በመዲናችን አዲስ አበባ ተመሳስሎ ያልተሰራ፣ከጎኑ ማታለያ ያልተቀመጠለት፣አለያም ባዕድ ነገር ያልተቀየጠበት አገልግሎት ማግኘት ላሳር ነው። አሁን አሁንማ ቆመው የሚሄዱት ሰዎችም ተመሳስለው የተሰሩ እየመሰሉኝ መጥተዋል። የሚሸመቱ እቃዎችን ተዋቸው። ከአይን እይታ የዘለሉ ማታለያዎችን ጭምር መጠቀም ተክነውበታል። ምነው በዚህ ደረጃ ለማታለያነት የሚያውሉትን (የሚያስቡበትን) አዕምሮ ህብረተሰቡን ቢጠቅሙበት፣ ቢመረቁበት እና የሚለወጡበት ተግባር ቢፈጽሙ ያሰኛል። የሚገርመው በዘላቂነት የሚጠቅም ነገርን መኮረጅ አለመቻላቸው ነው። እንደ ቴክኖሎጂ አይነት እውቀትን ምነው በኩረጃም ማስፋት በተቻለ። ተጠቅመውበት እልፍ ሲልም ተሸልመውበት መንገስ ይችሉ ነበር።
ተፈላጊነታቸውም በገበያ ላይ ይጨምራል፡ ምክንያቱም የሀገሪቱ የኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ በአዲስ መልክ መፍጠር ያልተቻሉ ቴክኖሎጂዎችን ለራስ በሚሆን (በሚጠቅም) መንገድ መኮረጅን ይመክራል። ለካ በነካ እጃቸው ነው ሟች ነፍሳቸውን ይማረውና ‹‹መስረቅ ካልተያዙ ሥራ ነው፣ ከተያዙ ግን ወንጀል ነው›› አሉ ተብለው የሚታሙት። ልብ በሉ ሃሜት ነው። አሁን ላይ በእነሱ የማታለያ ማሽኖች ተፈብርኮ ከእኛ የማየት አቅም በላይ ተሸፍኖ ያልቀረበ ቁስ ያለ አይመስለኝም።
ህብረተሰባችን በጫንቃው ተሸክሟቸው የሚኖሩ እልፍ አታላዮች ከጓዳ እስከ አደባባይ ሞልተዋል። ምን ህብረተሰቡ ብቻ መንግስት ጭምር እንጂ ተሸካሚው። ከእለት ጉርስ ፈላጊው እስከ አገር ኢኮኖሚ ሾፋሪው ቱጃር ድረስ ማታለል፣ መዋሸት፣ ማጭበርበር በሙያነት ተመርቀውበታል። ከታች እስከ ላይ ያደግንበትን ወግ፣ ባህልና እምነታችንን አስክዶ ትውልዱን የወረረ አደገኛ ተዛማች በሽታ ሆኗል። የሰው ልጅ በዘመን ዥረት መሃል ሲፈስ በአዎንታም ሆነ በአሉታ ለውጦች ማሳየት ተፈጥሯዊ ግዴታ ነው።
የሚጠቅሙትን በእጁ ጨብጦ የማይጠቅሙትን ከመዳፉ እያራገፈ ሰዋዊ ባህሪን ተላብሶ መገስገስ የእሱ ፋንታ ነው። አሁን ላይ አውሬነት ባህሪያችን ይመራን ይዟል። ሰሞኑን አንዲት ጎረቤቴ ያጫወተችኝን ልንገራችሁ፤ መቼም ሚስጥር ብዬ የነገርኩህን በአደባባይ ለምን አወራኸው እንደማትለኝ ተስፋ አደርጋለሁ። ምክንያቱም የእሷ ልብ ያልቻለውን ሚስጥር እንዴት የእኔ ልብ ይችላልና። ለሁላችንም መቻያውን ይስጠን። ምነው? አሜን፣ አሜን… አይባልም!? እንዴ? ሲሆን ሲሆን ቆሞ ከወገብ ጎንበስ ተብሎ እጅ ተዘርግቶ የሁለት እጅ መዳፍን እስከ መሳም ነበር። ለነገሩ ይሄስ ቢሆን ተመሳስሎ ሳይሰራ ይቀር ብላችሁ ነው?ድሮ ለምርቃት ተብሎ እግር እስኪነቃ ይኬዳል፤ አገልግሎት ይሰጣል። ለሚከወን መልካም ተግባር ምርቃት በሂሳብነት ይከፈላል።
በዚያኛው ጫፍ ደግሞ እርግማንም የመብረቅ ያህል ይፈራል፤ ይከበራል፤ ያለ ቦታው አይወረወርም። እርግማን ከማደህየት አልፎ እድሜን ይቀጫል፤ያሣጥራል። እነዚህ ህግጋት ሰጥ ለጥ አድርገው ሀገር ሙሉ ሕዝብ ያስተዳድሩ ነበር። የሰው ልጆች ወንጀል የሚፈሩ እጆች እና ኩነኔ የሚፈሩ አንደበቶች ባለቤት ሆኖ ለእልፍ ዘመናት እንዲኖር አስችለውታል። ዛሬ እርግማንም፣ ምርቃትም፣ እምነትም ረክሰዋል፤ ዋጋ አጥተዋል፤ የአውሬነት ድርጊታችንን የመመከት አቅማቸው ሞቷል። ማን ከቁብ ቆጥሮ ጆሮ ይሰጣቸዋል። ታዲያ እነዚህ ፎርጂድ አልሆኑም ትላላችሁ? እንደ ‹‹ሥድ አደግ›› በሄድኩበት ቀረሁ እኮ። ጨዋታየን አስረሳችሁኝ። እናም እኚሁ ጎረቤቴ ቀጠሉ ‹‹የጤፍ እብቅ ከማበጠር፣ከወፍጮ ሥር ዱቄት ከማቡነን ተገላገልኩ እያልኩ ዘወትር እመርቃለሁ።
ዘወትር ሥል በየወሩ ማለቴ ነው። ዱቄትና ደመወዝ ከእኛ ቤት አብረው ይመጣሉ፤አብረው ይሸኛሉ። እንዲህ ነው ኡደታቸው›› ብለው በረዥሙ ተነፈሱ። ቀጥለውም ‹‹ዱቄት ሲቀርለት አይኔም ብርታት ያገኘ መስሎ ይሰማኛል›› ወፍጮ ቤት ድረስ የምሄደው በአይኔ አይቼ ነጭ፣ቀይ፣ማኛ ጤፍ ለመምረጥ ነበር። አሁንስ ሂጀ አላውቅም። እኔም ቀረሁ፣ሥሙም ቀረ፣ጣዕሙም የለ›› አሉኝ። ምነው ሥል ጠየቅኳቸው። እሳቸውም ‹‹ አሁን ላይ ከቤቴ ሁኜ ይሄን ያህል ኪሎ በሚል ነው የማዘው። ጤፍ የበፊት ሥሟንም ቀይራለች። የአሁን መጠሪያዋ ነጭ፣ቀይ ማኛ ሳይሆን አንደኛ ደረጃ፣ሁለተኛ ደረጃ በሚል ሆኗል። የበፊቱን ወዛምና በምጣድ ላይ የሚዘናፈል፣ ለምለሙን እጥፍ አድርገህ ቆርሰህ ሥመህ የምትጎርሰው የጤፍ እንጀራ እግርህ እስኪ ነቃ ድረስ ብትሄድ ለመድሃኒት አታገኝም። ጣዕሟንም ቀይራለች ያልኩህ ለዚህ ነው›› አሉኝ።
ጤፍና የወፍጮ ቤት ውሎዋን ተርከህመቋጨት አትችልም። እናም ወተት የመሰለ ነጭ ጤፍ ወይም በዘመኑ አጠራር አንደኛ ደረጃ ጤፍ ብታዝም፣ባታዝም እንጀራው እንደሆነ መናገር አቁሟል። ከምጣዱ የተሰፋውን እንጀራ ለማውጣትም በሠፌድ ያለሰለሰ መማጸንን ይጠይቃል። ወዶ አይምሰልህ። ከወፍጮ ቤት እስከ ምጣድ ድረስ በየደረጃው ለቁጥር የሚታክቱ ሥመ ጤፍ አረሞች ያለፍላጎታቸው ተዋህደው እንዲኖሩ ይደረጋል። በዚህ የተነሳ ጤፍ ማንነቷን ትነጠቃለች። በሀገር ደረጃ የሚስተዋለው የለውጥ እስትንፋስም በወፍጮ ቤቶቻችን አካባቢ ደርሶ የጠፋችውን የጤፍ ጣዕም ለአፍቃሪዎቿ ሊያስመልስ ይገባል።
በተመሳሳይ በወፍጮ ቤት ሰፈር ደርሰው የተመለሱ እህሎችን ጤንነት እና ደህንነት በማረጋገጥና በማስጠበቅ መስራት የሚያስችል ጠንካራ አሰራርን መዘርጋት ቢችል ለዜጎች የማይተካ ሚና ያበረክታል። ዜጎች ለዚህ ተግባር ምቹ መደላድል በመፍጠር አጋርነታቸውን እንደሚያሳዩ ጥርጥር የለውም። የሱቅና የመጋዘን ባዕድ ቁስ ማብላያዎች ሥፍር ቁጥር የላቸውም ይባላል። በየወፍጮ ቤቶችም በርካታ ትርክቶች ትሰማላችሁ። ‹‹ደንበኛ ንጉስ ነው›› የሚሉት የግድግዳ ጌጥ ጽሁፎች ከነጋዴዎች አንደበት የተተነፈሱ አይምሰሏቹህ። እንደውም የሚተያዩት እንደ ባላንጣ ነው። በተመሳሳይ ‹‹ደረሰኝ ሳይቀበሉ ሒሳብ አይክፈሉ›› የሚሉትም በነጋዴዎች የተጠሉ ናቸው።
በእነዚህ ህግጋቶች ልመራ ሞክሬ የገጠመኝን ላጫውታችሁ። ቀኑን ሙሉ አንዲት እቃ ሸምቼ መመለስ ተስኖኛል። ይልቁንስ ዱላ አትርፋችሁ ልትመለሱም ትችላላችሁ። እነዚህ ትዕዛዛት የገቢዎች ሚኒስቴር ሥሜት እንጂ የነጋዴው ሥሜት አያነባቸውም። አልተዋሃዱትም። አንተ አስተገብራቸዋለሁ፤እኔ መጀመርም እችላለሁ ካልክ አንተ የብርቱዎች ብርቱ ነህ። ክንድህም ኪስህም ብርቱ መሆንአለበት። ሩቅ ማሻገር የሚያስችል። በእርግጥ ይህ እሳቤ እና ድርጊት ከለውጡ በፊትና በኋላ በሚሉ ሁለት ብልቶች ተክፍሎ ሊታይ የሚችል እንደሆነ ከዕለት ኑሯችን በላይ መስካሪ አያሻም። የለውጡን መሪ በሁለት እጇ የጨበጠችው የገቢዎች ሚኒስቴር እንስት በቀላሉ ክንዷ የሚዝል አይመስልም። ይልቁንስ የእኛም ጠጠር መወርወር ዋጋ እንዳለው ተገንዝበን ድርሻችንን ልንወጣ ይገባል። በአገራችን ከሰው ልጆች ክብር በላቀ ደረጃ የገንዘብ ክብር ልቋል።
የሰው ልጅ የሚዛን የልኬት ደረጃው የት እንደነበረ መመርመር ይኖርብናል። መዋደዳችንን፣መከባበራችንን፣መተዛዘናችንን ፈልገን መልበስ አለብን።ለዚህም በየቀየው የሚገኙ ሽማግሌዎች ትምህርት ቤቶቻችን ናቸው። አትጠራጠሩ የኋላውን ዘንግቶ ወደ ፊት መራመድ የቻለ የትውልድ ሰንሰለት የለም። ለተወሰነ ደቂቃም ቢሆን ጊዜያችሁን ሰጥታችሁ በርከክ ብላችሁ የአገራችሁን ወግና ባህል ከአዛውንቶች ጋር ተጨዋወቱ። ህይወታችሁም ይታደሳል። የሰውን ልጅ በዋጋ የማይተመን የክብር ልክ ማጤን የምትችሉበት ልቦና ይነቃቃል። ሳይበረዝ፣ሳይደለዝ እና ሳይጋነን ተፈጥሯዊ እውነታው ከእነርሱ ጋር ነው።
የሰውን እምነት የለሽነት ልክ፣ ቅጣባሩ የጠፋውን የነጋዴውን ሥግብግብ ባህሪና አመል፣ የንግግርንና የቃልን ዋጋ ማጣት እንዲሁም የሰው ልጅ ሚዛን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀለለ መምጣት በአይናችን ከምናየው ሀቅ በተጨማሪ በንጽጽር አስረጂዎች ናቸው። ‹‹የተናገሩት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ›› የሚሉት አባቶች አስገዳጅ ህግ ፈርተው አይደለም። መዋሸት፣ መቅጠፍ፣ መካካድ ከነውርነቱም በላይ የተወገዘ ነበር። እንደ ርካሽ ያስቆጥራል። የዘመድ አዝማድን ሥምና ክብር ያሳጣል። የእገሌ ቤተሰብ የሆነው አቶ እገሌ ዋሾ ነው፣ ቃል አያከብርም።‹‹እሱን ያመነና ጉም የዘገነ አንድ ነው›› ከተባለ በዝምድናቸው ቤተሰቡ ያፍራል። በመሆኑም እርምጃ የሚወስድበት ሕግ ሳይሆን ቤተሰብ ነበር። ያውም የማያዳግም ቆራጥ ርምጃ። እነዚህ ሁሉ የአብሮነት ውብ መስተጋብሮች አሁን ላይ አርገዋል አለያም ሰርገዋል። በአጭር ጊዜ መመለስ ካልቻልን የእኛም እጣፋንታ ይሄው ነው። መ…ክ…..ሠ……ም።
አዲስ ዘመን መጋቢት 5/2011
በሙሀመድ ሁሴን