ኢትዮጵያዊቷ ወጣት አትሌት ያለምዘርፍ የኋላው የዓለም የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር ክብረወሰንን አሻሻለች።
የሃያ ሁለት ዓመቷ አትሌት ያለምዘርፍ ከትናንት በስቲያ በስፔን ካስቲሎን በተካሄደው የጎዳና ላይ ውድድር አሸናፊ ሆና ስታጠናቅቅ ያስመዘገበችው 29:14 ሰዓት የርቀቱ አዲስ የዓለም ክብረወሰን ሆኖ ተመዝግቧል።
የዓለም ግማሽ ማራቶን የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊዋ አትሌት ያለምዘርፍ የርቀቱን የቀድሞ ክብረወሰን በሃያ አራት ሰከንዶች ያሻሻለች ሲሆን ይህን ሰዓት ለማስመዝገብ በአማካኝ አንድ ኪሎ ሜትርን በ2:55 ደቂቃ ሮጣለች። በቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ የ10ሺ ሜትር የብር ሜዳሊያ አሸናፊዋ ትውልደ ኢትዮጵያዊት በባህሬን አትሌት ቃልኪዳን ገዛኸኝ ባለፈው ዓመት ጄኔቫ ላይ በተካሄደ ውድድር የተመዘገበው 29:38 ሰዓት የርቀቱ የቀድሞ ክብረወሰን እንደነበር ይታወቃል።
ያለምዘርፍ አዲሱን ክብረወሰን ባስመዘገበችበት ውድድር ጠንካራ ተፎካካሪ የነበሩ ኬንያውያን አትሌቶች ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።
ቪኮቲ ቼፕጌኖ ካለምዘርፍ በ1:59 ደቂቃ ዘግይታ ውድድሯን በሁለተኛነት ስታጠናቅቅ 30:14 ሰዓት አስመዝግባለች። ሌላኛዋ ኬንያዊት ሜርሲ ቺሮኖ በ30:48 ሰዓት ሶስተኛ ሆና አጠናቃለች። ‹‹ዛሬ ህልም እውን የሆነበት እለት ነው፣ በውድድሩ ተደንቄያለሁ፣ የውድድሩ የመጀመሪያ 5 ኪሎ ሜትሮች ፈጣን ነበሩ፣ እኔም በነዚህ ኪሎ ሜትሮች ታግያለሁ፣ ፈጣን በነበረው የሩጫ ትግልም የመቀጠል አቅሙ ነበረኝ›› በማለት ባለክብረወሰኗ ከድሉ በኋላ ለመገናኛ ብዙሃኃን አስተያየቷን ሰጥታለች።
ያለምዘርፍ ባለፈው የውድድር ዓመት በግማሽ ማራቶን በታሪክ ሁለተኛዋ ፈጣን አትሌት የሆነችበትን ሰዓት ማስመዝገቧ የሚታወስ ነው።
ያለምዘርፍ በግማሽ ማራቶን ቫልንሲያ ላይ ሁለተኛውን የዓለም ፈጣን ሰዓት ሁለተኛ ሆና ስታጠናቅቅ ባስመዘገበችበት ውድድር ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት ድንቅ አትሌት ለተሰንበት ግደይ የርቀቱን የዓለም ክብረወሰን ማሻሻሏ አይዘነጋም።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን የካቲት 22 /2014