ዓለም በሩሲያና ዩክሬን ጦርነት በእጅጉ ተጨንቋል። የዩክሬን ሰማይና ምድር በመሳሪያ አረር መታረስ ከጀመረ ሰነበተ።
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ እንዲህ አይነት አሰቃቂ ግጭት ታይቶ አይታወቅም በተባለለት የሞስኮና ኪዮቭ ፍጥጫ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ዩክሬናውያን ወደ ጎረቤት አገራት ተሰድደዋል።
ይህ ቁጥር አሁንም ድረስ በማሻቀብ ላይ ይገኛል። ጦርነቱ ይዞት የመጣው ዳፋ ለአውሮፓውያን ብቻ ሳይሆን መላው ዓለም ላይ የክፋት አሻራውን እያሳረፈ እንደሚገኝ የፖለቲካ ተንታኞች በየግዜው እየተናገሩ ይገኛሉ።
በተለይ ውጊያው ተባብሶ ወደ ኒኩለር ጦርነት የሚቀየር ከሆነ ምድራችን አይታው የማታውቀው እልቂት እንደምታስተናግድ ስጋታቸውን ይገልፃሉ። አሜሪካንን ጨምሮ አውሮፓ አገራት በሩሲያ ላይ የማእቀብ ማአት ቢያዠጎደጉዱም ፑቲን ግን ከአቋሙ ንቅንቅ የሚል አይመስልም።
የተባበሩት መንግስታትን ጨምሮ አያሌ ተቋማት አውዳሚው ጦርነት እንዲቆም ቢማፀኑም የሩሲያ ፍላጎት እስካልተሳካ ድረስ ዩክሬን ላይ የመሳሪያ በረዶ ማዝነብ እንደማያቆሙ የሩሲያ ጀነራሎች ተማምለዋል።
ከ70 ዓመታት በኋላ ከተደረጉ ግጭቶች አስከፊው የተባለው በዓለም ኢኮኖሚ ላይ እያሳረፈ የሚገኘው ጫና በቀላሉ እንደማይታይ የኢኮኖሚ ተንታኞች ትንበያቸውን እየሰጡ ነው። በተለይ በዓለም ገበያ ላይ የምግብና የነዳጅ ፍላጎታቸውን ከሁለቱ አገራትና ሌሎች የአውሮፓ አባላት ላይ የሚገዙ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ላይ ጫናው እንደሚያይል ይጠበቃል።
ሁለቱ አገራት ከምስራቅ አፍሪካ አገራት ጋር ካላቸው የምግብ አቅርቦት ግብይት በተያያዘ ጦርነቱ ይዞት የሚመጣው የኢኮኖሚ ጫና መዘዝ ከፍተኛ እንደሆነ ይጠበቃል። በተለይ በዚህ አውዳሚ ግጭት ምክንያት ኢትዮጵያ በአገር ውስጥ ብቻ ከማትሸፍነው የምርት አቅርቦት ጋር በተያያዘ ሊኖር የሚችለውን እጥረት የኢኮኖሚ ምሁራን በዚህ መልኩ ያስቀምጡታል።
ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ብሩህ ተስፋ የኢኮኖሚ ምሁር ናቸው። ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ በሰጡት አስተያየት እንደሚሉት፤ በሩሲያና ዩክሬን መካከል እየተካረረ የመጣው ግጭት በተለይም በአዳጊ አገራት ላይ ከፍተኛ ጫና ያስከትላል። ጦርነት በተፈጥሮ ከሚያደርሰው ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ በተጨማሪ የኢኮኖሚ ውድመቱና የሚፈጥረው ጫናም ቀላል የሚባል አይደለም።
የጦርነት ኪሳራው ዘርፈ ብዙ እና በርካቶችን የሚያካልል እንደሆነ የሚናገሩት ባለሙያው መቋጫ ቢያገኝ እንኳን በሰው ልጆች ዘንድ ጥሎት የሚያልፈው ጠባሳ የከፋ እንደሚሆን ይናገራሉ። “ከዚህ ቀደም በዓለም ላይ የተደረጉ ጦርነቶች በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ዘርፎች ሁሉ መጥፎ አሻራ አሳርፈውና በርካቶችን ጎድተው አልፈዋልም” የሚሉት የኢኮኖሚ ምሁሩ፤ በሩሲያና ዩክሬን መካከል እየተካረረ የመጣው ጦርነት ብዙ መዘዞችን የሚያመጣና በርካታ ጉዳቶችን የሚያስከትል መሆኑን ገልፀዋል።
ጦርነቱ በሁለቱ አገሮች መካከል የሚካሄድ ቢሆንም ብዙዎችን መነካካቱ እንደማይቀር ጠቅሰው በተለይም በአዳጊ አገራት ላይ ሊያስከትል የሚችለው ጫና ቀላል አይሆንም ነው ያሉት። በኢኮኖሚው መስክ ሩሲያ ከሳዑዲ አረቢያ በመቀጠል ሁለተኛዋ ከፍተኛ የነዳጅ ላኪ አገር በመሆኗ ጦርነቱ ሲያስተጓጉለው በሚፈጠረው የዋጋ ንረት ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ አገራት ተጎጂ እንደሚሆኑም ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ያስረዳሉ።
በጦርነቱ ሳቢያ በዓለም ገበያ የነዳጅ ምርት በበርሜል ከ100 ዶላር በላይ እያሻቀበ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ይኖረዋል በማለት ጉዳዩን ያብራራሉ። በዚህም ምክንያት በኢትዮጵያ በተለይም በምግብ እና በነዳጅ ምርቶች ላይ ከፍተኛ ጫና ሊያሳድር እንደሚችል ያላቸውን ግምት አስቀምጠዋል።
“ኢትዮጵያ በበጋ እያመረተችው ያለው በመስኖ የሚለማ የስንዴ ምርት ትልቅ ትርጉም አለው” የሚሉት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፤ ሌሎች ፈጥነው የሚደርሱ ሰብሎችን ማብቀል ይገባል ሲሉ መክረዋል። በግብርናው መስክ ፈጥነው የሚደርሱ የቆላ ስንዴ እና የመሳሰሉትን የምርት አይነቶች በስፋት ማልማት ጊዜ ሊሰጠው አይገባም ሲሉ ምክረ ሃሳባቸውን ይሰጣሉ።
የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ዋሲሁን በላይ የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት በኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ አስመልክተው እንዳሉት፤ ለዓለም ከ30 በመቶ በላይ የሚሆነውን የስንዴ ምርት የሚያቀርቡት ሩሲያና ዩክሬን ናቸው። በጦርነቱ ምክንያት በዓለም ላይ ነዳጅን ጨምሮ የምግብ ዋጋዎች ከፍተኛ ጭማሪ አሳይተዋል።
ጦርነቱ ለኢትዮጵያም ጭምር የምጣኔ ሀብት ስጋት ስለሚፈጥር ኢትዮጵያ አማራጭ የንግድ ስትራቴጂዎችን ማየት ይኖርባታል። በአሁኑ ወቅት በሁለቱ አገራት በሚደረገው ጦርነት ምክንያት በአውሮፓና በዓለም ገበያ የነዳጅና የስንዴ ዋጋ ጨምሯል። ባለሙያው እንደሚሉት እነዚህ አገራት የኢትዮጵያ የውጭ ንግድ ቁልፍ አገራት በመሆናቸው ግጭቱ ከሚያስከትለው ምጣኔ ሀብታዊ ቀውስ አንጻር በቀላል እንደማይታይ ይገልጻሉ።
በሁለቱ አገራት ምክንያት ዓለም አቀፍ ገበያ ላይ እየታየ ያለው የዋጋ መጨመር ኢትዮጵያን ጨምሮ በታዳጊ አገራት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እ ን ደ ሚ ያ ሳ ድ ር ም አስረድተዋል። ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ነዳጅ ከሩሲያ ባትገዛም በዓለም አቀፍ ገበያ የነዳጅ ዋጋ መጨመሩ ግን ምጣኔ ሀብቷን ሊጎዳ እንደሚችል ጠቁመዋል። እንደ አቶ ዋሲሁን ማብራሪያ፤ ወደ 16 በመቶ የ ሚ ሆ ነ ው ን በቆሎ ለዓለም የምታቀርበው ዩክሬን ናት። በነዳጅም ቢሆን ከሳዑዲ አረቢያ ቀጥሎ ዩክሬን ለዓለም ገበያ በማቅረብ ከፍተኛ ድርሻ አላት። ኢትዮጵያ ስንዴ፣ የምግብ ዘይት፣ ብረትና መሰል ነገሮች ከእነዚሁ አገራት ጋር ትገበያያለች። ዩክሬን የቆዳ ውጤቶችንና መሰል ምርቶችን ከኢትዮጵያ ትገዛለች።
ሁለቱ አገራት በኢትዮጵያ ንግድ ግንኙነት ውስጥ ከምርጥ አስር አገራት ውስጥ የሚመደቡ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ወቅቱ ኢትዮጵያ የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ ከፍተኛ ስንዴ ግዥ የምትፈጽምበት በመሆኑ ግጭቱ ተጽእኖ ያሳድራል ሲሉ ያብራራሉ።
ምርት ወደ አገር ቤት ማስገባት ብቻ ሳይሆን ጦርነቱ ወደ ተቀሰቀሰባቸው አገራት መላኩም አስችጋሪ ሊሆን ይችላል። ታዳጊ አገራት ላይ የሚኖራቸው የድጋፍ መጠንም እንዲሁ ሊቀንስ ይችላል ሲሉ የጦርነቱ ኢኮኖሚያዊ ተጽእኖ አስረድተዋል።
በጦርነቱ ምክንያት የንግድ ግንኙነቱ ከተጎዳ ችግር ውስጥ የመውደቅ አዝማሚያ እንዳለ ጠቅሰው፤ ሁሉም ጉዳዩን የሚመለከተው ከራሱ ጥቅም አንጻር በመሆኑ ያዋጣኛል የሚለውን እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚገባ ነው የተናገራት።
በዚህም በንግድ ስትራቴጂ ሌሎች መሸመት የሚቻልባቸውን የገበያ አማራጮችን ማየት፣ ረዘም ላለ ጊዜ ምርት የሚገኝበትን ገበያ ፈልጎ አስፈላጊውን ምርት ሸመታ ማድረግና አከማችቶ የመጠቀም ልምድን ማዳበር መፍትሄ ሊያመጣ እንደሚችልም ይጠቁማሉ።
ከዚህ ባሻገር ሁኔታው በሰላም እንዲያልቅ ከሌሎች አገራት ጋር አጋር መሆን እንደሚጠበቅና፤ እንደ አንዳንድ አገራት ጎራ መለየትና አንዱ ጋር መለጠፍ ሳያስፈልግ ሚዛናዊ ሆኖ መንቀሳቀስም ይበጃል በማለት አቶ ዋሲሁን አሳስበዋል።
የቁጥር መረጃዎች ምን ያሳያሉ
ኤፍ ቢሲ ዘ ኮንቨርሴሽን ያወጣው መረጃ ጠቅሶ እንዳስነበበው፤ የአፍሪካ አገራት መሪዎች አሁን ላይ በሩሲያና ዩክሬን መካከል ለተከሰተው ግጭት ትኩረት ሊሰጡ ይገባል ይላል።
አሃዞች እንደሚጠቁሙት በሁለቱ አገራት እና በአፍሪካ መካከል ትርጉም ባለው መልኩ የግብርና ምርቶች ግብይት ይፈፀማል። በአውሮፓውያኑ 2020 ላይ የአፍሪካ አገራት አራት ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የሚያወጣ የግብርና ምርትን ከሩሲያ ገዝተዋል።
ከዚህ ውስጥ 90 በመቶ የሚሆነው ስንዴ ነው። በዚሁ ተመሳሳይ ዓመት አፍሪካውያን አገራት ሁለት ነጥብ ዘጠኝ ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የሚያወጣ የግብርና ምርት ከዩክሬን አስገብተዋል፤ ግማሽ የሚሆነው ስንዴ ሲሆን፤ 31 በመቶው ደግሞ የበቆሎ ምርት ነው።
በዋናነት ከእነዚህ አገራት የግብርና ምርቶችን በማስገባት ግብፅ ግንባር ቀደም ስትሆን፥ ሱዳን፣ ናይጄሪያ፣ ታንዛኒያ፣ አልጄሪያ፣ ኬንያ እና ደቡብ አፍሪካ ይከተሏታል። ሩሲያ እና ዩክሬን በዓለም የሸቀጦች ገበያ ውስጥ ትርጉም ያለው ድርሻ እንዳላቸው ነው የሚነገረው። ሩሲያ የዓለምን 10 በመቶ፣ ዩክሬን ደግሞ አራት በመቶ ስንዴን ያመርታሉ።
አገራቱ ምንም እንኳን ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚያውሉት ምርት ቢኖርም በፈረንጆቹ 2020 ላይ ከዓለም የስንዴ ገበያ ውስጥ ሩሲያ የ18 በመቶ እና ዩክሬን የስምንት በመቶ ድርሻ ነበራቸው።
አገራቱ በበቆሎ ምርት አቅርቦት ላይም ቢሆን ትርጉም ያለው ድርሻን ይዘዋል። ዩክሬን 40 በመቶውን የዓለምን የሱፍ አበባ ዘይትንም ታቀርባለች። በመሆኑም አሁን ሩሲያ በዩክሬን የጀመረችው ወታደራዊ ዘመቻ እና አገራቱ ወደ ግጭት ውስጥ መግባታቸው በዓለም የምግብ አቅርቦትን እንደሚረብሸው ይታመናል። የዚህ አሉታዊ ተፅእኖ በተለይም ከሁለቱ አገራት በስፋት የስንዴ እና የሱፍ አበባ ዘይት የምታስገባው የአፍሪካ አህጉር የግጭቱን አሉታዊ ተፅእኖ እንደምትቀምሰው ተገምቷል።
በተለይም አሁን ላይ በአንዳንድ የአፍሪካ አገራት የተከሰተው ድርቅ እና ረብሽ የገጠመው የዓለም የትራንስፖርት አገልግሎት ተደማምረው በአፍሪካ ቀድሞውኑ የከፋውን የምግብ ዋጋ ግሽበት እንዳያባብሰው ተሰግቷል። ላለፉት ሁለት ዓመታት በቋሚነት እየጨመረ የመጣው የዓለም የምግብ ዋጋ በዚህ ግጭት መባባሱ እንደማይቀር እና በተለይም ለስንዴ ምርት በሁለቱ አገራት ላይ የተደገፉት የአፍሪካ አገራት የምግብ ዋጋ በአጭር ጊዜ ውስጥ አሁን ካለበት እንደሚንርባቸው ይግመታል።
ኢትዮጵያም የዚህ ዳፋ ተቋዳሽ መሆኗን ልብ ይሏል። እንደ ዘ ኮንቬንሽን ዘገባ ካናዳ፣ አውስትራሊያና አሜሪካን የመሳሰሉ ዋነኛ ስንዴ አምራች አገራት በተፈጠረው ግጭት ምክንያት የተከፈተላቸውን የገበያ እድል ተጠቅመው ምርታቸውን በገፍ ሊያቀርቡ እንደሚችሉ ይገመታል።
ሆኖም የአገራት ዋነኛ ግብ ሊሆን የሚገባው በዓለም የምግብ ገበያ ውስጥ መሃል ተጫዋች የሆኑት ሩሲያ እና ዩክሬን ጠባቸውን አርግበው ግጭት እንዲቆም ማድረግ እንደሆነ ገልጿል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን የካቲት 30 /2014