በኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ታሪክ ውስጥ ስማቸው ተደጋግሞ ይነሳል። በውጭ ግንኙነት በሰሩት ሥራ በተደጋጋሚ ይመሰገናሉ። ንጉሡ እሳቸውን ቢሰሙ ኖሮ ለውድቀት አይዳረጉም ነበር ሲሉ በርካቶች ይናገሩ ነበር ይባላል።
እኚሁ የዲፕሎማሲ አባት የባለፈው ዓመት የበጎ ሰው ሽልማት ልዩ ተሸላሚም ሆነዋል። በነገራችን ላይ ባለፈው ዓመት (2013 ዓ.ም) ኢትዮጵያ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ጥበብ የሚያስፈልጉትና ዓለም አቀፍ ጫናዎች የበዙባት ነበረች። ለዚያም ይመስላል ልዩ ተሸላሚ የተደረጉት፤ ፀሐፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ።
የተወለዱት በያዝነው ሳምንት መጋቢት 5 ቀን 1904 ዓ.ም ነው፤ በዚህም ምክንያት ነው እኛም የዛሬው ሳምንቱ በታሪኩ ጉዳያችን ያደረግናቸው። ተዋቂ ሰዎችን ታሪክ በደማቁ ያስታውሳቸዋልና እኛም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ ካሳተመው ‹‹የአክሊሉ ማስታወሻ›› ከተሰኘው መጽሐፍ፣ ከአምባሳደር ዘውዴ ረታ ‹‹የኤርትራ ጉዳይ›› መጽሐፍ እና ከተለያዩ ድረ ገጾች ባገኘናቸው መረጃዎች ላይ ተመስርተን ሥራዎቻቸውንና የሕይወት ታሪካቸውን እናስታውሳለን።
የተወለዱት በምሥራቅ ሸዋ አስተዳደር በአድአ ወረዳ ልዩ ስሙ ደምቢ በሚባል ሥፍራ ነው። አባታቸው አለቃ ሀብተወልድ ካብቴነህ ሲሆኑ እናታቸው ደግሞ ወይዘሮ ያደግድጉ ፍልፍሉ ይባላሉ። የአማርኛ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ቅዱስ ራጉኤል ቤተክርስቲያን፣ ዘመናዊ ትምህርታቸውን በዳግማዊ ምኒሊክ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል፤ በ1917 ዓ.ም. ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ግብጽ ተልከው በ1923 የፈረንሳይን ባኩሎሪያ በማዕረግ ተመረቁ። በፈረንሳይ በሶርቦን ዩኒቨርሲቲ በሕግ ትምህርት ሊሳንስ (ኤል ኤል ቢ) አገኝተዋል። አክሊሉ በፐብሊክ ሎው እና በኢኮኖሚክስ ዲፕሎማ ደ ዶክትራ፣ እንዲሁም በንግድና በፖለቲካ ሳይንስ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ሰርተፊኬት ተቀብለዋል።
ከለጋ እድሜያቸው ጀምረው ነው ኢትዮጵያን ያገለገሉት። ታሪክ በደማቁ ከሚዘክርላቸው የጸሐፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ዋና ዋና ሥራዎች መካከል የሚከተሉት ይገኙባቸዋል። ፓሪስ በተደረገው የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፍጻሜ የሰላም ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ ከሌሎች መንግሥታት ጋር በእኩልነት ተካፋይ እንድትሆን፣ በቅኝ አገዛዝ ሥር የሚኖሩ የአፍሪካ አገሮች ነጻነታቸውን እንዲያገኙ፣ ኢጣልያ በቅኝ ግዛት የያዘቻቸውን አገሮች እንድትለቅ ብዙ ጥረት አድርገዋል፤ ለኢትዮጵያ 25 ሚሊዮን ዶላር የጦር ካሳ እንድትከፍል እንዲሁም ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኘውን የጠላት ንብረት ኢትዮጵያ እንድትወስድ አስወስነዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተር በአሜሪካ ሳንፍራንሲስኮ ከተማ በ1937 ሲረቀቅ ኢትዮጵያ የመንግሥታቱ ማሕበር መስራች አገር እንድትሆን ከፍተኛ ጥረት አድርገው በመሳካቱም ቻርተሩን በሚያዘጋጀው ጉባኤ ላይ ተካፍለው በመጨረሻ ቻርተሩን በኢትዮጵያ መንግሥት ስም ፈርመዋል።
ከ1937 እስከ 1945 አራቱ ታላላቅ መንግሥታት የኤርትራን ጉዳይ ለመመርመር በአደረጉት ጉባኤና ከእዚያም በኋላ ለተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ቀርቦ በታየበት ጊዜ ኤርትራ ከእናት አገሯ ጋር እንድትቀላቀል ተከራክረው በማሳመን አዎንታዊ ውጤት አስገኝተዋል።
የስዊስ ካናል ችግር በደረሰ ጊዜ የኢትዮጵያ መልእክተኞች መሪ በመሆን በለንደን ጉባኤ ላይ ከተካፈሉ በኋላ ወደ ግብጽ ፕሬዚዳንት ናስር ከተላኩት አምስት አገሮች መልእክተኞች አንዱ ሆነው ተመርጠዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ አሥራ አምስተኛ ዓመቱን እስካከበረበት ድረስ የኢትዮጵያ መልእክተኞች መሪ በመሆን በስብሰባው ላይ እየተገኙ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በኮሌክቲቭ ሴኩሪቲና በተባበሩት መንግሥታት ላይ ያላቸው ጽኑ እምነት ግንዛቤ እንዲያገኝ አድርገዋል።
የአፍሪካ ነጻ መንግሥታት አራት ብቻ በነበሩበት ጊዜ የተባበሩት መንግሥታት በ1948 ዓ.ም. በአደረገው ጠቅላላ ጉባኤ በአንድ ድምጽ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ጉባኤውን መርተዋል። በዚያን ጊዜ አንድ አፍሪካዊ ለዚህ ኃላፊነት ሲመረጥ እርሳቸው በታሪክ የመጀመሪያው ነበሩ። የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በአዲስ አበባ ውስጥ ባደረጋቸው የመሪዎች ስብሰባ ላይ አዘውትረው ተካፍለዋል።
በተለይም ከግንቦት 14 እስከ 17 ቀን 1955 ዓ.ም. በተደረገው የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ ላይ የሶማሊያ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት የጎሳ ጉዳይ አንስተው ባሰሙት ንግግር ‹‹የሶማሊያ ዜጎች በኢትዮጵያ፣ በፈረንሳይና በእንግሊዝ ግዛት ስር ይገኛሉ። ኢትዮጵያ ያለ ሶማሊያ ሕዝብ ፈቃድ የሶማሊያን መሬት ነጥቃ ወስዳለች›› ማለታቸውን የሰሙት ክቡር ጸሐፊ ትእዛዝ አክሊሉ፣ የቀረበውን ክስ መሰረተ ቢስ ሲሉ አጣጥለውታል።
ወሰን እንዲከበር፣ አለመግባባቶች በሰላም መንገድ እንዲያልቁ ለአፍሪካ አንድነት ጥረት እንዲደረግ ኢትዮጵያ አጥብቃ ስለምትጠይቅ የሶማሊያ መንግሥትም በዚህ ዓለማ ተመርቶ እንዲሰራ ያላቸውን ምኞት በመግለጽ በዲፕሎማሲ ዘርፍ የተዋጣላቸው ሰው መሆናቸውን አሳይተዋል።
ፀሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ቀን ከሌሊት እየተጓዙ ለኢትዮጵያ ጥቅም ቢደክሙም፣ እረፍት አጥተው ለኢትዮጵያ የተሟገቱ ቢሆኑም፤ ኅዳር 14 ቀን 1967 ዓ.ም ከ60 የንጉሠ ነግሥቱ ባለሥልጣናትና ሌሎች ታላላቅ ሰዎች ጋር በደርግ ታጣቂዎች በጥይት ተደብድበው ተገደሉ።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን መጋቢት 11 ቀን 2014 ዓ.ም