የንግዱ ዘርፍ በስፋት በሚከናወንበት ሀረር ከተማ ተወልደው እንደማደጋቸው ወደ ንግዱ ዓለም በመሳብ በተለያዩ የንግድ ዘርፎች ውስጥ ተሳትፈዋል፡፡ ከትውልድ መንደራቸው ሀረር ከተማ ከጀመሩት የጫት ንግድ አንስቶ በውጭ አገራት ጭምር በተለያዩ የንግድ ሥራዎች የመሰማራት ዕድልም አጋጥሟቸዋል፡፡
አሁንም አብላጫ ጊዜያቸውን በውጭ አገራት በማድረግ የተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎች የተሰማሩ ጠንካራ ሴት ናቸው፡፡ ማርች 8 ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በተከበረበት ማግስት ያገኘናቸው ነጋዴዋ ሴት በንግድ ዓለም ለመሰማራታቸው ምክንያቱ አካባቢያቸው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
የዛሬው የስኬት አምድ እንግዳችን ወይዘሮ ራሔል ወልደማርያም ይባላሉ። ወይዘሮ ራሔል በአገር ውስጥና በውጭ ሀገር ንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ናቸው፡፡ ሾፌር ከሆኑት ወላጅ አባታቸው ጋር የተለያዩ አካባቢዎች ላይ የመንቀሳቀስ ዕድል አግኝተዋል፡፡ ባገኙት ዕድልም ገና ልጅ እያሉ ስለንግድ ሁኔታ በአዕምሯቸው ማመላለስ እንዲችሉ ሁኔታው አስገድዷቸው የንግዱን ዓለም ለመቀላቀል ችለዋል፡፡
‹‹ከወላጅ አባቴ ጋር በቼንቶ መኪና ከቦታ ቦታ መንቀሳቀሴ ንግድ ምን እንደሆነ እንድረዳ አድርጎኛል›› የሚሉት ወይዘሮ ራሔል፤ በወቅቱ ሥራ ማለት መነገድ ብቻ እስኪመስላቸው ድረስ የአደጉበት ቦታ ተጽዕኖ አሳድሮባቸዋል። ታዋቂ ነጋዴ ለመሆን ምኞቱ ያደረባቸው ገና ከልጅነታቸው በመሆኑ ዛሬ ለደረሱበት ደረጃ አድርሷቸዋል።
በትዳር ዓለም ውስጥ ገብተው ኑሮን ‹‹ሀ›› ብለው በጀመሩበት ሀረር ከተማ ላይ አራት ልጆች ወልደው በማሳደግ፤ አስተምረው ከማስመረቅ ባለፈ ኩለው ድረዋል፡፡ ታድያ በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ በርካታ ፈታኝና የማይቻል የሚመስሉ ችግሮችን ተቋቁመው ማለፍ እንደቻሉ የሚናገሩት ወይዘሮ ራሄል፤ የዘጠነኛ ክፍል ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደ ንግድ ዓለም ነበር የገቡት፡፡ በአሁኑ ወቅት በዋናነት ዱባይ፣ ቻይና፣ ባንኮክና በሌሎች አገራትም በመዘዋወር የሽፎን ጨርቆችን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት በስፌት ሥራ ተሠማርተው የሥራ ዕድል ከፈጠሩላቸው አራት ሠራተኞቻቸው ጋር በጋራ ይሠራሉ፡፡
የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ሆነው ወደትዳር ዓለም የገቡ በመሆናቸው ነፍሰጡር እያሉ ጀምሮ የንግድ ሥራን ጀምረዋል፡፡ የመጀመሪያ ልጃቸውን ባረገዙበት ወቅት ትምህርታቸውን አቋርጠው በመሆኑ የራሳቸው ገቢ እንዲኖራቸው በማሰብ የንግድ ሥራ ሠርተዋል፡፡
ልጃቸውን ወልደውም ከተወሰነ እረፍት በኋላ በንግዱ ዓለም ጠንካራ ሠራተኛ ሆነው እርሳቸው ያጡትን ትምህርትና ሌሎች ዕድሎችን ልጆቻቸው ማግኘት እንዲችሉና የተሻለ ደረጃ ለማድረስ ብሎም ኢኮኖሚያዊ ጥገኛ ላለመሆን የጀመሩትን ንግድ አጠናክረው ለማስቀጠል ወስነው ተንቀሳቅሰዋል፡፡
ከልጅነት ጀምሮ ሲያስተውሉት የነበረውንና በተግባር ሲከወን እየተመኙ ያደጉትን የንግድ ሥራ ቀዳሚ ምርጫቸው በማድረግ ከላይ ታች በማለት ነግደዋል፡፡ ሞቅ ደመቅ ያለው የሀረር ከተማም ለንግድ እንቅስቃሴያቸው ምቹ ሁኔታን የፈጠረላቸው በመሆኑ በጫት ንግድ የመጀመሪያውን ምዕራፍ ተቀላቅለዋል።
ከሀረር ወደ ድሬደዋ ጫት በማመላለስ ንግዳቸውን ያስቀጠሉት ወይዘሮ ራሔል፤ አራት ልጆቻቸውን ወልደው ሲያሳድጉም በዚሁ የጫት ንግድ በመሆኑ በወቅቱ ከቦታ ቦታ ተሯሩጠው ከወንዶች እኩል ጫት ሸጠዋል፡፡ የንግዱ ሁኔታ እንደጊዜው ሲቀዛቀዝም ከአካባቢ አካባቢ ያለውን የንግድ ሙቀት እየተከተሉ በተለያዩ አካባቢዎች ጫትን በስፋት መነገድ ችለዋል።
ንግዱ መስመር ይዞ አዋጭነቱን ማረጋገጥ ሲችሉም ከፍ ወዳለ ንግድ ለመሰማራት በማሰብ ወደ አዲስ አበባ አቅንተዋል፡፡ ወትሮውንም ልጆቻቸውን የተሻለ ትምህርት ቤት ለማስተማር ጽኑ ፍላጎት የነበራቸው ወይዘሮ ራሔል፤ አዲስ አበባ ሲገቡ ግን ነገሮች እንዳሰቡት አልጋ በአልጋ አልሆነላቸውም፡፡ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋርም በቀላሉ ለመግባባት አዳጋች የነበረ መሆኑን ያስታውሳሉ።
በተለይም በንግድ ውስጥ ያለው የንግድ ስርዓትና ውድድርንም በቀላሉ መልመድ ሳይችሉ ቀርተው ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፈዋል፡፡ በመሆኑም ወደ አዲስ አበባ ባቀኑበት የመጀመሪያዎቹ ዓመታት ልጆቻቸውን እንደተመኙት በመረጡት የግል ትምህርት ለማስተማር አቅማቸው አልፈቀደምና በመንግሥት ትምህርት ቤት አስተምረዋል፡፡ ተወልደው ባደጉበት ሀረር ከተማ የጫት ንግድ የቆዩት ወይዘሮ ራሔል፤ አዲስ አበባ ገብተው የጀመሩት የቅቤ ንግድ ነበር፡፡
ለሸራተን አዲስ ሆቴል የምግብ ቅቤ ከምታስረክብ አንዲት ሴት ጋር ተዋውቀው እርሳቸው ከወላይታ የምግብ ቅቤ ሰብስበው በመግዛት ለዚህችው ሴት ያስረክባሉ፡፡ በወቅቱ ጥሩ የሥራ እንቅስቃሴ መፍጠር እንድችል አድርጋኛለች ሲሉ ያመሰግናሉ። ከእርሳቸው የተረከበችውን ቅቤ እሴት ጨምራ ማለትም አንጥራ ለምግብ ዝግጁ በማድረግ ለሆቴሉ ታስረክብ እንደነበርም ያስታውሳሉ፡፡
የቅቤ ንግዱን ማስቀጠል በቻሉ ጊዜም ሌሎች ሥራዎችንም ጎን ለጎን ማከናወን በመቻላቸው ልጆቻቸውን ከመንግሥት ትምህርት ቤት አስወጥተው በተመኙት የግል ትምህርት ቤት ማስተማር ችለዋል፡፡ ‹‹የእኔን ጥንካሬ ተመልክተው ልጆቼም ጠንካራ ሆነው አደጉልኝ›› የሚሉት ወይዘሮ ራሄል፤ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ በሆነው ልጃቸው አማካኝነት ደግሞ ሌላ የንግድ አማራጭ የተፈጠረላቸው መሆኑን ይናገራሉ።
በአጋጣሚውም በወቅቱ ቲያንስ በሚባል ካምፓኒ ውስጥ መግባት እንደቻሉና የውጭውን ዓለም ማየት መብቃታቸውን አጫውተውናል፡፡ ከበርካቶች ጋር ግንኙነት የነበራቸው በመሆኑ ካምፓኒው የሚፈልገውን የደንበኞች ቁጥር በማሟላት መድረስ የሚገባቸው ደረጃ ላይ ደርሰው የተለያዩ ዕድሎች ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡
በወቅቱ የመኪና ተሸላሚ የሆኑ ሰዎች እንዳሉ በማስታወስ እርሳቸው ደግሞ የውጭውን ዓለም ማየት የቻሉበትን የመጀመሪያውን ዕድል አግኝተው ወደ ባንኮክ አቅንተዋል፡፡
ባገኙት ዕድልም ከአገር ውጭ ያለውን የንግድ እንቅስቃሴ ከመረዳት ባለፈ መሳተፍ የሚችሉበትን ምቹ ሁኔታ ፈጠረላቸው፡፡ በዚህ አጋጣሚም ለንግድ የማይቦዝኑት ወይዘሮ ራሔል፤ ሁኔታዎችን በማጥናት የውጭ አገር ንግድ ውስጥ ገቡ፡፡
በወቅቱ ከእርሳቸው ጋር የነበሩትን ሰዎች በማወያየት አገር ቤት ምን ቢወሰድ ይጠቅማል፤ የትኛው ነገር ይረክሳል የቱስ ውድ ነው የሚለውን ሃሳብ እያመላለሱ ባላቸው ጊዜ የተለያዩ የገበያ ቦታዎችን በማፈላለግ አዋጪ ናቸው የተባሉ አልባሳትን ጨምሮ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ወደ አገር ውስጥ በማምጣት የአስመጪነት ንግዱን ቀጥለዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ የጀመሩትን የውጭ አገር ንግድ ወደ ዱባይ ንግድ ከፍ በማድረግ የተለያዩ የሴትና ወንድ አልባሳትን ጨምሮ ብትን ጨርቆችን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ለነጋዴዎች በማስረከብ ንግዱን ያቀላጥፉት ጀመር፡፡
ወይዘሮ ራሄል፤ የዱባይ ንግድ ማግኘትም እንዳለ ሁሉ ኪሳራም ሲያጋጥማቸው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ይሁንና ንግዱን በስፋት ለማስቀጠል በማሰብ ወደ አገር ውስጥ አስገብተው ለነጋዴ የሚያስረክቡትን በተለይም ሽፎን የተባለውን ጨርቅ በግላቸው ሰፊዎችን ቀጥረው ማሰራት የተሻለ እንደሚሆን በማሰብ ቤት ተከራይተውና አራት የስፌት መኪናዎችን ገዝተው ሌላኛውን አዋጪ ያሉትን የንግድ መንገድ አስቀጠሉ፡፡
አዳዲስ ነገሮችን የመመልከት የመረዳትና የማወቅ ጉጉት ያላቸው ወይዘሮ ራሔል፤ ቻይና፣ ባንኮክናዱባይ በመመላለስ ለስፌት የሚሆኑ የሽፎን ጨርቆችን በሚያመጡ ጊዜ ታድያ የሚያጋጥማቸውንና አዲስ የመሰላቸውን ነገሮች ሁሉ ይጠይቃሉ። ከመጠየቅ ባለፈም ምቹ ሁኔታ ካለውና ጠቃሚ ሆኖ መሳተፍ ከቻሉ ይሳተፋሉ፡፡ በተሳትፏቸውም ሌሎች ሴቶችን ጨምረው ለመጓዝ ጥረት በማድረግ ከቤተሰቦቻቸው ጀምሮ በዙሪያቸው ያሉ ሴቶችን እንዲህ ብናደርግ፤ ይህን ብንሠራ ማደግ እንችላለን በማለት ብዙዎችን ለሥራ እንደሚያነቃቁም ይናገራሉ፡፡
‹‹አብዛኞቻችን ድፍረት የለንም እንጂ በርካታ ዕድሎች ገጥመውናል›› የሚሉት ወይዘሮ ራሔል፤ ያገኙትን ዕድል ሁሉ የመጠቀምና የመሞከር ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው፡፡ በዚህም ሁለት ጊዜ ወደ አውሮፓ ጣልያንና ፈረንሳይ አገር የመሄድ ዕድል የገጠማቸው መሆኑን አጫውተውናል፡፡ ታድያ ለንግድ ካላቸው ፍላጎት የተነሳ በሄዱበት ሁሉ የንግድ እንቅስቃሴን ማጥናትና ከአገራቸው ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማወዳደር ተገቢና ወሳኝ የሚሏቸውን ቁሳቁሶች ወደ አገር ቤት አምጥተው ሸጠዋል ፡፡
በአንድ ነገር ብቻ ታጥረው መቀመጥ የማይችሉትና የተለያየ እይታ ያላቸው ወይዘሮ ራሔል፤ የዓለምን ታሪክ መረዳት እንደቻሉ ለሌሎችም የሚቻልና የሰማይ ጥግ እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡
ለዚህም ታድያ ከፍላጎትና ከተነሳሽነት ጋር ድፍረት አስፈላጊ እንደሆነ በማንሳት በርካቶች ግን በቂ ዕውቀት አቅምና ችሎታ እንዲሁም ገንዘብ እያላቸው የውጭውን ዓለም ተሞክሮ ሲወስዱ አይታይም ፡፡ ነገር ግን አውሮፓና አፍሪካን መጎብኘትና የንግድ ስርዓቱን መመልከትና ልምድ መውሰድ በምንሠራው ሥራ ላይ የሚያተርፍ ብዙ ነገር መኖሩን ነው ያስረዱት፡፡
በውጭ አገራት በርካታ ጠቃሚ የሆኑ አሰራሮች አሉ፡፡ ሴቶች በውጭ አገር ያለውን የሥራ ተሞክሮ በተለይ ሴቶች ማየት ቢችሉ ብዙ ነገር ይቀየራል ። ነጋዴ ሴቶችንና የተለያዩ ምርቶችን እያመረቱ ላሉ ሰዎች የውጭውን ዓለም መጎብኘት እንዲችሉና የተለያዩ ስልጠናዎችን እንዲያገኙ ማድረግ ቢቻል ሰፊ ሥራ መሥራትና መለወጥ ይቻላል በማለት እራሳቸውን አብነት አድርገው ያቀርባሉ፡፡
የውጭውን ዓለም መረዳት ሲችሉ ለሥራ ያላቸው ፍላጎትና ተነሳሽነት በእጥፍ የጨመረ መሆኑን በማንሳት ለዚህም ነጮቹ በዕድሜ ሳይገደቡ የትኛውንም አይነት ሥራ መሥራት መቻላቸው አንዱ ማሳያ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ ብዙ መሥራት በሚችሉበት ዕድሜያቸው በተለይም ሴቶች የቤት እመቤት ሆነው ቀድመው እንደሚወድቁና ይህም የሚቆጫቸው መሆኑን እና መቀየር ያለበት እንደሆነም አጽንኦት ሰጥተው ይናገራሉ።
በአገራችን ገና ያልተነኩ በርካታ የሥራ ዘርፎች መኖራቸውን እና በእነዚህ የሥራ ዘርፎች ላይ በመሰማራት እራሳችንን ለውጠን አገርን መለወጥ እንችላለን የሚሉት ወይዘሮ ራሔል፤ ለዚህ ግን በቅንነትና በታማኝነት በመተጋገዝ ጭምር መሥራት አስፈላጊ ከመሆኑም በላይ ድፍረትና ቆራጥ መሆን ወሳኝ ነው ይላሉ፡፡ በተለይም ሴቶች አንድ ነገር ላይ ብቻ ትኩረት አድርገን ከምንሰራ ዕይታችንን ሰፋ በማድረግ በርካታ ያልተነኩ ዘርፎች ጋር በመድረስ ልንሰራ ይገባል፡፡
ለዚህም በተገኘው አጋጣሚ የውጭውን ዓለም ማየት ከተቻለ የአመለካከት ለውጥ በማምጣት ተአምር መሥራት ይቻላል በማለት ያላቸውን ሀሳብ አካፍለውናል፡፡ በአሁኑ ወቅት የዱባይ ንግድ የተቋረጠ ቢሆንም ቀደም ሲል የገቡ ምርቶችን በመጠቀም የስፌት ሥራውን እየሰሩ ነው።
ባጋጠማቸው የተለያዩ የውጭ እድሎች በውጭው ዓለም መቅረት የሚችሉ ቢሆንም እርሳቸው ግን ከውጭው ዓለም ቴክኖሎጂያቸውን፣ ለሥራ ያላቸውን አመለካከትና ሌሎችም በርካታ ጠቃሚ ባህሎቻቸውን ብቻ በመውሰድ በአገራቸው ተግባራዊ ማድረግን ይሻሉ፡፡
ለሌሎችም ይህን ይመክራሉ። በቀጣይም የጀመሩትን የንግድ ሥራ አጠናክረው በመቀጠል ለበርካቶች አርአያ መሆንና ለዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሮ በአገራቸው ላይ ከዚህ በበለጠ ለመሥራትና ለመለወጥ እየተጉ ናቸው፡፡
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን መጋቢት 3 /2014