እ.ኤ.አ ከ2015 የቤጂንግ የዓለም ቻምፒዮና ወዲህ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከአንድ እስከ ሦስት ተከታትለው በመግባት ከትናንት በስቲያ በሰርቢያ ቤልግሬድ በተጠናቀቀው የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና የአረንጓዴውን ጎርፍ ታሪክ ደግመዋል።
በዚያ የቤጂንግ ቻምፒዮና አምስት ሺ ሜትር ሴቶች ውድድር አልማዝ አያና፣ ሰንበሬ ተፈሪና ገንዘቤ ዲባባ አረንጓዴውን ጎርፍ ከሠሩ በኋላ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለያዩ ታላላቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ተመሳሳይ ታሪክ አልሠሩም።
ባለፈው ቅዳሜ ምሽት ግን ወጣቶቹ እንስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና ታሪክ አዲስ ክስተት ሆነዋል። አዲስ ክስተት ያደረጋቸውም በቻምፒዮናው ከአርባ አመታት በላይ የዘለቀ ታሪክ የትኛውም አገር በየትኛውም የውድድር ዓይነት ከአንድ እስከ ሦስት ተከታትሎ በመግባት ሁሉንም ሜዳሊያ ጠራርጎ መውሰድ አለመቻሉ ነው።
በአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር ፍጻሜ አረንጓዴውን ጎርፍ እየመራች የወርቁን ሜዳሊያ ያጠለቀችው የሃያ አምስት አመቷ ድንቅ ኢትዮጵያዊት አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ፣ ባለፉት አምስት ሳምንታት በቤት ውስጥ የዙር ውድድሮች ካሳየችው ድንቅ አቋም አኳያ የቻምፒዮናው አሸናፊ መሆኗ አይደንቅም።
ጉዳፍ በውድድሩ በራሷ ተይዞ የሚገኘውን የቤት ውስጥ የርቀቱን የዓለም ክብረወሰን ለማሻሻል ያደረገችው አስደናቂ ጥረት ባይሳካም ውድድሩን በወርቅ ሜዳሊያ ብቻ አልፈጸመችም፣ እኤአ በ2008 በገለቴ ቡርቃ ተይዞ የነበረውን የቻምፒዮናውን ክብረወሰን ማሻሻል ችላለች። በሦስት ታላላቅ ውድድሮች በተለያዩ ርቀቶች የነሐስ ሜዳሊያዎችን ያጠለቀችው ጉዳፍ በቤልግሬድ ወደ ወርቅ ሜዳሊያ በመሸጋገር በአትሌቲክስ ሕይወቷ የመጀመሪያውን ትልቅ ስኬት አጣጥማለች።
እኤአ በ2016 የቤት ውስጥ ቻምፒዮና በ1500 ሜትር፣ በ2019 የዶሃ የዓለም ቻምፒዮና በ5ሺ ሜትር እንዲሁም ባለፈው ቶኪዮ ኦሊምፒክ በተመሳሳይ ርቀት የነሐስ ሜዳሊያዎችን ማሸነፏ ይታወቃል። ጉዳፍ ታላቁን ድል በቻምፒዮናው ክብረወሰን ታጅባ በ3:57:19 ስታጠናቅቅ አረንጓዴውን ጎርፍ ለማብሰር ተከትላት የገባችው እኤአ በ2014 የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊ የነበረችው ድንቅ ኢትዮጵያዊት አትሌት አክሱማይት አምባዬ ናት።
አክሱማይት በውድድሩ መጨረሻ ከጉዳፍ ጋር የነበራት ልዩነት እንደ አጭር ርቀት ሰፊ የሚባል ቢሆንም የብር ሜዳሊያውን የግሏ ለማድረግ ብዙም አልተቸገረችም።
አክሱማይት 4:02:29 በሆነ ሰዓት ውድድሩን ስታጠናቅቅ የአረንጓዴው ጎርፍ ታሪክ እንዲደገም አሻራዋን ያሳረፈችው ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት ድንቅ አትሌት ሂሩት መሸሻ ነሐሱን ያጠለቀችው 4:03:39 በሆነ ሰዓት በማጠናቀቅ ነው።
በተያያዘ ዜና ትናንት በተካሄደ የሦስት ሺህ ሜትር ወንዶች ፍጻሜ ኢትዮጵያ የወርቅና የብር ሜዳሊያዎችን አግኝታለች።
በሦስት ሺህ ሜትር ወንዶች ፍጻሜ አትሌት ሰለሞን ባረጋ 7 ደቂቃ ከ41 ሰከንድ ከ38 ማይክሮ ሰከንድ አሸናፊ በመሆን ለኢትዮጵያ በሻምፒዮናው ሦስተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ አስገኝቷል። ሌላኛው አትሌት ለሜቻ ግርማ 7 ደቂቃ ከ41 ሰከንድ ከ63 ማይክሮ ሰከንድ ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ አግኝቷል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን መጋቢት 12 /2014