ኢትዮጵያ በኦማን ዋና ከተማ ሙስካት አዘጋጅነት ነገ በሚጀመረው ዓለም አቀፉ የእርምጃ ቻምፒዮና ላይ ትሳተፋለች። በውድድሩ ላይ አራት አትሌቶች አገራቸውን ወክለው እንደሚሳተፉ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
ከመላው ዓለም የተውጣጡ ጥቂት አገራት ብቻ በሚካፈሉበትና ለሁለት ቀናት በሚካሄደው በዚህ ውድድር ላይም ኢትዮጵያ ተሳታፊ እንደምትሆን ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ድረገጹ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። ኢትዮጵያን ወክሎ በውድድሩ ላይ የሚሳተፈው ልዑክ በተያዘው ሳምንት መጀመሪያ አሸኛኘት ተደርጎለታል።
በዚህ ውድድር ላይ ኢትዮጵያ ተሳታፊ የምትሆነው በሁለቱም ጾታ ሲሆን፤ ሁለት ሴቶችና ሁለት ወንዶች ተሳታፊ ይሆናሉ። በወንዶች አትሌት ዮሐንስ አልጋው እና አትሌት ቢራራ ዓለም፣ በሴቶች ደግሞ አትሌት የኋልዬ በለጠው እና አትሌት ስንታየሁ ማስሬ ናቸው በቻምፒዮናው የሚሳተፉት። አሰልጣኝ ሻለቃ ባዬ አሰፋ ደግሞ ዋና አሰልጣኝ በመሆን ከአትሌቶቹ ጋር ወደ ሙስካት ተጉዘዋል።
አትሌቶቹ ፌዴሬሽኑ ባዘጋጀው የመምረጫ መስፈርት ተመርጠው ራሳቸውን ሲያዘጋጁ መቆየታቸውም በድረገጹ ተጠቁሟል። በርምጃ ውድድር በተለይ ስኬታማ የሆኑት ቻይና እና ስፔንን የመሳሰሉ አገራት ሲሆኑ፤ ኢትዮጵያም እስከ ኦሊምፒክ የደረሰ ተሳትፎ አላት። በዚህ ውድድር በተለይ ታዋቂ የሆነችውና ከፍተኛ ልምድ ያላት አትሌት የኋላዬ በለጠው በሪዮ እና ቶኪዮ ኦሊምፒኮች እንዲሁም በዶሃ የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮናዎች ላይ ተካፋይ ነበረች።
የዓለም ርምጃ ቻምፒዮና በየሁለት ዓመቱ በዓለም አትሌቲክስ አዘጋጅነት የሚካሄድ ውድድር ነው። እ.አ.አ በ1961 መካሄድ የጀመረው ቻምፒዮናው፤ እ.አ.አ በ2020 ቤላሩስ እንደምታዘጋጅ ቢጠበቅም፣ በኮቪድ 19 ምክንያት ሊራዘም ችሏል። በዚህም ኦማን አስተናጋጅነቱን የተረከበች ሲሆን፤ ከነገ በስቲያ ይጀመራል። ውድድሩ በተለያዩ ርቀቶች የሚካሄድ ሲሆን፤ ኢትዮጵያውያን ተሳታፊ የሚሆኑበት የ20 ኪሎ ሜትር ሴቶች ውድድር ነገ ይካሄዳል። ወንዶችን የሚያፎካክረው የ20ኪሎ ሜትር ርምጃ ውድድር ደግሞ ከነገ በስቲያ የሚደረግ መሆኑን ነው የውድድር መርሃ ግብሩ የሚጠቁመው።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን የካቲት 24/2014