ባለፉት ዓመታት ውስጥ አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሀገሮች ውስጥ የዜጎች የጤና ሁኔታ የተሻሻለ ቢሆንም በርካታ አዳዲስ እውነታዎችም ተፈጥረዋል። ከእነዚህ መካከል ደግሞ እንደእኛ ሀገር ጦርነቱ የፈጠራቸው ችግሮች በዋናነት የሚነሱ ናቸው፡፡
በዚህም የተለወጡ የጤና አጠባበቅ ፍላጎቶችና አገልግሎቶች ቢኖሩም አዳዲስ አሰራሮችና አገልግሎቶች ካልተጨመሩ በስተቀር ችግሩን በፍጥነት ለመፍታት አዳጋች ነው፡፡ በተለይም እያደጉ ያሉ የማህበረሰብ ጥያቄዎች እና ከፍ ያሉ የጤና አገልግሎት ፍላጎቶች መፍትሔ ይሻሉ፡፡
እነዚህን ፍላጎቶች ለማሟላት ቀጣይነት ያለው አገልግሎት መስጠት፣ በእያንዳንዱ አውድ የጤና ሁኔታን የሚያሻሽሉ ከፍተኛ ጥራት ያላቸው የጤና አገልግሎት ስርዓቶች መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ የተሻሻለ የጤና አገልግሎት እና ፍትሃዊ ስርጭት፤ ሰዎች በጤና አገልግሎት ስርዓታቸው ላይ ያላቸውን መተማመን፤ የሚኖራቸውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እና የአገልግሎት አቅርቦቱ ተወዳዳሪነትና አወንታዊ የተጠቃሚ ተሞክሮ መፍጠርን ጨምሮ በሚያመጧቸው ለውጦች እያዩ መሥራትም ተገቢ ነው፡፡
ይህንን ተግባር እንደ አገር እውን ለማድረግ ሰሞኑን በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ይፋ የተደረገው የተንቀሳቃሽ ጤና ቡድን መሠረታዊ የጤና አገልግሎት ስርዓት ብዙ ችግሮችን እንደሚፈታ ታምኖበታል፡፡ በተለይም በመመሪያና በትብብር የሚሰራ በመሆኑ ድርጊቱን ፈጣንና ስርዓትን የተከተለ እንደሚያደርገው በዘርፉ ያሉ ምሁራን ይናገራሉ።
የተንቀሳቃሽ ጤና ቡድን መሠረታዊ የጤና አገልግሎት በዓለም ላይ ጥሩ ለውጥ ያመጣና ማህበረሰቡን በብዙ መልኩ የጠቀመ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡ እንደ እኛ አይነት ላሉ ሀገራት ደግሞ ፋይዳው የሚቆጠርና ተመንዝሮ የሚያበቃ አይሆንም።
ምክንያቱም ብዙ የጤና ጣቢያዎች በአገር ደረጃ የሉም፡፡ በዚህም ርቀት ተሄዶ ነው አገልግሎቱ የሚገኘው፡፡ ይህ ደግሞ በነበረ የጤና ችግር ብቻ ሳሆን አዳዲስ በሚፈጠር የጤና ችግርም የሚሰቃይ የማህበረሰብ ክፍል እንዲኖር ያደርገዋል። ስለሆነም ይህ አገልግሎት መጀመሩ ከንግልቱም በላይ በቅርበት ዜጎች የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ ያደርጋቸዋልና ጅማሬው ብቻ ሳይሆን ፈጻሜውም እንዲያምር እንመኛለን፡ ፡
ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ይህ አገልግሎት ምን አይነት ጠቀሜታ እንዳለው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በድረገጹ ላይ ያስቀመጠውን ልናጋራችሁም ወደናል፡፡ የተንቀሳቃሽ ጤና ቡድን መሠረታዊ የጤና አገልግሎት በተለይ ለአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ፣ በግጭት ምክንያቶች ለተፈናቀሉ ወገኖች እና ተደራሽ ላልሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ማቅረብ በጣም ውጤታማ መንገድ ነው፡፡ በዚህም የተንቀሳቃሽ ጤና ቡድን አገልግሎት አተገባበር መመሪያ ተዘጋጅቷል፡፡
ከዚያም አልፎ በቅርቡ ለውይይት ቀርቦ ብዙዎች አስተያየቶችን ቸረውበታል፡፡ ጠቀሜታው የተረጋገጠባቸው ክልሎችም ጭምር አሉ፡፡ መመሪያው በቀረበበት ወቅት በድረገጹ እንዳስታወቀው፤ መመሪያው መሰረታዊ የጤና አገልግሎቶችን ተደራሽ ላልሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በማድረስ ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ ቁልፍ ሚና ይኖረዋል። ስለዚህም የጤና ሚኒስቴር የተንቀሳቃሽ ጤና ቡድን ለማጠናከር ብሔራዊ የተንቀሳቃሽ ጤና ቡድን አገልግሎት አተገባበር መመሪያ ዝግጅት ማጠናቀቂያ አውደ ጥናትም በአዳማ ከተማ አካሂዷል፡፡
የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ በአውደ ጥናቱ ላይ ተገኝተው በመልዕክታቸው እንዳሉትም፤ የተንቀሳቃሽ የጤና ቡድን ተደራሽ ላልሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የጤና አገልግሎትን በማድረስ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡
በተለይም የህብረተሰቡን ጤና በማሻሻል ላይ የማይተካ ሚናን ይጫወታል፡፡ ከፍተኛ ውጤት እንዳመጣም በሶማሌና በአፋር ክልሎች ተሞክሮ ተረጋግጧል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገራችን በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉ የህብረተሰብ ክፍሎች መኖራቸው እሙን ነው ያሉት ዶክተር ደረጄ፤ ይህ የተንቀሳቃሽ ጤና ቡድን መሠረታዊ የጤና አገልግሎት በቅርበት የጤና ችግራቸውን ለመፍታት ጥሩ መፍትሄ ሰጪ ነው፡፡ በተጨማሪም በአርብቶ አደር አካባቢዎች፣ በልማት ኮሪደሮች፣ በስደተኛ ካምፖች፣ በገጠርና በከተሞች አካባቢ በርካታ ለጤና አገልግሎት ተደራሽ ያልሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ይኖራሉና ለእነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች መሠረታዊ የጤና አገልግሎት ለማድረስ እንዲሁም ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ የተንቀሳቃሽ የጤና ቡድን አገልግሎቱ የማይተካ ሚና ይኖረዋል፡፡
በአተገባበር መመሪያው መደገፉ ደግሞ ፋይዳውን ይበልጥ እንደሚያጉላው ያነሱት ዶክተር ደረጄ፤ አያይዘውም የመመሪያው መዘጋጀት ብቻ በቂ አለመሆኑንና መመሪያውን ወደ ተግባር ቀይሮ ውጤታማ ለማድረግ የጤና ሚኒስቴር፣ የክልል ጤና ቢሮዎችና አጋር ድርጅቶች በጋራ ትኩረት ሰጥተው መሥራት ይገባቸዋል፡፡ ለዚህም ዩኒሴፍ እና ሌሎች አጋር ድርጅቶች እስካሁን ላደረጉት ድጋፍ እናመሰግናለን ብለዋል፡፡
በጤና ሚኒስቴር የጤና ስርዓት ማጠናከርና ልዩ ድጋፍ ዳይሬክተር አቶ ገሙ ቲሩ በበኩላቸው በድረገጹ ላይ ተናግረዋል ተብሎ እንደተቀመጠው፤ በአርብቶ አደር አካባቢዎችና በተለያዩ ምክንያቶች ለተፈናቀሉ የህብረተሰብ ክፍሎች በተንቀሳቃሽ የጤና ቡድን አማካኝነት የጤና አገልግሎት ለማድረስ ከአጋሮች ጋር በመሆን በተሠራው ሥራ አመርቂ ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን የአገልግሎት አሰጣጡ እንደ ሀገር የሚመራበት መመሪያ ባለመኖሩ ይህ ብሔራዊ የተንቀሳቀሽ ጤና ቡድን አገልግሎት አተገባበር መመሪያ መዘጋጀቱን አስረድተዋል፡፡
የአተገባበር መመሪያው በቀጣይ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ለማሻሻል ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ መመሪያውን ተከትሎ መሥራት ላይ ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡ በተለይም አብረው የሚሰሩ ባለሙያዎችና አጋሮች ለዚህ መመሪያ ትግበራ የተቻላቸውን ሁሉ ሊያደርጉ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
በአውደ ጥናቱ ላይ የተሳተፉ በተለይ ከሶማሌና ከአፋር ክልሎች የመጡ ከፍተኛ ጤና ባለሙያዎችን አነጋግሮ በድረ ገጹ ላይ እንዳሰፈረውም፤ ተንቀሳቃሽ የጤና ቡድን በክልላቸው ተደራሽ ላልሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች መሠረታዊ የጤና አገልግሎትን በማድረስ የብዙ ህብረተሰብ ክፍሎች ሕይወትን መታደጉን እራሳቸው ምስክር መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ አገልግሎቱን የበለጠ ለማጠናከር ይህ የአተገባበር መመሪያ መዘጋጀቱ እንዳስደሰታቸው ገልፃዋል፡፡
ለፕሮግራሙ ውጤታማነትም ጤና ሚኒስቴር፣ ክልሎችና አጋር ድርጅቶች የበጀት፣ የግብዓትና የቴክኒካል ድጋፍ አጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው ተሳታፊ ባለሙያዎች ጠይቀዋል፡፡
መመሪያውን ለማዘጋጀት ከዚህ ቀደም ተከታታይ የምክክር አውደ ጥናቶች እንደተካሄዱ የተገለጸ ሲሆን፤ በዚህ የማጠናቃቂያ አውደ ጥናት ላይ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ከክልል ጤና ቢሮዎችና ከአጋር ድርጅቶች የተውጣጡ ከፍተኛ ጤና ባለሙያዎች ተሳትፈው ተገቢውን ግንዛቤ መያዛቸውንም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በድረገጹ ላይ አስቀምጧል፡፡
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን መጋቢት 3 /2014