የአፍሪካ ቡድኖችን በላቀ ልዩነት በመርታት አስደናቂ አቋሙን አስመስክሯል፤ ለቀጣይ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን (ሉሲዎቹ) ተተኪ ለመሆን ከፍተኛ ተስፋ እንዲጣልበትም አድርጓል፤ ለሌሎች ታዳጊዎችም ተምሳሌት እየሆነ ነው፤ የኢትዮጵያ ሴቶች ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን።
ቡድኑ ለኮስታሪካው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ በመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ይገኛል። ከቀናት በኋላም ከጋና ብሔራዊ ቡድን ጋር አዲስ አበባ እና አክራ ላይ በሚኖረው የደርሶ መልስ ጨዋታ በዓለም ዋንጫው ከሚሳተፉ ከሁለቱ አፍሪካውያን አገራት መካከል አንዱ መሆኑን ያረጋግጣል።
ቡድኑ ለዚህ ውድድር እንዲረዳውም ከየካቲት 7 ቀን 2014ዓ.ም ጀምሮ በመሰባሰብ ዝግጅት እያደረገ መሆኑ ይታወቃል። በዓለም ዋንጫው አህጉርና አገርን ለመወከል ከጫፍ የደረሰውን ይህንን ቡድን ሊያበረታታ የሚችል የገንዘብና የትጥቅ ድጋፍ በባለሀብቶችና ተቋማት የተደረገለት መሆኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በድረገጹ አስነብቧል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ደጋፊዎች ማህበር ከቢኤፍ ፕሮሞሽን እና ኤቨንት ጋር በመተባበር ከትናንት በስቲያ በተዘጋጀው የእራት ግብዣ ላይ ማበረታቻው ለቡድኑ አባላት ተበርክቷል።
በዚህም ንብ ባንክን ጨምሮ የተለያዩ ባለሀብቶች ባደረጉት የገንዘብ ድጋፍ በጥቅሉ 267ሺ ብር ለቡድኑ ተበርክቷል። ጎፈሬ የስፖርት ትጥቅ አምራች በበኩሉ 150ሺ ብር የሚያወጣ የትጥቅ ድጋፍ ሲያደርግ፤ ሌሎች ደግሞ በቀጣይ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የቀድሞ ተጫዋቾች፣ ዳኞችና ጥሪ የተደረገላቸው አካላት ተገኝተዋል።
በእግር ኳሱ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎችም ቡድኑን ሊያነቃቃ የሚችል ንግግር አድርገዋል። በመርሃ ግብሩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት አንጋፋው የቀድሞ የብሔራዊ ቡድን ተጫዋች እና አሰልጣኝ ንጉሴ ገብሬ፤ ብሔራዊ ቡድኑ ወደ ኮስታሪካ እንዲያመራ መልካም ምኞታቸውን ገልጸው አበረታተዋል። የዕለቱ የክብር እንግዳ አሰልጣኝ ንጉሴ ገብሬ የእግር ኳስ ሰው ለቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል እና ለአምበሏ ናርዶስ ጌትነት የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማንም አስረክበዋል።
ሌላኛው በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን በበኩላቸው፤ ‹‹በመጀመሪያ ቡድኑ በቢሾፍቱ ተሰባስቦ የማጣሪያ ዝግጅቱን ሲጀምር በቦታው በተገኘሁበት ወቅት የተነጋገርነው ኮስታሪካ እንገናኝ የሚል ነበር። እነሱም አላሳፈሩንም 180 ደቂቃ ብቻ ቀርቷቸዋል›› ብለዋል።
ቡድኑ ለዚህ ማጣሪያ ዝግጅት እንዲሆን እና ለተሳትፎ ያህል ወደ ሴካፋ እንዲያመሩ ቢደረግም፤ በፍፃሜው ጨዋታ ለብዙዎች ትምህርት በሚሆን መልኩ አሸንፈው ዋንጫውን ይዘው ተመልሰዋል ያሉት አቶ ባህሩ፣ አሁንም የጋናን ጨዋታ አሸንፈው ወደ ኮስታሪካ እንደሚጓዙ እምነቱ እንዳላቸው ተናግረዋል።
ፌዴሬሽኑ ባለው ውስን በጀት ለቡድኑ የሚያስፈልገውን እያሟላ እንደሚገኝም ጠቅሰው፣ ቡድኑ የፌዴሬሽኑ ብቻ ባለመሆኑ ሁሉም እገዛ ማድረግ እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል። የማበረታቻ መርሃ ግብሩን ላዘጋጁ አካላትም ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ቡድኑ ለተደረገለት ድጋፍና ማበረታቻም በአምበሏና አሰልጣኙ በኩል ምስጋናቸውን አቅርበዋል። የኢትዮጵያ ከ20ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን አምበል ናርዶስ ጌትነት፤ ቡድኑ ወደ ኮስታሪካ ለሚደረገው ጉዞ ትኬት ለመቁረጥ እንደተዘጋጀ በልበ ሙሉነት ገልጻለች።
ቡድኑን አሁን ላለበት ደረጃ ያደረሱት ዋና አሰልጣኙ ፍሬው ኃይለገብርኤል በበኩላቸው፤ ከቁሳዊ ነገሮች ባለፈ የተለያዩ አካላት ወደ ቡድኑ ተጠግተው ማበረታቻ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በንግግራቸውም ቡድኑ የሴካፋ ዋንጫን ሲወስድ የጋምቤላ ክልል ለሁለት የቡድኑ ተጫዋቾች ላደረገው የመሬት ሽልማት ሊበረታታ የሚገባው መሆኑን እና ሌሎች ክልሎችም ተጫዋቾቹ በያሉበት መሰል ተግባራትን ቢያደርጉ መልካም እንደሚሆን ጠቁመዋል።
ኢንተርናሽናል አርቢትር ሊዲያ ታፈሰን ጨምሮ፤ አሰልጣኞችና ታዋቂ የእግር ኳስ ደጋፊዎችም ቡድኑን የሚያበረታታና የሚያነቃቃ ንግግር ማድረጋቸውን ከፌዴሬሽኑ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን የካቲት 26 /2014