ወቅታዊነት ለፋሽን ዋንኛ መገለጫው ነው። ዘናጮች እንደ አየር ንብረትና አካባቢያዊ ሁኔታ ከልብስ እስከ ጫማ መርጠውና ተስማሚውን ለይተው ለምቾትም ለማማርም አልባሳትን መርጠው ይጎናፀፋሉ።
የዛሬ ጉዳያችን ጫማ ነው። በጋ ላይ በብዛት የሚደረጉ ጫማዎች ክረምቱን መደርደሪያ ላይ ይከርማሉ። እንዳሁኑ በጋ ሲሆን ደግሞ ከመደርደሪያ ወርደው ፀድተው ለመጫማት ይበቃሉ። ክረምት ላይ ያገለገሉት ቡትሶች አሁን ወቅታቸው አይደለምና ለበጋ ጫማዎች ቦታቸውን ለቀዋል።
በሞቃታማው ወቅት በአብዛኛው የሚዘወተሩት እስኒከርና ሸራ ጫማዎች ሲሆኑ፣ ገበያውም ላይ በብዛትና በስፋት ወቅቱን እና ፋሽንኑ ባሟሉና ባማሩ ዲዛይኖች ይገኛሉ።
በተለምዶ ስኒከር በሚል ጥቅል ስም የሚጠሩት የተለያዩ ከቆዳ፣ ከሸራና ከመሳሰሉት የሚሰሩ ስኒከር ጫማዎች ደግሞ በተለይ በበጋ ወቅት በብዛት ይለበሳሉ፤ በዘመናችን ተወዳጅነትና ተቀባይነት እያገኙ መሆናቸውን ተከትሎ የጫማ ቤቶች ጥሩ እንጀራ ሆነዋል።
እነዚህ ጫማዎች አዳዲስ ብቻም አይደሉም የተደረጉትም በስፋት ገበያ ላይ ይታያሉ። ቀደም ባለው ጊዜ ሰዎች በአዘቦት ቀን ብቻ ያደርጓቸው ነበር፤ ስፖርተኞች ደግሞ ለአካል ብቃት እንቅስቃሴ፣ ለውድድር፣ ጅምናዚየሞችን ለአካል እንቅስቃሴ ይፈልጓቸዋል።
ቀላልና ምቹ መሆናቸውንም ተጠቃሚዎችም ይመስክራሉ። ለጉዞ ወቅትም ተፈላጊ እየሆኑ መጥተዋል፤ በዘመናችን ደግሞ ብዙ ሰዎች በማንኛውም ቀን በሥራ ቀንም ጭምር ለመጫማት ምርጫቸው አድርገዋቸዋል።
አንዳንዶቹን ስኒከሮች ወንዶችም ሴቶችም ጭምር ያደርጓቸዋል። ወንድ የእህቱን አዲዳስ ጫማ ከበቃው ተጫምቶ መሄድ ይችላል። የሴት ጫማ አጠለቀ ብሎ የሚያማው ወይም የሚያብጠለጥለው የለም።
አሁን አሁን ደግሞ ለወንዶችም ለሴቶችም የሚሆኑ ስኒከር ጫማዎች ይመረታሉ። ሁሉም ስኒከር ጫማዎች ቀለል ያሉ ለእግር ምቾት የሚሰጡ ስለመሆናቸው ጫማውን አድርገው ለሥራ የሚንቀሳቀሱ ሰዎችም በጫማ ንግድ የተሰማሩም ይናገራሉ።
በመርካቶ በአዳራሽ ገበያ አካባቢ በዚሁ ጫማ ንግድ የሚተዳደሩት አቶ ሙባሪክ አስራር ስኒከር ጫማዎቹ በጣም ተመራጭ ተወዳጅ መሆናቸውን ይገልጻሉ። ለእግር ቀለል ያሉና ምቾት የሚሰጡ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ወንዶችም ሴቶችም ሊያደርጓቸው የሚችሉ የጫማ ዓይነቶች እንዳሉም ያብራራሉ፤ አንዳንዶቹ ስኒከር ጫማዎች ለበጋም ለክረምትም ተስማሚ መሆናቸውን የሚገልጹት አቶ ሙባሪክ፣ ዋጋቸው እንደ ጫማዎቹ ሞዴል እንደሚለያይም ነው የሚናገሩት።
ከውጪ የሚመጡት ውድ መሆናቸውን ይናገራሉ። የተወሰነ አገልግሎት የሰጡ ወደ አገር ውስጥ እንደሚገቡም ነው የሚገልጹት። እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ወንዶችም ሴቶችም አድርገው ሊንቀሳቀሱባቸው የሚችሉ ጫማዎች እንዳሉ አቶ ሙባሪክ ጠቁመው በተለይ ሴቶች ቀሚስ አድርገው ሲጠቀሙባቸው እንደሚታይና ይህም ለእግር ተስማሚና ቀለል ያሉ ጫማዎች መሆናቸው ያሳያል።
በዚህም በሰዎች ዘንድ ተፈላጊነታቸው እየጨመረ ነው ሲሉ ተናግረዋል። በአራዳ ክፍለ ከተማ በፒያሳ አካባቢ አዲዳስ ወይም ስኒከር እና ቆዳ ጫማዎች በመሸጥ የሚተዳደሩት አቶ ተክሉ ተስፋዬም የአቶ ሙባሪክን ሀሳብ ይጋራሉ።
ስኒከር ጫማዎቹ በዘመናችን በጣም ተፈላጊነታቸው እየጨመረ መሆኑን ገልጸው፣ ቀደም ሲል ሴቶች ዞር ብለው የማያዩት እንዳልነበር ያስታውሳሉ። ምክንያቱም የወንዶች ጫማዎች ተብለው ይታሰቡ እንደ ነበር ጠቅሰው፣ አሁን ግን በሴቶችም ጭምር ተፈላጊ መሆኑን ይናገራሉ። አዲዳስ ጫማዎቹ በአገር ውስጥ መመረት እንደጀመሩ የሚናገሩት አቶ ተክሉ፣ ፋብሪካዎቹ ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅ ጥረት ሲያደርጉ እንደማይታዩ ግን ያመለክታሉ። ስኒከሮች በቢሮ ሠራተኞች፣ ነጋዴዎች፣ የፋብሪካ ወዛደሮች፣ ጉልበት ሠራተኞችና በተለያየ የሥራ መስክ የተሰማሩ ሁሉ እያዘወተሯቸው መሆኑን ያብራራሉ።
የአገልግሎት ዘመናቸውም ረጅም መሆኑን ይናገራሉ። ተጠቃሚው ጥራታቸውን ሶሉን ገበሩን በማየት ያውቃቸዋል፤ በዕድሜ ገፋ ያሉ ሰዎች በብዛት ይጠቀሙዋቸዋል፤ በተለይ ትንሽ የእግር ሕመም ካለባቸው ወይም እንደ ስኳር ዓይነት ህመም ያለባቸው ለጤንነታቸው እንደሚመርጡዋቸውም ነው አቶ ተክሉ የሚያብራሩት።
ጫማዎቹ ሁሉን አካታች ስለመሆናቸው ሲያብራሩም፡ በሕፃናት፣ በወራዙት (ወጣት) እና በአዛውንት የዕድሜ ክልል ያሉ ሲያደርጉት ለማየት በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ዞር ዞር ማለቱ ብቻ ይበቃል ይላሉ። ጎረምሳም ሆነ ጎልማሳ፣ ኮረዳም ሆነ ኮበሌ፣ ወዘተ ወንዶችም ሴቶችም ተጫምተውት ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀሱ ማየት ይቻላል።
አንዳንዶቹ አዲዳስ ስኒከር ጫማዎች በውሃ ብቻ ተወልውለው አራት ዓመትና ከዚያ በላይ ውበታቸውም ምቾታቸውም ሳይለወጥ እንደሚያገለግሉ ያነጋገርኩዋቸው ተጠቃሚዎችም አስረድተውኛል። ሌሎች ተጠቃሚዎች እንደሚሉት አንዳንድ ስኒከሮች የተወራላቸውን ያህል ምቹና ለብዙ ጊዜ የሚያገለግሉ አይደሉም።
ተመሳስለው የተሰሩ ስኒከሮች እንዳሉም ጠቁመው፣ ዋናዎቹ ምርቶች ከተገኙ በሙቀትም በክረምትም ጊዜ እንደሚያገለግሉ ምቾት እንዳላቸውም ይገልጻሉ፤ ያነጋገርናቸው የጫማ ፋብሪካዎች እንዲሚሉት ስኒከር ጫማዎች በአገር ውስጥም ይመረታሉ፤ ማምረት ከተጀመረ አምስት ዓመት ይጠጋል፤ ምርቶቹም በየመደብሮቹ ለገበያ ቀርበዋል፤ ከፍተኛ ተቀባይነትም አላቸው። ከደንበኞቻቸው ጥሩ ግብረ መልስ እንዳላቸውም ነው የሚናገሩት።
ይህን ተከትሎም የቀለም ምርጫ ዲዛይን ካለው የደንበኞች ፍላጐት አንፃር እያስተካከሉ ከፋሽኑም ጋር እንዲሄድ እያረጉ ያመርታሉ። ሰው በጫማ ረገድ ቀለል ወዳለ ነገር እያዘነበለ መሆኑን ይጠቅሳሉ፤ ሲሄድ የሚመቸውን መርገጫቸው (ሶላቸው) በጣም ቀለል ያሉ ፤የስፖርት ዓይነት ጫማዎችን እያዘወተረ መሆኑን ይገልጻሉ። ከእዚህም መረዳት እንደሚቻለው ጫማዎች በፋሽንነት እንደሚፈለጉም ነው።
ከነጋዴዎቹም ከተጠቃሚዎቹም ከፋብሪካዎቹም የተገኙ መረጃዎች እንዲሁም ኅብረተሰቡም ስኒከር እያዘወተረ የመጣበት ሁኔታ ጫማዎቹ በእርግጥም ተፈላጊ እየሆኑ መምጣታቸውን ነው። ይህ ፍላጎት ግን እየተሟላ ያለው ከውጪ በሚመጡ ምርቶች ነው። ስኒከር ጫማዎች ከውጪ የሚገቡ መሆናቸው ብቻ አይደለም አሳሳቢ የሚሆነው።
የተደረጉ ስኒከር ጫማዎች በሕገወጥ መንገድ በስፋት ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ እየተደረገ ያለበት ሁኔታም አገርንም ይጎዳል፤ የጫማዎቹን በስፋት በአገር ውስጥ ማምረት የግድ ያደርገዋል።
ጫማዎቹ በአገራችን በፋሽንነት ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ እንዲሁም በአገር ውስጥም የሚመረቱ እንደመሆናቸው፣ ፋሽኑ የሚፈልገውን ለማሟላት የጫማ ኢንዱስትሪዎቻችን ይህን ፍላጎት መሠረት ያደረገ አመራረትን መከተል ይኖርባቸዋል።
ገበያው አዳዲስ የስኒከር ጫማ ፋብሪካዎችንም እንደሚፈልግ ተረድቶ መሥራት የመንግሥትም የባለሀብቱም የቤት ሥራ መሆን ይኖርበታል።
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን መጋቢት 12 /2014