ሰሞኑን ከምንሰማቸው ወሬዎች ቅድሚያ የሚይዘው በሕገወጥ መንገድ ሲዟዟሩ የነበሩ ዘይት እና የሕገ ወጥ መሳሪያዎች ተያዙ የሚለው ነው። በተለይም ከዘይት ዋጋ መናር ጋር ተያይዞ የተለያዩ የሬዲዮ እና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ይህንን ያህል ሊትር ዘይት «እከሌ ከሚባል ቦታ ተያዘ» የሚለውን ዜና ጆሮአችን እስኪሰለቸው ድረስ ደጋግመው መዘገብ ከጀመሩ ውለው አድረዋል። ምናልባትም ከዩክሬን እና ሩስያ ጦርነት በላይ ደጋግመው ሲዘግቡት ሰምተናል።
ተያዘ እየተባለ የሚዘገበው ዘይትም ምናልባትም በሊትር ደረጃ ሲገለጽ መንግሥት ከውጭ አገር አስገባዋለው ከሚለው ጭምር የሚበልጥ ይመስለኛል። ለመሆኑ አጀንዳው የማን ይሆን? የመንግሥት ወይስ የነጋዴዎች? ብለን ጥያቄ እንድናነሳ ያስገድዳል።
በየቀኑ በሕገወጥ መንገድ የተከማቸ ይሄን ያህል ሊትር ዘይት ተያዘ እየተባለ በመንግሥት ደረጃ ይፋ የሚደረጉ ሪፖርቶችን ስንመለከት እንደሃገር መላ ኢትዮጵያን ያለምንም ችግር መመገብ የሚያስችል ከፍተኛ የሆነ የተከዘነ የዘይት ክምችት መኖሩን ከማመላከቱም ባለፈ፤ መንግሥት በሕገወጥ መንገድ ዘይት የሚከዝኑ ነጋዴዎች ላይ የሚያደርገው ቁጥጥር እጅጉን የላላ መሆኑን እና በሕገወጦች ተይዞ የነበረን ነገር ግን መንግሥት ከሕገወጦች የወረሰውን ዘይት ለሕዝብ ለማከፋፈል ያለውን ቁርጠኝነት ደካማ መሆኑንም የሚያሳይ ነው።
ኃላፊነታቸውን በአግባቡ የማይወጡ የመንግሥት አመራሮች የሚፈጥሩትን ክፍተት ስግብግብ ነጋዴዎች ራሳቸውን በአቋራጭ ለማበልጸግ እንደ ጥሩ አጋጣሚ ይጠቀሙበታል። በዚህም ከእጅ ወዳፍ የሚኖረውን የኢትዮጵያ ሕዝብን በእሳት ላይ ከተጣደ ብረት ምጣድ በባሰ የኑሮ ውድነት እሳት ላይ አስቀምጠው እየጠበሱት ይገኛሉ። ከጉዳዩ አሳሳቢነት አንጻር መንግሥት ኮሚቴም ቢያቋቁም በተፈለገው ደረጃ ችግሩን መቅረፍ አልተቻለም።
ኮሚቴው በተለያዩ በክፍለ ከተሞች በሕገ ወጥ መልኩ የተከማቸ ብዙ ሺህ ሊትር ዘይት መያዙን ከመናገር አልፎ ከሕገወጦች የተያዘው ዘይት ለተጠቃሚው ማሕበረሰብ መድረሱን ይፋ ማድረግና ማረጋገጥም ይገባዋል። በሕገወጥ መንገድ የተያዘው ዘይት መልሶ በኤግዚቢትነት ከተቀመጠ ግን ለሕዝቡ እንዴት በሚፈልገው ጊዜ እንዳይደርስ፤ ይልቁንም ነጋዴው አጋጣሚውን ለእኩይ ስራው እንዲጠቀምበት በር የሚከፍት ነው። ሁለቱ ነገሮች ተዳምረው ዛሬም ሕዝቡን ከሰቆቃ መታደግ እንዳልተቻለ በብዙ መልኩ ይታያልና የሚመለከተው ልብ ይበለው፡፡
ምክንያቱም የመንግሥት የሕዝብ ወገንተኝነት የሚታየው ዘይት ከውጭ እስኪያመጣ ድረስ ሕዝብን በኑሮ ውድነት በማሰቃየት ሳይሆን ከውጭ ከሚያመጣው በላይ በሕገወጥ መንገድ ሲያዘዋውር የያዘውን ዘይት ለሕዝቡ ማድረስ ሲችል ነው። ከዚህ ጎን ለጎን አገር እና ሕዝብ የሰጣቸውን አደራ ወደ ጎን በመተው አገር እና ሕዝብን ለችግር የዳረጉ አካላትንም መጠየቅ አለበት። ምክንያቱም ድርጊቱን ፈጻሚዎቹ ቅጣታቸውን ሳያገኙ ከቀሩ የሚማር ነጋዴ አይኖርም።በተመሳሳይ በሙስና ብር ተቀብሎ ሕገወጦችን የሚለቅ አመራርም ካለ አመራሩ መማር አይችልም። እናም ነጋዴውንም ሆነ አመራሩን ሊያስተምር በሚችል መልኩ መንግሥት ቅጣቶችን ማስተላለፍ አለበት። በዚህ ተግባር ላይ የተሰማራው ሕገወጥ ነጋዴም ሆነ ሕዝብ የሰጠውን ሃላፊነት በአግባቡ ያልተወጣን አመራር ምን አይነት ቅጣት እንደተወሰደበት ለሕዝብ ሊገለጽ ይገባል፡፡
ከዚህ ባለፈ መንግሥት የዘይት ፋብሪካዎቻችንንም በስፋት የሚያመርቱበትን እድል ማመቻቸት ይገባዋል። ከውጭ ከሚመጣው ይልቅ ይህ እድል ጥሩ ገንዘብም ሆነ ጊዜን ቆጣቢ ነውና ቢጠቀምበት መልካም ነው። ምን ያህል የማምረት አቅማቸውን አሟጠው ተጠቅመውበት ሕዝብ ጋር ደርሰዋል የሚለውም ሊመረምር፤ ፋብሪካዎቻችን በተሰጣቸው ልክ ሰርተዋል ወይ? ሕዝብ ጋር በቀጥታ እንዳይደርሱ ምን ገደባቸው? እና መሰል ጉዳዮችን አንጥሮ ማወቅም ተገቢ ነው። ሌላው መንግሥት ማድረግ ያለበት ነገር የአገር ውስጥ ምርት በቂ ካልሆነ ከውጭ የሚያመጣውን በፍጥነት ማስገባት ነው።
ከውጭ የሚመጣው ዘይት የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ ሕዝብ በከፍተኛ ደረጃ ተስፋ የጣለበት ነው። ነገር ግን ከዘይት ግዥ ጋር ተያይዞ በመንግሥት ኃላፊዎች የሚሰጡ መግለጫ እርስ በርሳቸው ሲጣረሱ ይታያል። ለአብነትም የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የንግድና እቃዎች ዋጋ ጥናት ክትትልና ቁጥጥር ዳይሬክተር ወይዘሮ መስከረም ባህሩ ለጋዜጠኞች ሲገልጹ፤ የተስተዋለውን የዘይት ዋጋ መናር ለማስተካከል መንግስት 40 ሚሊዮን ሊትር ዘይት በቅርቡ ያስገባል አሉ። ነገር ግን 40 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ግዢ ገንዘብ የሚፈቅደው አካል ጉዳዩን እንደማያውቀው ተናግሯል፡፡
ይህ ደግሞ መንግሥት በገባው ቃል ተስፋ አድርጎ የተቀመጠውን ሕዝብ ተስፋ እንዲያጣ ያደርገዋል። ስለሆነም እንደነዚህ አይነት ችግሮች እየታረሙ መሄድ ይኖርባቸዋል። ምክንያቱም ሕዝብ እንዲያማርር፣ እንዲያለቅስ የሚፈልጉ ነጋዴዎች በአገራችን ተፈጥ ረዋል። በዚያው ልክ አመራሮችም መኖራቸውን መንግሥት ጭምር ይረዳዋል። አስመሳይና ሌባ አመራርን ደግሞ መርምሮና አጣርቶ ወደ ትክክለኛው ሃዲድ ማስገባት የመንግሥት ተቀዳሚ ተልዕኮ ነው። ሰውን እያስለቀሱ መምራትም ሆነ ማስተዳደር በምንም መልኩ አይቻልም፡፡
እናም ብልጽግና ይህንን በሚገባ ተረድቶ አገሩን ለማበልጸግ የመጀመሪያው የቤት ስራው መሆን ያለበት ስውር ደባ ጠንሳሽ አካላትን ማስወገድ ነው።ሕዝብ መሪውን ይመስላልና በየደረጃው ሥልጣን ተሰጥቷቸው የተቀመጡ አካላት አደራቸውን እንዲወጡ ማድረግ ላይ እጅግ ሰፊ ምርመራ ማድረግ ይኖርበታል።አደራ በስጋ ብቻ ሳይሆን በነፍስም ጭምር አስጠያቂ ነውና ያንን አስበው እንዲሰሩ ማድረግ ላይ ትልቅ ንቅናቄ መፍጠር ይጠበቅበታል፡፡
አገርን የመጠበቅ ግዴታ ከሕዝብም በላይ ኃላፊነት የተሰጣቸው አካላት በአመራር ቦታ ላይ ያሉ መሆናቸው እሙን ነው። እናም እነርሱ ለሕዝብ ታማኝና አገልጋይ ካልሆኑና ተገቢውን አመራር ሰጥተው ነገሮችን ካላስተካከሉ ሕዝብ ብቻውን ሊያደርግ የሚችለው ነገር አይኖረውም። ምክንያቱም መረጃ እንኳን አያገኝም። እናም በተባለው መንገድ ብቻ እንደ ውሃ ይፈሳል። ዝምታውም ስቃዩ ሆኖ ዓመታትን ይገፋል። ስለሆነም ለሕዝብ አሳቢ ከሆኑ ለሕዝቡ ታማኝነታቸውን ማሳየት ይኖርባቸዋል። ይህ ሲሆን ደግሞ ብቻችሁን ሳይሆን አጭበርባሪውን በማጋለጥ ጭምር ነው።
በእናንተ ስም የሚነግዱ ብዙ ሌቦች ይኖራሉ። እነርሱ ከሰረቁ በታማኝነት እያገለገሉ ያሉ አመራሮችንም በጅምላ አስጨፍልቆ ማስተቸቱ አይቀሬ ነው። ድሮስ ከኢህአዴግ መቼ የነጻ አመራር አለና ያስብለዋል። መልካም ሰሪ አመራሮች በክፉዎች ተሸፍኗልና ወህኒ ጭምር ሊወርዱ ይችላሉ። ስለሆነም ዛሬ መኝታን ሳትሹ ራሳችሁንም ሆነ አገራችሁን ከሌቦች ነጻ ማውጣት ይጠበቅባችኋል። ስማችሁም በተግባራችሁ መቀየር አለበት። ሌቦቹ ለሕዝብ በታማኝነት የሚሰሩ አገልጋዮች እንጀራ መብላት የለባቸውም። «በጨው ደንደስ አዋዜ ተወደስ» እንዲሉ፤ ምስጉን አመራሮች በሰሩት ሌቦች አብረው ሊመሰገኑም አይገባቸውም፡፡
ዘይት ላይ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም በዚህ መልኩ እየታዩ መፍትሄ ሰጪነታቸው ሊተኮርበት ይገባል። ይህ ሲሆን ደግሞ መንግሥት እንደ መንግሥት የተጣለበትን ኃላፊነት መውሰድ ይገባዋል። በተለይም አመራሩን ከመሞረድና ቦታቸውን እንዲያውቁ ከማድረግ አንጻር ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት አለበት። ከራሳቸው ጥቅም ይልቅ የአገርና የሕዝብ አደራ ሰጪነትን እንዲመለከቱ ጥብቅ የሆነ አመራር መስጠትና መከታተል ይጠበቅበታል። በተመሳሳይ ነጋዴዎችና አምራቾችም ሕዝብ ሲኖር ነውና እነርሱም መክበር የሚችሉት፤ ይህንን አስበው እንደ አገር ልጅነታቸው ይስሩ። ለዛሬ ሃሳቤን ቋጨሁ። ሰላም!
መንበረ ልዕል
አዲስ ዘመን መጋቢት 4 ቀን 2014 ዓ.ም