
ሰሜን ኮሪያ አዲስ አህጉር አቀፍ ባለስቲክ ሚሳኤል (አይሲቢኤም) በቅርቡ መሞከሯን እና ይህም ነገሮችን “ይበልጥ የሚያባብስ ነው” ስትል አሜሪካ አስታወቀች።
ፒዮንግያንግ የካቲት 26 እና መጋቢት 4 የተካሄደው ሙከራ የወታደራዊ ስለላ ሳተላይት በማዘጋጀት ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልጻለች።
ፔንታጎን እንዳለው ሙከራዎቹ አይሲቢኤም ከማስወንጨፍ በፊት የተደረጉ ጅምር ሙከራዎች ናቸው።
በትንሹ 5ሺህ500 ኪሎ ሜትር የሚጓዙት አይሲቢኤም፤ አሜሪካ ሊደርሱ የሚችሉ ሲሆን ለኒውክሌር ጦር መሳሪያ አቅርቦት የሚሠሩ ናቸው። የፔንታጎን ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ ሐሙስ ዕለት የሰሜን ኮሪያ ሁለት ሙከራዎች “አዲስ አህጉር አቋራጭ የባለስቲክ ሚሳኤሎችን ያካትታሉ” ብለዋል።
ሁለቱም ሙከራዎች የአይሲቢኤም አቅም እንዳላቸው ባያሳዩም “ወደፊት ሙሉ በሙሉ ሙከራ ከማድረጋቸው በፊት አዲሱን ስርዓት ለመገምገም የሚያስችል ሊሆን ይችላል” ሲሉ ኪርቢ ተናግረዋል።
“አሜሪካ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔዎችን የሚጥሱትን እነዚህን ሙከራዎች በፅኑ ታወግዛለች። አላስፈላጊ ውጥረትን የሚጨምሩ እና የአካባቢውን ፀጥታ ሊንዱ ይችላሉ” ብለዋል። ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓንም የአሜሪካን መግለጫ አረጋግጠው ፒዮንግያንግ አውግዘዋል።
የደቡብ ኮሪያ የመከላከያ ሚኒስቴር አርብ ዕለት በሰጠው መግለጫ ሁለቱን የቅርብ ጊዜ ሙከራዎች “አዲስ በመበልጸግ ላይ ካለው የአይሲቢኤም ስርዓት” ጋር በማገናኘት ቀደም ሲል የሰሜን ኮሪያ ገዥ ፓርቲ በጥቅምት ወር ባደረገው ወታደራዊ ትርኢት ይፋ ተደርጎ ነበር ብሏል።
ሴኡልም ሙከራዎቹን አጥብቃ አውግዛለች። ጃፓን በበኩሏ “የሠላም እና የደህንነት ስጋት ሲሆን ፈጽሞ ሊታለፍ የማይችል” ስትል ሙከራውን ገልጻዋለች። አንድ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣን ሙከራዎቹን ውጥረትን “ይበልጥ የሚያባብሱ” ሲሉ ገልጸው ዩናይትድ ስቴትስ በሰሜን ኮሪያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀቦችን እንደምትጥል ገልጸዋል።
ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉት ባለስልጣኑ እንዳሉት አዲሱ እርምጃ ፒዮንግያንግ የሚሳኤል ፕሮግራሟን የበለጠ ለማሳደግ የሚረዷትን “ዕቃዎችን እና ቴክኖሎጂዎችን” እንዳታገኝ ያደርጋል።
ሰሜን ኮሪያ በሚሳኤል እና በኒውክሌር ጦር መሳሪያ መርሃ ግብሯ ምክንያት ዓለም አቀፍ ማዕቀብ ተጥሎባታል።
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ-ኡን አንዳንድ ጊዜ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ፍንጭ ቢሰጡም ፒዮንግያንግ ከ 2017 ጀምሮ ምንም አይነት የአይሲቢኤም ወይም የኒውክሌር ሙከራ አላደረገችም።
አዲስ ዘመን መጋቢት 3 /2014