
ፕሬዚዳንት ባይደን የሩሲያ ኢኮኖሚ የደም ስር ነው ባሉት ነዳጅ ላይ እገዳ መጣላቸውን አስታውቀዋል የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የሩሲያ ነዳጅ ወደ አሜሪካ እንዳይገባ አገዱ:: ባይደን የሩሲያ ኢኮኖሚ የደም ስር ነው ባሉት ነዳጅ ላይ እገዳ መጣላቸውን ትናንት ከቤተ መንግሥታቸው ሆነው በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል::
በባይደን ውሳኔ መሰረት ከአሁን ቀደም የተደረጉ የነዳጅ ግብይት ስምምነቶች በ45 ቀናት ውስጥ መቋጫ የሚያገኙ ይሆናልም ተብሏል:: እርምጃው ሩሲያ ዩክሬንን መውረሯን ተከትሎ የተወሰደ መሆኑ ተነግሯል:: የነዳጅ ዋጋ እንዲያሻቅብ አድርጋለች በሚል ለተከሰሰችው ሩሲያ የተሰጠ ምላሽ እንደሆነም ነው የተነገረው::
ይህ የባይደን እርምጃም የነዳጅ ዋጋን ይበልጥ እንዳያንረው ተሰግቷል:: አንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ በዓለም ገበያ ከ 140 ዶላር በላይ በመሸጥ ላይ ይገኛል:: ሆኖም ፕሬዚዳንቱ እርምጃውን ተከትሎ የሚመጡ ተያያዥ የዋጋ ንረት ችግሮች ቢኖሩም ንረቱን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ አፋጣኝ እርምጃዎችን እንደሚወስዱ አስታውቀዋል::
እርምጃው ከአውሮፓ አጋሮቻቸው ጋር በመመካከር የተወሰደ መሆኑንም ነው ባይደን የገለጹት:: እንግሊዝን መሰል የአውሮፓ አገራት ተመሳሳይ እርምጃዎችን ሊወስዱ እንደሚችሉ ሲያሳስቡ ነበር:: ሆኖም በሩሲያ የነዳጅ ምርቶች ላይ የከበደ ጥገኝነት ያለባት ጀርመን ሌሎቹን ተከትላ እርምጃ ልትወስድ እንደማትችል አስታውቃለች:: ምክንያቱም ከአሁን ቀደም ኖርድ ስትሪም 2 ተብሎ በሚጠራው የሩሲያ የጋዝ ማስተላለፊያ መስመር ላይ በጣለችው እገዳ ምክንያት ለከፍተኛ የነዳጅ ዋጋ ግሽበት ተጋልጣለች:: ይህ አብዛኛው የኃይል ፍጆታዋ በሩሲያ ለሚሸፈነው ጀርመን አደገኛ ነው::
ሃንጋሪና ቱርክም የአሜሪካንና ምዕራባውያንም እናደርገዋለን የሚሉትን ይህን እርምጃ ተቃውመዋል:: የሩሲያን ነዳጅ መግዛታቸውን እንደሚቀጥሉም ነው የገለጹት:: ሃንጋሪ 90 በመቶ የነዳጅ ፍጆታዋን የምታገኘው ከሩሲያ ነው:: ቱርክም ብትሆን 45 በመቶ የተፈጥሮ ጋዝ፣ 17 በመቶ የጋዝ እና 40 በመቶ የቤንዚን ፍላጎቷን ከሩሲያ ነው የምታገኘው:: በመሆኑም መግዛቷን እንደምትቀጥል አስታውቃለች::
እርምጃው አደገኛ እንደሚሆን ያሳሰበችው ሩሲያም የተለያዩ የአጸፋ ምላሾችን ልትሰጥ እንደምትችል አስታውቃለች:: በአሜሪካ የተጣለውን እገዳ ለመቋቋም የሚያስችሉ ጡረታን ከፍ የማድረግና ለአነስተኛና መካከለኛ ቢዝነስ አንቀሳቃሾች መጠነኛ ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል ውሳኔ መስጠታቸውንም ፕሬዚዳንት ፑቲን ይፋ አድርገዋል::
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን መጋቢት 1/2014