በኢትዮጵያ በመጀመሪያው የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት በዘመቻ ከ 5 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች መከተባቸውን ከጤና ሚኒስቴር የተገኙ መረጃዎች ያሳያሉ።
ከዛ በፊት ደግሞ ቁጥሩ ከዚሁ ጋር የሚመጣጠን የኅብረተሰብ ክፍል ክትባቱን መውሰዱንና እስካሁን ባለው ሂደት ባጠቃላይ 10 ሚሊዮን ዜጎች ክትባቱን ማግኘታቸውን መረጃዎቹ ይጠቁማሉ። ከሰሞኑ ደግሞ ከየካቲት 7 ቀን 2014 ጀምሮ ሁለተኛው ዙር የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ዘመቻ በአገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ ይገኛል።
በዚህ የክትባት ዘመቻም የጤና ሚኒስቴር 20 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎችን በክትባት ተደራሽ ለማድረግ አቅዶ እየሠራ ነው። 30 ሚሊዮን የሚጠጉ የክትባት ዶዞችንም በእጁ ይዟል ።
ከዚህ አንፃር ፍላጎቱ ታይቶ በዚህ ዘመቻ ከተያዘው እቅድ በላይ ክትባቱ የሚሰጥበት እድል እንዳለም ተነግሯል።
በዘመቻው እድሜያቸው ከ12 ዓመት በላይ የሆኑ፣ ከዚህ ቀደም ክትባቱን ያልወሰዱ፣ የመጀመሪያውን ክትባት ወስደው ሁለተኛውን በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ፣ ከዚህ በፊት ሙሉ የኮቪድ ክትባት ወስደው ስድስት ወር የሞላቸውና አሁን ላይ የማጠናከሪያ ክትባት /booster dose/ መውሰድ የሚፈለጉ ክትባቱን እየወሰዱ ይገኛሉ።
በጤና ሚኒስቴር የብሔራዊ ክትባት ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ዮሐንስ ላቀው እንደሚናገሩት የሁለተኛው ዙር የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ዘመቻ ከየካቲት 7 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በአብዛኛዎቹ የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ በተሳካ መልኩ እየተከናወነ ነው።
እስካሁን ባለው ሂደትም ወደ 13.3 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች ክትባቱን ወስደዋል። 6.7 ሚሊዮን የክትባት ዶዝ ደግሞ ለተቀረው የኅብረተሰብ ክፍል እየተሰጠ ይገኛል። እንደ አስተባባሪው ገለፃ በተለያዩ ምክንያቶች ዘመቻው ሙሉ በሙሉ ያልተጠናቀቀባቸው አካባቢዎች አሉ።
ይሁንና እነዚህን አካባቢዎች በክትባት ዘመቻው ውስጥ የማስገባት ሥራዎች ተከናውነው በተለይ በአማራ ክልል የደቡብና ሰሜን ጎንደር፣ ጎጃምና አዊ ብሔረሰብ እንዲሁም ሰሜን ሸዋ የክትባት ዘመቻውን እንዲጀምሩ ተደርጓል።
በተመሳሳይ በተባለው ቀን ያልጀመሩ ሌሎች አካባቢዎችም የክትባት ዘመቻውን እያከናወኑ ይገኛሉ። በአፋር ክልልም ከጦርነቱ ነፃ በሆኑ አካባቢዎች ላይ ክትባቱ የተሰጠ ሲሆን በቀጣይ አስቻይ ሁኔታዎች ሲኖሩ በጦርነት ቀጠና በቆዩ አካባቢዎች ክትባቱ የሚሰጥ ይሆናል።
ክልሎች አስቻይ ሁኔታዎችን እያዩ የክትባት ዘመቻውን እያከናወኑ የሚገኙ ሲሆን በዚሁ መሠረት ክትባቱ በጥሩ አፈፃፀም ሂደት ላይ ይገኛል። ከ 20 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎችን በክትባት ተደራሽ ለማድረግም በጤና ሚኒስቴር በኩል እቅድ ተይዟል።
እስካሁን ባለው ሂደትም 13.3 ሚሊዮን ያህል ዜጎች ተከትበዋል ። ይሁንና አስቻይ ሁኔታዎችን በማየት ከዚህም በላይ ኅብረተሰቡን በክትባት ተደራሽ ለማድረግ ሥራዎች እየተሠሩ ነው። አገሪቱ ሰፊ ከመሆኗ አኳያና ሌሎች አገራዊ ሁኔታዎችም በመኖራቸው በጤና ሚኒስቴር በኩል ይህንኑ ያገናዘበ እቅድ ወጥቶ የክትባት ዘመቻው አስቻይ ሁኔታዎችን በማየት እየተከናወነ ይገኛል። በቅርቡም የክትባት ዘመቻው ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
አስተባባሪው እንደሚሉት በዚህ የክትባት ዘመቻ በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ በፀጥታ ችግር ምክንያት ክትባቱን ለመስጠት ያልተቻለበት ሁኔታ አጋጥሟል። ለአብነትም የአፋር ክልል አንዳንድ አካባቢዎችን፣ አርሲ ነገሌ፣ ወለጋና የሶማሌ ክልልን መጠቀስ ይቻላል።
በተመሳሳይ በቤኒሻንጉል ክልልም ክትባቱን ለማሰራጨት ችግሮች አጋጥመዋል። ይህም ከጤና ሚኒስቴር ቁጥጥር ውጪ በመሆኑ የክትባት ዘመቻውን አዘግይቶታል። የክትባት ዘመቻው በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች በተለያዩ ምክንያቶች ወጥ በሆነ መልኩ ሊከናወን አይችልም።
አገሪቱ ያለችበትን የፀጥታ ሁኔታም ከግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል። ከክትባቱ ጋር በተያያዘም በርካታ አሉባልታዎች ሲናፈሱ ቆይተዋል።
ሆኖም እነዚህ ሁኔታዎችን ሁሉ አልፎ አጠቃላይ የክትባት ዘመቻው ትልቅ ውጤት አስመዝግቧል። በዚህ የክትባት ዘመቻ 20 ሚሊዮን የክትባት ዶዞችን ለመስጠት የተያዘው እቅድ እንደአገር ለመከተብ ያለውን አቅም የተፈተሸበት በመሆኑ ጠቃሚ ነገር ተገኝቶበታል።
የተከተቡ ሰዎችንም በበሽታው እንዳይያዙ መታደግ ተችሏል። ኢኮኖሚውን ለመክፈትና የኮቪድ ተፅዕኖንም ለመቀነስ ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል።
ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ጉባኤዎች በአዲስ አበባ እንዲካሄዱም አስችሏል፤ በቀጣይም ያስችላል። በሌላ በኩል ደግሞ የኅብረተሰቡን የአስተሳሰብ ልክ በተለይ ደግሞ ከክትባቱ ጋር በተያያዘ የሚናፈሱ አሉባልታዎች ለመስበር የተሠሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችም ለዘመቻው መሳካት ትልቅ አስተዋፅኦ አድርገዋል።
በቀጣይም ለሚሠሩ ሥራዎችና ለሚደረጉ ተመሳሳይ የክትባት ዘመቻዎች ለማከናወን ትልቅ እገዛ አድርጓል።
አስተባባሪው እንደሚሉት ከሌሎች አገራት ጋር ሲወዳደር የኢትዮጵያ የኮቪድ ክትባት አፈፃፀም ዝቅተኛ ነው። በኅብረተሰቡ ውስጥ ያሉ የተዛቡ መረጃዎች እንዳሉ ሆነው ክትባቱን ለመውሰድ አነስተኛ ፍላጎት ያላቸው አካባቢዎችም አሉ።
ከዚህ አንፃር ጤና ሚኒስቴር በርካታ የግንዛቤ ማስጨበጫዎችን እየሠራ ቢሆንም እነዚህ ሁኔታዎች ምክንያቶች ሆነው ሰዎች እንዳይከተቡ እንዳያደርጓቸው ኅብረተሰቡ ክትባትን በተመለከተ ትክክለኛ መረጃዎችን ከጤና ሚኒስቴርና ከሚመለከታቸው አካላት በመወሰድ ክትባቱን መከተብ ይኖርባቸዋል።
በተለይ ደግሞ ኅብረተሰቡ በከተሞች አካባቢ በማኅበራዊ ሚዲዎች ክትባቱን አስመልክቶ ከሚናፈሱ አሉባልታዎችና የተዛቡ መረጃዎች ራሱን ማራቅ ይጠበቅበታል።
የግንዛቤ ማስጨበጫውን ይበልጥ ወደ ኅብረተሰቡ ለማስረፅም አሁንም ጤና ሚኒስቴር አጠንክሮ ይሠራል። ዓለም ከዚህ በሽታ ራሷን እየጠበቀች ያለችው በክትባት ነው። ሌላ መውጫ መንገድም የለም።
ከዚህ አኳያ የተለመዱት የኮቪድ-19 መከላከያ መንገዶች እንዳሉ ሆነው እስካሁን ክትባቱን ያልወሰዱ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተቀሩት የክትባት ዘመቻ ጊዜያት በአቅራቢያቸው ወደሚገኙ ጤና ጣቢያዎችና ጊዜያዊ የክትባት መስጫ ጣቢያዎች በመሄድ ክትባቱን እንዲወስዱ ይመከራሉ።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን የካቲት 26 /2014