የዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን/ በፈረንጆቹ ማርች 8/ በአለም አቀፍ እና በኢትዮጵያም ሰሞኑን ተከብሯል።በአለም ለ111ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ49ኛ ጊዜ ‹‹እኔ የእህቴ ጠባቂ ነኝ›› በሚል መሪ መፈክር ነው የተከበረው ።
ቀኑ የሚከበርበት ዓላማ ፍትሕ ርትዕ ላጡ መብታቸው ከሚገፈፍ ሴቶች ጎን ለመቆም እንዲሁም ድምፅ ላጡ ሁሉ ድምፅ ለማሰማት ነው።በኢትዮጵያ መከበር የጀመረው የዘወዳዊው አገዛዝ ከወደቀና ወታደራዊው አገዛዝ በሁለት እግሩ ከቆመ በኋላ ነው፡፡
ማርች 8 በየዓመቱ ለመከበር እንደምክንያት የሆኑት በሩሲያና በሰሜን አሜሪካ የነበሩ የሴቶች መብቶች ለማስከበር የሚደረጉ ንቅናቄዎች ነበሩ፡፡ንቅናቄዎቹ የሴቶችን የሲቪል ማኅበራዊ ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ መብቶች ለማስከበር የተካሄዱ ናቸው፡፡
እ.ኤ.አ. በ19 08 በአሜሪካ ኒውየርክ 15ሺ ሴቶች ለሰላማዊ ሰልፍ አደባባይ ወጡ።ዓላማቸውም ጥሩ ደመወዝ፣ ምቹ የሥራ ቦታና ሁኔታ እንዲሁም የሥራ ሰዓት ማስተካከያ እንዲደረግ ለመጠየቅ ነበር።በዋናነት ደግሞ በአሜሪካ ለመምረጥ እና ለመመረጥ የማይችሉ ሴቶች መምረጥ እንዲፈቀድላቸው ለመጠየቅም ነው።በአሜሪካ የመጀመሪያው የሴቶች ቀን የተከበረውም ከእዚህ ሰልፍ ከዓመት በኋላ የካቲት 20 ቀን 1909 ሲሆን፣ የአሜሪካ ሶሻሊስት ፓርቲ ብሔራዊ የሴቶች ቀን በሚል ሰይሞ በአሜሪካ ኒውየርክ ከተማ ነው የተከበረው።
የአሜሪካ ሶሻሊስት ፓርቲ ለብቻው የሴቶች ቀንን ቢያከብርም በድጋሚ በዓመቱ ከ17 አገሮች የተውጣጡ 100 ሴቶች በተገኙበት ክላራ ዘትኪን የተባለችው አንቂ በዴንማርክ ኮፐንሀገን በተካሄደ በዚሁ ጉባዔ ላይ የሴቶች ቀን በአሜሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም ደረጃም እንዲከበር ጠየቀች።ጥያቄዋ በተወሰነ መልኩም ተቀባይነት አግኝቶ መከበር ጀመረ።ይህም የሴቶችን እኩልነትን ለማበረታታትና ለማረጋገጥ በሴቶች ላይ የሚደርስ ጭቆናን ለማጋለጥና ለማስወገድ ነበር።
በማርች 19 ቀን 1911 የመጀመሪያው የሴቶች ቀን ኦስትሪያ፣ ዴንማርክ ፣ጀርመን እና ስዊትዘርላንድ በማክበር ፈር ቀዳጅ ሆነው ተገኙ።በሰልፉም ከሚሊየን በላይ ሰዎች ተገኝተውበታል።በኦስትሪያና ሀንጋሪ ብቻ 300 ሰልፎች ታይተዋል።በቪየና በተካሄደው ሰልፍ የፓሪስ ኮሚዩን ሰማዕታትን በማክበር ባነሮችን የያዙ ተገኝተዋል።
ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ማርች 8 እንዲሆን የተመረጠው ግን በሩሲያ 1917 ሴቶች የመመረጥ መብት ፍለጋን በመጠየቅና ‹‹ ሰላምና ዳቦ ›› የሚል መፈክር ይዘው በሞስኮና ፒተስትበርግ ከተሞችን አጥለቅልቀው መውጣታቸውን ተክተሎ ነው። ተቃውሞው ለአራት ቀናት የዘለቀ ነበር።ተቃውሞውን ለማብረድ ያለው አማራጭ የሩሲያ መንግስት የሴቶችን ጥያቄ መቀበል ሆነ፤ እናም ሴቶች የመምረጥ መብት እንዲኖራቸው ፈቀዱ።በአሉ የሚከበርበት ቀንም በጎርጎሮሲያዊያኑ ማርች 8 ቀን እንዲሆን ተደረገ፡፡
በሩሲያ ፔትሮጋርድ በማርች 8 ቀን 1917 የሴቶች ጨርቃ ጨርቅ ሠራተኞች ባካሄዱት ንቅናቄ መላው ከተማ ተውጦ ነበር ።በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት መሰናበቻ ‹‹ዳቦና ሰላም ›› በሚል በምግብ ችግርና በዛሩ ሥርወ መንግሥት ላይ ያተኮረ ተቃውሞ አካሄዱ።ይህም የፌብሩዋሪ አብዮት እንዲብት ክዚያም ሁለተኛው የሩሲያ የጥቅምት አብዮት እንዲፈነዳ ምክንያት በመሆንም ይጠቀሳል፡፡
መረጃዎች አንደሚያመለክቱት፤ በአሜሪካውያን ብሔ ራዊ የሴቶች ቀን በፌብሩዋሪ መውጫ ባለው የመጨረሻ እሁድ ይከበር እንደነበር ነው ሰነዶች የሚያሳዩት። በሩሲያ ማርች 8 ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ተብሎ መከበር የጀመረው ከ19 13 ጀምሮ እንደሆነ ሰነዶች ያስረዳሉ። በተመሳሳይ ማርች 8 ቀን በዓመቱ በ19 14 ማለት ነው በጀርመን ለመጀመሪያ ጊዜ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ተብሎ የተከበረ ሲሆን ቀኑም እሁድ ቀን ነበር።
ቀኑ በኢትዮጵያ መከበር የጀመረው በደርግ ስርአት ሲሆን ዘንድሮም ለ49ኛ ጊዜ ተከብሯል፡፡
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን መጋቢት 4 ቀን 2014 ዓ.ም