
የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቪላድሚር ፑቲን የምዕራባውያን ማዕቀብ ጦርነት እንደማወጅ ይቆጠራል፤በዩክሬን የአየር ክልል ላይ በረራ ማገድ አስከፊ የሆነ ችግር ያመጣል ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬንና በሩሲያ ግጭት ምክንያት በምዕራባውያን አገራት የተጣሉትን ማዕቀቦች “ጦርነት ከማወጅ ጋር ተመሳሳይ ነው” ሲሉ ገልጸዋል ።
ዩክሬን ከበረራ ቀጠና ውጭ መደረግ አለባት በሚል የዩክሬን ባለስልጣናት ከፍተኛ ግፊት እያደረጉ ሲሆን ይህንንም አስመልክቶ ፕሬዚዳንት ፑቲን የበረራ ክልከላ ሙከራ በጦርነቱ ውስጥ ቀጥታ ተሳትፎ እንደሚታይ አስጠንቅቀዋል።
ከጦርነቱም ጋር ተያይዞ በሩሲያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊያውጁ ይችላሉ የሚለውን ሃሳብ ውድቅ አድርገውታል ። ፕሬዚዳንት ፑቲን ይህንን ያሉት በሞስኮ አቅራቢያ በሚገኘው የኤሮፍሎት ማሰልጠኛ ማዕከል ውስጥ ሴት የበረራ አስተናጋጆች ቡድን ባነጋገሩበት ወቅት ነው።
አስራ አንደኛ ቀኑን ባስቆጠረው የሁለቱ አገራት ግጭትን ተከትሎ ምዕራባውያን አገራት በሩስያ የሚያደርጉትን ማዕቀብ አጠናክረው ቀጥለዋል። እስካሁን ከተጣሉ ማዕቀቦች መካከል የፕሬዚዳንት ፑቲን የውጭ ሃብት ማገድን ጨምሮ የሩስያ ባንኮችን ስዊፍት ከተሰኘው ዓለም አቀፍ የክፍያ ሥርዓት ማስወጣት ይገኙበታል።
ፕሬዚዳንት ፑቲን በቅርቡ በሰጡት አስተያየት፣ በዩክሬን ያለውን ጦርነት ለማስረዳት ሞክረዋል። የሩሲያ ቋንቋ ተናጋሪ ማኅበረሰቦችን በአገሪቱ እየተደረገ ካለው “ከፍተኛ ወታደራዊነትና ናዚነት” ጥፋት ለመከላከል እንደሚፈልጉ ገልፀዋል።
የምዕራባውያን የመከላከያ ተንታኞች የሩሲያ ወታደራዊ ዘመቻ እንደተጠበቀው እየሄደ አይደለም ለሚሉት አስተያየትም ፕሬዚዳንቱ ምላሽ ሰጥተዋል “ሠራዊታችን ሁሉንም ተግባራት ይፈጽማል። ምንም ጥርጥር የለኝም። ሁሉም ነገር በእቅድ እየሄደ ነው” ብለዋል።
በጦርነቱ ላይ የሚሳተፉት በሙያቸው ወታደሮች የሆኑ ብቻ መሆናቸውን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ ምንም አይነት ተቃራኒ ዘገባዎች ቢኖሩም ዜጎች በአስገዳጅ ሁኔታ ወደ ውትድርና አለመግባታቸውን ገልጸዋል። የሩሲያው መሪ በዩክሬን ሰማይ ላይ በረራ ለመከልከል የሚደረገው ጥረት ወታደራዊ ግጭቱን አንድ እርምጃ ወደፊት እንደሚወስደውና ተሳታፊዎቹም እንደ ጠላት ተዋጊ እንደሚወሰዱ ተናግረዋል።”አሁን ያለው አመራር በአሁኑ ተግባራቸው ከቀጠሉ የዩክሬንን የወደፊት እድል አደጋ ላይ እንደሚጥሉ ሊገነዘቡ ይገባል እንደሚገባ ቢቢሲ ዘግቧል። አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 28 ቀን 2014 ዓ.ም