በአገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነት አሁን አሁን የሸማቹን የመግዛት አቅም በእጅጉ አዳክሞታል። የኑሮ ውድነቱ እንደወትሮው ሁሉ እጅን በአፍ ላይ ከማስጫን ባለፈ ለአንድ ሰሞን ጉድ አንድ ሰሞን ነው ብለን የምንተወው ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ቆም ብለን በማሰብ ዘላቂ መፍትሔን መፈለግና ማፈላለግ ላይ አይናችንን መጣል እንዳለብን የሚያሳስብ ወቅት ላይ አድርሶናል። በተለይም በየዕለቱ ጭማሪ እንጂ ቅናሽ የማይታይባቸው ምግብ ነክ የፍጆታ ዕቃዎች ላይ የሚታየው መረን የለቀቀ የዋጋ ጭማሪ ከሸማቹ አቅም በላይ ሆኖ ትከሻውን አጉብጦታልና ከመንግሥት አፋጣኝ ምላሽ ይጠበቃል።
የሸማቹ ገቢ ባለበት ሆኖ እየታየ ላለው መረን የለቀቀ የዋጋ ጭማሪ መንግሥት አፋጣኝ እርምጃ ካልወሰደ ከፍተኛ የሆነ ማኅበራዊ ቀውስ ያስከትላል። እርግጥ ነው ማኅበራዊ ቀውሱን ለማረጋጋት የሚመስሉ ‹‹ቀልዶች›› እዚህም እዚያም ይደመጣሉ። ይሁንና አሁን ላይ እየታየ ያለው ከመጠን ያለፈ የኑሮ ውድነት ‹‹የሀብታም ምግብ ሥጋ የደሃው ደግሞ ሽሮ›› አይነት ቀልድ ቀልደን የምናልፈው አልሆነም።
ይብላኝ ለድሆች እንጂ ባለጸጎችማ ዘይት ቢጠፋ በቅቤ ይበላሉ አይነት ሽሙጥም ዛሬ ላይ አይሠራም። ምክንያቱም ‹‹አፍንጫ ሲመታ አይን ያለቅሳል ለካ›› እንዲሉ ባለጠጎችም ሆኑ ድሆች የሚኖሩባት ዓለም አንድ ናትና አንዱ ለሌላው የመኖር ምክንያት ነው። ስግብግቡም ሆነ ሐቀኛው ነጋዴ ከደሃው ሸማች ውጭ መዳረሻ የላቸውም። ከአስመጪዎች ጀምሮ ጅምላ አከፋፋዮችና ቸርቻሪዎች ጋር እስኪደርስ ያለው የንግድ ቅብብሎሽ ጤናማ ባለመሆኑ ሁሉም ነገር ሸማቹ ጋር ሲደርስ እውነተኛ ባህሪው ተገልጦ ጩኸቱ ይበረክታል።
በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየታየ ያለው የምግብ ሸቀጦች እጥረትና የዋጋ ንረት ሕዝቡን ብቻ ሳይሆን መንግሥትንም ግራ እያጋባ ያለ ይመስላል። ይሁንና ሁሌም ቢሆን የምርቶች መሰወርና የዋጋ ንረት በነጋዴዎች አሻጥር የሚቀነባባር ድራማ እንደሆነ መንግሥት ጆሯችን እስኪጠግብ ነግሮናል። በቅርቡም በዘይት ላይ የተፈጠረው ይኸው ነው። ዋጋው አልቀመስ ከማለቱም ባለፈ በቅጽበት ከዓይናችን መሰወሩ ቃሉ ሊገልጻቸው ባይችልም ቅሉ ያው የስግብግብ ነጋዴዎች እጅ ያለበት ስለመሆኑ ነጋሪ አያሻንም።
ምክንያቱ ቢገባንም ታድያ መፍትሔው ግን ከእኛ አቅም በላይ ነውና ዞሮ ዞሮ አቤቱታችን ለመንግሥት መሆኑ አይቀርም። ይሁንና መንግሥት ምክንያቱን በሚነግረን ፍጥነት ለመፍትሔው አለመሽቀዳደሙ እንዲሁም በአጥፊዎች ላይ የማያዳግም እርምጃ አለመውሰዱ ለምን ይሆን? በማለት ከማጉተምተም ውጭ ምርጫ የሌለው ሸማች የመፍትሔ ሀሳብ ቢያጣ ናላው በሚያዞረው የኑሮ ውድነት የተለያዩ ሀሳቦችን በማንሸራሸር ይቀልዳል፤ ያፌዛል፤ ይተቻል ብዙዎቻችን መንግሥትን ተጠያቂ በማድረግ ብናማርርም ቅሉ ዓለም አቀፍ ሁኔታው የፈጠረው ስለመሆኑ የሚያስረዱም አልታጡም። የዓለም ዓቀፉ የኑሮ ውድነት እንዳለም ሆኖ የበርካቶች እምነት ግን ቀደም ሲል እንደተባለው መንግሥትም እንደነገረን ጭምር ስግብግብ ነጋዴዎች የፈጠሩት ችግር ነው።
የችግሩ ምንጭ ከየትም ይሁን ከየት አሁን ላይ ሕዝብ እየደረሰበት ያለውን የኑሮ ጫና ጫንቃው ሊሸከም ከሚችለው በላይ በመሆኑ ዘላቂ መፍትሔን ይሻል። እርግጥ ነው መንግሥት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ሲባል በድጎማ የሚያስገባቸው ምርቶች መኖራቸው ይታወቃል። ያም ቢሆን ጊዜያዊ መፍትሔ ከመሆኑ ባሻገር ምርቶች ለታለመላቸው ዓላማ እየዋሉ ስለመሆናቸው ግን አጠራጣሪ ከመሆን ባለፈ ትርጉም ባለው መንገድ ገበያውን ሲረጋጋ አልተስተዋለም።
መንግሥት ድጎማ አድርጎ ከሚያስገባቸው ዘይት፣ ዱቄትና ስኳር በተጨማሪ ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ የፈቀዳቸው ምርቶችም እንዲሁ እየተባባሰ የመጣውን የኑሮ ውድነት ማረጋጋት ሳይችሉ ቀርተው ለስግብግብ ነጋዴዎች መበልጸጊያ ሆነዋል። ስለዚህ ለችግሩ መፍትሔ ይሆናሉ ተብለው የተወሰዱ እርምጃዎች ውጤት ካላመጡ አማራጮችን በማስፋት አመለካከትን አስተካክሎ ዘላቂ መፍትሔን መሻት ከመንግሥት የሚጠበቅ አፋጣኝ ሥራ ነው።
በአገሪቱ ያለው የንግድ ሥርዓት በሕግ የማይመራ ማጭበርበርና ማታለልና መታለል የሞላበት ስለመሆኑ ብዙዎች ያነሳሉ። አገር ይታደጋል የተባለው የንግድ ሕግ አጭበርባሪዎችንና አታላዮችን አበልጽጎ ሐቀኞችን ከጨዋታ ውጭ ያደርጋል። ሸማቾችንም እንዲሁ አኮስሷል፤ አሸማቋል፤ አስለቅሷልም። ሸማቹ ዛሬም ገቢውን ከወጪው ጋር እያሰበ ነገሩ ተምታቶበታል። በየዕለቱ በሚሰማው የዋጋ ጭማሪ ናላው እየዞረ ያለ በመሆኑ የኑሮ ውድነቱን ማረጋጋት የሚያስችሉ አፋጣኝ እርምጃዎች ከመንግሥት ይጠበቃሉ። ይህ ካልሆነ ግን ከፍተኛ ማኅበራዊ ቀውስ ሊፈጠር ይችላል። ማኅበራዊ ቀውሱ ደግሞ ዘርፈ ብዙ የጎንዮሽ ጉዳቶችን ያስከትላል።
እርግጥ ነው ልጓም ያጣውን የኑሮ ውድነት ለማርገብ መንግሥት ብቻውን የመፍትሔ አካል ሊሆን አይችልም። እያንዳንዱ ዜጋ ድርሻ አለውና የድርሻውን ሊወጣ ይገባል። በተለይም ባለሙያዎች መፍትሔ ናቸው የሚሏቸውን አማራጮች አንድ ሁለት ብለው ለሚመለከተው አካል ሊያቀብሉ ይገባል። መንግሥትን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ሰሚ ጆሯቸውንና አስተዋይ ልቦናቸውን ወደ መፍትሔው በማዘንበል የኑሮ ውድነቱንም ሆነ ሕዝቡን ማረጋጋት ያስፈልጋል።
መንግሥት በየጊዜው እሳት የማጥፋት ሥራ ከመሥራት ወጥቶ አልረግብ ላለው የኑሮ ውድነት ዘለቄታዊ መፍትሔ መፈለግና ማፈላለግ የግድ ይለዋል። ከሰሞኑ ጩኸት የበዛበት ዘይት ላይ የተፈጠረውን ማየት ይቻላል። ካጋጠመው የምርት እጥረት በበለጠ በስግብግበ ነጋዴዎች ምክንያት ተከማቸ የተባለው የዘይት መጠን መላው ኢትዮጵያን ሊያዳርስ የሚችል ሆኖ ተገኝቷል። ታድያ እንዲህ አይነት አሻጥሮችን መንግሥት ስለምን ይታገሳል፤ ሰለምንስ ጥርስ የሌለው አንበሳ ይሆናል፤ መልስ ያላገኘ የብዙዎች ጥያቄ ነው።
ከዚህ በተጨማሪም መንግሥት መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎችም ሆኑ ሌሎች ምርቶች በሚፈለገው መጠን መመረታቸውን ወይም መቅረባቸውን ብቻ ሳይሆን፣ በተገቢው መንገድ ለሸማቾች መሠራጨታቸውንም ጭምር ማረጋገጥ የግድ ይለዋል። የግብይት ሥርዓቱን ጤናማነት የሚያውኩ፣ የአቅርቦትና የፍላጎት መመጣጠንን የሚያሰነካክሉና በአጠቃላይ ለኢኮኖሚው ፈተና የሆኑ ብልሹ አሠራሮችን ማስወገድ የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥቶ መሥራትም ይገባዋል። ብልሹ አሠራሮች የሚስተዋሉት በመንግሥት መዋቅር፣ በንግዱ ማኅበረሰብና በሕገወጥ መንገድ በሚንቀሳቀሱ ተዋንያን ውስጥ በመሆኑ እያንዳንዱን ችግር ስግብግብ በሆነውና ባልሆነው ነጋዴ ላይ መደፍደፍ አይገባም። ስለዚህ በጥናት ላይ የተመሠረተ የመንግሥት ዕርምጃ በሁሉ መልኩ እየተበደለ ላለው ሸማች ይሁን በማለት አበቃሁ።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን መጋቢት 6 ቀን 2014 ዓ.ም