ክቡር አቶ ደመቀ መኮንን፣ የብልጽግና ፓርቲ
ምክትል ፕሬዚዳንት፤
ክቡር አቶ አደም ፋራህ፣ የብልጽግና ፓርቲ
ጽህፈት ቤት ኃላፊ፤
የተከበራችሁ የብልጽግና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት፣
እንዲሁም የታሪካዊው አንደኛ ጉባዔ
ተሳታፊዎች በሙሉ፤
የተከበራችሁ የተፎካካሪ ፓርቲ
አመራሮችና ተወካዮች፤
የተከበራችሁ እህት ፓርቲዎችን ወክላችሁ ከተለያየ
አገር የመጣችሁ እንግዶች፤
ሁላችሁም ለዚህ ታሪካዊ ቀን እና ደማቅ የጉባዔ መክፈቻ ሥነሥርዓት ስለተገኛችሁ በራሴና በብልጽግና ማዕከላዊ ኮሚቴ ስም እንኳን ደህና መጣችሁ እላችኋለሁ።
ንግግሬን ከመጀመሬ በፊት ለአራት ዓመት የነበረንን ጉዞ እጅግ አስደናቂ በሆነ መንገድ በጥበብ ለገለጹ፤ በሙዚቃ፣ በቴአትር፣ በስነጽሁፍ በተለያየ መንገድ የነበርንበትን ፈተናና ከፊታችን ያለውን ተስፋ ያመላከቱን፤ እንዲሁም በብዙ አገራት ስናይ፣ ስንመኝ የቆየነውን ይህንን የምናውቀውን አዳራሽ እንዲህ አስውበው ኢትዮጵያ ነን ወይስ ቻይና እንድንል ያደረጉንን በሙሉ እጅግ አድርጌ ማመስገን እፈልጋለሁ።
በሕዝብ ግፊት፣ በለውጥ ፈላጊ አመራሮች ወይም በድርጅት ሳቢነት እንዲሁም በፈጣሪ እርዳታ ብልጽግና ተወለደ።ብልጽግና ዛሬ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካም ግዙፍ ፓርቲ ነው።ብልጽግና የተመዘገበ፣ መዋጮ የሚያወጣ፣ ከ11 ሚሊዮን በላይ አባላት ያሉት ነው።በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በዚህ ቁጥር ልክ ኢህአዴግም፣ ኢሰፓም ተደምረው አያክሉም።ብልጽግና እጅግ ግዙፍ ፓርቲ ነው ሲባል፤ በቁጥር ብቻ ሳይሆን ከኢሰፓም፣ ከኢሃፓም፣ ከሜኢሶም፣ ከኢህአዴግም የሚለየው መጤ በሆኑ እሳቤዎች ሳይሆን መደመርን እንደመርህ፣ መደመርን እንደመንገድ፣ ብልጽግናን እንደመዳረሻ የወሰደ በአገር በቀል ሀሳብ ራሱን የተከለ በመሆኑ ነው፡፡
በሱማልኛ ‹‹ወይ ተራራ ሁን ወይ ከተራራ ተደገፍ›› እንደሚባለው፤ ትንሽዬ ተራራ ሆኖ ከትልቁና ከማይናደው ኢትዮጵያ ከሚባለው ተራራ የተንተራሰ ስለሆነ፤ ብልጽግናን በኢትዮጵያ ምድር ለማረጋገጥ የሀሳብም፣ የቁጥርም፣ የአደረጃጀትም ብቃት ያለው ፓርቲ ነው።ስለሆነም የዚህ ፓርቲ አባል በመሆናችን እጅግ ኩራት ይሰማናል፡፡
በዚህ በአንደኛው ጉባኤያችን ላይ ብልፅግናን የምናየው ሁሉም ብሄሮች በሚገባቸው ቁጥር ልክ የሚሳተፉበት ፓርቲ መሆኑን ነው። ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ የምናውቃቸው ፓርቲዎች 90 በመቶ ኦሮሞ፣ አንድ ወላይታ፣ አንድ ጋምቤላ አንድ ሲዳማ ይዘው ህብረ ብሄራዊ ፓርቲ ነበሩ። ዛሬ ግን የብልፅግና ፓርቲ ሁላችሁም እንደምታውቁት ከሁሉም ብሄር ከሁሉም አካባቢ በቂ የሆነ ውክልና ያለው የስም ኢትዮጵያዊ ፓርቲ ሳይሆን እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ፓርቲ ሆኖ (ቢክ ቴንት ሆኖ) ሁሉን ሰብስቦ ኢትዮጵያን መስሎ ኢትዮጵያን ሊያበለፅግ የመጣ ፓርቲ ስለሆነ፤ ከእስካሁኖቹ በእጅጉ የሚለይና በሚያመጣውም ውጤት በታሪክ ውስጥ በአሻራ የሚታወስ ይሆናል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ቅንጅት፣ ህብረት፣ ኢህአዴግ እንዲሁም በደርግ ጊዜ እጫት፣ ማለሊት ሚባሉ ሌሎችም ፓርቲዎች ለመሰብሰብ በህብረት የጋራ ፓርቲ ለማቋቋም ያደረጉት ሙከራ ሁሉ ሳይሳካ ቀርቶ በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ በርከት ያሉ ፓርቲዎች በአንድ ፕሮግራም ስርና በኢትዮጵያ ጥላ ስር ሰብሰብ ብለው አንድ የሆኑበት የመጀመሪያው ፓርቲ ብልፅግና ነው።ይህ ብቻም ሳይሆን ብልፅግናን ካዩ በኋላም ሌሎች ለመከተል ድፍረት ያጡበትና ብዙ ቋንቋ፣ ብዙ ህዝብ፣ አጋርና ዋና የሚባለውን ከፋፋይ ግንብ ያፈረሰ የቀደመውን ሁሉ ያልናደ ነገ ደግሞ ብሩህ ተስፋ የሰነቀ ፓርቲ ነው፤ ብልፅግና።
በብዙ ፈተናዎች ውስጥ የቆየ ቢሆንም የህዝባችንን እራስን በራስ የማስተዳደር መብት በሪፈረንደም በሲዳማ፣ በምእራብ ኢትዮጵያ ማረጋገጥ የቻለ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ነው፤ ብልፅግና። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ገና ብዙ ሊሰራበት የሚገባም ቢሆን፤ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ የሚባልና መራጩ ህዝብ እኩለ ሌሊትም ጭምር ካርዴን ኮሮጆ ውስጥ ሳላቀላቅል አልሄድም ያለበት ሰላማዊ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማረጋገጥ የቻለ ፓርቲ ነው፤ ብልፅግና።
ተመርጦ ካሸነፈ በኋላ አካታች መሆኑን ለማረጋገጥ በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን የካብኔ አባል፤ በየክልሉም እንዲሁ በተለያየ የኃላፊነት ደረጃ ላይ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች መሾም የቻለ በእውነተኛ አካታችነት የሚያምን ፓርቲ ነው፤ ብልጽግና።
የመጀመሪያው ጉባኤያችን ከፈተና ወደ ልእልና ያለበት ዋናው ምስጢር፤ ድል ባለበት ሁሉ ፈተና ስላለ ነው።እንዲሁ የሚገኝ ድል የለም።ብልጽግና ድል አስፓየር የሚያደርግ /የሚመኝ/ ስለሆነ በማንኛውም ሰዓት የሚገጥመውን ፈታና ወደ ድል መቀየር እንዳለበት የሚያምን ነው።ፈተና ስንል የሚያሸንፍ ፈተና አለ፤ የሚገዳደር ፈተና አለ፤ የሚሸነፍ ፈተና አለ፡፡
እኛ በዚህ በአንደኛው ጉባዔያችን ብልጽግናን አሸናፊ የሚያደርግ፣ የሚያሸንፈውንና የሚገዳደረውን ፈተና የሚረታ ሀሳብና ጉልበት፣ እንዲሁም አንድነት የሚገኝበት ጉባኤ እንደሆነ እናምናለን።ልእልና ስንል ከወጀብ፣ ከአውሎ ንፋስ፣ ከመሬት ስበት ሁሉ ልቆ /ከፍ ብሎ/ ያሰበውን ራዕይ ማሳካት የሚችል ፓርቲ መሆን መቻል ማለታችን ነው።
ዓላማችን ጠንካራ ፓርቲ በእርሱም የሚከወን ጠንካራ አገረ መንግሥት መገንባት ነው።ሌብነትን የሚታገል፣ ሌብነትን የሚጠየፍ፣ ለህዝብ እፎይታ የሆነ፣ ከህዝብ ያልተነቀለ፤ ለህዝብ የቀረበ ፓርቲ መሆን ነው፡፡
የገጠሙንን ፈተናዎች በጥበብ ለመሻገር በጉልበት በስሜት ብቻ ሳይሆን በስሌትም ጭምር፤ ስሌትን አስቀድሞ ጉልበትን አስከትሎ (ጉልበት ለእርሻም ስለሚያገለግል ማለት ነው፤ ለውጊያ ብቻ አይደለም) እነዚህን አጣምሮ የሚሰራ ፓርቲ እንዲሆን ነው።ህብረብሄራዊ አንድነትን የሚያጠናክር፤ ሁሉም ብሄሮች ሁሉም ቋንቋዎች ተከብረው የሚኖሩባት ኢትዮጵያን ማየት ነው።
በዚህ ቤት እያንዳንዱ የጉባኤ ተሳታፊ እራሱን እንዲጠይቅ የምፈልገው፤ ቀደም ሲል በርከት ያሉ ቋንቋዎችን ከመድረክ እንደሰማነው ሁሉ በየግድግዳው ላይ ያሉ መፈክሮችን ብትመለከቱ ከእናንተ መካከል የቻይና ወይም የአረብኛ ቋንቋ ወይም የእንግሊዘኛ ቋንቋ ሲሰማ ይህ ቋንቋ አረብኛ ነው፤ እንግሊዘኛ ነው ማለት የማይችል ሰው የለም።
ነገር ግን በአፋርኛ፣ በሲዳምኛ፣ በሶማሌኛ የተፃፉ መፈክሮችን አይቶ ሳይቸገር ይህ ሲዳምኛ ነው ወይም ይህ አፋርኛ ነው ማለት የሚችል ብዙ ሰው ያለ አይመስለኝም።እኛ የአገራችንን ባህልና ቋንቋ መነጋገርና መግባባት ባንችል ቢያንስ አፋርኛ ቢያንስ ሲዳምኛ ወይም ሌላ ቋንቋ መሆኑን ካለነጋሪ ማወቅ ይገባናል። ንቅል ከሆንን ኢትዮጵያን ማፅናት ስለሚያስቸግር፤ ሁሉን ያቀፈ፣ ሁሉን ለማወቅ የጣረ፣ ወደ ሁሉ የተጠጋ ፓርቲ መሆኑን ለዛሬው በየግድግዳው ላይ ያለው መፈክር ሁሉን የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡
ብልፅግና እንደ ዔሊ ነው።ብልፅግና እንደ ዓሣ አይደለም።እንደ ዓሳ በውሀ ውስጥ የሚዋኝና ከውሀ ሲወጣ መንቀሳቀስ የሚሳነው ሳይሆን፤ እንደ ኤሊ በውሀ ውስጥ የሚዋኝ በአሸዋ ውስጥ ደግሞ የሚራመድ ፓርቲ ነው።በፈተና ውስጥ ሀሳብ እያፈለቀ ወደአሸናፊነት የሚሄድ፣ በሰላም ጊዜ ችግኝ እየተከለ ከተማ እያፀዳ ልማትን የሚያፋጥን ፓርቲ ነው።ብልፅግናን በምናስበው ልክ የተሳካና ውጤታማ እንዲሆን ለማድረግ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በከፍተኛ ቅርበት መስራት ያስፈልጋል፡፡
ብልፅግና 11 ሚሊዮን ነው ሲባል ትዕግስቱም የዚያን ያህል ሰፊ መሆን ይኖርበታል።ብልጽግና ዴሞክራሲን ማረጋገጥ የሚፈልግ አሳታፊ ፓርቲ ነው ስንል፤ አንዳንድ ተገቢም ባይሆኑ የሚሰሙ ድፆች ሲኖሩ በትዕግስት የማድመጥና የማለፍ፣ ትከሻ ሳፊ የመሆን አቅም ሊኖረው ያስፈልጋል። ይህ አቅም እንዲኖረው የምንመኘውና የምንፈልገው ኢትዮጵያን ለማልማት ካለን ፍላጎት ነው፡፡
የሚፎካከሩም ፓርቲዎች በዚሁ አጋጣሚ ብልፅግና አንደኛ፣ በውስጣቸው ዲሞክራሲን እንዲለማመዱ፣ በውስጣቸው አዳዲስ መሪዎችን ማምጣት እንዲለማመዱ፣ በውስጣቸው በሀሳብ ልዕልና መነጋገር የሚችሉ መሆናቸውንና በዚህም ልምዳቸው ለእኛም ለተቀረውም የኢትዮጵያ ህዝብ የዲሞክራሲያዊ ባህልን ለማስፈንና ለማረጋገጥ የሚያግዙ እንዲሆኑ ብልፅግና ከሚፎካከሩም ፓርቲዎች ይጠብቃል።
ተፎካካሪ ፓርቲዎች በሀሳብ የሚታገሉ ነገር ግን አብሪ ኮከብ ያልሆኑ፤ ብልፅግና ሲሳሳት አንድ ስልጣን ላይ ያለ ሰው ሲሳሳት ያቺን አጀንዳ እያስጮሁ ብሄርን ከብሄር፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት፣ ሰውን ከሰው ጋር የሚያጋጩ ሳይሆኑ፤ ሃሳብ ያላቸው፣ የሚነበብ፣ የሚደመጥ፣ የሚያታግል ሃሳብ ያላቸው፤ በሃሳብ ልእልና የሚሞግቱ እንዲሆኑ፤ እንደ አብሪ ኮኮብ ብርሃናቸውን ከሌላ ቋሚ ብርሃን ካላቸው ኮኮቦች እየወሰዱ ቦግ እያሉ የሚጠፉ የሶሻል ሚዲያ ሃይሎች ሳይሆኑ፤ ሃሳብ ያላቸው እና በሃሳብ የሚሞግቱ ፓርቲዎች እንዲሆኑ ብልጽግና ይጠብቃል፡፡
እነዚህን ካሟሉ በጋራ ለሃገር ግንባታ ለመስራት ህግን ለማስከበር ቀደም ሲል ካደረግነው በላይ ተጨማሪ ሰዎች ወደ ፓርቲያችን፣ ወደ መንግሥታችን በማሳተፍ፣ በጋራ ለመስራት ብልጽግና ከምንጊዜውም በላይ ዝግጁ መሆኑን ለማረጋጋጥ እንወዳለን።
የአካታች ሃገራዊ ምክክሩ ሃሳብም ቢሆን መንግሥት እና ብልጽግና ከፍተኛ ፍላጎት ቁርጠኝነት ያላቸው መሆኑ ታውቆ ሁሉም ፓርቲዎች በዚያ ልክ ራሳቸውን እንዲያዘጋጁና ብትብብር ኢትዮጵያን የሚያጸና ሃሳብ ከምክክር መድረኩ እንዲወለድ እኛም ቀዳሚ ፍላጎት መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን።
ለውጡን ለማሳካት፤ እኛ ብልጽግናዎች ለውጡ እንደ ገመድ ዝላይ እንደሆነ እናምናለን። ገመድ ዝላይ እግር ይዘላል፤ እጅ ገመዱን ያዞራል።እግር ወይም እጅ ከዛሉ መውደቅ ይመጣል። እኛ አመርቂ ሃሳብ ስላለን፣ የላቀ ሃሳብ ስላለን ብቻ ሳይሆን ከህዝባችን ጋር ተቀራርበን ተባብረን የምንሰራ በመሆን፣ ቢያንስ በሚቀጥለው ጉባኤ አዳዲስ የብልጽግና መሰረት ጥለን የምንገናኝ እንድንሆን፤ ወደ ህዝባችን የቀረብን፣ ሌብነትን የምንጠየፍ፣ ህዝባችን የሚሰቃይበትን የኑሮ ውድነት ተቀራርብን የምንፈታ፣ የምንመራ ብቻ ሳይሆን የምናገለግል መሪዎች፣ ዜጎች እንድንሆን በዚሁ አጋጣሚ ለብልጽግና ከፍተኛ አመራሮች በታላቅ ትህትና ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡
አንደኛው ጉባኤያችን ወሳኝ ወሳኝ የልማት፣ የዴሞክራሲ፣ የእኩልነት፣ የሰላም አቅጣ ጫዎች የሚወ ሰኑበት ጉባኤ እንዲሆነ ተስፋ አደርጋለሁ። ለኢትዮጵያ ሰላም ከሁሉም ነገር ስለሚልቅ፣ ትናንት ከጦርነት ስለወጣን ሁሉም ጉልበተኛ ነኝ ባይ ሃይል ተረጋግቶ ወደ ሰላም፣ ወደ ንግግር፣ ወደ ማረፍ እና ወደ መልማት እንዲሸጋገር፤ ከዚያ ውጭ ያለው አማራጭ ሁሉ ለኢትዮጵያም ለኢትዮጵያውያንም የማይበጅ መሆኑን ተገንዝበን ለሰላም ለዴሞክራሲ ለልማት በጋራ እንድንቆም አደራ ማለት እፈልጋለሁ።
ቀሪ ጊዜአችን ይበልጥ ጠቃሚ ውይይቶችን የምና ደርግበት፣ የምንቀራረብበት፣ ብልጽግናንን ለማረጋገጥ መሰረት የሚጥሉ አመራሮችን የምንመር ጥበት እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ።ከሰሞኑ እንደሰማችሁት በርካታ የሶሻል ሚዲያ እንቅስቃሴ ብልጽግና ላይ ያተኮረ ነው። ይሄ የሚያሳያው ተቃዋሚ ነን ቢሉም፣ በሌላው ጊዜ ቢሰድቡንም ከዚህ ጉባኤ በእጅጉ በተስፋ የሚጠብቁት ነገር አለ ማለት ነው። ተስፋ ካላደረጉ ስለኛ እያወሩ ሊውሉ እና ሊያድሩ አይገባም። ተስፋ ስለሚያደርጉ እኛም በቀና መንገድ ምርጥ ሃሳብ በማፍለቅ እነሱንም በማቅረብ ኢትዮጵያ የሁላችንም ስለሆነች በጋራ ተባብረን የምናጸናት ሃገር እንድትሆን አደራ ልላችሁ እፈልጋለሁ።ቀሪ ጊዜአችሁ ያማረ ይሁን።እጅግ አመሰግናለሁ!
ያስጀመረን እና የሚያስጨርሰን ፈጣሪ
የተመሰገነ ይሁን!
አዲስ ዘመን መጋቢት 4 ቀን 2014 ዓ.ም