ኢሕአዴግ የአራት ክልሎች እና የፌዴራል መንግሥቱ ገዢ ፓርቲ ነበር። የሌሎቹን አምስት ክልሎች ገዢ ፓርቲዎች ኢሕአዴግ ‘አጋር’ በሚል ይጠራቸው ነበር። በምርጫ ቦርድ አሠራር ‘አጋር’ የሚለው አደረጃጀት ስለሌለ እንደተለያዩ ፓርቲዎች ነበር ሲታዩ የኖሩት።
ከ ‘አጋር ድርጅቶቹ’ ጋር ኢሕአዴግ የነበረው ግንኙነት ግን በምርጫ ቦርድ የማይታወቅ የነበረ ከመሆኑም በላይ ደንቡም ግልጽ ያልሆነ ሆኖ ነው የኖረው። እነዚህ ክልሎች አጋር ተብለው ከኢህአዴግ ጋር በቆዩባቸው ጊዜያት ውስጥም የሚታወቅ የጋራ የሆነ የሥራ አስፈፃሚ አልነበራቸውም።
ይህ ጉዳይ ደግሞ ኢሕአዴግ ቀድሞውንም ቢሆን እነዚህን አምስት ክልላዊ መንግሥታት ሁኑ እንዳላቸው ብቻ የሚሆኑ አሻንጉሊቶች መሆናቸውን አሳይቷል።
ምክንያቱም ‘አጋር ድርጅቶቹ’ ከኢሕአዴግ ያፈነገጠ ውሳኔ አሳልፈው እንዲሁም በምድራቸው ያለውን የተፈጥሮ ሀብትም ይሁን ሌሎች ገጸ በረከቶች ለማልማት ሕዝባቸውን ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ ለመሥራት አይደለም አስበውም አያውቁም ነበር።
ይህም ብቻ አይደለም የሚሾሙላቸው አስተዳዳሪዎች ሞግዚቶች ስለነበሩም ጥያቄያቸውም ድምጻቸውም ተሰምቶ የመብታቸው ተጠቃሚ መሆን ሳይችሉ ነው 27 ዓመታት እንደ ቀልድ ያለፉት።
እነዚህ አጋር ተብለው ወደኋላ ተገፍተው የነበሩ በአገራቸው ጉዳይ ላይ መወሰን እንዳይችሉ የተደረጉ ክልሎችም ከኅዳር 21 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ከብልጽግና ፓርቲ ጋር ተዋህደው እንደሌሎቹ ክልሎች ሁሉ የሚሰማ ድምፅ ተቀባይነት ያለው ሃሳብ እንዲሰጡ ብሎም ድምጻቸው እንዲቆጠር ሆኗል። ይህም እንደ አገር ልንገነባው ላሰብነው ትልቅነትና አንድነት ትልቅ እርሾ ሆኖም አገልግሏል ማለት ይቻላል።
እነዚህ አጋር ተብለው የኖሩ ፓርቲዎች (ክልሎች) እንደ ዜጋ ታይተው ወደ አንድ መድረክ ሲመጡም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ይህንን ብለው ነበር፤ «የብልጽግና ፓርቲ በእውነትና እውቀት ላይ ተመስርቶ ኢትዮጵያን አሁን ካለችበት ወደብልጽግና የሚያሻግር እውነተኛ ድልድይ ነው፡፡
የብልጽግና መለያ እውነትና እውቀት ነው፤ ኢትዮጵያ ለሕዝቦቿ ተስፋ የምትሆን፣ ለመኖር የምታጓጓ እና ሁሉም ዜጋ ደስተኛ የሚሆንባት አገር እንድትሆን በእውነትና እውቀት ላይ ተመስርተን እንሠራለን»፡፡ «ብልጽግናዎች እውነትና እውቀትን በመያዝ ምኞትና ስሜትን መቀነስ ይጠበቅብናል፤ ምኞት በጥረትና ስኬት የሚከወን ካልሆነ ባዶ ተስፋ እንደሚሆንና ባዶ ምኞትና ያልተገራ ስሜትም በኢትዮጵያ ላይ ችግር እየፈጠረ ነው» ብለውም ነበር በፓርቲዎቹ ውህደት ላይ፡፡
አገር ለመምራት ዘመኑን የሚመጥን አደረጃጀት፣ ራዕይና ብቃት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ያልገባቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ቢኖሩም ነገ በኢትዮጵያ ብልጽግና ላይ በጋራ ቆመን ወደኋላ ስንመለከት ይህ ውሳኔ በእውነትና እውቀት ላይ ተመስርቶ ታላቋን አገር ወደሚገባት ቦታ የሚያደርሳት መሆኑን ሁሉም የሚያውቀውና የሚያየው እንደሚሆንም ተናረውም ነበር፡፡
ብልጽግና በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ሁኔታ ወደ ብልጽግና ምዕራፍ እንድትሸጋገር እቅዱን በግልፅ ቋንቋ በርካቶችን በማወያየት ያዘጋጀ ሲሆን አማራጭ ሀሳብ አለኝ ብሎ ራሱን ከምኞትና ከስሜት በማራቅ አስቻይ ሁኔታዎችን አካቶ የሚመጣ ካለ ለመማር ዝግጁ መሆኑን በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸው ነበር፡፡
እኛም በተለይም አጋር ተብለው ሲገፉ ከነበሩ አሁን ከብልጽግና ፓርቲ ጋር እኩል ቆመው በአገራቸው ጉዳይ ላይ እየተወያዩ ውሳኔዎችን እያሳለፉ ከዚያም አልፎ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል በመሆን ከተመረጡ ሰዎች መካከል የጋምቤላ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ከሆኑት ከአቶ ላክዴር ላክዴር ብርሃኑ ጋር ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፦ ባለፉት 27 ዓመታት ጋምቤላን ጨምሮ ሌሎች ክልሎችም አጋር ተብለው የቆዩበት ሁኔታ ነበርና እንዲያው ይህንን ወቅት እንዴት ይገልጹታል?
አቶ ላክዴር ላክዴር፦ ያለፉት 27 ዓመታት እውነት ለመናገር እኛን ጨምሮ መሰል ክልሎች ላይ አጋር በሚል ሰበብ ትልቅ ጫና ሲደረግ የቆየበት ጊዜ ነው። ሱማሌ፣ ጋምቤላ፤ አፋር፤ ቤኒሻንጉል፤ ሐረሪ የሚባሉ ክልሎች የተሰጣቸው ቦታ እጅግ የሚያሳፍር ነበር። ኢህአዴግ አጠራሩ ላይ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ይበል እንጂ በተግባር ግን አገር የጥቂት ክልሎች ብቻ ሆና እነዚህ ክልሎች በር ላይ ቆመው ተመልካች እንዲሆኑ ታዛቢ ብቻ ሆነው እንዲቀሩ አድርጎ ነበር።
በነገራችን ላይ ታዛቢ ስልሽ እነዚህ ክልሎች የነበራቸው የመታዘብ አቅምም ትክክለኛና ሕጉን የተከተለ አልነበረም፤ በአገር ጉዳይ ላይ ጥቂት ክልሎች እንደ ባለቤት ሲሳተፉ እነዚህ ግን ታዛቢ የሚል ታርጋ ተሰጥቷቸው እንደሌላ አገር ዜጋ ነበር ሲታዩ የቆዩት። በተለይም ትልልቅ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች ላይ ካለመሳተፍም አልፎ ምንም ዓይነት ውሳኔ ሲወሰን እጃችን አለመኖሩ ከፍተኛ የሆነ ጫናን አሳድሮብን ቆይቷል።
ምንም እንኳን ፓርቲው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች ቢልም ሕዝብነት የተሰጠው ለጥቂቶች ብቻ ነበር። እኛን ጨምሮ ሌሎች አጋር ተብለው የሚጠሩ ክልሎች የኢትዮጵያ ሕዝብ አልነበሩም ማለት ነው። በነገራችን ላይ ኢህአዴግ አራቱንም ክልሎች ይዞም ቢሆን ራሱን እንደ ዋና ያስብና ይቆጥር ስለነበር እነሱም አጋር ክልሎች ነበሩ ማለት ይቻላል።
ለውጡ ከመጣ በኋላ ግን አጋርነትን በተግባር እንድናሳይ በአገራችን ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ እኩል ተሳታፊ የሚያደርገንን ዕድል ማግኘት ችለናል። አዲስ ዘመን፦ ያለፉት 27 የአጋርነት አመታት እንዲያው በሕዝቡ ላይ ያደረሱት ጫና እንዴት ይገለጻል? አቶ ላክዴር ላክዴር፦ በሕዝቡ ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
ክልሎች ሕገ መንግሥቱ በሰጣቸው መብት መሠረት እራሳቸውን በራሳቸው ያስተዳድራሉ ቢባልም እነዚህ አጋር ተብለው ይጠሩ የነበሩ ክልሎች ላይ ለድጋፍ ተብሎ ከኢህአዴግ ሰዎች ተሹመው ይላካሉ፤ እነዚህ ሰዎች ደግሞ እውነት የክልሉን አመራር ብሎም ሕዝቡን በሀቅ ለመደገፍ የሚመጡ ሳይሆኑ የክልሉን መሬት የተለያዩ የተፈጥሮ ሀብቶች ለመቀራመት ብሎም ፖለቲካዊ ውሳኔዎች ላይ ጣልቃ በመግባት የመልካም አስተዳደር ችግር በሕዝቡ ውስጥ እንዲፈጠር ለማድረግ ነበር፤ ሲሠሩ የቆዩትም ይህንኑ ነው።
የክልሉ ሕዝብም ለምን በመሬቴ፣ በሀብቴ ተጠቃሚ መሆን አልችልም የሚል ጥያቄን ማንሳት ብሎም የመልካም አስተዳደር በደሎቹን የመናገር የመዳኘት መብት አልነበረውም። ምክንያቱም የሚተዳደረው በራሱ ልጆች ሳይሆን ኢህአዴግ በድጋፍ ስም ሾሞ በላከለት ሌሎች አካላት በመሆኑ ነው።
ከዚህ ቀደም ወደ ክልሉ በኢንቨስትመንት ስም የሚመጡ አካላት ነበሩ፤ እነዚህ አካላት ደግሞ የሚመጡት ከአንድ ብሔር ከመሆኑም በላይ የክልሉን መሬት ወስደው ሳያለሙም የተበደሩትን ብር ወስደው ሌላ ቦታ እየሠሩ መሬቱንም እንዳጠሩት ሕዝቡም የልማቱ ተጠቃሚ ሳይሆን ነው የኖረው። በሌላ በኩል ደግሞ ሕዝቡ አንድ ሆኖ ስለመብቱም ሆነ ስለመልማት ጥያቄ እንዳያነሳ እርስ በእርሱ እንዲጋጭ ሲደረግ ነው የቆየው፤ ጋምቤላ ከአምስት በላይ ብሔረሰቦች በዋናነት የሚኖሩባት ስትሆን በመላ አገሪቱ ያሉ ብሔረሰቦችም የሚገኙበት ክልል ነው። ይህም ቢሆን ግን እርስ በእርስ እንዲጋጩ እንዲገዳደሉ ሲደረግ ነው የቆየው።
አዲስ ዘመን፦ ከለውጡ በኋላስ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?
አቶ ላክዴር ላክዴር፦ በመጀመሪያው ጉባኤ ወቅት ነው እንግዲህ እኛም እንደ ኢትዮጵያዊና እንደ አራቱ ክልሎች ሁሉ ከብልጽግና ጋር ተዋህደን በአገራችን እንዲሁም በክልላችን ጉዳይ ላይ ተወያይተን የመወሰን መብትን ያገኘነው፤ ብልጽግናም ሁሉን የሚያቅፍ አካታች ፓርቲም ሆኖ ነው ያገኘነው፤ ሁሉም ብሔረሰቦች በአገር ጉዳይ ላይ በሚሰጡ ውሳኔዎች ላይ የራሳቸውን ሚና መጫወት ድምጻቸውን ማሰማት መቻል አለባቸው። አሁን ላይ እንደቀድሞው ጊዜ አንዱ ውሳኔ ሰጪ ሌላው ደግሞ በር ላይ ቆሞ ውሳኔ ተቀባይ የሚሆንበት አካሄድ ሙሉ በሙሉ እንዲወገድ ሆኗል።
በፓርቲው ውስጥም ያለው ህብረ ብሔራዊነትን የሚያጠናክር አካሄድ በተለይም እንደ እኛ ለተጎዱ ክልሎች ትልቅ አቅም የጨመረ ሆኗል። ሌላው ነገር እንደ አገር በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ስልጠናዎች ሲዘጋጁ እንኳን አራቱ ክልሎች ከተሰበሰቡ በኋላ መጨረሻ ላይ አጋሮች ይሰብሰቡ ነበር የሚባለው፤ ይህ በራሱ ከፍተኛ የሆነ ስነ ልቦናዊ ጫናን ሲያደርስብን ቆይቷል።
አሁን ላይ ግን ሁላችንም አንድ ስለሆንን የሚመጡ ጥሩም ይሁን መጥፎ ነገሮችን እኩል የምንጋራበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ሰሞኑን አካሂደን ያጠናቀቅነው ጉባኤ ለእኔ በጣም ታሪካዊ ነው፤ ይህንን ደግሞ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ ከሌሎች አገሮችም ጉባኤውን ለመታደም የመጡ ሁሉ የመሰከሩት ሀቅ ነው። ፓርቲውም በርካታ አባላትን የያዘ ከዚህ ቀደም እኛን መሰል አጋር ተብለው የተገለሉትን ወደፊት ያመጣ ከመሆኑ አንጻር ብዙዎችን አስደምሟል።
በሌላ በኩልም በመድረኩ ላይ በጣም ትልልቅ ጉዳዮች የተነሱ ሲሆን ጠንካራ ውሳኔዎችም ተላልፈዋል። ይህ ደግሞ ሁሉንም ያስደሰተ ብሎም ኢትዮጵያ ውስጥ ሲካሄዱ ከነበሩ ጉባኤዎች የተለየ ስለሆነ አባል ያልሆኑ ሁሉ ድጋፋቸውን የቸሩትም ነው። ከዚህ ወጣ ስንል ግን እንደ ክልልም እንደ አገርም ብዙ ጥያቄዎች የሚነሱበት ወቅት በመሆኑ ጉባኤው ባሳለፋቸው ውሳኔዎች አማካይነት እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ምን ያህል ርቀት ይሄዳል የሚለውም እየተጠበቀ ነው። በጠቅላላው ጉባኤው አንድነት የፈጠረ እርስ በእርሳችን እንድንተዋወቅ በተለይም እንደ እኛ የተዘነጉ ክልሎች ወደፊት እንዲመጡ መንገዱን የከፈተ ነበር ማለት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፦ በተለይም በዚህ ጉባኤ ላይ የውሳኔ ሰጪነት ሚናችሁ እንዴት ነበር?
አቶ ላክዴር ላክዴር፦ አዎ ውሳኔ ሰጪነት ብቻ ሳይሆን ሲካሄዱ በነበሩ ምርጫዎች ላይ ራሱ ቀጥተኛ ተሳታፊ ነበርን። ከዚያም ባለፈ በማዕከላዊ፤ በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እንዲሁም በሌሎች ላይ ያለው የብሔር ስብጥር በጣም አስደሳችና ከፍ ያለ ነበር።
በእነዚህ ኮሚቴዎች ውስጥ ያልተካተተ ክልል እንዲሁም ብሔር የለም። ይህ ደግሞ ቀደም ሲል የነበረው አመለካከት እንዲሁም የከፋፋይ አስተዳደራዊ አካሄድ የቀየረ ጉባኤ ሆኗል። በሌላ በኩልም የሚሰጠውን ውሳኔ ለመስማት እንኳን በር ላይ እንሆን የነበርን አጋር ድርጅቶች ዛሬ ላይ ተዋህደን ጉባኤው ላይ ድምጻችን ከመሰማቱም በላይ ትልልቅ ኃላፊነቶች ላይ ሁሉ እንድንገኝ ሆኗል።
ለምሳሌ አቶ አደን ፋራህ ከሱማሌ ክልል የመጡ ናቸው፤ አሁን በትልቅ የፓርቲ አመራር ቦታ ላይ ይገኛሉ። ይህ የሚያሳየው ዕድል ማጣት እንጂ ትልቅ አቅም እንዳለን ነው።
አዲስ ዘመን፦ መዋሀድን በተለይም እንደ እርስዎ ክልል ካለበት የተከማቸ ችግር እንዲሁም የመልማት ጥያቄ አንጻር እንዴት ያዩታል?
አቶ ላክዴር ላክዴር፦ አዎ ከመዋሀዳችን በፊት ያልታዩ እንዲታዩም ያልተፈለጉ ጉዳዮችና አካባቢዎች ሁሉ እንዲታዩ አድርጓል።
ለምሳሌ ባለፈው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በአፋር፤ በሶማሌ፤ በጋምቤላና በቤኒሻንጉል ያለው ችግር ምንድነው የሚለውን ለማየት ወደአካባቢዎቹ ሄደው ነበር፤ ይህ በራሱ ትልቅ ነገር ነው፤ ከዚህ ቀደምም ታይቶ አይታወቅም። በዚህ ደግሞ አሁን ላይ ጠቅላይ ሚኒስትራችን የጋምቤላን ችግር ከእኛ በላይ ነው የሚያውቁት ማለት ይቻላል።
ለምሳሌ ከዚህ በፊት በልማት ስም ቢወሰዱም ምንም ያልተሠራባቸው መሬቶች ወደልማት እንዲገቡ ከሁለት ወር በፊት ተገኝተው መመሪያ ሰጥተዋል። ይህ ደግሞ እንደ ጋምቤላ የመልማት ዕድላችንን አስፍቶልናል። ይህ ሁኔታ በጋምቤላ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ክልሎች እየሆነ ያለ ከመሆኑ አንጻር ሁኔታው አበረታች ለወደፊቱም ተስፋ ሰጪ ነው።
አዲስ ዘመን፦ አሁን የተሰጣችሁን ዕድል በመጠቀም ከክልላችሁ አልፎ እንደ አገር በጸጥታ፤ በኢኮኖሚ እንዲሁም በፖለቲካው መስክ ላይ ምን ለመሥራት አቀዳችኋል?
አቶ ላክዴር ላክዴር፦ አዎ አሁን ላይ እንደ ኢትዮጵያ ሕዝብ ተቆጥረን ወደፊት መጥተን የመሪነቱን ቦታ ይዘነዋል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ባለፈው ዓመት በተካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ ላይ ሕዝቡ የሰጠንም አደራ አለብን፤ አሁን ደግሞ በድጋሚ በጉባኤው ላይ የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች የሰጡን ኃላፊነት ትልቅ በመሆኑ ከዚህ በፊት የነበሩ ችግሮች በተለይም ከልማት ከዘላቂ ሰላምና አንድነት አንጻር ምን እንስራ ብለን እያቀድንም ነው።
ከዚህ ቀደም ሕወሓት ይኼ የዚህ ነው፤ የዛነው በማለት ከፋፍሎናል፤ ሸንሽኖናል፤ አሁን ግን እነዚህን ሁኔታዎች ወደጎን በመተው ሕዝቡን በማሳተፍና የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራት በተለይም የሕዝቡ ሰላም እንዲረጋገጥ ይሠራል። ሌላው ከዋጋ ግሽበት ጋር በተገናኘ ብዙ የቤት ሥራዎች ያሉብን በመሆኑ እነሱን መስመር ለማስያዝና እንደ አገር ምን ዓይነት መፍትሔ ይምጣ የሚለውን ለመቃኘት ሕዝቡ ድረስ ወርደን ያሉትን ችግሮች ከሕዝቡ ለመስማትና እራሱም የመፍትሔው አካል እንዲሆን የሚያስችሉ ሥራዎችን ለመስራት በዝግጅት ላይ ነን።
በሕዝቡ ላይ ፈተና ሆኖበት ያለው ሌብነት (ሙስና) እሱንም በተመለከተ አመራሩን የመፈተሽ ከዚህ በፊት እርምጃ የተወሰደ ቢሆን እንኳን አሁን ላይ የማጥራት ሥራው ተጠናክሮ እንደሚሠራ እቅድ አውጥተናል።
አዲስ ዘመን፦ አሁን ላይ እንደ አገር ከፍተኛ ስጋት እየጫረ ያለው የሰላምና የጸጥታ ጉዳይ በመሆኑ ከዚህ ጋር በተገናኘ ልትሠሩ ያሰባችሁት ጠንከር ያለ ሥራ ምን መልክ አለው?
አቶ ላክዴር ላክዴር፦ የሕዝቡን ዘላቂ ሰላም በሚመለከት በጣም ብዙ እቅዶች አሉ፤ እንደ ጋምቤላ ከዚህ ቀደም በውስጥ እርስ በእርስ የነበረው መጣላትና አንዳንድ ችግሮች ጋብ ያሉበት ሁኔታ ቢኖርም አሁን ላይ ፈተና ሆኖብን ያለው የውጭው አካላት ናቸው። በተለይም ከደቡብ ሱዳን ለዘረፋ የሚመጡ ታጣቂዎች ከፍተኛ ችግር ሆነውብናል። እነዚህ ሽፍቶች ሕፃናትንና ከብቶችን በመስረቅ ሰው በመግደል ይታወቃሉ፤ ይህ ደግሞ ከፍተኛ ችግር ሆኖብናል። ከላይ እንዳልኩት ውስጣዊ ችግሮቻችን መቶ በመቶ ፈተናል ባንልም መሻሻሎች አሉ። ከዚህ በኋላ መዋቅር እየሠራን በመሆኑ ከሕዝቡ ጋር በመቀናጀት ችግሮቹ በምን ዓይነት መልኩ ይፈቱ የሚለው ላይ ሰፊ ውይይቶች ይደረጋሉ።
የጸጥታ መዋቅሩን አቅም ከማሳደግ፤ የሰው ኃይልንም ከመገንባት አንጻር ብዙ ሥራዎች የተከናወኑ ቢሆንም በቂ ስላልሆኑ ከዚህ በኋላ ሌት ተቀን ሠርተን የሕዝባችንን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ ቁርጠኞች ነን። እንደ አጋጣሚ ሆኖ ጋምቤላ ክልል ድንበር ላይ ያለ ነው፤ ከዚህ አንጻር ደግሞ ደቡብ ሱዳን ላይ ሰላምና መረጋጋት ካልተፈጠረ በቀር ጋምቤላ ሰላም ውላ ልታድር አትችልም ።
በአሁኑ ጊዜ እንኳን ወደ ክልሉ እየገቡ ያሉ ስደተኞች ከ3 መቶ ሺ በላይ ደርሰዋል። ይህ በራሱ ክልሉ ላይ ጫና እየፈጠረ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ የሕገወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርም ፈተና ሆኖብናል። በመሆኑም ይህንን ሁኔታ ለመቆጣጠር ከፍተኛ ትግል ማድረግ ያስፈልጋል። እንደ ጋምቤላ ችግሮቹን ለመቋቋም ትግል አደረግን ማለት ደግሞ ኢትዮጵያን አዳንን ማለት ስለሆነ በዚህ በኩል ጠንክረን ለመሥራት እንደ ፓርቲ አመራር ተዘጋጅተናል። በመሆኑም እኛ እንደ ፓርቲ አመራር ትልልቅ ሥራዎችን ለመሥራት ስናስብ ሕዝቡም ከጎናችን ሆኖ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል።
አዲስ ዘመን፦ መዋሃድ ማለት አንድ መሆን ነውና እንዲያው ብልጽግና ፓርቲ በቀጣዮቹም ጊዜያት አንድ ሆኖ እንዲቀጥል ያላችሁ ዝግጁነት እንዴት ይገለጻል? አቶ ላክዴር ላክዴር፦ በጉባኤውም ላይ አይታችሁ እንደሆነ በምርጫ ወቅት ጥቆማ ሲደረግ የነበረው ጋምቤላ ጋምቤላን አይደለም፤ የነበረው ጋምቤላ ሌላውን ሌላው ደግሞ ከእሱ ብሔር ውጪ የሆነውን ነው። ይህም የሚያሳየው አንድነታችንን ነው። በመሆኑም አንድ ሆነን መቆም ከቻልን የኦሮሚያ ችግር የጋምቤላ ይሆናል፤ የአማራ ችግር የሲዳማ፤ የአፋር ጉዳት የሌላው ጉዳት ይሆናል።
አንድነታችንም የሚገልጸው በዚህ መልኩ ነው። ከዚህ ቀደም በአንዱ ክልል ላይ ችግር በሚኖርበት ወቅት ከመረዳዳትና አንድ ሆኖ ከችግሩ ለመውጣት ከመሥራት ይልቅ መጠቋቆም ነበር የሚበዛው፤ ከዚህ በኋላ ግን ይህንን ዓይነት ሁኔታ ፓርቲያችን፤ ለውጡ ይፈቅድልናል ወይ የሚለውን ነገር እንደ ትልቅ ጉዳይ አድርገን ማየት እንዳለብን ተግባብተናል።
ሌላው ለፓርቲያችን እንደ መለያ ካደረግናቸው ነገሮች መካከልም በመካከላችን ወንድማማችነትና እህትማማችነትን ነው ማስቀጠል ያለብን፤ እናታችን አባታችንም ደማችንም አንድ ነው የሚለውን እንድንይዝ ተስማምተናል።
ከዚህ ቀደም እንደነበረው እርስ በእርስ መናናቅ አንዳንዴም ቃላቶችን እየተወራወሩ አላግባብ መቋሰልና በተዛቡ ትርክቶች መራራቅ ስለማያዋጣ አሁን ላይ በአንድነት ስሜት ሥራዎችን በተለይም ሕዝብን የሚጠቅሙ አገርን የሚያሻግሩትን መሥራት ያስፈልጋል ብለን ይዘናል።
ይህም ቢሆን ግን ሂደቱ ከችግር የጸዳ ከዚህ በኋላም ችግሮች አያጋጥሙም ማለት ስላልሆነ ከመንደር ወሬ ርቀን ስለ አካባቢያችን ስለ ብሔራችን ወይም ስለራሳችን ብቻ ማሰብና ማውራት አቁመን የሚታይ ሥራን መሥራት ያስፈልጋል። ለከፍታችን የሚመጥን አስተሳሰብ አፍላቂ ልንሆን ይገባል። ይህንን ስናደርግ ብልጽግና በአገራችን፤ በአካባቢያችን እንዲሁም በቤታችን እውን የማይሆንበት ምክንያት አይኖርም።
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ::
አቶ ላክዴር ላክዴር፦ እኔም አመሰግናለሁ፡፡
ዕፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን መጋቢት 9 /2014