18ኛው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሰርቢያ ቤልግሬድ ትናንት ተጀምሯል፤ ነገ እንደሚጠናቀቅም ይጠበቃል። ነገ በሻምፒዮናው ፍጻሜ ዓለም በጉጉት የሚጠብቀው የወንዶች ሶስት ሺ ሜትር ውድድር ሶስት ድንቅ ኢትዮጵያውያን አትሌቶችን አፋጧል።
ፉክክሩ በኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች መካከል እንደሚሆን አትሌቶቹ በውድድር ዓመቱ ያሳዩት አቋም የሚያረጋግጥ ሆኗል። የዘንድሮው የዓለም የቤት ውስጥ የዙር ውድድሮች በጀርመን ካርልሹ ባለፈው ጥር ሲጀመር 7:26:20 የሆነ ሰዓት ማስመዝገብ የቻለው ወጣቱ ድንቅ ኢትዮጵያዊ አትሌት በሪሁ አረጋዊ ያስመዘገበው ሰዓት በሶስት ሺ ሜትር አምስተኛው ፈጣን ሰዓት ነው።
ይህ የሃያ አንድ ዓመት አትሌት በውድድሩ ለሃያ አራት ዓመታት በኬንያዊው ዳንኤል ኮመን ተይዞ የቆየውን የዓለም ክብረወሰን ለማሻሻል ያደረገው ጥረት በአራት ሰከንድ ዘግይቶ ባይሳካም የውድድር ዓመቱ ፈጣን ሰዓት ሆኖ ተመዝግቧል።
ከዚያ በኋላ በተካሄዱ ተመሳሳይ ውድድሮችም በሪሁ ካስመዘገበው የተሻለ ፈጣን ሰዓት አልተመዘገበም። በቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ አስር ሺ ሜትር ውድድር አራተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው በሪሁ በፈረንጆቹ 2022 አዲስ አመት ዋዜማ በባርሴሎና አምስት ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር የርቀቱን የዓለም ክብረወሰን በማስመዝገብ ማሸነፍ ችሏል።
ይህም አትሌቱ በተሻለ አቅምና ብቃት ላይ እንደሚገኝ ያረጋገጠ ሲሆን፣ በነገው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ለሜዳሊያ ከሚፎካከሩት ኢትዮጵያውያን አንዱ እንደሚሆን ተስፋ ተጥሎበታል። በሪሁ ባልተወዳደረባቸው ባለፉት አራት ሳምንታት ሶስት የቤት ውስጥ የዙር ውድድሮች እርስበርስ አስደናቂ ፉክክር ሲያደርጉ የቆዩት ወጣት ኢትዮጵያውያን ከዋክብት አትሌቶች በነገው ውድድር ለወርቅ የሜዳሊያ የሚያደርጉት ፉክክር የዓለምን ቀልብ ስቧል።
ሰለሞን ባረጋና ለሜቻ ግርማ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ለኢትዮጵያ ወርቅና ብር ያስመዘገቡ አትሌቶች ከመሆናቸው ባሻገር በቤት ውስጥ የዙር ውድድሮች በሶስት አጋጣሚ ያሳዩት ፉክክር የዛሬውን ውድድር ይበልጥ አጓጊ አድርጎታል።
በቶኪዮ ኦሊምፒክ ታሪካዊውን የብር ሜዳሊያ በሶስት ሺ ሜትር መሰናክል ያስመዘገበው ለሜቻ ግርማ በሌቪንና ቶረን የቤት ውስጥ ውድድሮች በአስደናቂ ብቃት ሲያሸንፍ ከሰለሞን ጋር እልህ አስጨራሽ ፉክክር አድርጎ በሚገርም አጨራረስ ብቃት እንደነበር አይዘነጋም።
የቶኪዮ ኦሊምፒክ የአስር ሺ ሜትር ብቸኛው የወርቅ ሜዳሊያን ለኢትዮጵያ ያስመዘገበው ሰለሞን በሁለቱ ውድድሮች(ሌቪንና ቶረን) በለሜቻ አጨራረስ ተበልጦ ሁለተኛ ሆኖ ቢያጠናቅቅም፣ ከሳምንት በፊት የአጨራረስ ድክመቱን አርሞ ከአስር ቀን በፊት ማድሪድ ላይ ለሜቻን ማሸነፍ ችሏል። ሰለሞን ያለፈው ዓመት የቤት ውስጥ የዙር ውድድሮች አጠቃላይ አሸናፊ በመሆኑ በቤልግሬዱ ሻምፒዮና በቀጥታ ተሳታፊ ሆኗል።
ለሜቻ በአንጻሩ በማድሪዱ ውድድር በሰለሞን ቢሸነፍም ሌቪንና ቶረን ላይ በማሸነፉ የዘንድሮው ዓመት አጠቃላይ አሸናፊ ሆኖ በነገው የዓለም ሻምፒዮና በቀጥታ ተሳታፊ ሆኗል። ይህም ባለፉት አራት ሳምንታት አስደናቂ ፉክክር ሲያደርጉ የቆዩትን ኢትዮጵያውያን ኮከቦች ዳግም የሚፋጠጡበትን እድል ፈጥሯል።
ሁለቱ ድንቅ አትሌቶች ባለፉት ውድድሮች እጅግ ጥንቃቄ የበዛበትና መፈራራት የነበረበት ውድድር በማድረጋቸው ፈጣን ሰዓት ከማስመዝገብ ይልቅ ውድድሮችን ማሸነፍ ላይ ብቻ ትኩረት ሲያደርጉ ተስተውሏል።
በዚህም ምክንያት አቅሙና ብቃቱ እያላቸው በሪሁ ያስመዘገበውን ፈጣን ሰዓት ሳያስመዘግቡ ቀርተዋል። በነገውም ውድድር ሁለቱ አትሌቶች እንዳለፉት ውድድሮች ጥንቃቄ ካበዙ የዓመቱን ፈጣን ሰአት በያዘው በሪሁ የወርቅ ሜዳሊያውን የመነጠቅ እድል ሊገጥማቸው ይችላል።
ያም ቢሆን ግን እነዚህ ሶስት ኢትዮጵያውያን ከዋክብት እርስበርስ የሚያደርጉት አጓጊ ፉክክር ሶስቱም ሜዳሊያ ከእጃቸው እንደማይወጣ ማሳያ ሊሆን ይችላል። በነዚህ አትሌቶች ደረጃ የሌሎች አገራት አትሌቶች ተፎካካሪ ይሆናሉም ተብሎ አይጠበቅም። ስለዚህ ቤልግሬድ ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ታሪኳ ሌላ አረንጓዴ ጎርፍ የምትመለከትበት ከተማ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ታሪክ በሶስት ሺ ሜትር ወንዶች ውድድር አንደኛና ሁለተኛ ሆነው በማጠናቀቅ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የተለየ ታሪክ አላቸው።
ይህም ከአራት አመት በፊት በበርሚንግሃም ነገ ለድል ከሚጠበቁት አትሌቶች አንዱ የሆነው ሰለሞን ባረጋና ዮሚፍ ቀጄልቻ ገና የአስራ ስምንት አመት ወጣት እያሉ የፈጸሙት ነው። በነገው ውድድር እነዚህ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ሶስቱንም ሜዳሊያ ጠራርገው ከወሰዱ ሌላ አዲስ ታሪክ ይሆናል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን መጋቢት 10 /2014