በተለያዩ የዓለማችን ከተሞች በየሳምንቱ እየተካሄዱ በሚገኙ የዓለም የቤት ውስጥ የዙር ውድድሮች ኢትዮጵያውያን ከዋክብት አትሌቶች እርስበርስ የሚያደርጉት አስደናቂ ፉክክር ቀጥሏል። በዓለም አትሌቲክስ የወርቅ ደረጃ ከተሰጣቸው ሰባት የቤት ውስጥ ውድድሮች የመጨረሻ በሆነውና በስፔን ማድሪድ በተካሄደው ፉክክርም፤ ኢትዮጵያውያኑ እጅግ አስደናቂ አቅማቸውን ለዓለም አሳይተዋል። ኢትዮጵያውያን ስኬታማ በሆኑበት በዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና እርስ በእርስ ትንቅንቅ ታይቷል።
ከሦስት ሳምንት በፊት በፈረንሳይ ከተማ ሌቪን የነበረው ፉክክር የስፖርት ቤተሰቡን ከረጅም ጊዜ በኋላ ያስደሰተ ሲሆን፤ ከትናንት በስቲያ በስፔኗ ከተማ ማድሪድ የታየውም በተመሳሳይ አጓጊና ልብ አንጠልጣይ ሁነቶች የታዩበት ነው። በተለይ የኦሊምፒክ ቻምፒዮናውን ከውድድሩ አሸናፊ ጋር ያገናኘው የወንዶች 3ሺ ሜትር ፉክክር እስከ ርቀቱ የመጨረሻዋ መስመር የዘለቀ ነበር። በቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ የ10ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤቱ ሰለሞን ባረጋ በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት ስኬቱን በቤት ውስጥ ቻምፒዮናው ይቀጥላል ተብሎ ቢጠበቅም ከሳምንታት በፊት በተደረገው ውድድር በአገሩ ልጅ ለሜቻ ግርማ መቀደሙ ይታወቃል። በዚህ ውድድር ላይ አቅሙን አሰባስቦ የገባው ሰለሞን ከስፔናውያን አትሌቶች ፉክክር ይልቅ የአገሩ ልጅ ፈተና ሆኖበታል።
የሩጫው 1ሺ ሜትር 2:31.67 በሆነ ሰዓት ሲሸፈን፤ 2ሺ ሜትሩ ደግሞ 5:05.32 በሆነ ሰዓት ተገባዷል። በመጨረሻው ዙርም የ22 ዓመቱ አትሌት ሰለሞን ሌላኛውን ወጣት አትሌት ለሜቻን አስከትሎ ወደ ማሸነፊያዋ መስመር ገሰገሰ። ሁለቱ አትሌቶች አንገት ለአንገት በተያያዙበት ፉክክርም እጅግ ተቀራራቢ በሆነ አጨራረስ ሰለሞን ባረጋ ሊያሸንፍ ችሏል። የገባበት ሰዓትም 7:34.03 ሆኖ ሲመዘገብለት፤ ሁለተኛ የሆነው ለሜቻ ደግሞ በስድስት ማይክሮ ሰከንዶች መዘግየቱ ተረጋግጧል።
ድሉን ተከትሎም ሰለሞን ‹‹ሁለት ጊዜ ሁለተኛ ሆኜ ካጠናቀቅኩ በኋላ በዚህኛው ውድድር ከ150ሜትር ፈጥኜ ለመውጣት አቅጄ ነበር ወደ ውድድር የገባሁት። ነገር ግን በውድድሩ ስፍራ የነበረው የአየር ሁኔታ እንዳሰብኩት በፍጥነት የሚያስሮጠኝ አልሆነም። ከኦሊምፒክ በኋላ ቀላል ልምምድ ስሠራ ከቆየሁ በኋላ ወደ ከባድ ልምምድ የገባሁት በዚህ ወር ነው፤ በመጨረሻም ቻምፒዮን በመሆን እቅዴን ለማሳካት ችያለሁ›› ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል። አትሌቱ በቤልግሬዱ የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና ኢትዮጵያን የሚወክለው ብሔራዊ ቡድን አባል ከሆነ በ3ሺ ሜትር አሊያም በ1ሺ500 ሜትር እንደሚሳተፍም አያይዞ ጥቆማውን ሰጥቷል።
ሌላኛው ተጠባቂ ውድድር ደግሞ የሴቶች 1ሺ500 ሜትር ሲሆን፤ ጉዳፍ ጸጋዬ ተከታታይ ድሏን በማስመዝገብ ቀጥላለች። ከአንድ እስከ ሦስት ያለውን ደረጃ ኢትዮጵያውያን በተቆጣጠሩት በዚህ ውድድር ጥሩ የሚባል ፉክክር ታይቶበታል። የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ 5ሺ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ ባለቤቷ ጉዳፍ ጸጋዬ ከሳምንታት በፊት ሌቪን ላይ በአንድ ማይል ውድድር ሌሎች ኢትዮጵያውያን አትሌቶችን በማስከተል አሸናፊ በመሆን ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው። አትሌቷ ሌላኛውን ድል ስትቀዳጅ ርቀቱን 3:57.38 በሆነ ሰዓት ነበር የሸፈነችው። ሁለተኛ ደረጃን የያዘችው አትሌት ሂሩት መሸሻ 4:02.22 በሆነ ሰዓት ስትገባ፤ ሦስተኛዋ አትሌት ፍሬወይኒ ኃይሉ ደግሞ 4:03.38 የሆነ ሰዓት አስመዝግባለች።
የዓለም አትሌቲስ ከሚያካሂዳቸው ዓመታዊ ውድድሮች መካከል አንዱ የሆነው የዓለም የቤት ውስጥ የዙር ቻምፒዮና ለሦስት ወራት ያህል በተለያዩ የዓለም አገራት በተከታታይ ይካሄዳል። የወርቅ፣ የብር እና የነሐስ ደረጃ የተሰጣቸው 36 የሚሆኑ የቻይና፣ የአሜሪካ እና የአውሮፓ ከተሞችም ውድድሩን እየተቀባበሉ ሲያካሂዱ ቆይተው ከአምስት ውድድሮች በኋላ የሚጠናቀቅ ይሆናል። በውድድሩ የተሻለ ነጥቦችን መሰብሰብም በተያዘው ወር አጋማሽ የሰርቢያ ዋና ከተማ በሆነችው ቤልግሬድ በሚካሄደው የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና አገርን ወክሎ ተሳታፊ ለመሆን ይጠቅማል። በዚህ ውድድር በርካታ ዝነኛና የዓለም እንቁ አትሌቶች የሚሳተፉ ሲሆን፤ ኢትዮጵያውያኑ የአትሌቲክስ ስፖርት ከዋክብትም በዚህ ውድድር በተለይ ይጠበቃሉ። የወርቅ ደረጃ በተሰጣቸው ሰባት ውድድሮች ውስጥ ሲሳተፉ ቆይተዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን የካቲት 25/2014