አዕምሯቸው መልካምነት የሚዘራበት፤ ዕውቀትና ጥበብ የሚተከልበት፤ ሰላምና ፍቅር የሚታነፁበት መሆን አለበት። አመለካከቶች፤ እሴቶች፤ ልምዶችና ዝንባሌዎች በየዕድሜ ደረጃ ሊለዋወጡ ይችላሉ። በዚህም ለወጣቶች ደምቆ የሚታያቸው ነገር ትልቅ መሆን ነው፡፡
የወደፊትንም ማየት ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ለሴት ልጅ ይህ ዕይታ ውዴታ ብቻ ሳይሆን ግዴታም ጭምር ነው፡፡ ምክንያቱም ሴት ሲኮን በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ መምራትና ቤተሰብን ማኖር ትልቅ ኃላፊነት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ገንዘብ ማምጣት ብቻ ሳይሆን የመጣውንም በአግባቡ ማስተዳደርና የሚሰፋበትን መንገድ መቀየስ ይኖርባታል፡፡ በሰው ጫንቃ ላይ መቀመጥም ሕመሟ ነው።
እናም ብዙዎች ያልተጠበቀ ቦታ ላይ ተሰማርተው የመሥራታቸው ምስጢር ይህ ይመስለኛል፡፡ ግን በዚያው ልክ ቆራጥና ብርቱ የሆኑ እንዳሉም ማመን ያስፈልጋል። ለዛሬ ለሴቶች አምድ ያቀረብናት መሰረት አዳነ የዚሁ ማሳያ ነች፡፡ ያለፈቻቸውን ውጣ ውረዶችና አሁን ያለችበትን ተሞክሮዋን በማንሳት ትማሩበት ዘንድም ጋብዘናችኋል፡፡
የአባት ልጅነትነት
መሰረት ተወልዳ ያደገቺው ደቡብ ጎንደር ውስጥ እብናት በተባለች ሥፍራ ነው፡፡ እናቷን በልጅነቷ ነው በሞት የተነጠቀችው፡፡ ስለዚህም ያሳደጓት አባቷ ናቸው።
ምንም አጉድለውባት አያውቁም፡፡ ዳግም ያገቧት ባለቤታቸውም እንዲሁ እንደእናት ሆና አሳድጋታለች፡፡ ነገር ግን እርሷ ብዙ ምቾት የማይሰጣት ነገር ይሰማታል፡፡ ከእንጀራ እናቷ ልጆች እኩል ራሷን አታይም፡፡ የሚጎልባት ያለ ይመስላታል፡፡ ይህም የእናት ፍቅር ነው፡፡
በዚህም ይህንን ቤተሰብ ትታ አክስቷ ጋር እዚያው ሰሜን ጎንደር ጸዳ የሚባል ሥፍራ ብዙውን የልጅነት ጊዜዋን አሳልፋለች። ይህም ቢሆን ብዙ ስላልተመቻት ዳግም ወደ አባቷ ጋር ተመልሳ ትኖር ነበር፡፡ አባት ትሂድም ትኑርም የቅርብ ጓደኛዋ ጭምር በመሆን ይንከባከቧታል፡፡
እናት ጭምር ሆነውላታልም፡፡ ነገር ግን ውስጧ እናቷ እንዳልሆኑ ይነግራታል፡፡ ብቻዋን ጭምር እንድታለቅስ ያደርጋታልም፡፡ የእንጀራ እናቷ መልካም ነገር ጭምር ስትናገራት ቶሎ ይከፋታልም፤ ተናዳ ጭምር እርሷ ከአሰበቺው ውጪ በመሆን የምትናገራት ነገር እንዳለ ታስታውሳለች፡፡
ስለሆነም በዚህ ሁኔታ ሁሉንም ማሰቃየቱን አልወደደችውም፡፡ እናም ተሞላቃ ከምትኖርበት አካባቢ ለቃ እንድትወጣ ሆናለች፡፡ እዚህ ቤተሰብ ውስጥ ባለችበት ጊዜ ከቡና ማፍላትና አንዳንድ ቀላል ሥራዎችን ከማገዝ ውጪ ምንም አይነት ጫና አይደረግባትም ነበር፡፡ ገንዘብም እንዳስፈለጋት ይሰጣታል፡፡ ይህን የለመደ እጅና ጉልበትም ነው አዲስ ሥራና ምዕራፍ ለመጀመር ወደሌላ ቦታ ያቀናው፡፡ ነገር ግን አንድ ነገር እንደተማረች ታነሳለች፡፡ በራስ ሰርቶ ራስን ማየትና እንዴት መቆም እንደሚቻል ማወቅን፡፡
ሥራና ፈተናው
ብዙዎች ተንደላቆ የኖረ ብቻውን ማደርና መኖር አይችልም ይላሉ፡፡መሥራትና መለወጥም እንደማይችል ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን ቆራጥ ከሆኑ የሚያቅት አንድም ነገር የለም፡፡ ተስፋ አለመቁረጥና መሥራት ሁልጊዜም ይለውጣል ትላለች፡፡ ለዚህም የራሷን ተሞክሮ ታነሳለች።
መጀመሪያ ከቤተሰብ ጠፍታ ስትመጣ የያዘችው 250 ብር ነበር፡፡ እርሱንም ቢሆን ለትራንስፖርትና ለምግብ አውጥተዋለች፡፡ የማታውቃት ግን በወሬ ሰምታ የናፈቀቻት አዲስ አበባ ላይ ተቀምጣ የምታደርገው ጠፍቷት ነበር፡፡ መንገድ ዳር ቁጭ ብላም ስታለቅስ ነው ያመሸቺው፡፡ ‹‹ሳይደግስ አይጣላ›› እንዲሉ አበው ሆነና አንድ ሹፌርን ጣለላት እንጂ የጅብ ራት ትሆን እንደነበርም ታስታውሳለች፡፡ ሹፌሩ ለምን እንደምታለቅስ ጠየቃት፡፡ ሁኔታውን በሙሉ ስትነግረው አሳዘነችውና ራት ከጋበዛት በኋላ የምታርፍበት ቤትም ለጊዜው አገኘላት፡፡ በወቅቱ ሰው ቤት መሥራት እንደምትፈልግ ጠይቋት ነበር፡፡ እርሷ ግን በቤት ውስጥ እንኳን ምንም አድርጋ ስለማታውቅና በዚያ ላይ ይህ ሥራ ዝቅ እንደሚያደርጋት ስለተሰማት እንደማትፈልገው መለሰችለት፡፡
ሁኔታው ያሳሰበው ደጉ ሹፌርም ፍላጎቷን ጠየቃት፡፡ ወደ አባቷ ጋር መመለስ እንደሆነ ነገረችው፡፡ ጠዋት እንደሚገናኙ ተነጋግረውም ሄደ፡፡ በማግስቱ ግን ለእርሷም ሆነ ለእርሱ መልካም አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡ ወደ አገሯ ከምትመለስ ይልቅ ጥሩ ሰው ቤት ብትቀጠር ራሷን ትለውጣለች በሚል ሳያስፈቅዳት በጣም የሚወደውን ጓደኛውን ይጠይቀዋል፡፡
እርሱም ‘በአንተ የመጣ ሰውን አግኝቼ ነው’ ብሎ ደስ አሰኘው። በዚህም ዘመድ ቤት እንደሚያስገባት አሳምኗት ይዟት ሄደ። ሁለቱም እዚያ ቤት ሲደርሱ ግን ያልጠበቁትን ነበር ያገኙት፡፡
ይህም በሠራተኝነት ልትቀጠርበት የነበረው ሰው ወንድሜ የምትለው የአክስቷ ልጅ ነበር፡፡ ተቃቅፈው መላቀስም ጀመሩ፡፡ ከዚያ በኋላም የአዲስ አበባ ኑሮ ቀጠለ፡፡ መሰረት ከመማር ይልቅ መሥራት ምርጫዋ ነው። ወንድሜ የምትለው የአክስቷ ልጅ ግን እንድትማር ብቻ ነው የሚፈልገው፡፡ በዚህም ሁለቱ ይጋጫሉ። ነገር ግን የምትጠጋበት እንደሌላት ስለሚያውቅ እንቢታዋን ወደ ጎን ይተውና ተያዥ ሆኖ ለሰው በቅጥር እንድትሰራ አደረጋት፡፡
ሥራዋ ቡና እያፈሉ መሸጥ ነው። እርሷ ታማኝና እንደራሷ አድርጋ የምትሠራ ቢሆንም ቀጣሪዎቹ ግን በብዙ መልኩ ያማርሯት እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ ለመውጣቷ መንስዔም ይህ ስቃይዋ ነበር፡፡ በተለይ በተደጋጋሚ የሚሆንባት ነገር እርሷን የሚመጥን አልነበረም፡፡
ቡና ሰፍራ ሰጥታት ‘ይህንን ያህል ብቻ እንዴት ወጣው’ ትላታለች፡፡ በዚያ ላይ በቲፕ መልክ ያገኘችው ጭምርም ትወስድባትም እንደነበር አትረሳውም፡፡ ስለዚህም የአንዳንድ ሰው ክፋት ለራስ የመሆንን መንገድ ያስተምራልና ይህ ጭካኔ ራሴን አስመልክቶኛል ትላለች፡፡
መሥራት የሚወድ ሰው ዓይኑ በአንድ አቅጣጫ ብቻ እንዲመለከት አያደርገውም፡፡ እጁም በአንድ ጉዳይ ላይ ብቻ አይሰማራም፡፡ ሁሉንም ነገር ለመፈተሽ በተለያየ አቅጣጫ ይቧጥጣል፤ ይቆፍራልም የምትለው መሰረት፤ ለምን የሚል ጥያቄን ሁልጊዜ ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ታነሳለች፡፡ ምላሹ ግን የማይሆን ይሆንባታል፡፡ ደጋግማም ታደርገዋለች፡፡
ግን አሁንም ያው ነው፡፡ እናም የዚህን ጊዜ አሳማኝ ውጤት ለማግኘት የራሷን እርምጃ ትጀምራለች። ለዚህም ነው የሰው ቤትን ርግፍ አድርጋ በመተው ቤት ተከራይታ ያንኑ ሥራ በራሷ መሥራት የጀመረችው፡፡
በባህርይው አዳዲስ ነገሮችን ለማወቅና ለመሥራት፤ ለመፍጠር ወይም ለማግኘት፤ ፈትሾና አረጋግጦ ለማሳየት የሚጓጓ ሰው የወደፊቱን ለማየት ብዙም አይቸገርም የሚል እምነት አላት፡፡ በዚህም ለዓመታት በቦታው ላይ መሥራትና ጥሩ ለውጥ ማምጣት ችላለች፡፡ ይሁን እንጂ አከራዩዋ በሥራዋ አልወደደቻትም፡፡ ብዙ ሰው ታበዢያለሽ በሚል ቦታውን እንድትለቅ አደረገቻት። ይህ ነገሯ እልህ ውስጥ የከተታትም መሰረት ምንም የማትነካካበትን ሰፊ ቦታ ይዛ ለመሥራት ወሰነች፡፡
ከቡናው አልፋ ምግብ ጭምር እያቀረበች ሌሎች በሥሯ የሚሰሩ ከሦስት ሠራተኛ በላይ ቀጥራ ወደ መሥራቱም ገባች፡፡ ዛሬ ያልተኮተኮተና ያልታረመ ማሳ ነገ በአረምና በአራሙቻ መወረሩ አይቀርም፡፡ ስለዚህም አረሙን ማስወገድ የመጀመሪያ ሥራ መሆን አለበት፡፡ ለዚህም ነው ከአንዱ ቦታና ሥራ አንዱን ለማየት የምጓጓውና ወደዚያ ሥራ የምገባው የምትለው መሰረት፤ ሴት ልጅ በተለይ ወጣት ሆና ሳለ ብዙ ነገሮችን መሥራትና መለወጥ የምትችል እንደሆነች ታምናለች፡፡ ለዚህም በአብነት የምታነሳው ራሷን ነው፡፡
ከሰው ቤት ተቀጣሪነት ወደ ራስ ሥራ የመግባቷም ምስጢር ይኸው ነው፡፡ መሰረት ማንነት በዛሬ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በትላንትና በነገ ውስጥ ይገኛል የሚል እምነት አላት። ይህንን ያለችበት ምክንያትም ዛሬን ስታሰብ ማንነት የሚለማ፤ የሚገነባ ወይም የሚታነፅ መሆኑን ለማሳየት ነው። ያለቀለት ሳይሆን በመሆን ሂደት ውስጥ ያለ እንደሆነ ደግሞ ነገን እንደሚያሳይ ስለሚታመን ነው፡፡
የሚታነፀው በራሱና በሌሎች ሲሆን እንዲሁ ትናንትን ያሳየናል ትላለች። ለዚህም በምክንያትነት የምታነሳው የትናንት ማንነት ገንቢው ቤተሰብ፣ ጎረቤት፣ ኅብረተሰብ፣ መንግሥት መሆኑን ለመጠቆም ነው።
እናም ማንነት የዚህ ሁሉ ውጤት ነውና ልናከብረው፤ ልናሻግረው፤ ልንኖርበት ይገባልም ባይ ነች፡፡ ችግሮች እየተወሳሰቡ የሚሄዱት ባንድ በኩል ደረጃ በደረጃ የማንፈታቸው በመሆናቸው በሌላ በኩል አፈጣጠራቸውንና አወጋገዳቸውን ባለማወቃችን እንደሆነ የምታስረዳው መሰረት፤ ለእኔ ችግር መፍቻ ቁልፍ አግኚ ራሴ ነኝ ትላለች፡፡ እኔ ወጣት ብቻ ሳልሆን ሴት ነኝ፡፡ ትኩስ ጉልበትና አዕምሮ ያለኝ ጤነኛ ሰው ነኝም፡፡
በዚህም ሊለውጠን የሚችልን ነገር አይቼ መሥራትና ደከመኝ ሳልል በቻልኩት ልክ መንቀሳቀስ እንዳለብኝ አምናለሁ፡፡ ይህ ደግሞ ነገን ያሳየኛልም የሚል አቋም አላት፡፡ ሰው ወርቅን በወርቅነት ሳያውቀው ለረጅም ጊዜ ኖሯል። የሚጠቅም ማዕድን ሆኖ ከመታወቁ በፊት የማይጠቅም የድንጋይ ክምችት ሆኖ ሲታይ ቆይቷል። እኛም ብዙ መልካም ነገሮች በራሳችን ውስጥ እንዳሉ ባለማወቃችን ከውጭ እንፈልጋቸዋለን።
ነገር ግን ካወቅነው ራሳችንን እናያለን የምትለው መሰረት፤ ሁሉም ሰው አዕምሯዊ፤ መንፈሳዊና አካላዊ አቅሙን በአግባቡ ከተጠቀመ ብዙ ችግሮችን ይፈታል፡፡ መፍትሔዎቹም ቀላል ናቸው፡፡ እናም በውስጣችን ያለውን መልካም ነገር መጠቀም ስንችል ከውጭ ያለውን ማግኘት አይከብደንም።
ከውስጥ ያለውን ሳንጠቀም ከውጭ ማግኘቱ ግን ቀላል አይሆንም። ሴቶች ደግሞ ይህን እውነት መረዳት አለባቸው ትላለች፡፡ ወርቅ በእሳት እንደሚፈተነው ሁሉ የሰው ልጅ በመከራ ይፈተናል። ይሁን እንጂ ከመከራው አንድ ቀን ይወጣል፡፡ ይህ የሚሆነው ደግሞ የወደፊቱን ሲያይ ነው።
ተስፋ አድራጊነትንም ሲያነግብ ነው፡፡ ስለዚህም ዛሬን ለመሻገር ተስፋ የሁላችንም ስንቅ፣ የመኖር ምክንያት፣ የመቀጠል ምኞት ወዘተ መሆን አለበት፡፡ ሰው ነገ ‘ይሄንን አደርጋለሁ’ ሲል ያው ተስፋ እንጂ ምንም የተጨበጠ ነገር ኖሮት አይደለም፡፡ እናም የተጨበጠውን ለማግኘት ያለምነውን መሥራት ያስፈልገናልም ባይ ነች፡፡
መልዕክት ለሴቶች
ትናንትና እና ዛሬ አይነጣጠሉም። አንዱ ሌላውን ባይሆንም አንዱ ያለ ሌላው አይኖርም። አንዱ ሌላውን ባይተካም አንዱ ከሌላው ውጪ አይደለም። ትናንት በሁለት መልኮች በዛሬ ውስጥ አለ። አንዱ መልክ በጎ ሲሆን ሌላው መጥፎ ነው። መልካሙ የሚወሰድ ሲሆን መጥፎው የሚወገድ ነው። ዛሬም በትናንት ውስጥ አለ።
የተፀነሰውና የበቀለው ከእርሱ ነው። ከትናንት የተወረሰ ወይም ከዛሬ የተገኘ መልካምም ሆነ መጥፎ አለበት። ስለዚህም ሁለቱን በእኩል ደረጃ አጣጥመን ነጋችንን ለማየት ወደኋላ እያየን ወደፊት ለመራመድ ማሰብ፤ ወደፊት እያየን ወደኋላ መጓዝ አያዋጣም የመጀመሪያው ምክሯ ነው። ሌላው ያነሳችው ሀሳብ በምድር ላይ ስኬት የሚመጣው በራስ መጠንከርና መድከም ልክ ነው። የአዕምሮ አጠቃቀም ጉድለታችን ስኬታችንን ይወስነዋል። ስለዚህም የሚሆነውንና የሚችለውን ፈልጎ የማግኘት ጉዳይ ካልሆነ በቀር በተፈጥሮ ደካማ ሆኖ የተፈጠረ አንድም ሰው የለምና ያለውን አቅም በአግባቡ የማይጠቀም ሰው ደካማ መሆኑ አይቀርም፡፡ እናም በተለይም ሴቶች ይህን በውል መረዳት አለባቸው። ተስፋ መሰነቅና ትልቅ ጉልበት ማግኘትም ይኖርባቸዋል፡፡
አንድ ሴት ምንም ነገር ከማድረጓ በፊት ራሷን መፈተሽ ይኖርባታል። ምንድነው የምችለው? የማልችለውስ? ብላ አቅሟን መለካት አለባት የምትለው መሰረት፤ ድክመትን ብቻ እያዩ መጓዝ የራስን ዋጋ ማሳነስ ነው። ስለሆነም ራስን ለማምጣት በመጀመሪያ ተገቢውን ዋጋ መስጠት ያስፈልጋል። ሰብዓዊ ፍጡርነት የተሰጠ ብቻ ሳይሆን ያለማቋረጥ የሚታነፅ ወይም የሚሰራ ነው። እናም ራስን በማክበርና በመከበር፤ በመሆንና ባለመሆን፤ በመስጠትና በመቀበል፤ በማግኘትና በማጣት ውስጥ ማሳለፍ ማንነትን እንደሚሠራ አምኖ መራመድ ይገባልም ምክሯ ነው፡፡ ለራሱ ዋጋ የሚሰጥ ሰው ራሱን ማነጽና ማብቃት ይጠበቅበታል። ይህ ሲሆን ደግሞ የተጋነነ ሳይሆን የሚመጥን ወይም የሚገባ ክብር ነው መስጠት ያለበት። ያልተገባ ዋጋ ከተሰጠ በመኮፈስ ውስጥ መዋረድን ልንከናነብ እንችላለን፡፡
መሥራትና መለወጥም አንችልም። ስለሆነም ራሱን የሚያከብር ሰው መጥፎ ከመሆንና ከማድረግ የሚታቀብና ሥራን የማይፈራ መሆን አለበት። በራስ ክብር ውስጥ ለሌሎችም ዋጋ የሚሰጥና ሰውን በሰውነቱ ልክ የሚያከብር ሊሆንም ያስፈልጋል። ምክንያቱም ለመከበር ማክበር ግድ ነው፡፡
ይህ ሲሆንም የምንዘራው ይበቅላል፤ የምንሠራው ይባረካል፡፡ እናም ለስኬት የምንሮጥ ሁሉ ይህንን እናድርግ ስትልም ትመክራለች፡፡ ሴቶች ለስብዕናቸውና ለማንነታቸው ቅድሚያ የሚሰጡ መሆን እንዳለባቸው የምትመክረው ባለታሪካችን፤ ባህርያቸውና ድርጊታቸው መብታቸውን በሚያስከብር መልኩ መሄድ አለበት፡፡ ለፍላጎታቸውና ጥቅማቸው ተገቢውን ክብር መስጠት በሚችልበት ሁኔታ ላይ መገንባትም ይኖርበታል፡፡ ነገር ግን ባህርያቸውና ድርጊታቸው የማያስከብራቸው ከሆነ ፈተናቸው ካሉበትም በላይ ይከብዳቸዋል፡፡ ልውጣ ቢሉም የሚፈቅድላቸው አይኖርም፡፡
ስለዚህም ምቾታቸው የወንድ ወይም የቤተሰብ ጫንቃ እንጂ የራሳቸው አይሆንም፡፡ እናም ይህንን እያዩና እያመኑ መንቀሳቀስ አለባቸው ትላለች፡፡ እኛም ምክረ ሀሳቧን ተጋሯት እያልን የዛሬውን አበቃን፡፡
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን መጋቢት 6 /2014