ለአንድ አገር የስፖርት እድገት ታዳጊና ወጣቶች ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት እንደሚያስፈልግ በተደጋጋሚ ይነገራል።
በኢትዮጵያም በተለያዩ አካባቢዎች የታዳጊ ወጣቶች የስፖርት ስልጠና ፕሮጀክቶች ተከፍተው ሲሠራባቸው ቆይቷል።
ባለፉት 10 ዓመታትም ከ2ሺህ በላይ በሚሆኑት የስልጠና ጣቢያዎች ከ50ሺህ በላይ የሚሆኑ ታዳጊ ወጣቶች በተለያዩ የስፖርት አይነቶች እንደሰለጠኑ ሪፖርቶች ያመለክታሉ።
ይሁን እንጂ በሚጠበቀው ልክ ተተኪና ውጤታማ የሆኑ ስፖርተኞችን ማፍራት ባለመቻሉ የፕሮጀክቶቹን ውጤታማነት ጥያቄ ውስጥ እንዲነሳበት አድርጓል። በቅርቡ የተሰራው የስፖርት ፍኖተ ካርታም የሥልጠና ፕሮጀክቶቹ በሚጠበቀው ልክ ውጤት አለማስገኘታቸውን አረጋግጧል። በተሰራው ጥናት መሰረትም ከዚህ ቀደም ስልጠና ይሰጥባቸው የነበሩ የስፖርት ዓይነቶችን ቁጥር በመቀነስ ጥራት ላይ ማተኮር እንደሚገባ አመላክቶ ነበር።
ይህንን መሰረት በማድረግም ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ በ1ሺህ 269 የሥልጠና ጣቢያዎች በ11 የስፖርት ዓይነቶች በየክልሉ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን፤ በኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የትምህርት፣ ሥልጠናና ውድድር ዳይሬክተር ወይዘሮ አበባ አማረ ይገልጻሉ።
ሥልጠናውን ውጤታማና ዘመናዊ ለማድረግ ይቻል ዘንድም የተለያዩ አሰራሮች ተዘርግተዋል፤ ከእነዚህ መካከል አንዱ የሠልጣኞች ምዝገባ ነው። ከዚህ ቀደም የሠልጣኞቹና አሠልጣኞቹ ሰነድ በወረቀት ላይ በሰፈረ መረጃ ብቻ ይገኝ የነበረ ሲሆን፤ ይህም ከእድሜ ተገቢነት፣ የክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ጥያቄ ያስነሳ ነበር።
ይህንን ለመቅረፍም ምዝገባው በቴክኖሎጂ በተደገፈ መልኩ የእድሜ ትመና ከተሰራ በኋላ በመረጃ ቋት እንዲገቡ ይደረጋል። ምዝገባው አሻራን የሚያካትት እንዲሁም ባር ኮድ የሚሰጥ በመሆኑ መረጃው ሊጭበረበር ይችላል የሚለውን ስጋት ይቀርፋል ተብሎ ታምኖበታል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስፖርት ቢሮም ቀዳሚ በመሆን የሠልጣኞችን ማንነት የሚገልጽ መረጃ ምዝገባ መጀመሩ ታውቋል። ከዚህ ቀደም ኮታ በሚመስል መልኩ በሁሉም ስፖርቶች በእኩል የእድሜ ክልል የሥልጠና ጣቢያዎች በየአካባቢው እንዲከፈት ይደረግ ነበር።
ፍኖተ ካርታው ባመላከተው መሰረት እንደየስፖርት ዓይነቱ ታዳጊዎች ተተኪና ምርጥ ስፖርተኛ ለመሆን የሚያስችላቸው እድሜ እንደየአስፈላጊነቱ እንዲለያይ መደረጉን ዳይሬክተሯ ያስረዳሉ።
ይህም የዓለም አቀፍ ተሞክሮን ከአገሪቷ ሁኔታ ጋር በማገናዘብ እንደየስፖርት ዓይነቱ እንዲለያይ ተደርጓል። ከውጤታማነት ጋር በተያያዘም እንደየ አካባቢው ዕምቅ አቅም እና ከስፖርቱ ተዘውታሪነት ጋር በተገናኘ ስልጠናዎች የሚሰጡ ይሆናል።
ይህም የተሰራው ክልሎች አለን ብለው ባቀረቡት እምቅ አቅም መሰረት መሆኑን አስረድተዋል። ከታዳጊዎች ስልጠና ጋር በተያያዘ በክለቦች፣ ማሰልጠኛ ማዕከላትና አካዳሚዎች የሚነሱ በርካታ ጥያቄዎች እንዳሉ ይታወቃል።
ክለቦችን ጨምሮ ታዳጊዎች ላይ የሚሰሩ አካላት በተለይ በምልመላ ወቅት አለመግባባት ይፈጠር እንደነበር በተለያዩ መድረኮች ላይ እንደቅሬታ ሲነሳ ቆይቷል።
ዳይሬክተሯ ከዚህ ጋር በተያያዘም ምዝገባው በፕሮጀክቶች ብቻ ሳይሆን ከ17 ዓመት በታች ተይዘው የሚሰለጥኑ ታዳጊዎች በሙሉ (ክለቦችን ጨምሮ በመንግስትም ሆነ የግል ማሰልጠኛ ማዕከላት ያሉትን) እንደየሥልጠናው በየፈርጁ በመሆኑ ችግሩን በተወሰነ መልኩ ለመፍታት የሚያስችል መሆኑን ነው የሚገልጹት። ይህ አሰራር ከዚህ ባለፈ በየትኛው የሥልጠና ሁኔታ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ይቻላል የሚለውንም ለመለየት ይጠቅማል ተብሎ ታምኖበታል።
ታዳጊዎች ጋር በተያያዙ ሥራዎች በአንድ ወገን ብቻ ሊተገበሩ እንደማይችሉ ግልጽ ነው። እንደ ትምህርት፣ ጤና ጥበቃ እና ከተማ ልማት ሚኒስቴሮችም ባለድርሻ አካላት ናቸው። በመሆኑም አብሮ ለመስራት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ምክክር በማድረግ የተናበበ ስራ መስራት የግድ ነው።
እንደ ጅምር ከትምህርት ሚኒስትር ጋር እየተሰራ ቢሆንም ከዚህም ይበልጥ መጠናከርና መቀናጀት እንዳለባቸው ዳይሬክተሯ ያብራራሉ። ከዚህ ጋር በተያያዘ በተለይ ለሚስተዋለው የማዘውተሪያ ሥፍራ ችግር አንዱ መፍትሄ የትምህርት ተቋማት ናቸው።
በመሆኑም ትምህርት ቤቶች ውስጥ ያሉ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ለትምህርት ቤት ማኅበረሰቡም ሆነ ለሌሎች ክፍት ሊሆኑ ይገባል የሚለው ሃሳብ ገዢ እንደመሆኑ እየተሰራበት እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ከመረጃ ማጥራቱ በኋላ የአሰልጣኞች ትጥቅ በሚኒስቴሩ የሠልጣኞች ደግሞ በክልሎቹ እንዲሸፈን ለማድረግ ውሳኔ ላይ መደረሱን ዳይሬክተሯ ጠቁመዋል።
የአቅም ግንባታ ሥራዎችም በተመሳሳይ በሚኒስቴሩ የሚሰራ ሲሆን፤ አንዳንድ ሥራዎችም የተጀመሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። ነገር ግን ለተገቢው አካል ተገቢውን ነገር ለማድረግ የጠራ መረጃ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መጋቢት 6 /2014