ናይኪ የተሰኘው ግዙፍ የስፖርት ትጥቅ፣ የልምምድና ውድድር ቁሳቁስ አምራች ኩባንያ እአአ የ2019 የሴቶች ዓለም ዋንጫ፤ ከቀድሞ የተለየ የተጫዋቾች ማሊያ አስተዋወቀ:: በዚህም ቀድሞ ከሚያገኘው ገቢ 7 ከመቶ የበለጠ፤ እአአ ከ2015ቱ የሴቶች ዓለም ዋንጫ ደግሞ አራት እጥፍ የላቀ ትርፍ ወደ ካዝናው ማስገባት ቻለ::
ይህ አነጋጋሪና በገበያው ደርቶ ድርጅቱ ረብጣ ዶላሮችን እንዲያፍስ ምክንያት የሆነው ትጥቅ ከተለመደው የተለየው በምን ይሆን? የሚለው ደግሞ የበርካታ መገናኛ ብዙሃን ትኩረት ነበር:: የድርጅቱ ምላሽም፤ አዲሱ የእግር ኳስ መጫወቻ ትጥቅ የሴቶችን ፍላጎትና ፋሽን፣ ተክለ ቁመና፣ ከስፖርቱ እንቅስቃሴ ጋር ሊሄድ በሚያስችልበት መንገድ እንዲሁም ቴክኖሎጂን መሰረት አድርጎ የተዘጋጀ መሆኑን የሚጠቁም ነበር::
ዜናውን ተከትሎም የመገናኛ ብዙሃን ‹‹ሴቶች በመጨረሻም በራሳቸው ዘይቤ በዓለም ዋንጫ ታዩ››፣ ‹‹ሌላኛው የዓለም ዋንጫው አሸናፊ››፣ ‹‹ህልምን ዕውን ያደረገው ናይኪ በዓለም ዋንጫው››፣… በሚሉ ርዕሶች መነጋገሪያ ሆነ:: የመገናኛ ብዙሃኑን ትኩረት የሳበው የስፖርት ትጥቆቹ ከተለመደው ውጪ በቅርጽና በቀለም አምረው መታየታቸው ሳይሆን በሴቶች ስፖርት የጎደለውን አንዳች ነገር የሞላ ምርት በመሆኑ ነው::
በእርግጥም የሴቶች ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ተሳትፎን በሚመለከት፤ በታሪክ አጋጣሚ የተሳትፎ ዘመን መዘግየትን መነሻ ያደርጋሉ:: ወንዶችን መስለው በስፖርት ሜዳ በቀረቡ የጥቂቶች ጥረትም ዛሬ ላይ ኦሊምፒክን ጨምሮ እንደየስፖርት ዓይነቱ የሴቶች የስፖርትተሳትፎ ተረጋግጧል:: ሴቶች ስፖርትን በቋሚነት የሚሳተፉበት የስራ መስክ ከሆነም በኋላ ‹‹ለእኩል ተሳትፎ እኩል ክፍያ›› የሚለው ሃሳብ በተከታይነት ሲንጸባረቅ ቆይቷል::
ነገር ግን አሁንም ሊሟሉ የሚገባቸው መሰረታዊ ጉዳዮች ትኩረት አግኝተው አልተዳሰሱም:: ከሴት እና ከወንድ አፈጣጠር አካላዊ ቁመና እና ጥንካሬ አንጻር የተለያየ ስለመሆኑ እሙን ነው:: በጥናትና ምርምር ላይ ተመርኩዞ የነገሮችን ግኝት የሚያስቀምጠው ሳይንስም ይህንኑ ያረጋግጣል::
ወንዶች በአማካይ በ10ከመቶ ከሴቶች ተክለቁመና ይበልጣሉ፤ በጥንካሬም ቢሆን በአማካይ 30 ከመቶ የላቁ ናቸው ይላል:: ከፊት ቅርጽ ጀምሮ ባለው የሰውነት አጥንት አቀማመጥ እንዲሁም ውስጣዊ የሰው ልጅ አካላትም በመጠናቸው ራሳቸውን የቻለ ልዩነት አላቸው:: በዚህም ምክንያት አንዳንድ ስፖርቶች ከወንዶቹ ባነሰ መጠን ሴቶችን እንዲያሳትፉ ይደረጋል:: በሌላ በኩል በውጤት ላይም የራሱን ልዩነት የሚፈጥር ሲሆን፤ ለማሳያነትም በተመሳሳይ የውድድር መስክ እኩል ውጤት አለማግኘታቸውን ማንሳት ይቻላል::
ይህ ሳይንስም ሆነ በልምድ የተረጋገጠ እውነታ ግን በሌሎች መሰረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ሳይደገፍ ቀርቶ ክፍተት ሲፈጠር ይስተዋላል:: ለአብነት ያህል አካላዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ የሚፈልጉ ጥንዶች የስፖርት ትጥቅ ለማሟላት ወደ ንግድ ስፍራ ቢያቀኑ፤ የቀለምና የመጠን ልዩነትን መሰረት በማድረግ ነው ሊገዙ የሚችሉት:: ከዚህ ጋር በተያያዘ ሳይጠቀስ የማይታለፈው ለሴቶች ተብሎ እአአ ከ1970 ጀምሮ ለስፖርተኞች በተለየ መልክ ተዘጋጅቶ የሚቀርበው ትጥቅ የጡት ማስያዣ ብቻ ነው:: የልምምድ መሳሪያዎችም ቢሆኑ አብዛኛዎቹ ተመሳሳይ በመሆናቸው ሴቷም በዚሁ ለመጠቀም ትገደዳለች::
የዌስት ኢንዲስ የተባለው የክሪኬት ክለብ ተጫዋች ስቴሲ አን ኪንግ የአንድ ወቅት ገጠመኟ ለዚህ ማሳያ ይሆናል:: በአንድ ቻምፒዮና ለመሳተፍ በትሪንዳድ እና ቶቤጎ በተገኘችበት ወቅት ለቡድኑ የተዘጋጀው ትጥቅ ለወንዶች የተዘጋጀ በመሆኑ ከመጠናቸው በእጅጉ የበለጠ ነበር:: በመሆኑም በውድድሩ ላይ ለመካፈል እሷና የቡድን አጋሮቿ ትጥቁን አጥፈው ለመልበስ ተገደው እንደነበር ታስታውሳለች::
በእርግጥ በዚህ ልክ በሴቶች ስፖርት በጥልቀት ገብቶ ለመስራት አሁንም ተጨማሪ ዓመታት እንደሚያስፈልጉ ይታመናል:: ምክንያቱም ባለንበት ዘመንም የሴቶች የስፖርት ተሳትፎ እንደየሃገሩ፣ የኢኮኖሚ ሁኔታው፣ እምነቱ፣ የቦታ አቀማመጡ፣ የግንዛቤ ደረጃው፣ … የተለያየ መሆኑ እርግጥ ነው:: በየሀገራቱ ካሉ ብሄራዊ የስፖርት ፌዴሬሽን እስከ ዓለም አቀፍ ፌዴሬሽኖች ድረስ የሚሰጠው ትኩረትም ከወንዶቹ በእጥፍ ዝቅተኛ ነው:: ይኸው የትኩረት ማነስም የስፖርት ትጥቅና ቁሳቁስ ዲዛይን ባለሙያዎችና አምራቾችም ክፍተቱን እንዳያጤኑት ምክንያት ሊሆን ይችላል:: ታሳቢ መደረግ የሚገባው ግን አምራቾችም ቢሆኑ ከፊሉ ደምበኞቻቸው ሴቶች ከሆኑ መዋዕለ ነዋያቸውን የሚያፈሱት ሁለቱንም ባማከለ መልኩ ነው::
የኤክሰርሳይስ ፊዚዮሎጂ እና የሥነምግብ ተመራማሪዋ ስቴሲ ስሚዝ ‹‹ሴት ትንሽ ወንድ ማለት አይደልችም›› ስትል ሴት የተለየና የራሷ የሆነ ተክለቁመና ያላት ስለመሆኑ ታሳስባለች:: በተለይ ሴትን ማዕከል አያደርጉም በሚል ቅር ከምትሰኝባቸው ስፖርቶች መካከል አንዱ ብስክሌት ነው:: ይህንን ጉዳይ በርካቶች ጉዳያቸው ባለማድረጋቸው ምክንያት ጥቂት የማይባሉ ሴቶች በቀላሉ የስፖርት ሕይወታቸው እንደሚቀየርና በዚህም እንደምታዝን ትናገራለች::
ሌላኛዋ የኪክ ቦክሲንግ የቀድሞ ተጫዋች ላይን ለተመሳሳይ የችግር ታነሳለች:: በተለይ ጓንቶች ወንዶችን ባማከለ መልኩ ስለሚዘጋጁ ሴቶች ጓንቶችን ለመጠቀም ያዳግታቸዋል:: ወደ ስልጠናው ዓለም ከገባች በኋላም ሴት ታዳጊዎች በስፖርቱ ይበልጥ እንዲሳቡና ደስተኛ እንዲሆኑ ለማድረግ ሮዝ ቀለም ያላቸውን ጓንቶች ለመጠቀም ብትሞክርም እንደሚጠበቀው ምቹ ሆኖ እንደማያገኙት ትገልጻለች::
ሊዲያ ግሪንዌይ ደግሞ ለረጅም ጊዜ ክሪኬትን በመጫወት ያሳለፈች አንጋፋ ስፖርተኛ ናት:: በስፖርተኝነት ሕይወቷ ታደርግ የነበረው ጫማ የወንዶች በመሆኑ ተደጋጋሚ ጉዳት ይደርስባት እንደነበር ታስታውሳለች:: ‹‹ተጫዋች ሳለሁ በተደጋጋሚ የቁርጭምጭሚት ጉዳት አጋጥሞኛል:: ይህም የሆነው ከመጫወቻ ጫማው የተነሳ ቢሆንም፤ ይህንን ታሳቢ የሚያደርግ መላ ማግኘት ግን አልቻልኩም ነበር:: ችግሩ የኔ ብቻ ሳይሆን አማራጭ ያጡ የበርካታ ሴት ተጫዋቾችም ነው›› ስትልም ቅሬታዋን ታቀርባለች:: እሷ ስፖርትን በጀመረችበት እአአ በ1980ዎቹ ለሴት የሚሆን የትጥቅ ዓይነት ባለመኖሩ የወንዶቹን ገዝታ ለመጠቀም ትገደድ ነበር:: አሰልጣኝ ከሆነችበት 2017 ጀምሮ ግን ጥቂት ለመመልከት ችላለች::
የስፖርት ባለሙያዎችም ሆኑ ሌሎች የስፖርት ትጥቅን የሴት እና የወንድ መባሉን ቦታ ባይሰጡትም፤ ሴት ስፖርተኞች ግን ከምቾታቸውና ተገቢነት ውጪ ከመስተናገዳቸው ባለፈ ለጉዳትም ይጋለጣሉ:: ስፖርተኞች ጉዳትን በልምምድም ሆነ በውድድር ወቅት ሊያስተናግዱ ይችላሉ:: የጉዳት ምክንያት ከሆኑት መካከል የመለማመጃ ትጥቆችና መሳሪያዎች አለመመቸት ይጠቀሳል:: ሴቶች ደግሞ ከወንዶች አንጻር ስስ የሆኑ የአካል ክፍሎች አሏቸው:: በመሆኑም ትጥቆቻቸው፣ የመለማመጃ መሳሪያዎቻቸውም ሆኑ መወዳደሪያዎቻቸው ይህንን ታሳቢ ያደረጉና ለጉዳት የማያጋልጡ ሊሆኑ ይገባል::
የሮሃምፕተን ዩኒቨርሲቲ የስፖርትና የባዮሜካኒክስ መምህር እንዲሁም የእንግሊዙ ክሪስታል ፓላስ ክለብ የሴቶች ቡድንን በሙያቸው የሚያገለግሉት ዶክተር አንድሬው ግሪንም ይህንን ሃሳብ ይደግፋሉ:: ሴቶች ከ2-10 በመቶ የሚሆን ብልጫ ያለው የጉልበት ጉዳት እንደሚገጥማቸውም ይጠቁማሉ:: ይህም የሚመጣው በዕለት ከዕለት የልምምድ እንቅስቃሴዎች በሚጠቀሟቸው የስፖርት ትጥቆችና ቁሳቁስ መሆኑንም ያመለክታሉ::
በመሆኑም ጥቂቶች የራሳቸውንና የሌሎች ሴቶችን መብት በማረጋገጥ በኩል በርካታ ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛሉ:: ከእነዚህ መካከል አንዷ ላውራ ያንግሰን ስትሆን ‹‹እኩል የውድድር ሜዳ›› የሚል ለትርፍ ያልተቋቋመ ንቅናቄ መስራች ናት:: በዚህ እንቅስቃሴ ላይም ከ20 አገራት የተወጣጡ 31 የሚሆኑ ሴቶች ተካፋይ እየሆኑ ነው:: ዕድሜያቸው ከ15-55 የሚደርሱ አማተር እና በስፖርቱ ያለፉ ሴቶችን ያቀፈው ይህ ማህበር፣ በተለይ በሴቶች እግር ኳስ ላይ የሚሰራ ነው፤ በኪሎማንጃሮ ተራራ አናት ላይ ውድድር በማድረግም ጭምር በጊነስ የዓለም ድንቃድንቅ መዝገብ ላይ መስፈር ችሏል::
የማሕበሩ መስራች የሆነችው ያንግሰን ይህንን ውድድር ባዘጋጀችበት ወቅት የመጫወቻ ጫማ ለማግኘት እጅግ በመቸገሯ ለታዳጊ ልጆች የተዘጋጀውን ለመጠቀም መገደዷን ታስታውሳለች:: ገጠመኙ እሷ ላይ ብቻ የደረሰ ሳይሆን በማሕበሩ አባላትም ያጋጠማቸው ነው፤ ይህም ሴት ስፖርተኞች የታዳጊዎችን አሊያም የወንዶችን ጫማ ለማድረግ የሚገደዱ መሆኑን በግልጽ ያመላክታል:: በመሆኑም ለሴቶች ተብሎ በመጠንና በምቾች የተዘጋጀ የስፖርት ጫማ ስለመኖሩ ባደረገችው ዳሰሳዊ ጥናት አስደንጋጭ ግብረመልስ ስለማግኘቷ ከኢኤስፒኤን ጋር በነበራት ቆይታ ጠቁማለች::
ሳይንቲስቶች እአአ ከ1990ዎቹ ጀምሮ በሴትና ወንድ እግር ኳስ መካከል ስላለው ልዩነት ምርምር በማድረግ ዲዛይኑ ሊለያይ እንደሚገባ አመላክተዋል:: ይኸውም የሴቶች እግር በአፈጣጠሩ ቀጭን እና የጣቶቻቸው ቅርጽም የተለየ በመሆኑ የውድድር ጫማቸው በጣቶቻቸው አካባቢ ተጨማሪና ሰፊ ስፍራ ያስፈልጋቸዋል:: የዳሌ እና ሽንጥ አካባቢ ያለው ቅርጽም በተመሳሳይ ከወንዶች ጋር የሚለያይ በመሆኑ በሰውነታቸው ላይ ሌላ ልዩነት የሚፈጥር በመሆኑ፤ ጫማቸው ይህንን ካላማከለ በታችኛው የእግራቸው ክፍል ላይ ጉዳት እንዲደርስ ምክንያት ይሆናል::
ጥናቱን ተከትሎም ያንግሰን ‹‹ሴቶች አማራጭ በማጣት ተገቢ ያልሆነውን የስፖርት ትጥቅ በመጠቀማቸው ራሳቸውን ለጉዳት ለማጋለጥ ተገደዋል:: ይህ ከሆነ ታዲያ ትልልቆቹ የስፖርት ትጥቅ አምራቾች ምን እየሰሩ ነው?›› የሚል መልስ አልባ ጥያቄና ቁጭት በአእምሮዋ መጫሩን ታስታውሳለች::
በምልከታዋ አስደሳች ነገር ባለማየቷ ከሌላኛዋ የማሕበሩ አባል ቤል ሳንዱ ጋር በመሆንም የሴቶች የስፖርት መወዳደሪያ ጫማ ለማዘጋጀት ከውሳኔ ደረሰች:: ሃሳቡ መሬት ለመርገጥ በርካታ መሰናክሎችን አልፎም ‹‹ኢዳ ጫማ›› በሚል መጠሪያ ከሁለት ዓመታት በኋላ እአአ በ2020 የመጀመሪያውን የሴቶች የስፖርት ጫማ ለተጠቃሚዎች ደርሷል:: በተለይ በአውስትራሊያ የሴት ሊጎች ተመራጭ ሲሆን፤ ተጫዋቾቹም እጅግ ምቹና እንደ ቀድሞው ለጉዳት አጋላጭ አለመሆኑን ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል::
ትልልቅ ስም ያላቸው የስፖርት ትጥቅና ቁሳቁስ አምራቾች ሴቶችን ማዕከል ያደረጉ ምርቶችን ለተጠቃሚዎች በማቅረብ ረገድ እንቅስቃሴያቸው በእጅጉ አናሳ የሚባል ቢሆንም ከሁለት ዓመታት ወዲህ ግን ለውጦች እየታዩ ነው:: ለማሳያነትም በናይኪ ተመርቶ ለገበያ የቀረበው የሴቶች የእግር ኳስ ትጥቅ እንዲሁም ለክሪኬት እና ቅርጫት ኳስ ስፖርቶች መጫወቻ እንዲሆን በልዩነት የተዘጋጀውን ጫማ ማንሳት ይቻላል:: ተጠቃሚ የሆኑ ስፖርተኞችም በቀረበላቸው ትጥቅ ምቾት በማግኘታቸው ደስተኛ መሆናቸውን በሰጡት ግብረመልስ አመላክተዋል::
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን የካቲት 29/2014