ሴትነት ውበት፤ ሴትነት እናትነት፤ ሴትነት ልእልና እና ከፍታ፤ ሴትነት ስፋት ማለት ነው ትላለች የዛሬዋ ባለታሪካችን ደራሲ ሊዲያ ተስፋዬ፡፡ ደራሲዋን ያገኘኋት አንድ መድረክ ላይ በልበ ሙሉነት ለልጆች የሚሆን አነቃቂ ንግግር ስታደርግ ነው። በወቅቱ ‹ሴት ልጆች እንዲህ ሁኑ… እንደዛ አድርጉ… › በሚል አይነት ትዕዛዝና ምክር ሳይሆን በታሪክ በተዋዛ አንደበት የምትፈለገውን መልእከት ስታስተላልፍ አስተዋልኳት፡፡ ለዛሬዋም የሴቶች ቀን እንግዳዬ ላደርጋት በመውደዴ እንደሚከተለው አጠናቅሬ አቅርቤያለሁና መልካም ንባብ።
ሁሉም ሰው የልጅነት ህልም አለው። ዛሬ የማስተዋወቃችሁ ወይዘሮም በልጅነቷ እንደ አብዛኞቻችን ዶክተርም ፓይለትም የመሆን ህልም እንደነበራት ትናገራለች፡፡ ከዚህ ሌላ በልጅነቷ መጻሕፍትን ባነበበች ቁጥር ደግሞ አንዴ ሰላይ የመሆን ምኞት፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ደራሲ፤ ደግሞ ሌላ ጊዜ ጋዜጠኛ በመሆን ህልም ውስጥ ስትመላለስ እንደነበር ትገልፃለች።
በጎልምስናው እድሜ መጀመሪያ አካባቢ የምትገኘው በፍልቅልቅ ገፅታና በማይሰለች አንደበት ከልጅነት እስከ እውቀት ያሳለፈችውን ጊዜ እንዲህ አጫውታናለች። ልጅነቷን በፍጹም ሥነ ምግባር በመታነጽ እንደሳለፈች የምትነግረን የዛሬዋ ባለታሪካችን፤ በአዲስ አበባ ጉርድ ሾላ አካባቢ በሚገኝ በገዳመ ስታዊያን ማሪያም ፅዮን ካቶሊክ ሚሽን ትምህርት ቤት ከፊደል ጋር ተዋወቀች። በትምህርት ቤቱ የሥነ ምግባር ጉድለት ለድርድር የማይቀርብ በመሆኑ ሥነ ምግባር ባለው የትምህርት ማሕበረሰብ ውስጥ ግብረ ገብነት እንደ አንድ የትምህርት አይነት የሚሰጥበት፤ መምህራኑም ከወላጅ ተቀበለው ሌላ ወላጅ በመሆን የማሳደግ ሃላፊነትን ወስደው ልጆቹ በፍጹም ሥነ ምግባር እንዲያድጉ የሚደረጉበት ሁኔታ እንደነበር ታስረዳለች።
መጀመሪያ ከንባብ ጋር የተዋወቀችበትን አጋጣሚ ስትናገር መጀመሪያ ያነበበቻትን ግርዶሽ የተባለችው መጽሐፍ ታስታውሳለች። ያችን መጽሃፍ ለመግዛት ግን ዳቦ ትምህርት ቤት አካባቢ በመሸጥ የአስር ሳንቲም እቁብ ገባች፤ በዚያች እቁብ የተገዛች መጽሐፍ ናት ለመጀመሪያ ጊዜ ከንባብ ጋር ያስተዋወቀቻት፡፡ ያቺ የአስር ሳንቲም እቁብ አድጋ 50 ሳንቲም ደረሰች። በምታገኛትም ገንዘብ ሌሎች መጻሕፍትን ለማንበብ እድሉን አገኘች፡፡
‹የልጅነት ህልሜ ይሳካል፤ ደራሲ መሆን እችላለሁ› እንድትል ያደረጋትን አጋጣሚ ታስታውሳለች፡፡ ይኸውም አምስተኛ ክፍል እያለች አንዲት ቆንጆ ግጥም ጽፋ ለሚኒሚዲያ ኃላፊያቸው ትሰጣቸዋለች። ‹ቆንጆ ግጥም ነው፤ ባንዲራ ላይ ታነቢያለሽ› ተባለች፤ በመሆኑም በርካታ ተማሪዎች ባሉበት አንብባ ሲጨበጨብላት ያኔ ‹እኔ ደራሲ መሆን አችላለሁ› የሚል ሥነ ልቦና እንድትገነባ እንዳደረጋት ደራሲ ሊድያ ታስታውሳለች።
ከዛም በትምህርት ቤት ውስጥ የሚኒሚዲያ ንቁ ተሳታፊ በመሆን የሥነ ጽሁፍ ልምዷን እያዳበረች ለመሄድ ቻለች። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህር እንደተጠናቀቀ በምስራቅ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመድባ ስትገባ ከነበረችበት ዓለም የተለየ ቦታ የተጣለች ያህል ከባድ የትምህርት ጊዜ እንደነበር ትናገራለች።
ቀደም ሲል ትማርበት እንደነበረው ትምህርት ቤት እርስ በእርስ የሚከባበሩ፣ የሚዋደዱ፣ እንደ እህትና ወንድም የሚተያዩ የአንድ ትምህርት ቤት ልጆች መሆናቸው ቀርቶ ወንዶች ሴቶችን የሚያስቸግሩበት፤ ፀብና ድብድብ የሞላበት ሆኖ አገኘችው፡፡ በጣም አስቸጋሪ የሆነ የትምህርት ማሕበረሰብ ውስጥ ገባች። በዚህ ሁሉ ትርምስ ውስጥ ሆናም ቢሆን ዩኒቨርሲቲ መግባት የመጨረሻው እድል ነው በሚል እሳቤ ትምህርት ላይ በመጠንከር የተሻለ ወጤት ለማምጣት መጣር ጀመረች።
በወቅቱ ዘጠኝና አስረኛ ክፍልን በመደበኛው ትምህርት ከተማረች በኋላ አስራ አንደኛና እስራ ሁለተኛ ክፍልን የንግድ ስራ ትምህርት ለብቻው አምስት ትምህርት ብቻ ያለውን የንግድ ሥራ ትምህርት ተማረች። የአስራ ሁለተኛ ክፍልን እንዳጠናቀቀች ቀድማ ባካበተችው የንግድ ሥራ እውቀት በ18 ዓመቷ አንድ የደራሲ ቢሮ ውስጥ በፀሃፊነት ተቀጠረች። ይህ አጋጣሚ የነፍሷ ጥሪ ከሆነው ድርሰት ጋር ለመገናኘት መንገድ እየጠረገላት እንደ ነበረ ትናገራለች።
በፀሃፊነት ስራዋ ላይ እያለችም ጭኮ ሰርቶ በየሱፐር ማርኬት እያዞሩ መሸጥ፤ አበባን በየቢሮው መሸጥ የሰርግ ዲኮር ስራን ብቻ ትርፍ ቀን በተባለው ቅዳሜና እሁድ የተሻለ ገቢ ለማግኘት መጣር ላይ ተሰማራች። በዚህ ሁሉ መሃል በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ በዲግሪ መርሃግብር በአካውንቲንግ ተምራ አጠናቀቀች፤ በመቀጠል አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በዲግሪ መርሃግብር ማርኬቲንግ ማኔጅመንት ተማረች። በመቀጠል የተለያዩ የንግድ ሥራዎች እየሰራች ቀጠለች።
በዚህ መሃል ወደ ትዳር ሕይወት የገባችው ደራሲ ሊዲያ፣ ልጆች ማሳደግ ብሎም የተለያዩ ኃላፊነቶችን በአንድ ላይ ማስኬድ ጀመረች። የመጀመሪያ ልጇን እርጉዝ በነበረችበት ጊዜ ለነፍሰጡር የሚሆኑ ልብሶችን እንደልብ ማግኘት ሳይሆንላት ሲቀር ‹ለምን የዚህን ንግድ አልጀምርም› በማለት የህፃናትና የእርጉዝ ልብስ የምትሸጥበትን ቡቲክ ከፈተች። ባለቤቷ የፊልም ባለሙያ በመሆኑ ቪዲዮ ኤዲቲንግ ሥራ እየረዳችው የራሷን የንግድ ሥራ ማራመድ እንደ ጀመረች ታስረዳለች። የተለያዩ ንግዶችን በተከታታይ ብትሰራም የልቧ ሊደርስ ባለመቻሉ ሁሉንም እርግፍ አድርጋ በመተው የሙሉ ጊዜ ደራሲ ለመሆን ወስና ገባችበት።
ለመፅሄት አጫጭር ፅሁፍ በመፃፍ የተጀመረው የድርሰት ሥራ ሶስት መጻሕፎችን እንድታበረክት አድርጓታል። መጀመሪያ የፃፈችው መጽሐፍ በቃለ መጠይቅ የተሰራ ሲሆን፣ የመጀመሪያ የግሌ የምትለው መጽሐፏ ግን በማሕበራዊ ሕይወት ዙሪያ የሚያጠነጥን ‹የምወድህ› የተሰኘ መጽሐፍ ነው፤ ሁለተኛው ‹ለእግዜር እዳ› የተሰኘና ‹ወደ ኋላ› የተሰኙ መጻሕፍትን አከታትላ በመፃፍ ለተደራሲ አቅርባለች።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ በተለያዩ ጊዜያት በሚያካሂደው የንባብ ሳምንት ላይ ተጋባዥ በመሆን የተለያዩ አነቃቂ ሃሳቦችን የምትናገረው ደራሲ ሊዲያ፣ በአብዛኛው ለልጆች በታሪክ የማስተማር ሃሳቦችን በመጀመር በተረት መቃኘት ባህሪ ማስተካከል የሚባሉ ሃሳቦችን በማንሳት በእያንዳንዱ መድረክ ለሰዎቹ የሚመጥኑ ንግግሮችን በማድረግ የተሻለ ስኬት ላይ ለማድረስ በመጣር ሥራ ትሰራለች።
ድርሰት፣ የንግድ ሥራ፣ ትዳር፣ ትምህርት ሁሉም ደረጃዎች በሕይወት ሂደት ያለፈችባቸው እንደሆኑ የምትናገረው ሊዲያ፣ እናት እንደመሆን ያለ መባረክን ግን ከምን ነገር ጋር እንደማታወዳድረው ትገልጻለች። እናት መሆን ሰው ስለፈለገ የሚያደርገው ሳይሆን የማንም ጥበብ ያልተገለፀበት የፈጣሪ ፀጋ መሆኑን ታስረዳለች። ልጅ እያለሁ አንድም ቀን እወልዳለው ብዬ የማላስብ ነበርኩ፤ ነገር ግን ሳገባ ለባለቤቴ ስል አንድ ልጅ መውለድ አለብኝ ብዬ ነበር የማስበው። በኋላ ግን ልክ እርግዝናው ሲመጣ የእናትነት ፀጋው፣ ለሌሎች ልጆች መራራቱ ትክክለኛው የእናትነት ስሜት እንዲኖራት እንዳደረጋት ትናገራለች። የመጀመሪያ ልጇ ፍቅር ትባላለች። ሁለተኛ ልጇም እውነት የምትባል ሲሆን፣ ‹የራሴ በምለው ሕይወት ውስጥ የሌላ ሰው ሕይወትን የማስቀጠል መቻሌ እርካታን ይሰጠኛል› ትላለች።
‹በሕይወቴ ከምንም ነገር በላይ መመሪያ የሆኑኝ እውነትና ፍቅር ናቸው› የምትለው ደራሲ ሊዲያ፣ ‹ለዚህም ነው የልጆቼን ስም እውነትና ፍቅር ያልኩት› ስትል ለልጆቿ ያላትን ስስት የምትገልጸው፡፡ ሊዲያ፣ የተሳካ የትዳርና የቤተሰብ ሕይወት እንዳላት ታስረዳለች። ፍቅር 19 ዓመቷ ሲሆን፣ የሁለተኛ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ናት፡፡ እውነት ደግሞ አስረኛ ክፍል ናት፤ ‹ልጆች ለኛ አደራ የተሰጡን በመሆናቸው ያንን አደራ ለመወጣት እተጋለሁ› ትለናለች።
ቤተሰብ ሲመሰረት ሰው አልጋ በአልጋ የሆነ ሂደት ያለው ይመስለዋል፤ የቤተሰብ ሕይወት ምስረታ ግን ቀላል አይደለም፡፡ በሕይወት ትክክለኛውን መንገድ ለመሄድ ግን መሞላላት ጎዶሎን መሸፋፈን የግድ ነው። ባለቤቴ እጅግ መልካም ሰው ነው፤ ሊረዳኝ የሚሞከርና ለእያንዳንዱ ስራዬ መደገፍ እንኳን ባይችል ህልሜን እንድኖር መንገዶችን የሚያመቻችልኝ አይነት የትዳር አጋር በማግኘቴም እድለኛ ነኝ ብላለች።
ትዳር ሲጀመር በፍቅር ከተጀመረ ፍቅር መንገዶችን ይጠርጋል፤ ከዚህም በላይ ግን ስሜት መጠባበቅና መረዳዳትን የመሰለ ነገር የለም። በኛ ትዳር ውስጥ እኔ መብቴ ነው የምል አይነት ሴት፤ እሱ ደግሞ እጅግ በጣም ትዕግስተኛ፤ እኔ ግለኝነቴን የማበዛ ስሆን፣ አንድ መሆን ግን የግድ የነበረ ትግሎች የነበረበት በየቤተሰባችን ያመጣነውን ባህል ትተን ሌላ ባህል የመንመሰርትበት መሆኑ ትንሽ ከባድ ያደርገዋል። ያም ሆኖ ግን ይሄው ለሃያ ዓመታት ቀጥ ያለ መስመርም ባይኖር ብዙም መንገራገጭ የለሌበት የሕይወት መንገድ አልፈናል ትላለች።
እኔና ባለቤቴ በፍፁም ጓደኝነት ውስጥ የትዳር ሕይወትን መስርተን በጥንካሬ እዚህ ደርሰናል። የባለቤቴ ጠንካራ ጎን ትእግስቱ ነው፤ የሱ ትእግስት ብዙ መንገድ እንድንሄድ አድርጎናል፤ የኔ ጠንካራ ጎን ደግሞ የፈለኩበት ካልደረስኩ መቆም አልችልም፤ ጠንካራ ሃሳቤን ይዤ ወደፊት እሄዳለሁ። ባለቤቴ የሚገርም ፅናት ስላለው የእኔ ደካማ ጎን የእርሱ ጠንካራ፤ የእርሱ ደካማ ጎን የኔ ጥንካሬ ሆኖ እየተሞላላን ትዳር ሳይከብደን እዚህ ደርሰናል ስትልም ታስረዳለች።
‹እናትነቴ ለሁለቱ ልጆች ብቻ እንዳይሆን አቅዳለሁ። በቀጣይ እቅድ ብዬ የማስበው በማሕበረሰባችን ውስጥ ለህፃናት የሚሉ ሃሳቦች ይነሳሉ፤ ብሎም ለወጣቶች የተለያዩ መጽሐፍ ሊኖሩ ይችላሉ፤ ነገር ግን ከሕፃንነት የዘለለ ወጣትነት እድሜ ላይ ያልደረሱ ልጆችን ሊደርስ የሚችሉ ሃሳቦችን በማንሳት መፃፍ፤ የፊልም አስክሪፕቶችና ሌሎች በንባብ ዙሪያ የሚሰሩ ሥራዎችን ለመስራት ሰፊ እቅድ አለኝ› ትላለች።
ሴት መሆን ሲታሰብ ሰው መሆን በሚለው ሃሳብ መነሳት አለበት። ሴት ከወንድ እኩል ናት ብሎ መገዳደር እንድ ፅንፍ መያዝ እጅግ በጣም ከባድ ነው። እራስን አሳንሶም ጓዳ ውስጥ መወሸቅ አግባብ አይደለም። ሴት በእኔ ዓለም ለባሌ ምቹ መሆን ወይም ልጆችን ማሳደግ ብቻ ነው የሚል ደሴት ውስጥ መግባት አይደለም፡፡ ይህ አይነቱ አተያይ ዓለም የትና የት በደረሰበት በዚህ ዘመን የሚታሰብ አይደለም። ሴት መሆን መጥበብ አይደለም ሴት መሆን እንዲያውም መሰፋት ነው። ሰፍቶ ወጥቶ ለቤትም ለውጭ መትረፍ ነው።
ማንበብም መፃፍም ይቻላል። እናት መሆንም ሚስት መሆንም ይቻላል። ግን ደግሞ ለሌሎች መኖር ይቻላል። የአስተሳሰብ አድማስን አስፍቶ ማየት፤ ከተጠቂነት ስሜት መውጣት፤ ተጎጂነት እያሉ ራስን አሳንሶ ከማየት የተሰራውን አጥር ፍርስርስ አድርገን ምስቅልቅሉ የወጣውን ዓለም መልካምነትን በማድረግ ውበት እንሰጠው ስትል ትናገራለች።
ሴቶች ከፍታ ላይ ሲወጡ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል፤ ‹ለስራው ብቁ ነኝ፤ እችላለሁ› በሚል ስሜት መራመድ አለባቸው። ሴት አለቃ ስትሆን የሚል ስያሜ እንዳይሰጣቸው በማድረግ ሥራና የሥራ ሃላፊነት የተጎዳችውን ስሜት ሳታንፀባርቅ ከፍ ስትል የእውነት ለከፍታው የምትመጥን መሆን እንዳለባት ማሳየት አለባት። ሴት በተፈጥሮዋ ጠንቅቅ ያለ ውበት ያለው ሥራ በመስራት የምትታወቀውን ያህል በትእቢት ሳትኮፈስና የዝቅተኝነት ስሜትም ሳይጫናት መስራት ይኖርባታል በማለት ከደራሲ ሊዲያ ጋር የነበረንን ቆይታችንን አብቅተናል።
አሥመረት ብሥራት
አዲስ ዘመን የካቲት 29/2014