ጀግናው ደጃችማች ዑመር ሰመተር ሌላው የሳምንቱ በታሪኩ አምድ ርእሰ ጉዳያችን ናቸው። እኚታ ታላቅ የአገር ባለውለታ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት በዚህ ሳምንት መጋቢት 6 ቀን 1936 ዓ.ም በመሆኑም ነው ልናስታውሳቸው የወደድነው።
ዑመር ሰመተር የተወለዱት በ1871 ዓ.ም በኦጋዴን አካባቢ ካልካዩ በተባለ ሥፍራ ነው። ለአካለ መጠን መድረሳቸውን ተከትሎም የኤልቡር አካባቢ ገዢ ሆነው የሰሩት ዑመር ሰመተር፣ ኢጣሊያ የ1928ቱን ወረራ ከመፈጸሟ በፊት ወልወል ላይ ጠብ የጫረችውም ዑመር ሰመተር በነበሩበት በምስራቁ የኢትዮጵያ ክፍል ነበር።
ኅዳር 26 ቀን 1927 ዓ.ም የኢጣሊያ ወታደሮች በኢትዮጵያ እና በእንግሊዝ ሱማሌላንድ መካከል ያለውን ወሰን ለመከለል የተላኩትን ሰዎች ይጠብቁ በነበሩት የኢትዮጵያ ወታደሮች ላይ ጥቃት ከፈቱባቸው። በወቅቱም ኢጣሊያ በአካባቢው ያለው የኢጣሊያ ሱማሌላንድ ግዛቷ ስለሆነ ወታደሮቿ በአካባቢው ነበሩ። ውጊያ ተደረገና በሁለቱም ወገኖች በኩል የሰው ሕይወት ጠፋ፤ የአካል ጉዳት ደረሰ…።
ኢትዮጵያም በአካባቢው ያለው የጣሊያን ጦር ችግር እንደፈጠረባት ለኢጣሊያ መንግሥት ክስ አቀረበች፤ ይሁንና የኢጣሊያ መንግሥት ይባስ ብሎ የተበደለ መሆኑን በመግለፅ የሚከተሉትን ‹‹የመደራደሪያ ጥያቄዎች›› አቀረበ።
አንደኛ፤ የወቅቱ የሐረርጌ ገዢ የነበሩት ደጃዝማች ገብረማሪያም ወልወል ድረስ ሄደው እዚያ የሚገኘውን የኢጣሊያ የጦር መሪ በኢትዮጵያ መንግሥት ስም ይቅርታ እንዲጠይቁ፣ አንድ የኢትዮጵያ የጦር ጓድ ለኢጣሊያ ሰንደቅ ዓላማ ሰላምታ እንዲሰጥ፣ በኢትዮጵያ በኩል ለተደረገው የማጥቃት እርምጃ ኃላፊ የሆኑት ባለሥልጣኖች ሁሉ ተይዘው የኢጣሊያን ሰንደቅ ዓላማ እጅ ነስተው እንዲሻሩና ተገቢውን ቅጣት በአስቸኳይ እንዲያገኙ፣
ሁለተኛ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ለቆሰሉት፣ አካላቸው ለጎደለውና ለሞቱት የኢጣሊያ ወታደሮች ካሣ የሚሆን 200 ሺ ማርቴሬዛ (ጠገራ ብር) እንዲከፍል እንዲሁም
3ኛ፤ በኢጣሊያ ወታደሮች ላይ ጥቃት ፈጽመው ከባድ ጥፋት ያደረሱት ዑመር ሰመተር ተይዘው ለኢጣሊያ መንግሥት እንዲሰጡ በማለት የለየለት የትዕቢት ጥያቄ አቀረበ።
የኢትዮጵያ መንግሥትም የኢጣሊያን ሃሳብ ሳይቀበል ቀረ፤ ጉዳዩ በእርቅ እንዲያልቅ ለማድረግ ቢጥርም
አልሆነም። ከዚህ በኋላ ነው ፋሺስት ኢጣሊያ ለ40 ዓመታት ያህል ስትዘጋጅበት የቆየችውን እቅድ እውን ለማድረግ በሁሉም አቅጣጫዎች ኢትዮጵያን ለመውረር መንቀሳቀስ የጀመረችው።
ኢጣሊያ የኢትዮጵያን ግዛት እወስዳለሁ ብላ ወልወል ላይ የጫረችው እሳት ወልወል ላይ ብቻ አላቆመም። ሁለቱንም ወገኖች ጎድቷል። ኢጣሊያ በኋላ ላይ እርቀ ሰላም አወርዳለሁ ብላ ቃል ስትገባም ድርድር ስታቀርብ የግጦሽ መሬት ከኢትዮጵያ ግዛት ተቆርሶ እንዲሰጣት ስትጠይቅ ‹‹በኢጣሊያ ወታደሮች ላይ በደል የፈጸመው ዑመር ሰመተር እጁ ተይዞ ተላልፎ ይሰጠኝ›› ብላ ጠይቃ ነበር። ዑመር ሰመተርም ይህን ሲሰሙ ‹‹ከአገሬ አፈር የሚደባልቅ ቤልጅግና ጎራዴ ይዤ እንጂ ጫት ተሸክሜ የምመጣ እንዳይመስልህ›› ብለው በመመለስ ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ከመውረር እንድትታቀብ ደጋግመው አስጠነቀቁ።
ለወልወሉ ግጭት እየተቀጣጠለ መላ አገሪቱን አዳረሰ። ዑመር ሰመተርም የቁርጥ ቀን ልጅነታቸውን ለአገራቸው ማሳየታቸውን ቀጠሉበት፤ ከደጃዝማች አፈወርቅ ወልደሰማዕት ጋር ሆነው ፋሽቶቹን ይፋለሙ ጀመር። የሰለጠነው የዑመር ሰመተር ጦር ገርለጉቤ መሽጎ ጠላትን መውጫ መግቢያ አሳጣው። ዑመር ሰመተር ኤልቡር ላይ በስድስት ባታሊዮን የጠላት ጦር ሲከበቡ፣ ያለውን ሁኔታ ተመልክተው ቦታ ለቀቁ፤ አንዳንዶች መሳሪያ አስረከቡ።
ከአምስት ወራት በኋላ ግን ጦራቸውን አጠናክሩ፤ ከመላ አገሪቱ የተውጣጣውን ኅብረተሰብ አስከትለው በ1930 ዓ.ም ገደማ አንድ ሌሊት በጠላት ጦር ላይ አደጋ ጣሉ። የኢጣሊያ ጦር ሺላቦ ድረስ እየመጣ ቢያስቸግራቸው እንደገና ገጥመው በማሸነፍ ውርደትን እንዲከናነብ አደረጉት። ከደጋው የኢትዮጵያ ክፍል በሚላክላቸው የሰው ኃይል፣ መሳሪያና ስንቅ ተጠናከሩ፤ እንደገናም ቆራሄ ላይ የጠላትን ጦር ድል መቱ። ከጠላት ምሽግ ውስጥ በመግባት የጨበጣ ውጊያ እስከማካሄድ የደረሱት ዑመር ሰመተር በዚም ሁሌም የሚታወስ ገድል ፈጽመዋል።
ከዚህ በኋላ ወደ ደገሃቡር ተመልሰው ከበላይ አዘዦቻቸው ጋር ተገናኙ። በዚህም ወቅት የጦሩ የአንዱ ክፍል አዛዥ የነበሩት ደጃዝማች ገብረማርያም የዑመርን ጀግንነት ተመልክተው በኦጋዴን አውራጃ ካሉት የአካባቢው ተወላጆች ወታደር መልምለው እንዲቀጥሩ ፈቀዱላቸው። በዚህም ጊዜ የፊታውራሪነት ማዕረግ ተሰጣቸው። ፊታውራሪ ዑመር ሰመተር ጠላትን በማንበርከክ በገርለጉቤ፣ በቆራሄ፣ በሃነሌ … የሚያስደንቅ ጀብዱ ፈጸሙ።
ደጃዝማች አፈወርቅ ከሞቱም በኋላ ወታደሩን እያረጋጉ ሲዋጉ ቆይተው በመጨረሻ እርሳቸውም በስድስት ጥይት ቆስለው ስለነበር ወደ ጂግጂጋ ተመለሱ። ፊታውራሪ ዑመር ሰመተር የደረሰባቸው ቁስል እጅግ ከባድ ስለነበር ለጦርነት መሰለፍ ከማይችሉበት ደረጃ ላይ ደረሱ። የጦር መሳሪያ የሚገኝበትን ዘዴ እየቀየሱ፣ ሕዝቡም ካለው የማረሻ በሬና ሌላም ቁሳቁስ እያዋጣ በመሸጥ ጥይትና ጠመንጃ እየገዛ ትልቅ ውጤት አስገኝቶ ነበር።
በኋላም ቁስላቸው እጅግ እየበረታባቸው ስለሄደ ወደ ሃርጌሳ መሰደድ ግድ ሆነባቸው። ከሃርጌሳ ተነስተው ኬንያ ገቡ። ከኬንያ ወደ ለንደንም ተወሰዱ። ከዚያም የቀረውን የጦርነት ጊዜ በስደት ላይ ሆነው ካሳለፉ በኋላ ነፃነት ሲመለስ ወደ አገራቸው ገቡ። ስድስት ጥይት በአካላቸው እንዳለ ነበር ወደ አገራቸው የተመለሱት። ቀጥሎም የደጃዝማችነት ማዕረግ ተሰጣቸውና የኦጋዴንና ጂግጂጋ ገዢ ሆኑ።
ይሁን እንጂ በአካላቸው ውስጥ ያሉት ጥይቶች እረፍት ነሳቸው፤ ቁስሉም እያመረቀዘ አስቸገራቸው። በሐረር ከተማ ሃኪሞች ባሉበት ቦታ ሁሉ እየተዘዋወሩ ቢታከሙም መዳን ግን አልቻሉም። መጋቢት 6 ቀን 1936 ዓ.ም፣ በተወለዱ በ65 ዓመታቸው አረፉ። ሥርዓተ ቀብራቸውም በሐረር ከተማ ውስጥ በአብዱል የመቃብር ስፍራ በሙሉ ወታደራዊ ሥነ-ሥርዓት ተፈጽሟል።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን መጋቢት 11 ቀን 2014 ዓ.ም