(“ሀ… ሁ… እውቀት ይስፋ፣ ድንቁርና ይጥፋ – ይህ ነው የኢትዮጵያ ተስፋ” ተስፋ ገብረሥላሴ ዘብሔረ ቡልጋ)፤ “ብዙ ጊዜ ትምህርትን እድሜ አይወስነውም” ሲባል ነው የሚሰማው። እኛ ደግሞ እንላለን “ኧረ ቦታም፤ ምንም … አይወስነውም”።
በተለይ በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ ሆነንና ተንቀሳቃሸ ትምህርት ቤቶች ሁሉ በተስፋፉበት በዚህ ዘመን ትምህርትን ስለሚገድቡ ነገሮች ከማውራትና ጉንጭ ከማልፋት ይልቅ፣ ስለማይገድቡት እያወራን ስለተደራሽነቱ አብዝተን ብንደክም የተሻለ ይሆናል።
በመሆኑም ከማንም በፊት የመሃይምነት ቀንደኛና ግንባር ቀደም ጠላት የነበሩትን የተስፋ ገ/ሥላሴ ዘብሔረ ቡልጋን የፊደል ገበታ እያስታወስን፤ ለመነሻ ያስቀመጥናትን ጥቅስ እያሰናሰልን እንቀጥል።
ይህ ጸሐፊ ለምን እንደ ሆነ (ባያውቅም?) ብዙ ነገሮቻችን ወደ ኋላ፣ በጣም ወደ ኋላ ሲሄዱ እየታዘበ ሰንብቷል።
ከተለያዩ የሰውም ሆነ የሰነድ ምንጮች መረዳት እንደ ቻለው ከሆነ ወሳኝ ወሳኝ ጉዳዮች ወደ ኋላ ተቀልብሰዋል። አንዳንዶቹንም ወደ ነበሩበት ለመመለስ ከፍተኛ ወጪን እየጠየቁ ናቸው። በምሳሌ እንመልከታቸው።
በዘመነ ደርግ ማረሚያ ቤቶች (“እስር ቤቶች” ይባሉ የነበሩት) ከማንኛውም መደበኛ ትምህርት ቤት ባልተናነሰ፣ እንደውም በተሻለ የ12ኛ ክፍል ፈተና (ማትሪኩሌሽን) በከፍተኛ ነጥብ የሚታለፍባቸው የጀት ተማሪዎች መፍለቂያ ነበር ይባላል። አሁን የለም።
በከፍተኛ ውጤት ከማረሚያ ቤት ወደ ተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የሚገቡ ተማሪዎችም ሥራቸው ከመስቀል (ሰቃይነት) ደብር ንቅንቅ ብሎ አያውቅም ይባላል። የዛሬ ዩኒቨርሲቲዎች ያንን ሁሉ እድል ተነፍገዋል። ይህ በዚሁ ይብቃን።
በፊት በፊት በመላ አገሪቱ የነበሩ ቤተ መጻሕፍት ቁጥራቸው የትየለሌ ነበር ይባላል (በአንድ ወቅት እንዳለጌታ ከበደ (ፋክት?) መጽሔት ላይ በቁጥር፣ በስፍራ፣ በአይነት … በመዘርዘር ለንባብ አብቅቶ እንድንታዘብ ሁሉ አድርጎን እንደ ነበር አስታውሳለሁ)። ዛሬስ፣ ዝም ነው። በዚሁ በእኛው እድሜ ፒያሳ የጥበብ ማዕከል ነበረች። ዛሬ፣ የመንግሥት ሲኒማ ቤቶቹ ካልተቆጠሩ በስተቀር፣ አንድም የለም። በሙሉ ወደ ጨርቅ፣ ሻይ፣ ጭማቂ …. ቤትነት ተለውጠዋል።
እንዲህ እንዲህ እያልን ብንሄድ ዝርዝሩ ብዙ ሲሆን “ዝርዝር ኪስ ይቀዳል” የሚለውንም ሊያመጣ ይችላልና በዚሁ በማብቃት ወደ ርዕሳችን፣ “የዲላው ማረሚያ ቤት አስኳላ?” እንመለስ። በእርግጥ ይህ ጸሐፊ ከዚህ በፊት የተለያዩ ማረሚያ ቤቶችን የማየት እድል አልገጠመውም።
በመሆኑም የማይሆን ንጽጽር ውስጥ ገብቶ አይዳክርም፤ ማለትም የዲላ ማረሚያ ቤት ከሌሎቹ በዚህ በዚህ ይበልጣል፤ በዚህ በዚህ ደግሞ ያንሳል … እያለ የሚመዝነው ነገር የለም ማለት ነው። በመሆኑም በራሱ፣ በዲላ ማረሚያ ቤት ላይ ብቻ በመመስረት ስለ ማረሚያ ቤቱ አጠቃላይ ገጽታ አንዳንድ ነገሮችን ያነሳል።
በተለይም፣ ከአምዱ ባህርይ አኳያ በትምህርት ላይ በማተኮር ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከተው አካል ጋር ይወያያል። ዲላ ማረሚያ ቤት እንደ ማንኛውም ማረሚያ ቤት ያው ማረሚያ ቤት ነው። ታራሚዎች፣ አስተዳደርና የተለያዩ የሥራ ክፍሎች አሉት።
ዛሬ እሱን አንመለከትም። ወደ ዲላ ማረሚያ ቤት ገና ሲገባ ለየት ያለ ነገር የሚታየው ከሃይማኖት ጋር ያለው ጉዳይ ሲሆን፤ ታራሚዎች መንፈሳዊ አገልግሎት የሚያገኙባቸው የተለያዩና በሥነ ሥርአት የተደራጁ (ውጪ ካለው የማይለዩ)፤ የየራሳቸው የእምነት ተቋማት አሏቸው።
በመሆኑም ሁሉም ታራሚ እንደየ ኃይማኖቱ ሥነ ሥርአቱን ይከታተላል ማለት ነው። ይሄ አንድ ሲሆን ማረሚያ ቤቱን ለየት የሚያደርጉት ሌሎች ገጽታዎችም አሉት። በስፍራው ተገኝተን እንደ ተመለከትነው በክልሉ መንግሥት በጀት የሚተዳደረው ዲላ ማረሚያ ቤት በተለያዩ የክስ አይነቶች ምክንያት ፍርደኞች የሆኑ፣ በቀጠሮ ያሉ ወዘተ ታራሚዎች የሚገኙበት ትልቅ ግቢ ነው።
በዚህ ሰፊ ግቢ ውስጥ የተለያዩ አይነት ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ ሲሆን አንዱም እየተስፋፋ በመሄድ ላይ የሚገኘው የዲላ ማረሚያ ቤት አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው።
በወቅቱ በዚሁ ገጽ ላይ ለንባብ ባበቃነው ጽሁፍ እንዳስነበብነው ብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተመጻሕፍት ኤጀንሲ በ800 ሺህ ብር ወጪ የገዛቸውን ከስድስት ሺህ በላይ መጻሕፍት በዞኑ ስር ለሚገኙና ከትምህርት ቤቶች ጀምሮ ላሉ ተቋማት ያስረከበ ሲሆን፤ ከእነዚህ መካከል አንዱ ይሄው የዲላ ማረሚያ ቤቶች አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው። የርክክብ ፕሮግራሙም በተለያዩ ሥነሥርዓቶች ተከናውኗል።
በእለቱ (እሁድ የካቲት 15 ቀን 2014 ዓ.ም)፣ ማለትም የንባብ ንቅናቄው በማረሚያ ቤቱ ትምህርት ቤት በተካሄደበት እለት “መጻሕፍት ለእውቀት ገበታ፤ መዛግብትና የጽሑፍ ቅርስች ለዘመን ትውስታ።” በሚል መሪ ቃል የተካሄደው “የወጣት ተኮር ንባብ እና የምርምር ንቅናቄ መድረክ” በሚገባ የተስተጋባና በደማቅ ሥነ ሥርዓት የተከናወነ ሲሆን፤ መላው የማረሚያ ቤቱ ማኅበረሰብ የተሳተፈበት፣ በተለያዩ ተሳትፎዎች ያሸነፉ የተሸለሙበት፤ ትምህርት ቤቱ እንደ አንድ ተቋም በርካታ መጻሕፍትን ከኤጀንሲው በድጋፍ ያገኘበት፤ ታዋቂ አርቲስቶች፣ ደራሲያን፣ በአንድ ወቅት ታራሚ የነበሩ አሁን ግን ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊነት ላይ ያሉ ሰዎች አነቃቂ ንግግርና የታራሚዎችን ስነ ልቦና ግንባታ ያደረጉበት ሆኖ አልፏል።
ከላይ እንዳልነው በማረሚያ ቤቱ ውስጥ ያለው የኅብረተሰብ ክፍል በእድሜና በፆታ የሚገለፅ፣ በሃይማኖት የሚገደብ፣ በብሔር የሚሰላ …. አይደለም። ከአንድ አመት ልጅ (ልጃቸውን ይዘው የገቡ፣ እዛው የወለዱ …) ጀምሮ ሁሉም የእድሜ ክልል አባላት አሉ። በትምህርት ገበታቸው ላይ የሚገኙትም እንደዛው። ከሁሉም ወገን ያሉ ናቸው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ጉዳዩ ብዙም የሚዲያ ሽፋን ካላገኙት አካላት አንዱ ነውና ስለ አጠቃላይ የት/ቤቱ ሁኔታ እንዲያስረዱን ወደ ትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አቶ ደስታ ጡጎ ቢሮ አመራን። በደስታ ተቀበሉን። ስለ ጉዳዩም እንዲህ ሲሉ አስረዱን፡፡ እኔ ወደ’ዚህ ተመድቤ የመጣሁት በ2010 ዓ.ም ነው። በዛን ጊዜ ከ1ኛ እስከ 7ኛ ክፍል ነበር። በ2011 ዓ.ም 8ኛ ክፍል እውቅና አግኝቶ ተጨመረ። አሁን ከ1ኛ እስከ 8ኛ የክፍል ደረጃ ድረስ ታራሚዎችን ያስተምራል። በክልሉ መንግሥትም ይደገፋል፡፡
ተማሪዎቻችን በሚያስገርም ሁኔታ የትምህርት ፍላጎት ያላቸው ናቸው። ትምህርታቸውን በሚገባ ይከታተላሉ። የሚሰጣቸውን ሁሉ በአግባቡና በጊዜው ይሠራሉ። እኛም ሁሌም ከጎናቸው አንጠፋም። አስፈላጊውን እገዛ ሁሉ እናደርግላቸዋለን። የምናስተምራቸው አካዳሚያዊውን ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊውንም (ከዋናው ክፍለ ጊዜ ውጪ) ነው።
የኃይማኖት ተቋማት አሉ፤ በእነሱ በኩል መንፈሳዊነትን ይከታተላሉ። ብዙዎቹም ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን በሚገባ የሚከታተሉ፤ የባህርይ ለውጥም ያመጡበት ናቸው። ተማሪዎቻችን በተቻለ መጠን ሁሉንም አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ እየሞከርን ነው። ለምሳሌ፣ በባለሙያ የተደገፈ የማማከር (ካውንስሊንግ) አገልግሎት አለ።
በዛ በኩል ችግሮች እንዲፈቱ ይደረጋል። ሌሎች አገልግሎቶችም ስላሉ ምንም ችግር የለም። መምህራንን በተመለከተ ከ1ኛ እስከ 8ኛ የሚያስተምሩ 14 ባለሙያዎች ያሉ ሲሆን፤ ከውጪ ማለትም ከዲላ ከተማ ተመድበው እዚህ እየሰሩ የሚገኙ ናቸው። የዲግሪም የዲፕሎማም ምሩቃን አሉ። ከእነዚህ ውስጥም ማቹርድ የሆኑ መምህራንም አሉ [“ማቹርድ የሆኑ” የሚለው እዛው ታራሚ ሆነው በሥነ ምግባራቸው የተመሰገኑና የማስተማር ልምድና ሙያ ያላቸውን መምህራን ለማመልከት ነው]።
እነዚህን ሁሉ ይዘን ነው እየሠራን ያለነው። ተማሪዎችን በተመለከተ ብዙ ጊዜ ሰው ከውጪ እዚህ ያለው የወንጀለኞች ስብስብና የባህርይ ችግር እንዳለ አድርጎ ነው የሚያስበው፤ ነገር ግን ያለው ሁኔታ እንደሱ አይደለም። ተማሪዎቻችን ጥሩ ባህርይ ያላቸውና ጎበዞች ናቸው። ከፍተኛ የሆነ የባህርይ ለውጥ እያመጡ፤ እየበሰሉ፤ የማረሚያ ቤት ቆይታቸውን እንደ አንድ ጥሩ አጋጣሚና እድል እየተጠቀሙበት ነው ያሉት።
አሁን ያለው ትልቁ ችግር ትምህርት ቤቱ እስከ 8ኛ ክፍል ብቻ መሆኑ ነው። በቃ፣ 8ኛ ሲደርሱ ያቆማሉ። ምክንያቱም 9ኛ፣ 10ኛ … ክፍሎች አልተከፈቱም። እነሱ ቢቀጥሉና የት/ቤቱ ደረጃው ቢያድግ ብዙ የተማሩ፣ የሰለጠኑ … ሰዎችን ማፍራት ይቻል ነበር። በእርግጥ እንዲያድግ ዞን ትምህርት መምሪያውን እየጠየቅን ነው፤ ወደ ፊት ይሳካል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።
ከቀለም ትምህርት ባለፈ ግን የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ይሰጣል። በዛም እየሰለጠኑ ነው። ጊዜአቸውን ጨርሰው የወጡና ትምህርታቸውን በመቀጠል፣ ከተማ ውስጥ በመማር 10ኛ እና 11ኛ የደረሱም አሉ። ባጠቃላይ ታራሚዎች ታርመውና ተምረው ነው የሚወጡት። እኔ እዚህ ከመጣሁ የማየው ይሄንን ነው። ከአዋቂዎቹ በተጓዳኝ ግን በማረሚያ ቤቱ ሕፃናት በብዛት አሉ፤ የእነሱስ ጉዳይ ላልከው እነሱም ይማራሉ።
የሚማሩት ግን እዚህ ሳይሆን እየተከፈለላቸው ከተማ ውስጥ ባሉ መዋእለ ሕፃናት ውስጥ ነው። ሆኖም ትምህርት ቤቱ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ እንዲቻል ደግሞ በየደረጃው ያሉ አካላት፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉ ይህንን ትምህርት ቤት እንደ ማንኛውም መደበኛ ትምህርት ቤት ቢያዩትና አስፈላጊውን ክትትል በማድረግ የጎደለውን እያዩ ቢያሟሉለት ተቋሙ ከፍተኛ ላይ ደረጃ መድረስ ይችላል። መምህራን የሚደጎሙበት መንገድ ቢፈለግ፤ የክፍል ደረጃው የሚያድግበት ሁኔታ ቢመቻች … ጥሩ ነው።
የብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጽሐፍት ኤጀንሲ (ወመዘክር) ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀውን (ከየካቲት 12 እስከ የካቲት 16 ቀን 2014 ዓ.ም)፣ ያደረገውን የመጽሐፍት ድጋፍ ስመለከት የተወለድኩ ያህል ነው የቆጠርኩት። በጣም ነው ደስ ያለኝ። አንድ የምለው ነገር ቢኖር ቢቀጥል ነው፤ ሁሌም ቢቀጥል።
ወደ ፊት ደግሞ ምን ያህል አንብበዋል የሚል ክትትል ለማድረግ ተመልሰው ቢመጡ ጥሩ ነው። ይሄንን ነው አደራ የምለው። ይሄንን ሁሉ መጽሐፍት አምጥተው ስለሰጡንም በጣም ነው የማመሰግናቸው። ከርዕሰ መምህሩ አቶ ደስታ ጡጎ በተጨማሪ ታራሚ ተማሪዎችን ያነጋገርን ሲሆን ትምህርት በመሰጠቱ ደስተኞች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ቢሻሻል ያሉትንም ገልፀውልናል። ማረሚያ ቤት መግባት የሕይወት መጨረሻ አይደለም፤ በመሆኑም እኛም ሌሎች ማረሚያ ቤቶች ከላይ በአጭሩ ከተናገርንለት የዲላ ማረሚያ ቤት ትምህርት ቤት (አስኳላ) ምንም ትሁን ምን የሚወስዱት ፍሬ ነገር አይጠፋምና የተሻሉትን ማየቱ ጊዜው ሊረዝም የሚችል ቢሆን እንኳን ዲላ ማረሚያ ቤት ያለበት ደረጃ የደረሱ ማረሚያ ቤቶችን በቅርብ የምናይበት እድል ይኖረናል ብለን እናስባለን።
በመጨረሻም፣ ልክ እንደ ብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት ኤጀንሲ ሁሉ ሌሎች ተቋማትም እንደየተቋማቸው ባህርይ ማረሚያ ቤቶችን ይጎበኙ ዘንድ አደራ ስንል በትህትና ነው።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን መጋቢት 12 /2014