
የኡጋንዳ ጦር ኃይሎች አዛዥ የሆነው የፕሬዚዳንት ዮዎሪ ሙሴቬኒ ልጅ ከኃላፊነቱ ራሱን በጡረታ ማግለሉን አስታውቋል። ሌፍተናንት ጄነራሉ ጡረታ ስለወጣበት ምክንያት በዝርዝር አልተናገረም ተብሏል፡፡
ላለፉት 20 ዓመታት በኡጋንዳ ወታደራዊ ተቋም ውስጥ ያለፈው ሙሆዚ ካይኔሩጋባ አሁን ሥልጣን የለቀቀው የአገሪቱ መሪ ለመሆን በማሰብ እንደሆነ ተገልጿል። በዚህም መሰረት ሌፍተናንት ጄነራሉ ከዛሬ ጀምሮ ጡረታ መውጣቱን ይፋ አድርጓል።
የዮዎሪ ሙሴቬኒ ልጅና የአገሪቱ ጦር አዛዥ ጡረታ የወጣው እ.ኤ.አ በ2026 የአገሪቱ መሪ ለመሆን ዝግጅት ለማድረግ እንደሆነ ምልክቶች አሉ ተብሏል። በርካታ ኡጋንዳውያን ካይኔሩጋባ አባቱን በመተካት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሊሆን እንደሚችል ያምናሉ ተብሏል።
የዮዎሪ ሙሴቬኒ ልጅ ባለፉት 28 ዓመታት በአገሩ ጦር ውስጥ ሲሰራ እንደነበር ገልጾ ጦሩም “በዓለም ትልቁ” እንደሆነ በትዊተር ገጹ ላይ አስፍሯል። ጡረታ ለመውጣቱ ምንም አይነት ምክንያት አልሰጠምም ነው የተባለው።
በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1986 ጀምሮ ኡጋንዳን እየመሩ ያሉት የ 77 ዓመቱ ዮዎሪ ሙሴቬኒ “ሥልጣኑን ለልጃቸው ሊያስተላልፉ ይችላሉ” የሚለውን ጉዳይ በተደጋጋሚ አስተባብለዋል።
ይሁንና የልጃቸው ካይኔሩጋባ ደጋፊዎች አገሪቱን ለመምራት ትክክለኛው ሰው እንደሆነ እየገለጹ ናቸው ተብሏል። ሌፍተናንት ሙሆዚ ካይኔሩጋባ ሩሲያ በዩክሬን ያደረገችውን ወታደራዊ ተልዕኮ መደገፋቸው የሚታወስ ነው። ምንም እንኳን የኡጋንዳ ሕግ ወታደር በፖለቲካ እንዲሳተፍ ባይፈቅድም የ47 ዓመቱ የሙሴቬኒ ልጅ ግን የአገሪቱ መሪ ሊሆን እንደሚችል እየተገመተ ነው።
ካይኔሩጋባ በይፋ የአባቱን ቦታ ስለመተካት ባይናገርም ደጋፊዎቹ ግን በማሕበራዊ ትስስር ገጾች ስለሱ ሲያወሩ ይሰማል ተብሏል። የመብት ተሟጋቾች ዮዎሪ ሙሴቬኒ ተቃዋሚዎቻቸውን በማሰርና በማንገላታት ይከሷቸዋል።
ሙሴቬኒ ባሳለፍነው ጥር የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኙን ቦብ ዋይንን በማሸነፍ ሥልጣኑን እንደያዙ ቢቆዩም ሙዚቀኛው ተፎካካሪያቸው ግን ውጤቱን ውድቅ አድርጎታል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን መጋቢት 1/2014