የኢትዮጵያ ሕዝብ 80 ከመቶ የሚሆነው አርሶ አደር እንደመሆኑ የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ መነሻ መሠረቱ ከግብርናው ነው።
የዛሬ እንግዳችንም ከአርሶ አደር የተገኘ እንደመሆኑ የግብርናውን ዘርፍ ጨምሮ የተለያዩ የጉልበት ሥራዎችን በመሥራት እራሱን ለማሻሻል ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። ሰፊ ቤተሰብ ውስጥ የተገኘው እንግዳችን ለቤተሰቡ 11ኛ ልጅ ነው።
አርሶ አደር ቤተሰቦቹም ከአስር የሚልቁ ልጆቻቸውን መሠረታዊ ፍላጎት አሟልቶ ለማሳደግና ለማስተማር ኑሮ ፈታኝ እንደሆነባቸው ያስታውሳል።
‹‹ሰፊ ቁጥር ካላቸው እህትና ወንድሞቼ መካከል በመገኘቴ ቤተሰቦቼ ትኩረት አልሰጡኝም›› የሚለው የዛሬው እንግዳችን በግብርና ሥራ ለሚተዳደሩት ቤተሰቦች 11ኛ ልጅ የሆነው አቶ ነጋሽ ላምቢሶ ነው። አቶ ነጋሽ ተወልዶ ያደገው በሲዳማ ክልል ዳራ ወረዳ ጌሎዋጮ ቀበሌ ሲሆን በአሁን ወቅት ደግሞ በቀባዶ ከተማ የአንድ ቀን ጫጩቶችን በማሳደግ በዶሮ እና በከብት እርባታ ሥራ የተሠማራ ታታሪ ነው።
ወደ እርባታ ሥራ ከመግባቱ አስቀድሞ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች በመሠማራት ከቤተሰብ ማግኘት ያልቻለውን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፍላጎቶች ለማሟላት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ይናገራል።
በተለይም እንጨት በስፋት ነግዷል። በጉልበቴ ሠርቼ መኖር እችላለሁ በማለት የቤተሰቡን ሸክም ለማቅለል ያገኘውን ሁሉ ሲሠራ እንደነበርና በተለይም በእንጨት ንግድ ብዙ የቆየው አቶ ነጋሽ፤ በንግዱ ዘርፍ አጥጋቢ ውጤት አላገኘም። ስለዚህ የሥራ ዘርፍ መቀየር እንዳለበት ወስኖ ፊቱን ወደ ዶሮ እርባታ ሲያዞር ደግሞ መነሻ ካፒታል አልነበረውም ።
ይሁን እንጂ ካሰበው ሥራ ላለመቅረት አማራጭ ወስዷል። አማራጩም ብድር መውሰድ ነውና በአቅራቢያው ከሚገኝ ኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ 30,000 ብር ብድር በመውሰድ 300 ጫጩቶችን ገዝቶ ዋጮ የአንድ ቀን ጫጩት ማሳደጊያ በሚል አቋቋመ። የስምንተኛ ክፍል ትምህርቱን አቋርጦ ወደ ዶሮ እርባታ የገባው አቶ ነጋሽ፤ የቤተሰቡ ቁጥር ከአርሶ አደር ወላጆቹ ገቢ ጋር የተጣጣመ አለመሆኑንና የቤተሰቡ ቁጥር መብዛቱን በምክንያትነት ያነሳል። በወቅቱም የትምህርትን ጠቀሜታ ያስረዳው እንዲሁም በትምህርት እንዲገፋ የሚያበረታታው ሰው ከጎኑ እንዳልነበር ይናገራል።
ይሁንና በሥራ መለወጥና ራስን ማሸነፍ እንደሚቻል በማመን በመጀመሪያው ዙር የገዛቸውን 300 ጫጩቶች በሁለተኛው ዙር 500 በሶስተኛው ዙር 1000 በማድረግ የጫጩቶቹን ቁጥር እየጨመረ የዶሮ እርባታ ሥራውን በስፋት አስቀጠለ።
እያስፋፋ የያዘው የዶሮ እርባታም በአሁን ወቅት በአንድ ጊዜ ብቻ እስከ ሁለት ሺ ጫጩቶችን በመረከብ የሥጋና የእንቁላል ጣይ ዶሮዎችንም ጎን ለጎን በማርባት ውጤታማ ሥራን እየሠራ ይገኛል።
‹‹በዶሮ እርባታ ሥራው የክልሉ ግብርና ቢሮ ይሰጥ የነበረው ሥልጠና ውጤታማ እንዲሆን አድርጎኛል›› የሚለው አቶ ነጋሽ፤ በተለይም ወላይታ ሶዶ፤ ባንሳ አርባጎና፣ ሀዋሳና በሌሎችም ቦታዎችም እንዲሁ በሚሰጠው ሥልጠና ተጋባዥ እየሆነ መሰልጠን መቻሉ እንደጠቀመው ይናገራል።
ከስልጠናው በተጨማሪም በግሉ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ የዶሮዎቹን ንጽሕና ከመጠበቅ ጀምሮ ምግባቸውንም በአግባቡ በማዘጋጀት ለውጤት እንዲበቁ አድርጓል። ጫጩቶቹ ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚፈልጉ ከመሆኑም በላይ አደጋ የማይችሉ መሆናቸው ብዙ ዋጋ እንዳስከፈለው የሚናገረው አቶ ነጋሽ፤ አንዳንድ ጊዜ ጫጩቶቹ ሲገቡ በአንድ ጊዜ ከ100 እስከ 300 ጫጩቶች የሚሞቱበት ወቅት እንደነበርና ሥራው ተስፋ አስቆራጭ የነበረ መሆኑን ያስታውሳል።
ይሁንና ሥራውን መልመድ በራሱ አንድ ውጤት ነው ፤ ዛሬ ቢታጣ ነገ ይገኛል በማለት በትዕግስት መቆየቱንም ይናገራል። ሥራው ምንም እንኳን ተስፋ አስቆራጭ የነበረ ቢሆንም አዋጭ መሆኑን በመረዳት ተስፋ ባለመቁረጥ ውስጥ በመሆን ሥራውን ለስምንት ዓመታት አስቀጥሏል።
ሥራውን ለመጀመር በቅድሚያ የተበደረውን 30,000 ብር በመክፈል ተጨማሪ 100,000 ብር በመበደር ከዶሮ እርባታው በተጨማሪ ሌሎች ሥራዎችን ለመሥራት ሲያቅድም አባላትን በመጨመር የከብት እርባታ ሥራንም ተቀላቅሏል። ሥራውን በስፋት ያስጀመረው አቶ ነጋሽ፤ ‹‹ከአንድ ብርቱ ሁለት መድኃኒቱ›› እንዲሉ የወተት ላሞችን ጨምሮ ፍየልና በጎችን ከአባላቶቹ ጋር ማርባት ጀመረ ።
በግሉ የጀመረውን ዋጮ የአንድ ቀን ጫጩት ማሳደጊያን ወደ ማኅበር በመቀየር ከዶሮ እርባታው በተጨማሪ ከብት እርባታና የግብርናን ዘርፍንም ተቀላቀለ በዚህ ጊዜ ታድያ ስድስት አባላትን በመጨመር ዋጮ የአንድ ቀን ጫጩት ማሳደጊያ ማኅበርን አቋቋመ።
ማኅበሩም እንቁላል ጣይ ዶሮዎችን በመንከባከብ በየጊዜው እንቁላል ለገበያ የሚያቀርብ ሲሆን፤ የሥጋ ዶሮዎችን ግን በዓመት ሶስት ጊዜ ማለትም በዘመን መለወጫ፣ በገና እና በፋሲካ በዓላት አደልበው ለገበያ ያቀርባሉ። መኖን በተመለከተም ለአንድ ቀን ጫጩትና ከ45 እስከ 48 ቀን ላሉት የሚሆነውን መኖ በአቅራቢያው ከሚገኘው ወላይታ ሶዶ የሚያስመጣ ሲሆን ለእንቁላል ጣይና ለሥጋ ዶሮዎች የሚሆነውን መኖም ደግሞ ከገበያ ያቀርባል።
ለዶሮ እርባታ ቀዳሚና ወሳኙ መኖ እንደመሆኑ በአሁን ወቅት መኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካን ለማቋቋም በዝግጅት ላይ መሆናቸውን የሚናገረው አቶ ነጋሽ፤ ማኅበሩ ያለውን የሥራ እንቅስቃሴ በመረዳት የዶሮ መኖ ማቀነባበሪያ ማሽን ማቆሚያ የሚሆን 600 ካሬ ሜትር ቦታ ከወረዳው አግኝተዋል። በተረከቡት ቦታ ላይም ማሽኑን ለማቆም መጋዘን ሠርተዋል።
በተረከቡት ቦታ ላይ የሚያመርቱት መኖ ከራሳቸው አልፎ ለሌሎችም ማኅበራትና ወረዳዎች ለማቅረብ ዕቅድ ይዘው እየሠሩ ይገኛሉ። ጫጩቶቹ ተገኝተው መኖ የሚጠፋበት ጊዜ መኖሩን ያስታወሱት አቶ ነጋሽ፤ በተለይም የመኖ እጥረት ብዙ ጊዜ ያጋጥማቸው እንደነበር ይናገራሉ። ስለሆነም ለዚህ ችግር የመኖ ማቀነባበሪያ ማሽን መዘጋጀቱ ዋነኛ መፍትሔ በመሆኑ በመኖ እጥረት የሚሞቱ ጫጩቶች ቁጥር በመቀነስ ከኪሳራ መዳን የሚያስችለን ነው ይላሉ።
ዶሮ በማርባት ሂደት የሚገጥሙ በርካታ ችግሮች ቢኖሩም ችግሩን ለመፍታትም የተለያዩ ዘዴዎችን የሚጠቀሙ ስለመሆኑ የሚያነሱት አቶ ነጋሽ፤ ለአብነትም ጫጩቶችን ለእርባታ የሚያስገቡት ከመስከረም እስከ ሚያዝያ ባሉት ወራት ውስጥ ሲሆን ክረምቱ በሚገባበት ሁለትና ሶስት ወራት ግን ዶሮዎቹ ክረምቱ የማይመቻቸው በመሆኑ ጫጩቶቹ ማስገባት ያቆማሉ።
ታድያ በዚህ ወቅት ተያያዥ የሆነውን የከብት እርባታ ሥራቸውን በሥፋት ይሠራሉ። አቶ ነጋሽን ጨምሮ ስድስት አባላትን ከያዘው ማኅበር በተጨማሪ ወርሐዊ ተከፋይ ሆነው ለሚሠሩ አራት ሰዎችም የሥራ ዕድል መፍጠር ችለዋል።
አባላቱ የተሰማሩበትን የሥራ የዶሮና የከብት እርባታ አጠናክረው መቀጠል በመቻላቸው ውጤታማ ሲሆኑ በተለይም ቀደም ሲል ትምህርት ጨርሰው ሥራ አጥ የሆኑት አባላት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ መሆን በመቻላቸው ደስተኞች እና ውጤታማ ከመሆናቸውም ባለፈ ከፍተኛ ተነሳሽነት ያላቸው መሆኑን አቶ ነጋሽ ያስረዳሉ ።
ተነሳሽነታቸውን አስመልክተውም በቀጣይ የተለያዩ ተጨማሪ ሥራዎችን ለመሥራት በየጊዜው አዳዲስ ሀሳቦችን እንደሚለዋወጡ ነው ያጫወቱን ። በአሁን ወቅትም ዶሮዎች፣ የወተት ላሞችና ፍየሎችን እንዲሁም ለመኖ ማቀነባባሪያ የሰሩትን መጋዘንና ማሽኑን ጨምሮ አንድ ሚሊዮን ካፒታል ማስመዝገብ ችለዋል።
የወተት ላሞቹ በቀን እስከ 40 ሊትር ማግኘት የሚችሉ እንደሆነ ያነሱት አቶ ነጋሽ፤ ከሁለትና ከሶስት በላይ ላሞች በተመሳሳይ ጊዜ ከወለዱ ደግሞ እስከ 80 ሊትር ወተት ማግኘት እንደሚችሉና ለገበያ እንደሚያቀርቡ ይናገራሉ። የገበያው ተደራሽነታቸውም ከይርጋለም አካባቢ በተጨማሪ ዲላ ለሚገኙ ሆቴሎችና ለሻይ ቤቶች ያቀርባሉ።
ፍየሎችንም በማደለብ ለበዓላት ወደ ገበያ በማውጣት አንድ ፍየል ከ4000 እስከ 4500 ብር ድረስ በመሸጥ ተጠቃሚነታቸውን እያረጋገጡ ይገኛሉ። ከዶሮና ከከብት እርባታው በተጨማሪ በግብርናው ዘርፍም የተሰማሩ ሲሆን ከከብቶችና ከፍየሎች የሚወገደውን ተረፈ ምርት ለእርሻ ሥራ በማዋል ይጠቀማሉ። ምንም አይነት ተረፈ ምርት የማይወድቅ መሆኑን ያነሱት አቶ ነጋሽ፤ በተለይም የዶሮ ኩስ ለበርበሬ እርሻ ጥቅም ያለው ነው ይላሉ።
ተረፈ ምርቱ እንሰሳትን ጨምሮ ለእርሻ ሥራ እያገለገለ ያለና በግብርናው ዘርፍም ውጤት እያስመዘገቡ ሲሆን፤ ለአብነትም በዘንድሮው ዓመት ብቻ ማኅበሩ 20 ኩንታል በቆሎ ማግኘት ችሏል።
ማኅበሩ የእርሻ ሥራውን የሚከውንበት መሬት ከግለሰቦች ላይ በኮንትራት ወስዶ ውጤታማ የግብርና ሥራ በማከናወናቸው በርካቶች መሬታቸውን በኮንትራት ለመስጠት ፈቃዳቸውን ይሰጣሉ ።
በመሆኑም የግብርና ሥራቸውን በማስፋፋት ላይ ይገኛሉ። ተያያዥነት ባለው የግብርና እንዲሁም የእርባታ ሥራን ጎን ለጎን በማስኬድ ውጤታማ እየሆነ የመጣው ማኅበር በቀጣይም ሰፋፊ ዕቅዶች ያሉት ሲሆን፤ በተለይም የዶሮና የከብት እርባታውን በስፋት ለመሥራት ዕቅድ ይዘዋል።
ሥራውን ሲጀምሩ ከግለሰብ በኪራይ የያዙትን የሥራ ቦታ በአሁን ወቅት ማኅበሩ የራሱ ያደረገው ቢሆንም ሥራውን በሥፋት ለማስኬድ ተጨማሪ ሰፊ ቦታ እያፈላለጉ ይገኛሉ።
በግል ጥረቱ የጀመረውን የዶሮ እርባታ ሥራ በማስፋፋት ተያያዥ የሆኑትን የከብት እርባታና የግብርና ሥራን ጨምሮ የግል ኢንቨስትመንቱን ወደ ማኅበር በማሳደግ ተጠቃሚነቱን ያሳደገው አቶ ነጋሽ ፤ ሰዎች የጀመሩትን ነገር ዳር ማድረስ እንዳለባቸውና ተስፋ መቁረጥ የሌለባቸው ስለመሆኑ ሲናገር እሱ በሥራ ውስጥ ያጋጠሙትን ውጣ ውረዶች በማስታወስ ነው።
አብዛኛው ሰው የሚያለፋና የሚያደክም ሥራን መሥራት የማይፈልግ መሆኑን በማንሳት ከልፋትና ከብዙ ድካም በኋላ የሚገኘው ውጤት ያማረ በመሆኑ ቅድሚያ መልፋት አስፈላጊ ነው ይላል።
ሥራውን በጀመረ ጊዜ የመጀመሪያዎቹ 300 ጫጩቶች ብዙ ዋጋ አስከፍለውት እንደነበርና በጥረት ግን ያሰበበት መድረስ እንደቻለ በማስታወስ ሰዎች በጥረትና በተነሳሽነት መሥራት ከቻሉ ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ ነው የገለጸው ።
ያላቸውን ተሞክሮ ለሌሎች በማጋራት እንዲሁም በከፍተኛ የሥራ ተነሳሽነታቸው ምክንያት ከተለያዩ መንግሥታዊ ከሆኑ አካላት ሰባት የሚደርሱ የዕውቅና ሰርተፊኬት ያገኘው አቶ ነጋሽ፤ ከወረዳቸው የገንዘብ ሽልማትም አግኝቷል።
በመጨረሻም አቅማቸው በፈቀደ መጠን የጀመሯቸውን የግብርና እንዲሁም የከብትና የዶሮ እርባታ ዘርፎች አጠናክሮ በማስቀጠል ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር አስበው እየሠሩ መሆናቸውን ይገልጻሉ።
ከወረዳ ባገኙት ቦታ ላይ በማሽን ተከላም ይሁን በሌላ ሊያግዛቸውና ሊረዳቸው የሚችል አካል ካለ ቢያግዘን እነሱም ተጠቅመው ማኅበረሰቡ ብሎም መንግሥትም ተጠቃሚ መሆን እንደሚችል ያለውን እምነት በመግለጽ ሀሳቡን ቋጭቷል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን የካቲት 26 /2014