የዓድዋ ድል ብዙ አዓዋዎችን ለመድገም በር የሚከፍት አንጸባራቂ ድል ነው። ያለንበት ወቅት ደግሞ ኢትዮጵያ ብዙ የዓድዋ ድሎችንና የዓድዋ ጀግኖችን የምትሻበትም ወቅት ነው። ታዲያ ስለምን በዚህ ደረጃ ዓድዋ የመነታረኪያ ርእስ ሊሆነን ይገባል። አብዛኞቻችን ኢትዮጵያውያን እንደምንረዳው ኢትዮጵያን የመበታታን አፋፍ ላይ አድርሷት የነበረው የአሸባሪዎች ስብስብ የሆነው ወያኔ የሚገባውን ቅጣት ተቀብሎ ወደ ተፈለፈለበት ዋሻ ቢመለስም፤ ዛሬም ሕዝብን ከሕዝብ ከማናከስ እኩይ ተግባሩ መታቀብ አልቻለም።
እነዚህን ሕዝብ ከሕዝብ የሚያናክሱና የሚያቃቅሩ ሥራዎችን እየሰራ ያለው ደግሞ በአውሮፓ አሜሪካና እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ የሞት መልእክተኞቹ ነው። እነዚህ የወያኔ ሴራ አስፈጻሚዎች ደግሞ በያሉበት ሆነው ማሕበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም በየወቅቱ አዳዲስ የመራራቅና የመተነኳኮስ አጀንዳ እየሰጡን ሲሻቸው ለቀናት ሲሻቸው ለወራት የጎሪጥ እየተያየን እንድንከርም እያደረጉን ይገኛል። አሁን ባለው ነባራዊ እውነት የተሸከምነው ችግር ሳያንሰን፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በየመንደሩ ሲፈበረኩ የሰነበቱት የተዛቡ የታሪክ ትርክቶችን እና በታሪክ የተፈጸሙ ህጸጾች እየተመዘዙ በሃሳብ ወደኋላ በመመለስ እያነታረኩን ይገኛሉ።
በመሰረቱ ያለፈም ታሪክ ሆነ አሁን እየተከሰቱ ባሉ ሁነቶች እንኳን እንደ ኢትዮጵያ ሰፊ ብዝሃነት ባቀፈ አገር ይቅርና በሌላውም ቢሆን የፍላጎትና የሃሳብ ልዩነት ማምጣቱ ማነጋገሩ አይቀርም። እንደ ተፈጥሮ ሕግ ደግሞ ማንኛችንም ብንሆን ያለፈውን ታሪክ ተመልሰን የምናርምበት እድል የለንም። ዋናው ቁም ነገር የተፈጠረውን የሃሳብ ልዩነት አሁን እየተከሰተ ያለውንም ሆነ ያለፈውን የምናስተናግድበት መንገድ ነው። የልዩነታችን ምንጭም ይሁን የአመለካከታችን ልዩነት ምንም ያህል የተራራቀ ቢሆን እንደሰለጠነ ሰው ከመተቻቸትና ከመሰዳደብ ወጥተን በሰላማዊ መንገድ በመነጋገር ካስተናገድነው ችግር ሊሆን አይችልም።
እውነት ለመናገር አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን አብዛኞቻችን ሃሳባችንን በጽሁፍም ሆነ በንግግር ስንገልጽ ጥላቻ ስድብ ንቀትና ትችት በተሞላባቸው ቃላት ነው። ይሄ ሳያንሰን በፖለቲካ አመለካከታቸውም ሆነ በሃይማኖታዊ እይታቸው የኛ ብለን የተቀበልናቸውን ሰዎች ጥፋት ለመመልከት አይናችንን መጨፈናችን ደግሞ በተወሰኑ ብልጣብልጦች የምንጋለብ እያደረገን ይገኛል።
በተጨባጭ አእምሮውን ከፍቶ በአገራችን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ለማስተዋል የቻለ ሰው እንኳን ለምእተዓመታት ወደኋላ ተመልሶ በታሪክ ሊነታረክ ይቅርና በወራት ውስጥ የተከሰቱትንም ይቅር ብሎ ነገን ብሩህ ለማድረግ መጣጣር ነበረበት። ያለው ሁኔታ ግን እንዲያ አይመስልም። በትንሹ አሜሪካ ኮንግረስ አባላት ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን በማዋከብ በጫና ውስጥ ለማቆየት እንዲጸድቅ ያቀረቡትን ሰነድ መቃወም ከምንም በፊት የሁላችንም ሃላፊነት መሆን ነበረበት።
እንዲህ ካላይ ባሰፈርኩት አይነት ጠንከር ባለ መልኩ የተሰማኝን ስሜት የገለጽኩት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሕዝብ ዘንድ መደናገርንና ቅሬታንና እየፈጠሩ ያሉ ሕዝባዊ አጀንዳዎች በመንግሥት ሃላፊነት ቦታ ላይ በተቀመጡ ባለሥልጣናትም እየተፈጸመ በማየቴ ነው። ከዚህ ቀጥሎ የማቀርበው ሃሳብ መንግሥት በሃላፊነት ቦታ ያስቀመጣቸውን ሰዎች ለመተቸት አልያም የሰሩትንና እየሰሩት ያለውን ሥራ ለመንቀፍ ሳይሆን ለቀጣይ ለአገሬም ለሕዝቤም ይበጃል የምለውን የመፍትሄ ሃሳብ ለመጠቆም ነው።
በመንግሥት ሃላፊዎች መካከልም እንደማንኛውም ዜጋ በሚሰሩ ስራዎችና በሚወሰኑ ውሳኔዎች ላይ የሃሳብ ልዩነት ሊኖር ይችላል። ነገር ግን በዚህ ሁሉ ችግር ንግግር አንዱን አስደስቶ አንዱን የሚያስቀይም በሆነበት ወቅት ለአንድ አገር ለአንድ መንግሥት እየሰሩ ያሉ ሃላፊዎች የተለያዩ ምን አልባትም የተራራቁ ውሳኔዎችን ማውጣት የለባቸውም የሚል ጠንካራ እምነት አለኝ። በቅርብ ጊዜያቶች ውስጥ የሕዝባዊ በአላት አከባበርን በማስመልከት እየወጡ ያሉ መግለጫዎች ለዚህ ሁነኛ ማሳያ ናቸው።
በመሰረቱ እኔ እስከምረዳው ድረስ በሃላፊነት ቦታ ላይ የተቀመጡ ባለሥልጣናት አንዳንድ የሕዝብ ስሜትን የሚስቡ ውሳኔዎች ከመወሰናቸው በፊት በቂ ውይይት በማድረግ አንድ የስምምነት ሃሳብ ላይ በጋራ መድረስ የሚጠበቅባቸው ይመስለኛል። ከሁሉም በላይ ደግሞ እንደመንግሥት በአንድ ጉዳይ ላይ የተለያዩ ውሳኔዎችን በሚዲያ ለሕዝብ ማድረስ መንግሥት ከራሱ ሳይስማማ ከሕዝብ ጋር እንዴት አብሮ ሊጓዝ ይችላል የሚል ጥያቄ የሚያስነሳ ነው። በመሰረቱ መንግሥት በሃላፊነት ቦታ ያስቀመጣቸው ሰዎች በሕዝብ ዘንድ ያላቸውን ተሰሚነትና ቅቡልነት ከግምት በማስገባት እንኳን ለሚዲያ ይቅርና በግል የማሕበራዊ ትስስር ገጾቻቸው የሚለቋቸው ነገሮች ሃላፊነት ሊሰማቸው ይገባል።
እንደነዚህ አይነት ክፍተቶች ወትሮም አገር ለመበታተን አሰፍስፈው ቀዳዳ ሲፈልጉ የነበሩና የአገር ሰላም እንቅልፍ የሚነሳቸው በር የሚከፍት ነው። እነዚህ ጥቅማቸው የተነካ በአገር ውስጥም ሆነ በመላው ዓለም የሚገኙ ራስ ወዳድ ኢትዮጵያውያን እንኳን የመነታረኪያ ርእስ ተፈጥሮላቸው ይቅርና በባዶ ሜዳም ኢትዮጵያውያን አንገታችንን ደፍተን እንድንኖር ስለሚፈልጉ የማይፈነቅሉት ድንጋይ አይኖርም።
የማሕበራዊ ሚዲያ በተለይም የፌስቡክ ተአማኒነትና ተቀባይነት ደግሞ ውሎ ባደረ እየተስፋፋ ይገኛል። ከመደበኛ ሚዲያዎች በላይ ተሰሚነትና ተቀባይነት ያላቸው የቲውተር የፌስቡክና ሌሎች የግለሰብ አካውንቶች ብዙ ናቸው። ከቀናት በፊት የዓድዋ በአል አከባበርን አስመልክቶ ተፈጥራ የነበረችው ሚጥጥዬ እሰጥ አገባ ይህን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ይመስለኛል።
የመጀመሪያው መግለጫ ሲወጣ እኔ በምከታተላቸው የማሕበራዊ ትስስር ሚዲያ ገጾች ሲወጡ የነበሩት ነገሮች አዲስ አበባ ውስጥ ደመቅ ያለ ችግር የሚፈጠር ያስመስሉ ነበር። እግዚአብሄር ይመስገን እድሜ ለሰላም ፈላጊው ሕዝባችንና ለጸጥታ አካላት እነ እረብሻ ጌጡ የተመኙት ሳይሳካላቸው ቀረ። ነገር ግን ይህኛው አጋጣሚ በሰላም አልፏል ማለት ሁሉም ነገር በዚህ ሁኔታ ይቀጥላል ማለት አይደለም።
በመሆኑም በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዲስአበባ ውስጥ እየተነሱ ያሉ ጉዳዮችን በተመለከተ በመረጃ በማስረጃና ዘላቂውን አገራዊ ሰላም ከግምት ባስገባ መልኩ የማያዳግም ውሳኔ ሊሰጥ እንደሚገባ ይሰማኛል። ለዚህ ደግሞ የሚመለከታቸው አካላት ደመቅ ያለ ትኩረት በመስጠትና ነገሮችን ከስር መሰረታቸው በጥንቃቄ በመመርመር እንዲሁም በመገምገም ለመነታረኪያ ርእስ የማይሆኑበትን ሁኔታ መፍጠር አለባቸው የሚል ጠንካራ አቋም አለኝ። በመሰረቱ የሕዝብ ፍላጎትም ሆነ ጥያቄ እንደማይቆም የሚታወቅ ነው። በዛ ላይ እያንዳንዱ ውሳኔ ሁሉንም ወገን ሊያስደስትም እንደማይችል ግንዛቤ ሊኖር ይገባል።
በመሆኑም እንደኔ እንደኔ አሁን የተፈጠሩ ችግሮችን በዘላቂነት ከመፍታት ባለፈም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሕዝባዊ የሆኑ ሁነቶችን የሚያስተናግድበት የሕግ ማእቀፍ ሊያዘጋጅ ይገባል። እነዚህ ማእቀፎች በጥንቃቄና በሃላፊነት ብሎም ከወገንተኝነት በጸዳ መልኩ ከተዘጋጁ በውሳኔ ሰጪነት ቦታ ላይ ማንም ቢቀመጥ የሚሰራበት ማእቀፍ እስከተቀመጠ ድረስ እንደፈለገ እንዳይሆን ስለሚያስረውና የሚሰራውና የሚወስነውም ውሳኔ ተጠያቂ ስለሚያደርገው እሰጥ አገባውን የሚቀንስ ይሆናል።
ከሁሉም በላይ ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች አጥጋቢ በሆነ ምክንያትም ሆነ በማሕበራዊ ሚዲያ በመነዳት ቅሬታና ትችቶችን በመንግሥትና በሃላፊዎች ላይ ለሚሰነዝሩ አካላትም ጨዋታውን ከግለሰብ ወደ መመሪያ ስለሚቀይረው ሥርዓት አልበኝነትን ለማስፈንም አስተዋጽኦ ይኖረዋል። በመሆኑም የጀመርነውን የለውጥ ጉዞ ከግብ ለማድረስ መንግሥት በሃላፊነት ቦታ ያስቀመጣቸው ግለሰቦች የግጭትና የንትርክ መፈብረኪያ ከመሆን ሊቆጠቡና በሕዝባዊ ጉዳዮች ላይ ቢሯቸው ቁጭ ብለው በውይይት ወስነው ወደ ሕዝብ ሊቀርቡ ይገባል፤ የሚለው የዛሬው መልእክቴ ነው። የአሁኑ መንግሥት ብልጽግናም በፓርቲው ጉባኤ ላይ ይሄን መሰል ችግር እልባት የሚያገኙበትን አቅጣጫ ያስቀምጣል የሚል እምነትም፤ ተስፋም አለኝ።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን መጋቢት 3 ቀን 2014 ዓ.ም