣ ስፖርትን ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በማቆራኘት ግንዛቤ ከመፍጠር አኳያ የጎዳና ላይ ውድድሩ ጥሩ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመዋል። በቀጣይም ከአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ጎን ለጎን የውድድሩን ደረጃ ከፍ በማድረግ በአካባቢው የሩጫ ውድድር እድሎች እንዲፈጠሩ መሰረት እንደሚሆን አብራርተዋል።
የጎዳና ላይ ውድድሩ ከአካባቢ ጥበቃና ከቱሪዝም አኳያ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ እንዳለ ሆኖ በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ የማስ ስፖርት እንቅስቃሴን በማስፋፋትና ስፖርትን ባህሉ ያደረገ ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት እንደሚያጠናክር ታምኖበታል።
ከዚህ ባሻገር የውድድሩን አቅምና ደረጃ በማሳደግ በቀጣይ ዓመታት በአካባቢው የሩጫ ተሰጥኦ ላላቸውና የውድድር እድሎችን ላላገኙ ወጣቶች ትልቅ እድል መፍጠር እንደሚቻል ታምኖበታል። በአገር አቀፍ ደረጃም ለበርካታ አትሌቶች የውድድር እድልና ሌላ አማራጭ በመሆን እንደሌሎቹ የአገራችን የጎዳና ላይ ውድድሮች የማደግ ተስፋ እንደሚኖረው ይጠበቃል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን መጋቢት 14 /2014