ዓለማችን የወንዶች ናት ቢባል ማጋነን አይሆንም። ዛሬም ድረስ ‹‹ምንም ሴት ብታውቅ በወንድ ያልቅ›› ከሚል ኋላቀር ተረት አልተላቀቅንም። እንዲህ አይነቱ ተረት የት ይደርሳሉ የተባሉ ኢትዮጵያውያን ሴቶችንም ኋላ አስቀርቷል:: ከተፅዕኖ ነፃ የመሆን ዕድሉ አላቸው የሚባሉና በመገናኛ ብዙሃን ውስጥ የሚሰሩ ሴቶች እንኳን አሁንም የወንዱ ተፅዕኖ ይንፀባረቅባቸዋል:: በመገናኛ ብዙኃን ተቋማት በኩልም የሴቶች ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶት ሲሰራበት አይታይም::
ይህን ዕውነታ ከሚያስረዱና በሞያቸው ለሴቶች እኩልነት እየታገሉ ከሚገኙ የሚዲያ ባለሙያዎች መካከል አንዷ አንጋፋ ጋዜጠኛ አባይነሽ ብሩ ናቸው::
ጋዜጠኛ አባይነሽ በኢትዮጵያ ራዲዮ ለበርካታ ዓመታት በሙያቸው አገልግለዋል:: ሴቶች በመገናኛ ብዙሃን ገፅታቸው በአግባቡ መታየቱና መገለፁ በማህበረሰቡ ውስጥ ሊኖራቸው የሚገባውን ቦታ እንዲያገኙ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያደርጋል ብለው ከሚሞግቱ ሴት ጋዜጠኞች ውስጥ አንዷ ናቸው::
በሬዲዮ ጋዜጠኛ ሆነው በኢትዮጵያ ሬዲዮ በሰሩባቸው በርካታ ዓመታት ሙሉ ትኩረታቸው በሴቶች ጉዳይ ላይ ነበር:: የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያ የሆኑ ሴቶች በሴትነታቸው ከሙያቸው ጋር በተያያዙ በሚያጋጥሟቸው ችግሮችና መፍትሄዎቻቸው ዙሪያ በርካታ ሥራዎችን ሰርተዋል::
መገናኛ ብዙኃን የሴቶች ጉዳዮችን በሥርዓተ ጾታ መነጽር ሊመለከቱ የሚችሉበትን ሁኔታ እንዲፈጥሩ፣ በተግባርም ለማሳየት እንዲችሉ በጋራ ሆነው የሚወያዩበት፣ አቅማቸውን የሚያሳድጉበት፣ የሙያ ማህበር እንዲመሰርቱም ብርቱ ትግል አድርገዋል::
ከዚህም በተጨማሪ ሴቶች የበለጠ ተጠቂ የሆኑበትን ኤች አይቪ ኤድስ ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚያስችሉ በርካታ የተግባቦት ሥራዎች ላይም ለረጅም ዓመታት ሲሰሩ ቆይተዋል::
በአሁኑ ወቅት ደግሞ ከሴቶች ብዙም ሳይርቁ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በዚሁ በሴቶች ጉዳይና በባህርይ ለውጥ ተግባቦት ዙሪያ የማማከር ሥራ እያከናወኑ ይገኛሉ።
ወይዘሮ አባይነሽ ‹‹ግሎባል ሚዲያ ሞኒተሪንግ›› በሚባል ድርጅት አማካኝነት ዓለም አቀፍ ጥናት በቅርቡ መካሄዱንና ኢትዮጵያም በዚህ ጥናት ውስጥ ስትካፈል ይህ ሁለተኛዋ ጊዜ መሆኑን እንደመንደርደሪያ ያነሳሉ:: የግሎባል ሚዲያ ሞኒተሪንግ ፕሮጀክት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሚዲያ ክትትል ሥራን የሚሰራ መሆኑንና የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያ ሴቶች ማህበር እንደተሳተፈበትም ይናገራሉ:: ስርዓተ ጾታን በተመለከተ የተደረገ የክትትል ሥራ ላይ ያተኮረ መሆኑን ይጠቅሳሉ::
እርሳቸው እንደሚሉት ሥራው የተሰራው አነስተኛ በሆነ ድጋፍና በበጎ ፈቃደኝነት ነው:: ይህ የሚዲያ ክትትል በግሎባል ሚዲያ ሞኒተሪንግ ፕሮጀክት አማካኝነት በየአምስት ዓመቱ ይካሄዳል:: ለአብነትም እ.ኤ.አ በ2010 እንዲሁም እ.ኤ.አ በ2015 እና በ2020 ተካሂዷል:: ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2010 በተካሄደው የክትትል ጥናት ላይ የተካፈለች ቢሆንም እ.ኤ.አ በ2015 በተካሄደው ጥናት ላይ ግን ሳትካተት ቀርታለች:: ለዚህም በወቅቱ የነበረው የበጎ አድራጎት ማህበራት ሕግ አሳሪ መሆን እንደ ዋና ምክንያት ይጠቀሳል::
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያ ሴቶች ማህበር እ.ኤ.አ በ2020 እንዲካሄድ ታቅዶ በነበረው የክትትል ጥናት ላይ እንዲሳተፍ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ይሁንታን አግኝቶ ከግሎባል ሚዲያ ሞኒተሪንግ ድርጅቱ የማስተባበር ፈቃዱን በመውሰድ ጥናቱን ለማካሄድ በቅቷል::
ጋዜጠኛ አባይነሽ በግሎባል ሚዲያ ሞኒተሪንግ ድርጅቱ አማካኝነት ግምገማው እንዴት እንደሚሰራ የሚያሳይ ስልጠና ከሌሎች አስተባባሪዎች ጋር በመሆን ወስደዋል። ስልጠናውም ታች ድረስ በመውረድ ሥራውን ለሚያሰሩ ብቻ ሳይሆን ለሚሰሩ ክፍሎችም ጭምር ተሰጥቷል።
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኞች ማሰልጠኛ ክፍል ጋር በመተባበር ሊሰራ የነበረው ጥናት በወቅቱ በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት እውን ሊሆን ባለመቻሉ ማህበሩ ፈቃደኛ ከሆኑ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ጥቂት ሠራተኞች ጋር ለመስራት መገደዱን አንጋፋዋ ጋዜጠኛ አባይነሽ ያስታውሳሉ::
እርሳቸው እንደሚናገሩት ግሎባል ሚዲያ ሞኒተሪንግ ፕሮጀክት ይህን በስርዓተ ጾታ ላይ ያተኮረ የክትትል ጥናት ቀን የሚወስነው በድርጅቱ ሲሆን የትኛውም ተካፋይ የሚዲያ ተቋም የክትትል ሥራው የሚካሄደበትን ቀን አያውቅም:: ቀኑም የሚያዘው በሚስጥር ነው። ሥራውም የሚሰራው በዓለም አቀፍ ደረጃ በአንድ ቀን፣ በአንድ ሰዓት በተመሳሳይ ሁኔታ ነው::
ይህም የሚደረገው ሚዲያዎቹ ቀኑን እንዳያውቁ ለማድረግ መሆኑን ይጠቁማሉ:: ቀኑን ካወቁት የሚዲያ ተቋማቱ ተዘጋጅተው ለሴቶች ጉዳይ ሽፋን ስለሚሰጡት እውነተኛውን ሁኔታ ለማወቅ ስለማያስችል መሆኑንም ይጠቅሳሉ:: ከዚህ አንፃር ዕውነተኛውን ሥዕል ለማግኘት ሲባል በዓለም ላይ ሞኒተሪንግ ወይም ክትትል የሚደረግበት ትክክለኛ ቀን በሚስጥር እንደሚያዝ ወይዘሮ አባይነሽ ያስረዳሉ::
እናም በዓለም ላይ በአንድ ተመሳሳይ ቀንና ሰዓት በሚወጡ ጋዜጦች፣በሚተላለፉ የሬዲዮ እና የቴሌቪዥን ዜናዎችና ፕሮግራሞች በቲውተር ገጾች እንዲሁም በሌሎችም የማህበራዊ ሚዲያዎች በሚወጡ ዜናዎች ላይ የክትትል ሥራው እንደሚካሄድ ይጠቁማሉ:: በዚሁ መሰረት የ2020 የክትትል ሥራ የተካሄደው እ.ኤ.አ መስከረም 29 ቀን 2020 በ116 የዓለም ሀገሮች ውስጥ ነበር::
በዚህ ዕለት በ116 ሀገሮች በሚገኙ የሞኒተሪንግ ቡድኖች አማካኝነት በጋዜጣ፣ በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥንና በድረ ገጾች ላይ የወጡ 30 ሺ 172 የዜና ታሪኮችና ፕሮግራሞች የጥናቱ አካል ሆነው ተካተዋል:: በተካሄደው የክትትል ሥራም 2 ሺ 251 የሚዲያ ተቋማት ተካፋይ የሆኑ ሲሆን ክትትል የተደረገባቸው 58 ሺ 499 የዜናው አካል የሆኑ ሰዎችና ምንጮች ይገኙበታል::
በዚህ ሥራ ውስጥ በቀረቡት ዜናዎችና ፕሮግራሞችም ላይ የተሳተፉት 28 ሺ 595 ጋዜጠኞች መሆናቸው በጥናቱ ላይ ተጠቅሷል:: በክትትሉ ላይ የሚካፈሉት ሀገሮች ቁጥር ሥራ ከተጀመረበት እ.ኤ.አ ከ1995 ጀምሮ በ63 በመቶ ያደገ ሲሆን ክትትል የተደረገባቸው የዜና ታሪኮችም ባለፉት 25 ዓመታት በእጥፍ እ.ኤ.አ ከ2015ቱ በስምንት ሺ ጨምሯል::
እንደ ወይዘሮ አባይነሽ ገለፃ ፤የክትትል ሥራው የሚካሄድበት የመገናኛ ብዙሃን ተቋም የሚመረጠው ተግባሩ ከመከናወኑ ቀደም ብሎ ነው። እ.ኤ.አ በመስከረም 2020 የታዩት የሚዲያ ተቋማትም የተመረጡት በዚሁ መንገድ ነበር:: በመረጣው ከህትመት ሚዲያው ቀደምት ታሪክ ያለው አንጋፋው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የሚያሳትማቸው ዕለታዊዎቹ አዲስ ዘመን እና ዘኢትዮጵያን ሄራልድ ጋዜጦች ቀዳሚውን ሥፍራ ይዘዋል:: ምንም እንኳን በኋላ እንደታየው ከ90 በመቶ በላይ ትኩረቱን ከሮይተርስና ከሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት የተወሰዱ ጉዳዮች ላይ በማድረጉ ዕለታዊ የኢትዮጵያ ጋዜጣ ተብሎ መቁጠሩ ቢያዳግትም ሞኒተር ጋዜጣም ከሕትመቱ ዘርፍ ተካትቶ የታየበት ነበር:: ከዜና ተቋማት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዲሁም ከቲውተር ኢትዮጵያን ኢንሳይት ተጠቁመው ነበር::
ከዚህ ባለፈ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ኢሳት፣ ዋልታ ፣ ኦ ቢ ኤን ከሬዲዮ ሸገር ኤፍኤም ተወስደው የታዩ መሆናቸውንም ወይዘሮ አባይነሽ አስታውሰው፤ በተለይ በሕትመቱ ዘርፍ ሲቃኝ የሞኒተሪንግ ሥራው ትኩረት አድርጎ የሚከናወነው በዕለታዊ ጋዜጦች ላይ እንደነበር ይገልፃሉ:: ከነዚህ ዕለታዊ የሕትመት ውጤቶች አንፃር የዓለም ሀገራት ብዙ ሥራዎች እንዳሏቸውና ለአብነት የኢትዮጵያ የቅርብ ጎረቤት ኬንያ ስድስት ዕለታዊ ጋዜጦች መኖራቸውን ይጠቅሳሉ::
ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ የሕትመት መገናኛ ብዙሃን ዘርፍ የሚያሳትማቸው ዕለታዊ ጋዜጦች አዲስ ዘመንና ኢትዮጵያን ሄራልድ እንዲሁም ዘ ሞኒተር ብቻ መሆናቸውንም ይናገራሉ:: እንዲያም ሆኖ ግን የግሎባል ሚዲያ ሞኒተሪንግ ሥራውን ለማከናወን በሚያስችለው መረጣ ወቅት ትልቁ ተግዳሮት የነበረው በኢትዮጵያ እንደ ሌሎቹ የዓለም ሀገራት በርከት ያሉ ዕለታዊ ጋዜጦች ያለመኖር መሆኑንም ጠቁመዋል::
ወይዘሮ አባይነሽ እንደሚናገሩት በነዚህ ተቋማት ላይ አንድ የኢንተርኔት ዜናን ጨምሮ ሁሉም ሽፋኖች ከስርዓተ ጾታ አንፃር ክትትል እና ግምገማ ተካሂዶባቸዋል:: ሆኖም ሥራው በተከናወነበት እ.ኤ.አ በመስከረም 29 ቀን 2020 የኢንሳይት ቲዊተር ገጽ ላይ ለዜና የተሰጠ ሽፋን እንዳልነበርና ሌሎቹ ሚዲያዎችም በአብዛኛው የፌዴራል ፖሊስን እንዲሁም የፋይናንስ ጉዳዮችን የሚያጎላ ዜና ይዘው መውጣታቸው መቃኘቱንም ያብራራሉ::
የክትትሉ ሥራ ሰባት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ እንደነበር የሚያስታውሱት ወይዘሮ አባይነሽ ፤ ፖለቲካ እና መንግሥት፣ኢኮኖሚ፣ሳይንስ እና ጤና፣ ማህበራዊና ህግ፣ወንጀል፣ ሥርዓተ ጾታና ተያያዥ ጉዳዮች እንዲሁም በታዋቂ ሰዎች ዙሪያ የሚሰሩ ታሪኮች ላይ የሚያጠነጥን እንደነበር ያብራራሉ:: እ.ኤ.አ በ2020 የግሎባል ሞኒተሪንግ በኢትዮጵያ ከሶስት ጋዜጦች፣ ከስድስት የቴሌቪዥንና አንድ የሬዲዮ ተቋማትና ከአንድ የኢንተርኔት ዜና ምንጭ 126 የዜናና ፕሮግራም ሥራዎች ክትትል እንደተደረገባቸውም ይጠቁማሉ::
ይሁንና በግሎባል ሚዲያ ሞኒተሪንግ ሥራውም ሆነ በክትትል ተግባሩ በሚዲያ ሽፋን ውስጥ ሴቶች በዜና ምንጭነትም ሆነ በሌላ መልኩ የሚቀርቡበት ሁኔታ እንዳልነበር ይገልፃሉ:: በየሚዲያዎቹ ተቋማት የሴቶች ድርሻ ምን ያህል ነበር ተብሎ በየዘርፉ ሲቃኝ በሕትመት ዜና መስኩ ያገኙት ሽፋን 18 በመቶ ብቻ መሆኑንም በምሳሌነት ያነሳሉ። በሬዲዮ በዕለቱ የሴቶች ሽፋን ምንም እንዳልነበረም ይጠቅሳሉ። በቴሌቪዥን 10 በመቶ ፣ እንዲሁም በኢንተርኔት 25 በመቶ ሽፋን አግኝተው እንደነበርም ይጠቁማሉ::
ወይዘሮ አባይነሽ እንደሚናገሩት፤ ክትትሉ በተደረገበት እ.ኤ.አ በመስከረም 29 ቀን 2020 አብዛኞቹ ሚዲያዎች ሴቶችን በተመለከተ ምንም አይነት ሽፋን አልነበረም።ለአብነት አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ በዕለቱ ሴቶችን በተመለከተ ምንም ነገር አልወጣም:: ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ላይም በተመሳሳይ ምንም ሴቶችን የተመለከተ ዘገባ አልነበረም። ይህም ጉዳዩ በሚዲያ ተቋማቱ ትኩረት እንዳልተሰጠው ያመለክታል። ክትትል እና ግምገማው ድንገት መደረጉም ይሄንኑ ለማወቅ አስችሏል::
ሆኖም ከዚህ በተቃራኒ በዕለቱ በሕትመቱ ዘርፍ በዜናው ውስጥ ሽፋን ያገኙት ወንዶች 83 በመቶ ነበሩ:: በዚሁ በዜና ጉዳይ ወንዶች በሬዲዮ መቶ ከመቶ ፤እንዲሁም በቴሌቪዥን 90 ከመቶ ሽፋን ያገኙበት ሁኔታ መኖሩን በግሎባል ሚዲያ ሞኒተሪንግ ሥራው ተረጋግጧል። በዕለቱ በሥራ ላይ ተማሰርተው የነበሩ ጋዜጠኞች ሲታይም የሴቶች ድርሻ በህትመት 22 በመቶ፣ በሬዲዮ 33 ከመቶ እንዲሁም በቴሌቪዥን 32 ከመቶ መሆኑ ታይቷል::
ሴቶችን በምንጭነት መጥቀስ፣ በፖለቲካና አስተዳደር ውስጥ ማስገባት፣ ሴቶችን ለሚመለከቱ ጉዳዮች ቦታ የመስጠት ሁኔታ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በጥናቱ ተረጋግጧል::
እንደእርሳቸው ማብራሪያ የሥርዓተ ጾታ ጉዳይ በነበረበት እንዳይቆይና በሚፈለገው ልክ እንዲለወጥ የመጀመሪያውና ዋነኛው ተግባር ማህበረሰቡ ስለ ሥርዓተ ጾታ ያለው አመለካከት ወይም ግንዛቤን መለወጥ ነው:: ይህም ስለ ሴቶች ያለውን አመለካከት ፣ የሴቶችን በቤትና በማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን ሚና የሚወስነውን ግንዛቤና አረዳድ ማስተካከልን ያጠቃልላል:: ይህ የሚስተካከል ከሆነም አሁን የሚታየውን የሴቶችን በሚዲያ እንደ ምንጭ፣ እንደ ባለሙያ፣ እንደ ሪፖርተር ሊኖራቸው የሚገባውን ድርሻ ለማሻሻል ያግዛል::
በተጨማሪም ሴቶች በሚዲያው የሚሰጣቸው ገጽታ ያላቸውና ሊኖራቸው የሚገባ እንዲሆን ያደርጋል፡ ይህን ለማምጣት ማህበረሰቡ ስለ ሴቶች ያለው አመለካከት ወሳኝ መሆኑ እንደተጠበቀ ሚዲያው ትልቁን ሚና ሊጫወት ይገባል:: ይህን በትክክል ለማግኘትም የሚዲያው ፖሊሲ የሥርዓተ ጾታ ሁኔታን ያገናዘበ መሆንና ስለተግባራዊነቱም ክትትል ሊደረግበት ያስፈልጋል:: ለዚህም የሚዲያው ባለሙያዎችና የሚዲያው ተቋማት ጥረት የግድ ይላል::
ሴቶች ሁኔታዎች ከተመቻቹላቸው ከወንዶች እኩል የማይማሩበት፣ የማያውቁበት፣ የማይሰሩበትና የማይፈጥሩበት ምንም ምክንያት የሌለ በመሆኑ ልጆችን ከአስተዳደጋቸው ጀምሮ በመቅረጽ ረገድ ትኩረት ሊደረግ ይገባል:: ልጆች ደግሞ የሚያድጉት በወላጆቻቸው ብቻ ባለመሆኑ ድርሻ ያላቸው ተቋማት ሁሉ በዚህ በኩል ብዙ ሊሰሩ ይገባል::
የማሰልጠኛ ተቋማትም የጋዜጠኝነትን ሙያ ሲያስተምሩ ተማሪዎች ሥርዓተ ጾታን በአግባቡ ተረድተው እንዲወጡ ቢያደርጓቸው ስለ ሴቶች በአግባቡ ከመዘገብ አንስቶ የሚዲያው ሥራ በሁሉም መስክ ሴቶችን አካታች እንዲሆን ለማድረግ ያስችላቸዋል:: የሚዲያ ክትትል ሥራ በተወሰኑ ጊዜያት ውስጥ እየተካሄደ ሚዲያው ምን ያህል አሰራሩን በሥርዓተ ጾታ መነጽር እያካሄደ እንደሆነ ማየትም ተገቢ ነው::
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን የካቲት 29/2014