በዛሬው የሳምንቱ በታሪኩ አምዳች የምናነሳው ሌላ ጉዳይ የካራማራ ድል ነው። በ1969 እና 1970 አ.ም የሶማሊያው ፕሬዚዳንት የነበረው ዚያድ ባሬ ታላቋን ሶማሊያ ለመመስረት በሚል በ1969 አ.ም ምሥራቅና ደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያን ሰርጎ ገቦች እያስገባ የጀመረውን ወረራ በማጠናከር ግልጽ ወረራ እስከ ማድረግ ደረሰ። ወቅቱ በኢትዮጵያ በ1966 የፈነዳውን አብዮት ተከትሎ ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ኃይሎች ሽኩቻ የነበረበት ነው፤ ይህን እንደ መልካም አጋጣሚ በመቁጠር ነው ወረራውን ያደረገው። ይሁንና እሱም ልክ እንደ ጌቶቹ አውሮፓውያን ሽንፈትን የተከናነበበት ወሳኝ ውጊያ የተደረገው በካራማራ ላይ ነው።
የወቅቱ የኢትዮጵያ መሪ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ‹‹ትግላችን ቅጽ ፩›› መጽሐፍ እና የካራማራ ድል በተከበረባቸው ዓመታት ከተሠሩ ዘገባዎችና ከተለያዩ ድረ ገጾች መረጃዎችን አሰባስበን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በየዓመቱ የካቲት 26 እየተከበረ ያለውን የካራማራ ድል በዛሬው ሳምንቱ በታሪኩ አምዳችን እናስታውሳለን።
ሶማሊያን ለ21 ዓመታት የመራት ጀኔራል ዚያድ ባሬ ኦጋዴንን በመጠቅለል ታላቋን ሶማሊያ የመመሥረት የቆየ ራዕይ ነበረው። ጊዜ አይቶ ወቅትን ገምቶ ኢትዮጵያ በገንጣይ አስገንጣዮች ትግል የተዳከመች ሲመስለው እቅዱን ለማሳካት ጊዜው አሁን ነው ብሎም ወረራውን ፈጸመ። ይህ የዚያድ ባሬ ጦር ከሐምሌ 1969 ዓ.ም እስከ የካቲት 1970 ዓ.ም ድረስ ምሥራቃዊዋ የኢትዮጵያ ክፍል ኦጋዴን ላይ ጦር ነት ከፈተ።
ዚያድ ባሬ ያሰበውን ዳር ለማድረስ የኢትዮጵያን ጠላቶች ተጠቀመ። ያዋጣኛል ያለውን የሴራ መንገድ ሁሉ ተከተለ። ሶማሊያ በ1969 ዓ.ም በኢትዮጵያ ላይ ግልፅ ወረራ ከመፈፀሟ በፊት በህቡዕ በተደራጀ ቡድን ተደጋጋሚ ጥቃት በመሰንዘር የኢትዮጵያን የመከላከያ ኃይል ማዳከም የሴራው አካል ነበር። ጦርነቱ በግልፅ በታወጀበት በሐምሌ ወር 1969 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት ተከታታይ ሳምንታት የሶማሊያ ጦር ባልታሰበ መልኩ ጅግጅጋ፣ ሐረርና ድሬዳዋ ድረስ ዘልቆ ገባ።
በመጀመሪያ በሶቭየት ኅብረት እና በመቀጠልም በአሜሪካ ድጋፍ የነበረው የፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬ ጦር ለድል የተቃረበ መሰለ። የኋላ ኋላ የውጭ ድጋፍ እየቀነሰበት ቢመጣን የኢትዮጵያ የውስጥ ተገንጣይ ኃይሎች የውስጥ ለውስጥ ድጋፍ ስላልተለየው ጦርነቱን ከመግፋት አልተቆጠበም ነበር።
ልክ እንደ ዓድዋው ሁሉ በዚህን ጊዜም የኢትዮጵያው መሪ ኮሎኔል መንግሥቱ ለጀግናው የኢትዮጵያ ሕዝብ የክተት ጥሪ አቀረቡ። ሚያዝያ 4 ቀን 1969 ዓ.ም በብሔራዊ ቴሌቪዥን ቀርበው ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም፡- ‹‹… ታፍራና ተከብራ የኖረችው ኢትዮጵያ ተደፍራለች። ለብዙ ሺህ አመታት አስከብሮን የኖረው አኩሪ ታሪካችን በዚህ አብዮታዊ አዲስ ትውልድ ጊዜ መጉደፍ የለበትም። አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያዊት! የኢትዮጵያ ሕዝብ! ክብርህንና ነፃነትህን ለመድፈር አገርህን ለመቁረስ የተጀመረው ጣልቃ ገብነትና ወረራ ከመለዮ ለባሹ ጋር ተሰልፈህ ለመደምሰስ የምትዘጋጅበት ጊዜ አሁን ነው። ተነስ! ታጠቅ! እናሸንፋለን!›› ሲሉ የክተት ጥሪ አቀረቡ።
የኢትዮጵያ ሕዝብም በተደረገለት ጥሪ የአገሩን ዳር ድንበር ለማስከበር ቀፎው እንደ ተነካ ንብ በቁጣ ወጣ። በእዚህ ጥሪም ከ300 ሺ በላይ ሚሊሺያ በታጠቅ ጦር ሰፈር ገብቶ የሦስት ወር ስልጠና ተከታትሎ ሰራዊቱን ተቀላቀለ።
የኢትዮጵያ ጦር ወደ ፍፁማዊ ማጥቃት እና እልህ አስጨራሽ ጦርነት መግባቱን የሚያመላክቱ እርምጃዎች መታየት ጀመሩ። ከኦጋዴን ሞቃታማ ቦታዎች በአንዱ ‹‹ካራማራ›› ከሚባለው ተራራ ከምድርም ከሰማይም እሳት የሚተፉ የኢትዮጵያ ወታደር የጦር አረሮች ምድሪቱን ዘነቡባት።
ታላቋን ሶማሊያ የመመሥረት ህልም አንግቦ የነበረው የዚያድ ባሬ ጦር አይቀጡ ቅጣት ተቀጣ። ኢትዮጵያ በታሪክ እንደለመደችው አሁንም ድል አደረገች።
የካቲት 26 ቀን 1970 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጦር፣ የእናት አገር ወዶ ዘማቾች እና 16 ሺህ የሚደርሱ የኩባ አጋር ወታደሮች፣ እንዲሁም በመቶዎች የሚቆጠሩ የየመን ወታደሮች ይህን ታሪካዊ ጦር ተቀላቅለው የዚያድ ባሬን ጦር ድባቅ መትተው የኢትዮጵያን አሸናፊነት ታወጀ።
ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም የጻፉት አንዲት ገጠመኝ እዚህ ላይ እንጥቀሳት። በኩባ እና በሌሎች ወዳጅ አገራት አማካኝነት ኮሎኔል መንግሥቱ እና ዚያድ ባሬ ለውይይት ተጠርተው በየመን ይገናኛሉ። ዚያድ ባሬ እብሪተኛ ስለሆነ ኮሎኔል መንግሥቱ የእብሪት መልስ እንዳይመልሱ በወዳጆቻቸው ተመክረዋል።
የተፈራው አልቀረም በውይይቱ ላይ ዚያድ ባሬ ኮሎኔል መንግሥቱን ‹‹ጦርነት የት ታውቃለህና ነው! ጦርነት እንዴት እንደሆነ አሳይሃለሁ›› ብሎ ፎከረ። ዳሩ ግን ኮሎኔል መንግሥቱም እብሪተኛ ነበሩና (መታገስ አልቻልኩም ነው የሚሉ እርሳቸው) ምክሩን ጥሰው ‹‹ማን ጦርነት እንደሚችል እንተያያለን! እዚያው እንገናኝ!›› ብለው ፎከሩ። ውይይቱም ያለ ስምምነት ተቋጨ። እነሆ ጦርነት ማን እንደሚችል ታየ! ኢትዮጵያውያን ሁልጊዜም አሸናፊ ናቸው! የካራማራ ድል ዘንድሮ 44ኛ አመቱ ትናንት በኢትዮ ኩባ የወዳጅነት አደባባይ ተከብሯል።
አዲስ ዘመን የካቲት 27/2014