መልካም ሥራ እድሜ ጾታ አልያም ሌሎች ማንነቶች አይገድቡትም። በተለይም ብዙ ተፈጥሯዊና አካባቢያዊ ስሜቶች በሚጋፉበት በወጣትነት እድሜ ሲሆን ደግሞ ሥራው በምድርም በሰማይም የሚቀመጥ፤ የሚታወስ ስንቅ ይሆናል። የዛሬ የሀገርኛ አምድ እንግዳ አድርገን የምናቀርብላችሁም በወጣትነት እድሜያቸው ትልቅ የቅንነት አላማን ሰንቀው በመጓዝ ላይ የሚገኙ ወጣቶችን እንቅስቃሴ ነው። የማህበሩን ጅማሮና አጠቃላይ ጉዞ የማህበሩ ሰብሳቢ የሆነውን ወጣት አልአዛር ብዙዬን አነጋግረን እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
በሁለት ሺ አስር አመተ ምህረት ነበር በአዳማ ከተማ አዋሽ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ላለመራራቅ አንድ ነገር ማድረግ እንዳለባቸው የወሰኑት። አብዛኛዎቹ ልጆች ከአንደኛ ክፍል ጀምረው አብረው የተማሩ በመሆናቸው ወዳጅነታቸው ጥብቅ ነበር። እናም የነበራቸውን ግንኙነት ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ እንዳይላላ በማሰብ ለመታሰቢያ እንዲሆናቸው በማህበረሰቡ ውስጥ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን እየሠሩ ለመገናኘት ይወስናሉ።
በወቅቱ ማህበሩን «ከሰው ለሰው» የሚል ስያሜ በመስጠት የመሠረቱት ቢሆንም በሕጋዊ መንገድ ለመመዝገብ እንቅስቃሴ ሲጀምሩ ግን ተመሳሳይ ስያሜ ያለው ማህበር ከእነሱ በፊት የተመዘገበ በመኖሩ እንዲቀይሩት ይጠየቃሉ። እናም ባለን አቅም ለሁሉም ብርሃን እንሁን በሚል እሳቤ «ቀንዲል የበጎ አድራጎት ማህበር» የሚል ስያሜ ሊሰጡት በቅተዋል።
እነዚህ ወጣቶች በትምህርት ቤታቸው ከሚከናወኑ ትናንሽ የበጎ አድራጎት እንቅስቃሴዎች ውጪ ምንም ተሞክሮ ያልነበራቸው በመሆኑ የመጀመሪያ ሥራቸው ያደረጉት ወደ ሌሎች በአዳማ ከተማ ከሚንቀሳቀሱ የበጎ አድራጎት ማህበራት ጋር በመሄድ አረጋውያንን ሕፃናትን የመንከባከብና ሌሎች አገልግሎቶችን መስጠት ነበር።
ነገር ግን ውለው አድረው ልምዳቸውም እየዳበረ ተነሳሽነታቸውም እየጨመረ ሲመጣ ራሳቸውንም ችለው መንቀሳቀስ ይጀምራሉ። ቀዳሚ ሥራቸው ከነበረው መካከልም የአቅመ ደካሞችን ቤት ማደስ ነበር። በወቅቱ እማማ ቦንቱ ቱለማ የሚባሉ ጧሪና ተንከባካቢ የሌላቸው አንዲት አቅመ ደካማ እናት ይኖሩበት የነበረው ቤት እላያቸው ላይ ሊፈርስ ትንሽ ቀርቶት በአስጊ ሁኔታ ውስጥ ነበሩ። ይህንን የሰሙት የቀንዲል አባላትም እኒህ እናት ቤታቸው እላያቸው ላይ ፈርሶ ለከፋ ነገር ከመዳረጋቸው በፊት አንድ ነገር ማድረግ እንዳለባቸው ይወስኑና ያላቸውን አቅም በመጠቀም ቤቱን ለማደስ መንቀሳቀስ ይጀምራሉ።
በወቅቱ ሁሉም ተማሪዎች ስለነበሩ ለዚህ ሥራቸው የገቢ ምንጭ ማስገኛ ማድረግ የመረጡት ደግሞ በከተማዋ አራዳ በሚባለው አካባቢ ያሉ ነጋዴዎችን የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ትብብር መጠየቅን ነበር። ሥራውን ሲጀምሩ የቤቱን ጣራ ለማድስ ብቻ የነበረ ቢሆንም በጣም አርጅቶ ስለነበር ቆርቆሮው ሲነቀል ቤቱ መፍረስ ይጀምራል። በመሆኑም ሙሉ ለሙሉ በማንሳት እንደ አዲስ መሥራት የግድ አስፈላጊ የሆነበት ሁኔታ ይፈጠራል።
ለዚህ የሚበቃ ገንዘብ ደግሞ እጃቸው ላይ ስላልነበር የጀመሩትን ሥራ አቁመው በአዳማ ከተማ በገበያ ቦታዎችና ሌሎችም አካባቢዎች በመዘዋወር ገቢ ማሰባሰብ ይጀምራሉ። ይህን ሲያደርጉ ከቀበሌ የትብብር ወረቀት የነበራቸው ቢሆንም በቂ ስላልነበር በደንብ አስከባሪዎችና ፖሊሶች ተይዘው ወደማቆያ ቤት ይወሰዳሉ። እዚያ ከደረሱ በኋላ ግን ያሉበትን ሁኔታ የተረዱት ኃላፊዎች ፈቃድ ሳያወጡ ደግመው እንዲህ ዓይነት ሥራ እንዳይሠሩ በማስጠንቀቅ ይለቋቸዋል። የቀንዲል አባላትም የጀመሩትን የእማማ ቦንቱን ቤት ግንባታ እንደምንም ተሯሩጠው ሁለት ክፍል አድርገው ሠርተው ለማስረከብ ይበቃሉ። ነገር ግን በነፃነት ሥራቸውን ለመስራት በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው መንቀሳቀስ እንዳለባቸው በመወሰን ፈቃድ ለማውጣት ሥራቸውን ይጀምራሉ።
አስፈላጊውን ሁሉ አሟልተው በፌዴራል ደረጃ የተመዘገበ ፈቃድ ካወጡ በኋላ ሥራቸውን በተጠናከረ መልኩ ይጀምራሉ። በዚህ ጊዜም በተመሳሳይ መዳረሻቸው ያደረጉት እማማ ብርቄ ወልዴ የሚባሉ እናት ቤትን ማደስ ነበር። የእኒህም እናት ቤት በፍጥነት ካልታደሰ እላያቸው ላይ ሊወድቅ የሚችልበት አጋጣሚ ነበር። እናም ቀንዲሎች የኢትዮ ቴሌ ኮም አዳማ ቅርንጫፍ ሠራተኞች ተገልግለውባቸው የነበሩ ነገር ግን ጥሩ ይዞታ ላይ ያሉ የቤት መስሪያ ቁሳቁሶችን ድጋፍ አድርገውላቸዋል ቤቱን ሰርተው ለማስረከብ ይበቃሉ።
በዚህ ሁኔታ ሥራቸውን የጀመሩት ወጣቶች በአሁኑ ወቅት አርባ አረጋውያንን በያሉበት ሙሉ የወር አስቤዛ በማድረስ ሕክምና በመውሰድና ቤታቸውን በማጽዳት መንከባከባቸውን ይቀጥላሉ። ይህም ሆኖ በአንድ ወቅት አስደንጋጭ አጋጣሚ ይፈጠራል። በማህበሩ ድጋፍ እየተደረላቸው ይኖሩ የነበሩ አንድ አባባ መልካ የሚባሉ አባት ነበሩ። ይኖሩ የነበረውም ከባለቤታቸው ጋር ሲሆን ባልየው ሙሉ ለሙሉ ፓራላይዝድ በመሆናቸው መንቀሳቀስ የማይችሉ ናቸው።
ባለቤታቸው እማማ ትክክል ደግሞ የደም ግፊትና ዓይናቸው የማየት ችግር ነበረባቸው። እኒህ ጥንዶች አምስት ልጆች የነበሯቸው ቢሆንም በአሁኑ ወቅት አንዳቸውም በሕይወት ባለመኖራቸው የሚኖሩት ብቻቸውን ነበር። በአካባቢው ዘመዶች ያሏቸው ቢሆንም ሁሉም ኑሯቸው ከእጅ ወደ አፍ በመሆኑ ጥንዶቹን መደገፍና መከታተል የሚችሉበት ሁኔታ ላይ አልነበሩም። ታዲያ አንድ ቀን እናትየው ዓይናቸውን ስለሚጋርዳቸው ወጥ ሲሠሩ ዘይት መስሏቸው ላርጎ ይጨምሩበታል። የሆነውን ነገር ያውቁት ደግሞ ምግቡን አቅርበው ከባለቤታቸው ጋር ሲቀምሱት የተለየ ጣእም ሲደርሳቸው ነበር።
ይህ አጋጣሚ ነበር የማህበሩን አባላት በእነዚህ ደካሞች ቤት በመገኘት የምግብ ቁሳቁስ ከማቅረብ አልፈው በየቀኑ አብስለው መመገብ እንዳለባቸው ለመወሰን የበቁት። በዚህም መሠረት ለእነዚህ ጥንዶችና በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ አረጋውያን እያንዳንዱ የማህበሩ አባል በወጣለት መርሃ ግብር መሠረት በየቀኑ እቤታቸው በመገኘት ምግብ የማብሰልና የመመገብ፤ ቤት የማጽዳትና ልብስ የማጥብ እንዲሁም በየቀናት ልዩነት አረጋውያኑን ገላ የማጠብ ጥፍር የመቁረጥና ሌሎች እንክብካቤዎችንም ማድረግ ይጀምራሉ። ከዚህ በተጨማሪ የማህበሩ አመራሮች የአባላት ቀን በሚል በተሰየመው እሁድ ቀን በየአረጋውያኑ ቤት በመገኘት አብረው የተለያዩ እንክብካቤዎችን እያደረጉ ይገኛሉ። ይህ እንግዲህ በማህበሩ አጠቃላይ ስብሰባ ተወስኖ በየወቅቱ በአቅመ ደካሞች ቤት በመገኘት ከሚሠራው ቀለም የመቀባት፤ ጣራ የመቀየር፤ ኮርኒስ የማደስና በርና መስኮት የመጠጋገን ሥራዎች በተጨማሪ ነው።
በሌላ በኩል ቀንዲል የበጎ አድራጎት ማህበር አምስት ልጆችን ሙሉ የትምህርት ቁሳቁስ በማሟላት የጀመሩትን የማስተማር ሥራም በማስፋፋት ዛሬ አስራ ሰባት ሕፃናትን ሙሉ ወጪ በመሸፈን በማስተማር ላይ ይገኛሉ። እነዚህን ልጆች የትምህርት ቁሳቁስ እያሟሉ ወደ ትምህርት ቤት መላኩ ብቻ ውጤታማ ስለማያደርጋቸው በአዳማ ዩኒቨርሲቲ ከሚማሩ በጎ አድራጊ ተማሪዎች ጋር በመነጋገር በተጨማሪ በየቤታቸው የጥናት አገልግሎት እየተሰጣቸው ይገኛል።
የቀንዲል አባላት በአመት አራት ጊዜ አባላቱ በተገኙበት በአዳማ ከተማ የደም ልገሳ የሚያደርጉ ሲሆን ነገር ግን ሁሉም አባላት በያሉበት የጤና እክል እስካልገጠማቸው ድረስ ደም የመለገስ ግዴታ አለባቸው። በአገሪቱ የተከሰተውን ወቅታዊ ችግር ተከትሎም እንደ ዜጋ ኃላፊነታችንን መወጣት አለብን በሚል ከተለያዩ ማህበራት ጋር የሰሯቸውም ሥራዎች አሉ። ከእነዚህም መካከል በጦርነቱ ለተጎዱ ወገኖች በአዳማ ከተማ ከሚንቀሳቀሱ አስር ማህበራት ጋር በመሆን በርካታ አልባሳት የምግብና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን በማሰባሰብ ለሚመለከተው ያስረከቡ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅትም ሁለተኛ ዙር ተመሳሳይ ስጦታ ለማበርከት በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛሉ።
በዚህ ሁኔታ ማህበሩ ተመስርቶ አመታትን ካሳለፈ በኋላ የተደጋፊዎቹ ቁጥር እየጨመረ ሲመጣና ተጨማሪ ገንዝብ ማግኘት ሲያስፈልግ አባላቱ ራሳቸው የገቢ ምንጭ ማሰባሰብ እንዳለባቸው በማመን መንቀሳቀስ ይጀምራሉ። የመጀመሪያ ሥራቸውም ያደረጉት በየጎዳናው በመዞር ጫማ የመጥረግ ሥራ ነበር። ከዚህም አያይዘው የተለያዩ ሃይማኖታዊና ሌሎች ክብረ በአላት ሲኖሩ የላስቲክ ውሃ በመሸጥ ፖስት ካርድ በማዘጋጀትና ሌሎች ወቅታዊ ሥራዎችንም መሠራት ይጀምራሉ። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ እያንዳንዱ አባል እንደየአቅሙና ፈቃደኝነቱ ተማሪ ከሆነ ከሰላሳ ብር ጀምሮ እንዲሁም ሠራተኛ ከሆኑ ከሃምሳ ብር ጀምሮ ወርሃዊ ክፍያ መሰብሰብም ይጀምራሉ።
እነ አልአዛር በዚህ ሁኔታ ማህበሩን ሲመሰርቱትና ወደሥራ ሲገቡ አብረው የተማሩ ሰላሳ አራት ልጆች ብቻ ሆነው ነበር። ነገር ግን በተመሳሳይ ወቅት ከሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ የተቀላቀሏቸው በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችም ስለነበሩ ቁጥራቸው አርባ ስምንት ደርሶ ነበር። በአንድ ወቅት ግን አብዛኛዎቹ ተማሪዎች በተለያዩ ምክንያቶች ማህበሩን እየለቀቁ ሄደው ስድስት ብቻ ይቀራሉ። ነገር ግን እነዚህ ስድስት አባላት በነበራቸው ጽናት በአሁኑ ወቅት ሃምሳ ተማሪዎችና አርባ ባለ ሥራ በድምሩ ዘጠና አባላት የያዘውን ማህበር ዛሬ ላለበት ደረጃ ለማድረስ በቅተዋል። አብዛኞቹ የማህበሩ አባላት በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞችና ከአገር ውጪም የሚኖሩ ሲሆን ከሳምንት በፊት የማህበሩን ምስረታ አራተኛ አመት በድምቀት ለማክበርም ችለዋል።
ማህበሩ ራሱን እንደ ተቋም ሲያደራጅ የተለያዩ ክፍሎችን ይዞ ሲሆን ሙሉ የአረጋውያን ጉዳዮችን የሚከታተል የአረጋውያን ክፍል አለው። በተጨማሪም ማህበሩ ተደጋፊ ሕፃናትን የሚለይና የሚደረግላቸውን ድጋፍ የሚከታተል የሕፃናት ክፍል፣ የቁጥጥርና የማስተባበር ሥራ የሚሠራ የአባላት ሰብሳቢ ክፍል፣ አባላትን መዝጋቢና የክብር አባልና አምባሳደር የሚመርጥ ክፍል፣ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል የአባላቱን ወርሃዊ መዋጮ በየወሩ የሚሰበስብ፤ የገቢ ምንጭ የሚያፈላልግ እንዲሁም የማህበሩን ገቢና ወጪ የሚቆጣጠር ፋይናንስ ክፍልም አሉት። ማህበሩ ያለውን ንብረት የሚቆጣጠር ንብረት ክፍል ያለው ሲሆን እነዚህ ክፍሎች በየሦስት ወሩ ሁሉም አባላት በያሉበት ስብሰባ በማካሄድ ላይ ይገኛል።
ምንም እንኳን አረጋውያን ቢቻል ከቤተሰቦቻቸው አልያም ከማህበረሰቡ ጋር ሆነው አስፈላጊው ድጋፍ ቢደረግላቸው የተሻለ ቢሆንም አንዳንድ ነባራዊ ሁኔታዎች ግን ይህንን ለማድረግ የሚፈቅዱ አይደሉም። በመሆኑም ማህበሩ ለቀጣይ የሕፃናትና አረጋውያን ማቆያ ማእከል ለመገንባት እቅድ ይዞ ከመንግሥትም ቦታ ለማስፈቀድ በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል። የማዕከሉ መገንባት አረጋውያኑን በተሻለ ሁኔታ ለመንከባከብ ከማስቻሉም በላይ ማህበሩ እየሠራቸው ያሉ አጠቃለይ ሥራዎችን በተቀላጠፈና በተሻለ መንገድ ለመከወን የሚያስችለውም እንደሆነ ወጣት አልአዛር ይናገራል።
የቀንዲል በጎ አድራጎት ማህበር አባላት ለቀጣይ ከያዙትና ከቀዳሚ እቅዳቸው መካከል ደግሞ አንደኛው ኢትዮጵያዊነትን በተግባር ማሳየትና በማህበረሰቡም ውስጥ ማስረጽን ነው። ለዚህም በበአላት ቀናት ሁሉንም የእምነት ተቋማት የማጽዳት እቅድ ይዘው በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ። ይህንን ሥራቸውን ለማህበሩ አባላት ብቻ ሳይሆን ለመላው የአዳማ ከተማ ነዋሪዎች በማሳወቅ የክርስትና በአላት ሲከበሩ ሁሉም ወጣቶች በቤተክርስቲያናት በመገኘት የጽዳት ሥራ እንዲሠሩ። በተመሳሳይ የእስልምና በአላትም ሲከበሩ መስኪዶችን ለማጽዳት በዝግጅት ላይ ይገኛሉ።
በሌላ በኩል ከተሞችን ለኑሮ ምቹና ሰላማዊ ለማድረግ በከተማ ጽዳትና ጥበቃ አገልግሎት እንዲሁም ለመላው ሕዝብ የየዕለት ስጋት የሆነውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ በትራፊክ ዝውውር ቁጥጥር ለመሰማራት እቅድ አላቸው። እነዚህ አገልግሎቶች ለወረት ብቻ የሚከወኑ እንዳይሆኑም በአንድ ወገን በጎንዮሽ ከሌሎች በጎ አድራጎት ማህበራት ጋር በሌላ በኩል ከመንግሥት ኃላፊዎችና ከሃይማኖት አባቶች ጋር የማህበሩ አባላት ግንኙነት በመፍጠር ውይይት በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ቀንዲል ከአስገዳጅ እንቅስቃሴዎች ባለፈ አባላቱን በያሉበት በበጎ አድራጎት ሥራ እንዲሰማሩ የሚያደርግ ሲሆን፤ ወደፊት በአንድ አመራር ስር ሳይሆን ራሳቸውን ችለው የሚንቀሳቀሱ ማህበራት በየከተሞች ለመፍጠርም የረጅም ጊዜ እቅድም አላቸው።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን የካቲት 25/2014