ወረርሽኙ በዓለም ከ6ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል፤ ሀገራችንንም ከ7 ሚሊዮን 480 ሺ በላይ ዜጎቿን ነጥቋል፤ የስነ ልቦና፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውሱ ከፍተኛ ነበር፤ የዓለምንም የሀገራችንንም ኢኮኖሚ በእጅጉ ተፈታትኗል፤ ኮቪድ 19።
በበሽታው የሚያዙ ሰዎችን ለማከምም ሆነ ተጠርጣሪዎችን ለመመርመር ሆስፒታሎችና ሌሎች የህክምና ተቋማት እንደማይችሉት ታውቆ፣ ህሙማኑን ለይቶ ለማከም እንዲቻል በሚል የሀገሮች የተለያዩ አዳራሾች፣ ስታዲየሞች፣ወዘተ. የሕክምና ተቋም ተደረጉ፤ ሆቴሎች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የመሳሰሉት ማግለያ ተደረጉ።
በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ያልተሞከረው የለም፤ እንዲያም ሆኖ ሚሊዮኖችን ቀጠፈ፤ በመቶ ሚሊዮኖችን ደግሞ ለአልጋ ቁራኛ ዳረገ።በጣልያን በአሜሪካ በስፔን በእንግሊዝ፣ወዘተ በቀን ይሞቱ የነበሩት ሲታሰብ የሰለጠኑት ሀገሮች በእዚህ ልክ ከተጎዱ አፍሪካ፣ ኢትዮጵያ ወዮላት እስከመባል ደረሰ።
ወረርሽኙ ኮቪድ-19 የሚል መጠሪያ እስኪሰጠው ድረስ ‹‹ሳርስ ኮቪድ 2›› በሚል ይጠራ እንደነበርም መረጃዎች ይጠቁማሉ።እአአ ጀምሮ ደግሞ በዓለም ጤና ድርጅት ኮቪድ 19 በሚል እንዲጠራ ተደረገ።በሽታው የ2019 ክስተት ስለሆነ ነው በእዚህ መጠራቱ።
በ2019 የመጨረሻዎቹ ወራት አካባቢ በቻይና የተከሰተው ይህ በሽታ ዜናው ዓለምን አዳረሰ ፤ በዜና ብቻ ዓለምን አዳርሶ አልቀረም።አውሮፓ፣ አሜሪካ፣ አፍሪካ… እያለ ዓለምን አዳረሰ።እነሆ በዜና ብቻ ስንሰማው የነበረው ኮቪድ-19 ኢትዮጵያም ገባ! እስኪ የክስተቱን ስሜት እናስታውሰው።
ኮቪድ-19 በኢትዮጵያ የተከሰተበት ቀን ከሁለት ዓመታት በፊት ልክ በዛሬዋ ቀን መጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም ሲሆን፣ ዕለቱ ደግሞ ዓርብ ነበር።ዜናውን መገናኛ ብዙሃን፣ ህዝብ፣ወዘተ በፍጥነት ተቀባበሉት።
አስገራሚ የሚያደርገው ደግሞ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ የጤና ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት በዋዜማው መጋቢት 3 ቀን 2012 ዓ.ም መሆኑ ላይ ነው።በሹመታቸው ማግስት የኮቪድ-19 ወደ ኢትዮጵያ መግባትን ይፋ አደረጉ።እነሆ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የዶክተር ሊያ ታደሰ የማህበራዊ ገጽ በየደቂቃው በመላ ኢትዮጵያውያን የሚጎበኝ ሆነ።‹‹ዛሬስ ምን ተፈጥሮ ይሆን?›› በሚል ሁላችንም መጎብኘቱን ተያያዝነው።ቀጥሎ ወደሆኑ ነገሮች ከመሄዳችን በፊት መጋቢት 4 የተነገረችዋ አስደንጋጭ ዜና የፈጠረችውን ስሜት አልጨረስንም።
በዓለም እዚህም እዚያም ተገኘ እየተባለ አስፈሪነቱ ይነገርለት የነበረው ይህ አስደንጋጭ ወረርሽኝ የተመለከተ ዘገባ በውጭ መገናኛ ብዙኃን እያነፈነፍን መከታተል ውስጥ ገባን።እዚህ አገር ገባ ፤ እዚያ አገር ገባ ፤ በእዚህ ሀገር ይህን ያህል ሰው ሞተ፤ይህን ያህል ተያዘ፤ በሽታው የከፋባቸውን ሀገሮች መረጃ ማነፍነፍ ሆነ ሥራችን፤ አሜሪካ እንዴት አደረች፣ ጣልያን እንዴት አደረች ሆነ ጥያቄያችን።
ለሰው ብሎ ሲያማ ለእኔ ብለህ ስማ እንደመሆኑ የሌላውን ሀገር መረጃ እያየን ስለራሳችን ማሰብ ውስጥ ሰመጥን፤ ወደ ሀገራችን እንዳይገባ ፈጣሪያችንን መማጸኑን ተያያዝነው።
በዚህ ስሜት ውስጥ እያለን ነበር ዕለተ ዓርብ መጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም ከሰዓት አካባቢ የወቅቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አንድ አስደንጋጭ ዜና የለጠፉት።ይሄውም አንድ ጃፓናዊ ቫይረሱ ሳይኖርበት እንደማይቀርና ለማረጋገጥም ወደ ምርመራ ክፍል እንደገባ የጠቆሙት ነው።‹‹አቤቱ ፈጣሪ፤ አንተ አውጣን›› እየተባለ ሲጠበቅ ቆየ።ወዲያውኑ የጤና ሚኒስቴር አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ ጠራ።
አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫው በሁሉም የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የቀጥታ ሥርጭት የተላለፈ ነበር፤ ምክንያቱም ጋዜጠኞች ስቱዲዮ እስከሚደርሱ ማንም እንደማይታገስ ተገማች ነበር።በቀጥታ ሥርጭት በሚተላለፈው መግለጫ የመጀመሪዋ ቃል ቫይረሱ ወደ ኢትዮጵያ የመግባቱን መርዶ የምትናገር ሆነች፤ በቃ በዚያ ጃፓናዊ ኮቪድ-19 ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ ተረጋገጠ።ከዚያች ቅጽበት ጀምሮ የአገራችን ህዝብ ስጋት ውስጥ ገባ።መናጥ ሆነ።
በዓለም የሚሰሙ ዜናዎች ሁሉ አስደንጋጮች ነበሩ።ምናልባት ዛሬ ላይ ሆነን ስናስበው ቀላል ይመስል ይሆናል እንጂ ስሜቱ በወቅቱ ከባድ ነበር።እነሆ ዓለም ያጋጠማት መደነባበር ወደ ኢትዮጵያም ዘለቀ።
እየቆየ ሲሄድ ‹‹እያረሩ መሳቅ›› እንዲሉ ጭንቀት የፈጠራቸው አንዳንድ አስቂኝ ክስተቶችም ታይተዋል። የወቅቱ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቻይናን የጎዱ መስሏቸው ቫይረሱን ሲያጣጥሉና የማይጠጣ ነገር ሁሉ ‹‹መድኃኒት ነው ጠጡበት›› ማለታቸው አስቂኝ ክስተት ነበር።የቻይና በሽታ እያሉ በሽታውን ጠርተውም ነበር።በሽታው ማንንም የማይምር መሆኑን አሳየ፤ የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን፣ የአሜሪካው የቀድሞ ፕሬዚዳንት ትራምፕ በሽታውን አቀለሉት ተብለው ሲተቹ ቆይተው በኋላ ላይ ተያዙ።
ከመጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ አቅጣጫዎች ሁሉ ተቀየሩ።የኢትዮጵያ መንግሥት በተቃዋሚዎቹ ሳይቀር የተመሰገነበት በወቅቱ ነገሮችን ያረጋጋበት ፍጥነት ነበር።በዚያ ዓለም በተደነባበረችበት አስደንጋጭ ክስተት ውስጥ መንግሥትም የግል ባለሀብቱም በበሽታው ሳቢያ በህብረተሰቡ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ቀውስ ለመቀልበስ ርብርብ ውስጥ ገቡ።
በወቅቱ እንባ ያራጩ የሰብዓዊነት ድርጊቶች ታይተዋል። ህንጻዎቻቸውን ለማግለያ የሰጡ ባለሀብቶችም ነበሩ፤ መንግሥት ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ ወዲያውኑ ውሳኔ ሲያሳልፍ ዩኒቨርሲቲዎች የለጠፏቸው የስንብት ማስታወቂያዎች አንጀት የሚበሉ ነበሩ፤ በማህበራዊ ገጾችም ሲዘዋወሩ ነበሩ።
ያ አስደንጋጭ ክስተት ከተሰማበት መጋቢት 4 ቀን ጀምሮ በመንግሥት እና በጤና ሚኒስቴርና በሀገር ደረጃ በተቋቋመው ግብረ ኃይል በኩል የተለያዩ በተከታታይ ውሳኔዎች መተላለፍ ጀመሩ።እጅ መታጠብ፣ ርቀትን መጠበቅ፣ አፍንና አፍንጫን በማስከ መሸፈን የመከላከያው መንገዶች መሆናቸው ይፋ ተደረጉ።ቤታችሁ ቆዩ የሚል ማሳሰቢያ ተሰጠ።በእዚህም በጣም ወሳኝ ሰራተኞች ካልሆኑ በቀር ሰራተኞች በየቤታቸው እንዲቆዩ ተደረገ።አንዳንድ ሰራተኞች ደግሞ በኦንላይን መስራት ውስጥ ገቡ።የሃይማኖት ተቋማት የጸሎት ስነስርት ሊታወሱ ከሚገባቸው መካከል አንዱ ከስተት ነበር።
በዚያን ወቅት በየአደባባዩ ጎዳናው ወጣቶች እጅ ለማስታጠብ ያደርጉት የነበረው ርብርብ ሳይጠቀስ መታለፍ የሌለበት ነው።
በቅድሚያ የተደረገው የትምህርት ቤቶች መዘጋት ነበር።የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ጨምሮ የተለያዩ ህግና ደንቦች ወጥተው በጥብቅ መተግበር ውስጥ ተገባ።ገበያዎች የትራንስፖርት እንቅስቃሴዎች ታገዱ፤ የአየር ማረፊያና የድንበር ቁጥጥሩ እንዲጠብቅ ተደረገ።
መንግሥት ሥራ በመቆሙ ምክንያት ሊደርስ የሚችለውን ኢኮኖሚያዊ ችግር መፍታት የሚቻልበትን መንገድ ቀየሰ፤ ባለሀብቶችና ሌሎችም ለእዚህ ይህን ሰብዓዊ ተግባር ተቀላቀሉ።በዚያ አስደንጋጭ ክስተት ውስጥ ብዙ አይነት የሰብዓዊነት ትብብሮች ታዩ።አንዳንድ የግል ንግድ ቤቶች ሰራተኞቻቸውን ማሰናበት ግድ ሆነባቸው፤ የንግድ እንቅስቃሴዎች በመስተጓጎላቸው ሊጎዳ የሚችለውን ማህበረሰብ ለመርዳትም ርብርብ ማድረግ ተጀመረ፤ የኢትዮጵያዊነት ወግም በዚህ ወቅት ነጥሮ ታየ፤ መተባበር ባህላችን ነው የሚባለው በተግባር ተገለጠ።
አጭበርባሪዎችና ጨካኞች የሚያማርሩንን ያህል በእነዚያ ደጋግ ሰዎች ኢትዮጵያዊነት ተመሰከረ። ብዙ አከራዮች የአንድና ሁለት ወር የቤት ኪራይ አንቀበልም አሉ፤ አንዳንዶችም 50 በመቶ ቅናሽ አደረጉ፤ አንዳንዶችም የዚያ አስከፊ ወረርሽኝ ስጋትነት እስከሚቀንስ ድረስ ሙሉ በሙሉ አንቀበልም አሉ።
የመገናኛ ብዙኃን የ24 ሰዓት ሽፋን ኮቪድ-19 ብቻ ሆነ።የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ሁሉ የዶክተር ሊያን ገጽ መጎብኘት ጀመረ።በየዕለቱ የሚነገሩ ክስተቶችን ከነሙሉ ዝርዝሩ ማጥናት ሥራችን ሆነ።
በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ እያለን የመጀመሪያውን ሞት መርዶ ስንሰማ ደግሞ ሌላ አስደንጋጭ ስሜት ተፈጠረ።በወቅቱ ዕድሜ ወሳኝ ጉዳይ ተደርጎ ይታሰብ ነበር፤ ሌላው ደግሞ ‹‹ተጓዳኝ ህመም›› ያለበትና የሌለበት እየተባለም ይገለጽ ነበር።
የመገናኛ ብዙኃን መደበኛ ፕሮግራሞች ሁሉ ቅኝታቸው በዚሁ ወረርሽኝ ላይ ያተኮረ ነበር።በዚያን ወቅት ከነበሩ አጀንዳዎች አንዱ የማስታውሰው ‹‹ኮንታጂን›› የተባለው ፊልም የዓለም መነጋገሪያ የነበረ መሆኑን ነው።ይህ ፊልም ሙሉ በሙሉ የኮቪድ-19ኝን ምንነት ያሳያል።በዚያ ፊልም ምክንያት ቫይረሱ ሰው ሰራሽ እና ሆን ተብሎ በዓለም እንዲሰራጭ የተደረገ የፖለቲካ አሻጥር ነው የሚል አሉቧልታም ተነዛ።
የሚገርመው ግን የፊልሙ ይዘት በሙሉ ከኮቪድ-19 ባህሪያት ጋር የሚመሳሰል መሆኑ ነው። የፊልሙ ገጸ ባህሪ ቻይና ሄዳ ነው ቫይረሱ የሚያገኛት።የሚተላለፈውም በመ ጨባበጥና በትንፋሽ ነው።ዓለምን በሙሉ ያዳርሳል።በመጨረሻም ክትባት ይገኝለታል። በፊልሙ ላይ የሚታዩ ህመምተኞችም ምልክታቸው ሁሉ የኮቪድ-19 ህመምተኞች ምልክትን የመሰለ ነበር።ያ ፊልም ግን የተሰራው ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰት 8 ዓመታት በፊት በፈረንጆቹ 2011 ነበር።
የፊልሙ መቼት በዋናነት አሜሪካ እና ቻይና ሲሆን በተለይም ቻይና የቫይረሱ መነሻ ናት።ያ ምናባዊ ፈጠራ በወቅቱ በቻይና እና በአሜሪካ መካከል የነበረውን ገሃዳዊ የኮሮና ወረርሽኝ ሁኔታ ያሳየ ነው።የቫይረሱ መነሻ ቻይና ነው።የተጠቂዎች ቁጥር የሚበዛው ግን አሜሪካ ውስጥ ነበር።በእርግጥ መረጃው በየዕለቱ ስለሚቀያየርና እስከአሁንም ስላልተጠናቀቀ ለጊዜው ማሳያ ሊሆን አይችልም።
በሀገራችን በሽታው መስፋፋቱን ተያያዘው። ከአዲስ አበባ ውጭ ለመጀመሪያ ጊዜ አዳማ፣ ቀጥሎም ባህርዳር፣ አዊ (አዲስ ቅዳም አካባቢ)… እያለ ቫይረሱ ከአዲስ አበባ ውጭ የመገኘቱ ዜና ሲጨመር ድንጋጤውም ጨመረ።
ኮቪድ-19 ገና እንደገባ የነበረው ዜና እና እየቆየ ሲሄድ የነበረው ይለያያል።የመጀመሪያዎቹን እናስታውስ።ኮቪድ-19 ገና እንደገባ አንድ ቫይረሱ የተገኘበት ግለሰብ ሙሉ ታሪኩ ይነገር ነበር።ከየት አገር እንደመጣ፣ ዕድሜው፣ ፆታው… የመሳሰሉ ታሪኮች ተነገሩ። በሰንጠረዥ ተዘጋጅቶ፣ የጉዞ ታሪኩ፣ ከሰዎች ጋር የነበረው ንክኪ ሁሉ ይነገራል።
ኮቪድ-19 በዓለም አቀፍ ደረጃ አስገራሚ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች እንዲተላለፉ፣ ሳይንሳዊ ምርምሮች እንዲካሄድ አስደርጓል።በአገራችንም ኮቪድን ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ ምርጫ 2012 እንዲራዘም ተደረገ።ይህ እርምጃ በአንዳንድ የፖለቲካ ቡድኖች ዘንድ ለፖለቲካ ፍጆታ ዋለ፤ በበጎ ጎኑ ብዙ የፈጠራ ሥራዎችን አስገኝቷል።ላለመመርመር ራሳቸውን ያጠፉ፣ ሸሽተው ሲያመልጡ የነበሩም የዚሁ ወረርሽኝ ትውስታዎች ናቸው።
ኮቪድ-19 በተለያዩ ዘመናት በዓለም ከተከሰቱ እንደ ስፓኒሽ ፍሉ አይነት ወረርሽኞች ሁሉ የክፍለ ዘመኑ ክስተት ሆኗል።እነሆ እንዲህ እንዲህ እያለ ዛሬ ላይ የደረሰበት ደረጃ ደርሷል።ምንም እንኳን ወረርሽኙ አሁንም ቢኖርም፣ ክትባት ተገኝቶለታል፤ አስደንጋጭነቱም (የማይለመድ የለም) እንደበፊቱ አይደለም።በዓለም ከ6 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ሕይወት ነጥቋል፤ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር መጋቢት 2022 ድረስም ወደ 500 ሚሊዮን ሰዎች በበሽታው ተይዘው በህክምና ላይ ይገኛሉ።
በሀገራችንም እስከ መጋቢት 2 ቀን 2014 ድረስ 7ሺ484 ሰዎችን ሕይወት ነጥቋል።ቫይረሱ የተገኘባቸው በአጠቃላይ 469 ሺ 153 ሰዎች ሲሆኑ፣ አሁን ቫይረሱ ያለባቸው ደግሞ 40 ሺ 234 በላይ ዜጎችን ህይወት ነጥቋል።ክትባት መሰጠቱ ተጠናክሮ ቀጥሏል፤ እስከ አሁንም 28 ሚሊዮን 471 ሺ 297 ሰዎች ተከትበዋል።
በሽታውን ለመከላከል በሚል የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና ሌሎች በርካታ መመሪያዎች ከሥራ ውጪ የተደረጉ ቢሆንም፣ አሁንም ስጋቱ ስላለ የተለያዩ መመሪያዎች ወጥተው እየተተገበሩ ይገኛሉ።ማስክ ማድረግ እንዳይዘነጋ ማሳሰቢያ እየተሰጠ ነው። በመረጃ ምንጭነት የተለያዩ ድረገጾችን ተጠቅመናል።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን መጋቢት 4 ቀን 2014 ዓ.ም