የተባበሩት መንግሥታት ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከአስር ዓመት በፊት ያወጣው ሪፖርት እንደሚያመለክተው፤ በተለያዩ ዓለማቀፍ የስፖርት መድረኮች ስፖርተኞችን በዘርና በቆዳ ቀለማቸው መገለል የተለመደ ነው። ይህ እውነታ አሁን ላይ አደጉ በምንላቸው አገራት ስፖርት ላይ እንኳን ነቀርሳ መሆኑን በተለያዩ አጋጣሚዎች እንመለከታለን።
በተለይም እንደ አሜሪካ፤ አውስትራሊያና አውሮፓ የመሳሰሉ አገራት ላይ ጥቁር ስፖርተኞች አሁንም ድረስ በዘረኝነት የሚዘለፉበት፤ የሚንቋሸሹበትና ዝቅ ተደርገው የሚታዩባቸው አጋጣሚዎች እየተበራከቱ መምጣታቸው ከዘር፤ ከሃይማኖትና ከፖለቲካ ነፃ መሆን የሚገባው ስፖርት ላይ መጥፎ አሻራ እንዲያርፍ እያደረገ ይገኛል።
በስፖርት ጥቁሮች አሁን ላይ በየትኛውም ዓለማቀፍ መድረክ ተፎካካሪ እንዲሆኑ ከማስቻል ባሻገር በትልቅ ደረጃ ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ ለማሳየት በርካታ ጥቁር ከዋክብት ብዙ ችግሮችን ተጋፍጠዋል። በተለይም ጥቁር አሜሪካውያን አትሌቶች በዚህ ረገድ ያዩት ፈተና ሳይጠቀስ የሚታለፍ አይደለም።
አፍሪካውያንም ቢሆኑ በርካታ መከራዎችን ተጋፍጠው ለታላቅ ክብር በመብቃት ለአሁኖቹአትሌቶች ፋና ወጊ ሆነው እኩልነትን ማንፀባረቃቸው አይካድም። ለዚህም ታሪካዊውን ኢትዮጵያዊ የማራቶን ኮከብ አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ በትልቁ የሚነሳ የጥቁር ሕዝቦች ኩራት ሆኖ እናገኘዋለን።
ኢትዮጵያውያን በስፖርቱ ብቻም ሳይሆን በዓድዋ ድል የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተምሳሌትና የማዕዘን ድንጋይ ሆነዋል። የጥቁር ሕዝቦች ኩራት የሆነው የዓድዋ ድል የሚዘከርበት የካቲት ወር በመላው ዓለምም የጥቁር ሕዝቦች መታሰቢያ ሆኖ ይከበራል።
በስፖርቱ ዓለም ለእኩልነት የታገሉ ቁንጮ አትሌቶችም በዚህ ወር ሳይዘከሩ አይታለፉም። በእርግጥ በስፖርት መድረክ ዘረኝነትን የታገሉ፤ እኩልነትን ያንፀባረቁና በድላቸው የጥቁር ሕዝቦችን አንገት ያቀኑ በርካታ ጥቁር ከዋክብቶች መኖራቸው አይካድም። ከነዚህ ከዋክብቶች ግን ተፅዕኗቸው ከፍተኛ የነበረ፤ ድላቸው በርካታ ትርጉም የነበረውና በትልቅ ደረጃ ከሚነሱት መካከል የታላቁ ዓድዋ ድል ባለቤት የሆነውን የኢትዮጵያ ሕዝብ እንቁ ልጅ አበበ ቢቂላና የሮም ኦሊምፒክ ህያው የማራቶን ድል ተጽእኖ ቀላል እንዳልነበረ በብዙ ድርሳናት ተጽፎ ይገኛል።
1928 ፋሺስት ጣሊያን በአምባገነኑ ቤኒቶ ሞሶሎኒ በመመራት ኢትዮጵያን ከወረረ ከሃያ አራት ዓመታት በኋላም ታላቁ አበበ ቢቂላ ታላቋን ሮም በባዶ እግሩ ወሮ ዓለምን ጉድ አሰኘ። የምን ጊዜም የማራቶን ንጉሱ የአፍሪካውያን ኩራትና የነፃነት ተምሳሌት እንዲሁም፤ የመጀመሪያው ጥቁር የማራቶን ኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ በጥቁሮቹ በጀግኖቹ መታሰቢያ ወር የካቲት የጥቁር ሕዝቦች ኩራት ሆኖ ከስልሳ ዓመት በፊት በኢትዮጵያውያን አዲስ ዓመት ዋዜማ በሮም ኦሊምፒክ የፈፀመው ታሪካዊ ጀብድ በመላው ዓለም ያሉ ጥቁር አትሌቶችን በእጅጉ ያኮራና ያነሳሳ ነበር።
ጳጉሜን 5 ቀን 1952 አስራ ሰባተኛው የሮም
ኦሊምፒያድ በታላቋ ሮም ጎዳናዎች በርካቶች አይናቸውን ለማመን የተቸገሩበት ጀብድ በአምባገነኑ ሞሶሎኒ አገር በበርካታ ነጮች መሐል አንድ ጥቁር በባዶ እግሩ ይጽፈዋል ብሎ ማንም አልጠረጠረም። የጥቁር ሕዝቦች ተአምርን ለመቀበል የሚተናነቃቸው ዘረኝነትን በደማቸው ያሰረፁ ነጮች እንዴት ይህ ሊሆን እንደቻለ አሁንም ድረስ ግራ ይጋባሉ። አፍሪካውያንን ያኮራ ኢትዮጵያውያንን ከልብ ያስፈነጠዘው ታሪካዊ ድል በአበበ ቢቂላ ቀጫጭን እግሮች በወርቅ ቀለም መጻፉን ግን እየተናነቃቸውም ቢሆን ሊያላምጡት ተገደዋል።
የአራት ዓመት ታዳጊ ሆኖ እናት አገሩ ኢትዮጵያ በጣሊያን ፋሺስት ስትወረር መጥፎውን ጊዜ ገና ባልጎለበተ የሕፃን አዕምሮው የሚያስታውሰው አበበ ቢቂላ ሃያ ስድስት ዓመታት ጠብቆ ታላቁን የሮም ጎዳና በባዶ እግሩ ወሮ የማይደገመውን ታሪክ አኑሯል።
ከአራት ዓመት በኋላም 1956 በድጋሚ ጫማ አጥልቆ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ክብረወሰን በማሻሻል ጭምር አሸንፎ ጥቁሮች በማይደፈረው ርቀት አሁን ላይ ቁንጮ እንዲሆኑ መሠረቱን ጣለ። እሱ በከፈተው በርም ቁጥር ስፍር የሌላቸው የማራቶን አትሌቶች ለዘመናት ለርቀቱ የተፈጠሩት እነሱ ብቻእስኪመስሉ አሁን ድረስ በዓለም አደባባይ እያንጸባረቁ ነው።
አበበ ምናልባት ያንን ውድድር ባያሸንፍ ኖሮ የጥቁር አትሌቶች በተለይም የረጅም ርቀት ታሪክ ዛሬ ከምናውቀው ተቃራኒ ሊሆን እንደሚችል በርካቶች ይስማማሉ።
እርግጥ ነው በሮም ኦሊምፒክ አበበ ብቸኛው ተሳታፊ አልነበረም። ብቸኛው ወርቅ ያጠለቀም አትሌት አይደለም። በዚያ ኦሊምፒክ ከተሳተፉ ጥቁሮች መካከል ሌላ ባለድልም ነበር። አሜሪካዊው ጥቁር የቡጢ ተፋላሚ መሐመድ ዓሊ በቀላል ሚዛን የወርቅ ሜዳልያ ተጎናፅፎ ነበር።
ቢሆንም ኦሊምፒኩ በመሐመድ ዓሊ ወርቅ ሜዳልያ እምብዛም የደመቀ አልነበረም። በወቅቱ ታሪክ የሚያስታውሰው ሌላ ክስተትም ነበር። ጊዜው ደቡብ አፍሪካ በአህጉራዊ ውድድሮች ለመጨረሻ ጊዜ ተሳትፋ የታገደችበት ነበር። የእገዳዋ ምክንያት ደግሞ ትከተለው በነበረ የአፓርታይድ ሥርዓት መሆኑ ነው። ቢሆንም የያኔ የሮሙ ኦሊምፒክ በመሐመድ ዓሊ የወርቅ ሜዳልያም ይሁን በደቡብ አፍሪካ መታገድ አይደለም የሚታወሰው።
ታዲያ በምን ይታወሳል ያሉ እንደሆነ በውድድር ዘመኑ የማራቶን ሩጫ ያለ ጫማ ሮጦ የርቀቱ አዲስ ክብረወሰን ባስመዘገበው ኢትዮጵያዊ አትሌት ሻምበል አበበ በቂላ ነው። በወቅቱ በርካታ ሊጠቀሱ የሚችሉ ነገሮች ቢከናወኑም አበበ ግን ታሪኮችን ሁሉ ልቆ የሚታወስ ድንቅ ታሪክ አስመዘገበ።
ያኔ፣ አይደለም አበበ ቢቂላ የሚባል አትሌት፣ ኢትዮጵያ ተብላ ስለምትጠራ አገርም የሚያውቅ የውጭ ዜጋ ብዙም አልነበረም። ይሁን እንጂ ውድድሩ በጣሊያን መካሄዱ እና የጣሊያን ወረራ በኢትዮጵያ ድል አድራጊነት ተጠናቅቆ ድል የመጨበጧ ወሬ ገና ከዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች የወሬ አጀንዳነት ባለመረሳቱ፣ የአበበ ቢቂላ ድል ገነነ። ለዚህም ነው ብዙዎች የአበበ ድልና ታላቁ የጥቁር ሕዝቦች የጦርነት ድል ዓድዋ የሚመሳሰልባቸው ወይም የሚገጣጠምባቸው።
የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ሳይቀሩ ባልተጠበቀው የአትሌት አበበ በቂላ ድል ተደምመው ደጋግመው፣ በባዶ እግር ሮጦ የወርቅ ሜዳልያ ስላገኘው ኢትዮጵያዊው አትሌት ተናገሩ። በውድድሩ ማግስትም የኢጣሊያ ጋዜጦች ‹‹ኢትዮጵያን ለመውረር የኢጣሊያ አገር ወታደር ሁሉ አስፈልጎ ነበር፤ ኢትዮጵያ ግን አንድ ወታደር ብቻ ልካ ድፍን ሮምን ወረረችው›› የሚል ጽሑፍ ይዘው ወጡ። ይህም አጋጣሚ ብዙ ጥቁር አፍሪካውያን በዓለም አቀፍ ውድድሮች እንዲሳተፉ በር ከመክፈቱ በዘለለ ከቅኝ ግዛት ለመላቀቀ የነጻነት ትግል በማድረግ ላይ ለነበሩ የዓለም ጥቁር ሕዝቦች ሁሉ የ”ይቻላል” መንፈስና ትልቅ የስነልቦና ስንቅ ሆኗቸዋል።
የአበበ ቢቂላ አንፀባራቂ ድሎች ለአፍሪካውያን በፋና ወጊነት ጠቅሟቸዋል። በኩራችን ብለውም ሰይመውታል። አዲስ አበባ በ2000 ዓ.ም. ያዘጋጀችውን 16ኛውን የአፍሪካ አትሌቲክስ ቻምፒዮና አጋጣሚን ምክንያት በማድረግ በ50 ዓመታት ውስጥ ለአፍሪካ አኩሪ ታሪክ የፈጸሙ አትሌቶች ሲሸለሙ፤ አውራው ተሸላሚ አበበ ቢቂላ ነበር። ‹‹የአፍሪካ ማራቶን አባት›› ተብሎም በዶክመንተሪው ፊልም ላይ ተመልክቷል።
አፍሪካውያን ለአበበ ያላቸው ፍቅርና አክብሮት እስከዚህ ድረስ ነው አይባልም። የአፍሪካ አትሌክስ ሻምፒዮና በሴኔጋል መዲና ዳካር በ1971 ዓ.ም. ሲጀመር ወደ ዳካር ስታዲየም የሚያስገባውን መንገድ ‹‹አበበ ቢቂላ ጎዳና›› በማለት መሰየሟ ይታወሳል። ኢጣሊያም ብትሆን ለአበበ ክብሩን አልነፈገችም። የሮም ኦሊምፒክ 50ኛ ዓመትን ስትዘክር አንድ ድልድይ በስሙ ሰይማለች።
አምስተርዳም ከተማም የአበበ ቢቂላ መንገድ አላት። ‹‹ቶኪዮ ኦሊምፒያድ›› በተባለው የትረካ ፊልም ላይ የአበበ ቢቂላ የቶኪዮ ድል ተጨምሯል። ከዚሁ ፊልም የተወሰደ ክፍልም በ1968 በተሠራው ‹‹ማራቶን ማን›› በተባለው ፊልም ላይ ይገኛል። ‹‹ቪብራም›› የተባለ የአሜሪካ የጫማ አምራች ድርጅት በ2002 ‹‹ፋይቭ ፊንገርስ ቢቂላ” (FiveFingers Bikila) የተባለ ጫማ ለገበያ አቅርቧል።
አበበ ቢቂላ ከሺ ዓመት እስከ ሺ ዓመት ሲወደስ የሚኖር ህያው የጀግንነት ታሪክ የሠራው፤ በዚህ ዓለም በቆየባቸው 41 ዓመታት ውስጥ ነው። በአንጎል የደም መፍሰስ ምክንያት አበበ በ1965 ዓ.ም. ሲያርፍ፤ በከፍተኛ ኃዘን የተመታው የኢትዮጵያ ሕዝብ ታላቁን ጀግና ባለታሪክ በክብር ሸኝቷል። የአበበ ቢቂላ የቀብር ሥነሥርዓት የተፈፀመው ቀዳማዊ ኃይለስላሴ በተገኙበት በአዲስ አበባ የቅዱስ ዮሴፍ ቤተክርስቲያን መካነ መቃብር ነው።
ለማራቶኑ ቁንጮ ሻምበል አበበ ቢቂላ ታላቁ ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን “አበበ እንጂ መቼ ሞተ!!” ሲል የፃፈው ሥነግጥም እንዲህ ይላል።
የጎበዝ ነባቢት ነፍሱ
የሰው መዝርዕቱ አርአያ፤ የማይታጠፍ መንፈሱ
በጥራት የታጠፈለት፤ የምድር
አጥናፍና አድማሱ
የየብስ የአየሩ ነበልባል
የማራቶን እፁብ አይጣል
የምድር አለሙ ገሞራ
አገሩን በክብር ያስጠራ
ሳተናው እግረ ጆቢራ
ሎጋ ቢቂላ ዋቅጂራ፤
የጎበዛዝ ንጥረ ወዙ
የተስፋ ብርሃን መቅረዙ።
ስሙን ላገር ስም ሰይሞ፤ የምስራች ያስደወለ
ስንቱን ስንቱን ልበ ሙሉ፤ ከአድማስ
አድማስ ያስከተለ።
የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ
ያረጋት የኦሎምፒክ ዓርማ
በወገኖቹ ልቦና፤ ቀና ኩራት ያሳደረ
እንደፍላፃ በአክናፉ፤ የአየርን ሰርጥ የሰበረ
የፍስሃዋን አዋጅ ለዓለም፤ በአቅመ ወዙ ያስነገረ
በአገር ፍቅር ልቡን ሞልቶ፤ ላቡን ነጥቦ የዋተተ
የዓለምን ጀግና በአድናቆት፤ በቅን
ቅናት ያስሸፈተ
አልሞተም እንበል እባካችሁ፤ “አበበ
እንጂ መቼ ሞተ!”
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን የካቲት 23/2014