እሌኒን እየጠበቅሁ ፒያሳ ቁጭ ብያለሁ፤ እንደ ዛሬ ሰው ለማግኘት ተስገብግቤ አላውቅም። ጓደኛዬ ቶማስ የመጀመሪያ ቀጠሮ ላይ ጥሩ ሆኖ መገኘት ዋጋ አለው ስላለኝ ጥሩ ሆኜ ለመታየት ያላደረኩት የለም። ጸጉሬን ከተማው ውስጥ አለ የተባለ ጸጉር ቤት ነው የተስተካከልኩት።
ቁም ሳጥኔ ውስጥ ያሉት የቱርክና የዱባይ ሱፍና ሸሚዞች አሮጌ መስለውኛል አዲስ የገዛሁትን ለብሻለሁ። የተቀባሁት ሽቶ በዋጋም በጥራትም የተለየ ነው። የቀረኝ እሌኒ ፊት ስቀርብ ምን ማውራት እንዳለብኝ ጥሩ ጥሩ ወሬዎችን ማዘጋጀት ነው። ለምን እንደሆነ አላውቅም እሌኒ አትወደኝም፤ ምኔ እንደሚያስጠላት አላውቅም። በቃ ትጠላኛለች፤ ስደውልላት እንኳን ከስድስት ሰባት ጥሪ በኋላ ነው የምታነሳው። እኔ ደግሞ እሷን መከተል አልተውኩም።
ይሄ ስንተኛ ቀጠሯችን እንደሆነ አላውቀውም፤ ብቻ በደወልኩላት ቁጥር እንገናኝ እንዳልኳት ነው፤ እሷም እንዲህ እንደ አሁኑ ፒያሳ እምብርት ላይ ትገትረኝና ይቅርታ መምጣት አልቻልኩም የምትል ትንሽዬ የጽሑፍ መልዕክት ትልክልኛለች። ግን አልቀየማትም፤ የእኔ እሷን አለመቀየም ምስጢሩ አይገባኝም። አመት ሙሉ ቀጥሬአት ስትቀር በመቅረቷ አልከፋም ነበር። ቤት ውስጥ ለቤተሰቤ አራተኛ ልጅ ነኝ፤ ከስምንቱ እህትና ወንድሞቹ ትዕግስት አልባው እኔ ነኝ.፤ ለመደባደብና ለመቀየም ቅርብ የሆነ ባህሪ አለኝ ፤ እሌኒን ግን አላኮርፋትም፤ አልቀየማትም።
የተዋወቅነው ባጋጣሚ ነው፤ ለአንድ ብርቱ ጉዳይ አንድ ቢሮ ገብቼ ስመለስ ከመኪናዬ ጎን መንገድ የዘጋ አንድ መኪና ቆሞ ተመለከትኩ። በጣም ቸኩዬ ስለነበር ጥበቃውን ጠርቼ ባለመኪናውን እንዲጠራልኝ ብነግረውም ባለመኪናው ሊገኝ አልቻለም። እየበገንኩ
መኪናዬን ተደግፌ ጠበኩ፤ ከአርባ ደቂቃ በኋላ አንድ ወጣት ምንም እንዳልተፈጠረ መንገድ የዘጋ መኪናዋን ከፍታ ስትገባ አየሁ፤ እንደዚያ ቀን ሰው ላይ ጮሄ አላውቅም።
‹አንቺ ሥርዓት አታውቂም እንዴ፤ ምን አይነት ብልግና ነው?ጋቢናዋን ከፍታ ልትገባ ያለችው ቆመች፤ ፊቷ ላይ የትኛውም ሰው ላይ ያላየሁት ርጋታና ስክንና ይታየኛል።
‹እንዴት እንደዚህ ታደርጊያለሽ…ስለ ትራፊክ ደንብና ህግ ሳታውቂ ነው እንዴ መኪና የገዛሽው?ዝም አለችኝ…ለዘለዓለም ከእንቅልፌ የሚያባንነኝን ዝምታ።
‹መኪናሽን እንዴት እንዳቆምሽው አይተሻል?…ዚግዛግ እኮ ነው ያቆምሽው፤ ማሰብ አትችይም፤ መንገድ ዘግተሽ ስትሄጂ ስንት የቸኮሉ ሰዎችን እንደምትበድይ አታውቂም? ምን ዓይነቷ ናት፤ መሃይም› ወረድኩባት..።
ምንም አላለችም፤ ከእርጋታዋና ከስክነቷ ላይ አንዳችም አልጎደለም። የጋቢናዋን በር እንደያዘች እስኪበቃኝ አደመጠችኝ። ለዘላለም በማይረሱኝ አይንና ጆሮ፣ ትዕግስትና ጽናት። እንደዚያ ቀን ጸጥ ብሎ ያደመጠኝ ሰው የለም። እንድትናገረኝ መንገድ ባመቻችላትም ዝም አለችኝ ‹ይሄ አያናድድም ትያለሽ? አንቺ ብትሆኚ ምን ታደርጊ ነበር? እስኪ አስቢው፤ በጣም ቸኩለሽ የሌላ ሰው መኪና መንገድ ሲዘጋብሽ? እንድታወራ ብዙ እድሎች ነበሯት ዝም አለችኝ። በዝምታ ናቀችኝ.፤ በዝምታ ዝም አሰኘችኝ።
በዝምታዋ መደንገጥ ጀመርኩ፤ ፈራኋት። ብዙ ልትለኝ የምትችለው ነገር ነበር ግን በዝምታ አሸነፈችኝ። የሰው ልጅ በዝምታ እንደሚሸነፍ እስከዚያች ሰዓት ድረስ አላውቅም ነበር። ዝምታ ከጩኸት እንደሚበረታ ያን እለት ነው ልብ ያልኩት። ሴት ሆና እንደ እሷ መለኮታዊ
ኃይል የተላበሰች አላውቅም፤ ሴት ሆና የወንድን ልጅ ድንፋታ በትዕግስቷ የመከተች ሴት አላውቅም። ነፍሷ አስቀናችኝ። ኃይሌ ብርታቴ፣ ወንድነቴ ሁሉ ጥያቄ ውስጥ ገባብኝ። እስከዛሬ ሰዎችን ሳሸንፍ የነበረበት መንገድ ልክ እንዳልነበር ገባኝ።
ወንድነቴን ከሴትነቷ ጋር እየቃኘሁ ሀሳብ ላይ ወደቅሁ። ከነፍሷ ጋር ነፍሴን እያስተያየሁ ለረጅም ጊዜ አሰብኳት። ያላትን ካለኝ ጋር እያመዛዘንኩ ቆዘምኩ። በብዙ በልጣኝ፤ በብዙ ርቃኝ አገኘኋት። የነፍሴን ነውር በነፍሷ ላድስ፣ የወንድነቴን እድፍ በሴትነቷ ልፈውስ ተመኘኋት፤ ማንንም ሴት እንደ እሷ ተመኝቼ አላውቅም። እስክይዛት ድረስ ለዘላለም ላሳድዳት ለራሴ ቃል ገባሁ። ምን ዓይነት ሴት ናት እያልኩ ወደ መኪናዬ ገባሁ።
መንገድ የዘጋውን መኪናዋን አንፏቃ ከእይታዬ እስከተሰወረችበት ጊዜ ድረስ ስለ እሷ እያሰብኩ ነበር። ከእይታዬ እንደተሰወረች ያደረኩት የመጀመሪያው ነገር ከጥበቃው መረጃ ወስጄ ስልኳን ማፈላለግ ነበር። ጓደኛዋ የሆነች አንድ ሴት አግኝቼ የተፈጠረውን ሁሉ ነገርኳት። ይቅርታ ልላት እፈልጋለሁ ስላት ስልኳን ሰጠችኝ። ስልክ ቁጥሯን ስልኬ ላይ ስመዘግብ ከመላዕክቶች የአንዱን ስልክ እየመዘገብኩ ነበር የመሰለኝ። የስልክ ቁጥሮቿ የአልማዝ ያህል ከብረውብኝ ነበር። ያን ቀን ስልኬ ላይ እሌኒ የሚል ስም መዘገብኩ።
በሕይወቴ ውስጥ ያላየሁት ደስታ የለም። ደስታዎችን ሁሉ ኖሬ እንደጨረስኳቸው ነበር የማስበው። አዲስና ሌላ ነፍሳዊ ደስታ እንዳለ ግን ያን እሌኒ አስተማረችኝ። ከእሷ ሌላ የትኛዋም ሴት እንዲህ እንዲሰማኝ አድርጋኝ አታውቅም። ከዚያን ቀን ጀምሮ እሌኒን ለማሳደድ ቆርጬ ተነሳሁ። እያሰብኳት መኪናዬ ውስጥ ገባሁ፣ እያሰብኳት ጉዞ ጀመርኩ።
በዝምታ እንደዚያ ያደናበረችኝ ስታወራ ምን እንደምትመስል ለማየት የናፈኩትን ያህል ምንም ናፍቄ አላውቅም። መጀመሪያ ቀን ስደውል ሄሎ እስክትለኝ ድረስ ያለው ጊዜ የዝንተአለም ያህል ርቆኝ ነበር። ሄሎ ስትለኝ..ነፍሴ ላይ ነፍስ አቆጠቆጥኩ። ለዘላለም የማትሞት ነፍስ። እንደዚያ ያደመጥኩት የሴት አንደበት የለም። ማንነቴን ሳልነግራት ሳምንት አወራኋት።
እሷም ማንነቱን ሳይነግረኝ ያወራሁት የመጀመሪያው ወንድ ነህ፤ ከዚህ በኋላ ግን አላወራህም አለችኝ። ማንነቴን ብነግራት እንደማታወራኝ ስላወኩ ነበር ማንነቴን የደበቅኳት። ያን ቀን ግን ማን እንደሆንኩ መናገር ነበረብኝ ከመናገሬ በፊት ግን ተላምደን ስለነበር ማንነቴን ስታውቅ ቅያሜ እንዳይገባት ቃል አስገባኋት።
ሉቋስ እንደምባል ከሳምንት በፊት መንገድ በዘጋ መኪናዋ እንዳስቀየምኳት ነግሬ ይቅርታ ጠየኳት.፤ ምንም እንዳልተፈጠረ ይቅርታ አደረገችልኝ። ከዚያ በኋላ እስከዛሬዋ ጠዋት ድረስ ለበርካታ ወራት አውርተናል፤ ምን ልታስተምረኝ እንደሆነ አላውቅም፤ በእያንዳንዱ መደወሌ ውስጥ እንገናኝ የሚል ቃል አለበት፤ እሷም እሺ ትለኛለች፤ ተቀጣጥረን መጥታ ግን አታውቅም።
ዛሬ እንቢ እንዳትለኝ በምትወዳቸው ሁለት ነገሮች ለምኛታለሁ። በሕይወቷ ውስጥ በነዚህ ነገሮች ተለምና እንቢ ብላ አታውቅም። እነሱም እናቷና ታናሽ እህቷ ናቸው። እመጣለሁ ፒያሳ ጠብቀኝ ብላኛለች፤ እኔም ማንንም ባላመንኩት እምነት አምኜ እየጠበኳት ነው።
ስምንት ሰዓት ላይ መጣች፤ ተዓምር የሆነልኝ ያህል ተሰማኝ። ብዙ አወራን።
‹ለምን ነበር እመጣለሁ እያልሽ ስትቀሪ የነበረው? ስል ጠየኳት።
‹አፍርሼ ልሰራህ፤ በዝምታ ማሸነፍን እንድታውቅ ብዬ» አለችኝ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን የካቲት 25/2014