ሰሞኑን በመንደሩ መመላለስ የያዙት ፖሊሶች ውሏቸው ከነዋሪዎች ከሆነ ሰንብቷል። ፖሊሶቹ ሁሌም በመጡ ቁጥር ጥያቄያቸው ይበዛል። የሚሹትን እየቀረቡና እያዋዙ በጥንቃቄ ያወጋሉ ። አንዳንዱን ደግሞ እያጫወቱ፣ እየቀለዱ ያናዝዛሉ ።
ከተጠያቂው የሚፈልጉትን ባገኙ ጊዜም ‹‹ይበቃናል!›› አይሉም። ዓይናቸው ለሌላ መረጃ ወደሌሎች ያልፋል። ለፖሊሶቹ የሚናቅ፣ የሚደነቅ ይሉት መረጃ የለም። ከጆሮ የሚደርሰውን ሁሉ ዋጋና ሚዛን እየሰጡ ይለዩታል። የሰሙትን እያሰቡ፣ያሰቡትን እየመነዘሩ አሻግረው ይቃኛሉ። ሀሳባቸው ከጥርጣሬ ሲወድቅ፣ ጥያቄያቸው ጥያቄን ያነሳል። ይሄኔ የሚጠረጥሩትን አጥብቀው፣ያጠበቁትን አድምተው በጥልቀት ይዘልቃሉ ።
ይህ እውነት የፖሊሶችን ማንነት ከሌሎች ውሎ ይለየዋል። የመንደሩ ነዋሪ የፖሊሶችን እግር ማብዛት የጠላው አይመስልም ፡፤ሰሞኑን በየቤቱ ለሚነሳው ጉምጉምታ መፍትሔ እንደሚያገኝ እየገመተ ነው። ፖሊሶቹ በመንደሩ መመላለሳቸው ‹‹ለበጎ ነው›› ያሉ የሚያውቁትን መናገር ይዘዋል።
ከነዚህ መሐል ጥቂቶቹ ከጥርጣሬ የዘለለ መላምት እያስቀመጡ ነው። አንዳንዶች ደግሞ የውስጣቸውን ሊናገሩ በእጅጉ ፈርተዋል። የሚያውቁትን ካወሩ የሚደርስባቸው ችግር ያስጨንቃቸዋል። ከሁሉም ዝምታን የመረጡ ግን ካሉበት ሆነው በትዝብት ይቃኛሉ።
ጉምጉምታው… አርሲ ዞን ጉና ወረዳ ዋጬሎ ቀበሌ ። ፖሊሶቹ ስለሰሙት አዲስ ጉዳይ ዕንቅልፍ አጥተው ከርመዋል። ሁኔታውን አጣርተው ፣ ችግሩን እስኪለዩም በመንደሩ ዘልቀው ምርመራ ቀጥለዋል። ሰሞኑን የአካባቢው ሰዎች ስለአንድ ቤተሰብ የጠቆሙት መረጃ በፖሊሶች ጆሮ በቀላሉ አላለፈም።
ፖሊስ የእማወራዋን ድንገት መሰወር ከእማኞች እንደሰማ በመንደሩ ዘልቆ መረጃዎችን መሰብሰብ ይዟል። የቤቱ አባወራ ስለባለቤቱ መጥፋትና መሰወር የሚወራው ሁሉ ያስደነቀው አይመስልም። አንዳንዶች ከምንም ተነስተው በሚያስወሩት አሉባልታ ንዴትና ብስጭት ይዞታል። ባልና ሚስቱ የዚህ መንደር ነዋሪዎች ናቸው። ሰባት ዓመታትን በቆጠሩበት ትዳር የአንዲት ህጻን እናትና አባት ሆነዋል።
‹‹አንተ ትብስ. ፣ አንቺ ›› ሲሉት በኖሩት ሕይወት የራሳቸውን ጎጆ ቀልሰው ሲኖሩ ቆይተዋል። ባል አቶ ደሞዝ ሰሞኑን ሚስቱ ጠፋች እየተባለ በሚወራው አሉባልታ መናደዱ ቀጥሏል። ቀረብ ብለው ለጠየቁት ሁሉ እውነታ ያለውን እያብራራ፣ እየገለጸ ነው ።
ደሞዝ የትዳር አጋሩን ወደ አረብ አገር መላኩን የነገራቸው አንዳንዶች በሚለው ሁሉ ሳያምኑት ቆይተዋል። በእነሱ እምነት ሚስት ከአገር ስትወጣ ወዳጅ ዘመድን ልትሰናበት፣ ፡ ብቸኛና ሕጻን ልጇንም ለጎረቤት መንደሩ ‹‹አደራ›› ልትል ይገባል ። የሚስትን በድንገት ተነስቶ ካገር መውጣት ሲነጋገርበት የከረመው ሰፈርተኛ ጉዳዩን ከወሬ በላይ አግዝፎታል። ይህ አይነቱ መነጋገር ሲበራከት ሕግ ይወቀው የሚሉ በዝተዋል ።
አንዳንዶች መጠጥ ቤት ተቀምጠው ፣ ነገሩን ሲያነሳሱት ያመሻሉ። በጨዋታ መሐል ስሟ የሚጠራው ወይዘሮ ድንገት የመጥፋቷ ጉዳይ ለብዙዎች አሳሳቢ መሆኑ ቀጥሏል። በጉዳዩ ጠልቀው የተጨነቁ ሁለት ሰዎች ወይዘሮዋ ቤተሰቦች ቤት ሄደው ሁኔታውን ጠይቀዋል።
ልጃቸው የት እንዳለች እንደማያውቁ ተነግሯቸዋል። ቤተሰቦቿ ልጃቸው ካገር ለመውጣት መኪና ስትሳፈርና ስትሸኝ ያዩዋት እንዳሉ ከመናገር ሌላ የገለጹት የለም። መሄዷን አምነው፣ ወሬዋን ከመጠበቅ ውጭም አንዳች ተስፋ አልያዙም። ጠያቂዎቹ እግረ መንገዳቸውን የሰሙት ወሬ ሰላም አልሰጣቸውም።
ባል አቶ ደሞዝ ቤተሰቦቿን አስፈራርቶ፣ ከእጃቸው ያገኘውን ገንዘብ ቀምቷል ፣ ስለእሷም እንዳይጠይቁት አስጠንቅቋል። ጠያቂዎቹ የቤተሰቦቿን መፍራትና በጉዳዩ መሸማቀቅ ካወቁ ወዲህ ዕንቅልፍ አልተኙም።
ሰዎቹ ከእሷ መሰወር አልፎ የቤተሰቦቿ በፍርሀት መሳቀቅ ቁጭት ላይ ጥሏቸዋል። ሰውዬው ከዚህ በፊት ወይዘሮዋን በድብደባ ያሰቃያት ነበር። እግሯን ሰብሮም በፈላ ውሀ አቃጥሏታል። ሲከፋት ወደ ቤተሰቦቿ ትመጣለች።
የእነሱ አቅመ ደካማነት ከጥቃት አላዳናትም። ቤታቸው በመጣች ቁጥር አጣድፈው ይልኳታል። ችግሩ ወደእነሱ እንዳያልፍም በፍርሀት ይሸኝዋታል። ወላጆቿ ዘንድ የሄዱት ሰዎች ሕግ ባለበት አገር፣ አባወራው በጉልበት እያስጨነቀ መኖሩ አበሸቃቸው። የእስከዛሬው ድርጊትም
በልባቸው ጥርጣሬን አሳደረ። ሁኔታውን እንደዋዛ ማለፍ እንደሌለባቸው ቢረዱ መሆን የሚገባውን አስበው በጋራ መከሩ። እንደዋዛ ከዓይን የተሰወረችው ወይዘሮ ከቀናት ሳምንታትና ወራትን አልፋ አንድ ዓመት ከስምንት ወር አስቆጥራለች ። ቀኑ በገፋ ቁጥር ስለእሷ ማሰብና መጨነቁ ቀጥሏል። ሰፈርተኛው ትንሽዬዋን ልጅ ባየ ቁጥር እናቲቱን ያስባል። እሷን ባሰበ ጊዜም የአባወራውን ገጽታና ግዴለሽነት እያጤነ ይነጋገራል። የሰፈርተኛው ጥርጣሬና ጉምጉምታ ማየል አሁንም ሰውዬውን አላስጨነቀም።
ጉዳዩ ከተለመደ የመንደር ወሬ እንደማያልፍ ቆጥሮ እንደወትሮው ሥራውን ቀጥሏል። አሁን የመንደርተኛው ስሜት ከቀድሞው ተለይቷል። የኣባወራው ግዴለሽነት፣ የሕጻኗ ብቸኝነት፣ የቤተሰቦች ፍርሀትና መሸማቀቅ ትርጉም እየሰጠው ነው፡ በሚስቱ በደል እንደሚያደርስ የሚያውቁ ጥቂቶች ሰውዬው ወይዘሮዋ ላይ የከፋ ጥቃት ስለማድረሱ ጠርጥረዋል ። ከዚህ ቀደም ግለሰቡ በአንድ የዩኒቨርስቲ ተማሪ ግድያ ሲጠረጠር ቆይቷል።
ይህን የሚያውቁ ብዙዎች ስለእሱ በጎ አያስቡም። ጥርጣሬ… ጊዜ ወስደው፣ በጉዳዩ አስበው ቤተሰቦቿን የጠየቁት ሁለት ሰዎች ስጋታቸው ከውስጣቸው አልቀረም። ሁኔታውን አገር ይፍረደው፣ ፖሊስ ይወቀው ሲሉ ከሚመለከተው ደጃፍ ደረሱ። ጥርጣሬያቸውን በማሳያ አስደግፈው ሕግ እንዲያውቀው ‹‹አቤት›› አሉ። የጉና ወረዳ ፖሊስ የሰዎቹን ሀሳብ አንድ በአንድ አዳመጠ፡፤ከአንደበታቸው የሚወጣው ቃልና ያደረባቸው ስጋት የተለየ ትርጉም ሰጠው።
ፖሊስ የአመልካቾቹን እውነታ በጥልቀት መርምሮ ሁኔታውን ለማጣራት ጥልቅ ፍተሻና ጥንቃቄ የሚያሻ ተግባር ይጠብቀዋል። በራሱ ስልትና ዘዴ ተጠቅሞ ከእውነቱ ለመድረስም የአካባቢውን ኅብረተሰብ እገዛና ድጋፍ ይሻል። የወረዳው ፖሊስ የሰዎቹን ቃል አድምጦ ካሰናበተ በኋላ ጠንካራ የምርመራ ቡድን ሊያዋቅር ግድ አለ።
በፖሊሳዊ ሳይንስ የተቀመረ የምርመራ ዘዴ ተዘርግቶ ሥራውን ለማስጀመር የሚያስችሉ መስመሮች ተዘረጉ። አሁን ፍንጭ የሚጠቁሙ መረጃና ማስረጃዎችን በአግባቡ ይዞ ከታሰበው ለመድረስ ጥንቃቄ የተመላበት ሂደት ያስፈልጋል። የምርመራ ቡድኑ አባላት ድንገት ተሰውራለች ስለተባለችው ወይዘሮ መድረሻ ለማወቅ ወንደመንደሩ መዝለቅና ሁኔታውን ከስሩ ማጣራት እንዳለበት ወስኗል።
በስፍራው ደርሶ ምርመራውን ሲጀመር ወደጉዳዩ የሚያቀርቡ በርካታ መነሻዎች ያጋጥማሉ። አንዳንዴ በጉዳዩ የሌሉበት ሰዎች ተጠርጣሪ ይሆናሉ። አንዳንዴም በተፈላጊዎቹ ምትክ ንጹሐን ወንጀለኞች ሆነው ይፈረጃሉ።
ፖሊስ በሥራና ሙያው አጋጣሚ እንዲህ አይነቶቹን እውነታዎች ያውቃቸዋል። ብዙኃን ከሚያስቡበት አዕምሮ፣ በርካቶች ከሚያዩበት ዓይን አለፍ ብሎ ምርመራውን ማካሄድ ግድ ይለዋል። ክራሞት በዋጩሎ ቀበሌ ሰሞኑን ፖሊስ በዋጩሎ ቀበሌ ውሎ ማርፈዱን ይዞታል። የፖሊስን በሰፈሩ ማዘውተር የተመለከቱ ነዋሪዎች ውስጣቸው ሰላም አግኝቷል። ከአንድ ዓመት በላይ የተጨነቁበት ጉዳይ መፍትሔ እንደሚያገኝ የገመቱ በርካቶች ከፖሊሶች ጎን ሆነው ላይ ታች ማለቱን ይዘዋል።
ፖሊስ በእጁ ያለውን መረጃና ፍንጭ ይዞ ጥበብ የተመላ ምርመራውን ቀጠለ። ከነዋሪው የተለየ ሀሳብና ወሬ መኖሩን በማጣራትም ከእውነታው ጫፍ ሊደርስ ታተረ። የተገኙ መረጃዎች ሁሉ አቅጣጫቸው ወደ አንድ ግለሰብ የሚያነጣጥር ሆኗል ።
ነዋሪው በወይዘሮዋ መጥፋት የሚጠረጠረው አባወራውን እንደሆነ በአንድ ቃል አረጋገጠ። ፖሊስ የደረሰውን መረጃ በሌላ መረጃ አጠናክሮ ተጠርጣሪውን አባወራ ከእጁ አስገባ ። ጉዳዩን በምርመራ የያዘው መርማሪ ረዳት ሳጂን ፈታሽ ጂቦ ከወረዳው የጸጥታ ዘርፍ፣ ከሚሊሻ አባላትና ከሌሎች የሙያ አጋሮቹ ጋር በዋጩሎ ቀበሌ ውሎውን ማድረግ ከጀመረ ሰንብቷል። ከቀናት በፊት በእጁ ያስገባውን አባወራም ጥበብ በመላው ጥያቄ እያዋዛ ይመረምረዋል።
ሰውዬው ፖሊሱ የሚለውን እየሰማ የተለመደውን መልስ ይሰጣል። በሚያቀርብለት ጥያቄ እየተገረመም የሚባለው ሁሉ ተራ ስም ማጥፋትና የጠላት ወሬ መሆኑን ደጋግሞ ይናገራል። መርማሪው አባወራው የሚለውን በጥንቃቄ እየሰማ የፊት ገጽታውን፣ የአንደበቱን ቃላት በጥልቀት ያጤናል።
ፖሊሱ ከአባወራው ግቢ ከተሰሩት የቆርቆሮና ሳር ቤቶች ላይ አተኩሯል። በስፍራው ደርሶም ቤቶቹ እንዲከፈቱ አድርጓል። ደሞዝ ከፖሊሱ ሳይርቅ የተጠየቀውን ሁሉ ይፈጽማል። ግቢውን እንዲያሳይ፣ ቤቶቹን እንዲያስፈትሽ ሲታዘዝ የተባለውን ያደርጋል።
አባወራው ደሞዝ አሁንም ቃሉን አልቀየረም። ዛሬም ከሚስቱ መጥፋት ጋር ተያይዞ የሚወራው አሉባልታና ስም ማጥፋት መሆኑን በእርግጠኛነት ይናገራል። ከፖሊሶችና ከምርምራ ቡድኑ አባላት የማይለየው በርካታ ነዋሪ እግር በእግር እየተከተለ የሚሆነውን ይታዘባል። ቁፋሮው… መርማሪው ረዳት ሳጂን ፈታሽ ጂቦ አንድ ማለዳ እንደተለመደው በስፍራው ተገኝቷል።
ዛሬም በርከት ያሉ ነዋሪዎች አብረውት አሉ። በዙሪያው ካሉት ጠንካሮች ጥቂቶችን መርጦ ፈጣን ትዕዛዝ ሰጠ። ፡ ሰዎቹ በታዘዙት መሠረት ከተባሉት ቦታ ቀርበው መሬቱን በዶማ መቆፈር፣አፈሩን በአካፋ መዛቅ ጀመሩ ። ድንገት የቦታውን መቆፈር ያስተዋለው አባወራ ደሞዝ ወደ ፖሊሱ ፈጥኖ ቀረበ። መርማሪው ሁኔታውን አይቶ የሚለውን ሊሰማ ጠበቀ።
ደሞዝ አንገቱን እንዳቀረቀረ ቁፋሮው እንዲቆምና ነዋሪው በከንቱ እንዳይደክም ተናገረ። ይህን የሰማው ፖሊስ ለምን? ሲል ደሞዝን ፈጥኖ ጠየቀው። ደሞዝ ከነበረበት ተነስቶ ወደ አንድ ስፍራ አመራ።
ካጠገቡ ቆሞም እጁን እየጠቆመ ቆፋሪዎቹ ዶማቸውን ቦታው ላይ እንዲያሳርፉ ጠየቀ። ፖሊሱ በጥርጣሬ እያስተዋለው ጉዳዩን እንዲያብራራለት ጠበቀ። ደሞዝ የሰባት አመት የትዳር አጋሩንና የአንዲት ልጁን እናት ገድሎ በዚህ ስፍራ ስለመቅበሩ በግልጽ ተናገረ።
ፖሊስ የቁፋሮውን አቅጣጫ አስቀይሮ ሰዎቹ ስፍራው ላይ እንዲያተኩሩ አደረገ። የአካባቢው ሰው የተባለውን ሊፈጽም ፣የተነገረውን ሊያገኝ እጅ በእጅ ቁፋሮውን አጣደፈው። አፈር የለበሰው፣ድንጋይ የተጫነው፣ሳር የሸፈነው ደረቅ ስፍራ በአቧራ ታጅቦ ሚስጥሩን ያጋልጥ ያዘ። ቀስ በቀስ ጓሉ እየተነሳ፣ ኮረቱ እየጸዳ መጥለቅ የጀመረው መሬት አፉን በገሀድ ከፈተ።
ከጥቂት ቆይታ በኋላም ስፍራው ቀድሞ የተቆፈረ ጉድጓድ ስለመኖሩ አጋለጠ። ይህን ያየው ነዋሪ ቀጥሎ የሚሆነውን እያሰበ በጩኸትና ለቅሶ ተራኮተ። ፖሊስ ሁኔታውን አረጋግቶ ቁፋሮው እንዲቀጥል ትዕዛዝ ሰጠ። የምርምራ ቡድኑ አባላት ስፍራውን በተሻለ ጥንቃቄ ማስቆፈሩን ቀጠለ ።
ዙሪያውን የከበበው የመንደሩ ነዋሪ ቀጥሎ የሚሆነውን እየገመተ ደረቱን ይደቃ ፣ፊቱን ይነጭ ያዘ። ዶማዎች ከጉድጓዱ የመጨረሻ ጫፍ ሲደርሱ አንዳች ነገር መንካታቸው ታወቀ።
መቁነጥነጡ ፣መጣደፉ አየለ። አካፋ የያዙ ቆፋሪዎች በዶማው የተነካውን ጉዳይ ሊያረጋግጡ እርምጃቸውን አፋጠኑ ። ጥቂት ቆይቶ በላስቲክ የተጠቀለለ፣ በእራፊ ጨርቅ የታሰረ፣ የሴት ልጅ በድን አካል ከጉድጓዱ አፍ ብቅ ሲል ታየ። ጩኸቱ፣ ለቅሶው እሪታው ደምቆ ተሰማ። ከአንድ ዓመት በፊት… በጊዜ ከማጀቷ ገብታ ደፋ ቀና የምትለው ወይዘሮ የአባወራውን መምጣት እያሰበች ትጣደፋለች ። ውሎ ሲገባ ከአፉ የሚያደርገው፣ እንጀራ ከጉሮሮው የሚያወርደው መጠጥ ቢጤ ያስፈልገዋል።
ይህን የምታውቀው ታታሪ ሴት የሚሻው ሁሉ እንዳይጎድልበት፣ ጉልበቷን ትከፍላለች። ሁሌም ሰላምና ፍቅር የማይሰጣት አባወራ ምክንያት ፈልጎ እንዳይጎዳት እያሰበች ነው። የሰባት ዓመቷ ሕጻን የእናቷን እግር ተከትላ ባለፈችበት ታልፋለች። ስትቀመጥ እየተቀመጠች፣ ስትጣደፍ እያስተዋለች አብራት ትሮጣለች። ምሽቱ ገፍቷል።
አካባቢው በጭርታ ተውጧል። ኮቴ እያዳመጠች የአባወራውን መምጣት የምትጠብቀው ወይዘሮ ልቧ ደጅ እንዳመሸ ነው። ትንሽዬዋ ልጅ ከእናቷ ጋር ኩርምት ብላ የአባቷን ድምጽ ትጠብቃለች። ጥቂት ቆይቶ የቤቱ በር ድንገት ተበረገደ። አባወራው ደሞዝ ነው። ወደውስጥ እንደዘለቀ ነገር ነገር ይለው ያዘ ።
ባልና ሚስቱ መሐል የተጀመረው ጠብ እንደጧፍ እየነደደ መግባባት ይሉት ጠፋ። ቃላት ቃላትን እያባዙ ጉዳዩ መካረር ጀመረ። መሐላቸው የቆመችው ሕጻን እንደልማዷ በፍርሀት ራደች። ጥንዶቹ መሐል የተጫረው የነገር ፍም እየጋየ ጣራ ነካ። ድንገት ወይዘሮዋ ላይ ያረፈው የአባወራው እጅ የከበደ ሆነ ።
አካሏን በስለት እየሸረከተ፣ ደሟን እያዘራ እስትንፋሷን ነጠቃት። የወይዘሮዋን መሞት ያስተዋለው አባወራ ጊዜ አልፈጀም። ጨለማና ጭርታው እያገዘው፣የሕጻን ልጁ ዓይን እየገረፈው ከግቢው በቆፈረው ጥልቅ ጉድጓድ አፈርና ድንጋይ ቆልሎ ቀበራት። ይህ በሆነ ማግስት ስለሚስቱ ለጠየቁት ሁሉ ምላሹ አንድ ሆነ ። ባለቤቱ በድንገት ዓረብ አገር ጥላው መኮብለሏን እየሳመነ ተናገረ።
የእናቷን በአባቷ መገደል በዓይኗ ያየችው ህጻን በፍርሀት እንደደነዘዘች ጊዜያትን ቆጠረች ። በወቅቱ ለመጮህና የእናቷን ሕይወት ለማትረፍ አቅሙ አልነበራትም። ዛሬ ደግሞ የሁለቱን ወላጆቿን ጸጋ ለማግኘት አልታደለችም።
ውሳኔ…
ፍርድ ቤቱ በበቂ መረጃና ማስረጃዎች ከፖሊስና ከዓቃቤ ሕግ ተጠናክሮ የደረሰውን ሰነድ መርምሮ አጠናቋል። ተከሳሹ ጭካኔ በተመላበት ድርጊት የትዳር አጋሩንና የልጁን እናት በግፍ መግደሉም ጥፋተኛ ስለመሆኑ አረጋግጧል። ፍርድ ቤቱ በችሎቱ በሰጠው የፍርድ ውሳኔም እጁ ከተያዘበት ጊዜ በሚታሰብ የሃያ ሁለት ዓመት ጽኑ እስራት ‹‹ይቀጣልኝ›› ሲል ብይን ሰጥቷል።
መልካም ሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን መጋቢት 10 /2014