(ንባብና ማንነት፤ የአንድ ስብዕና ሁለት ገጽታዎች)
ያለንበት ወቅት ህዳሴ ነው። አዎ ህዳሴ ነው፤ ለመሆኑም ምንም ጥርጥር የለውም። እንደገና ወደ ኋላ …… እየሆነብን ተቸገርን እንጂ የሚሌኒየሙ አጀማመራችን ዘመኑ ለእኛ የህዳሴ ዘመናችን መሆኑን፤ ወይም ህዳሴን “ሀ” ብለን ለመጀመር መዘጋጀታችንን የሚያረጋግጥ ነው።
ቻይና እና አንዳንድ አገራት “የባህል አብዮት”ን እንደ ርእዮት አለማቸው ማስፈፀሚያ፤ አላማቸው ግብ መምቻ አድርገውት ተሳክቶላቸዋል። በተለይ ቻይና በአለም ዙሪያ ምርጥ የተባሉ የህፃናት መጻሕፍትን ወደ ራሷ ቋንቋ በመተርጎምና የህፃናትን አእምሮ በማልማት ያለ ማንምና ምንም ተወዳዳሪ ንባብን እንደ መሸጋገሪያ ድልድይ በመጠቀሟ ዛሬ ራሷን ከተቀበረችበት በማውጣት ከአለም ቁ. 1 ተጠቃሽ አገር ሆናለች። ሌሎችም እንደዚሁ።
የአዲስ አበባ ከተማ ባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ የካቲት 9 ቀን 2014 ዓ.ም ባዘጋጀውና በአብርኆት ቤተ-መጻሕፍት በተካሄደው አራተኛው የንባብ ሳምንት (ከ20 በላይ የመጻሕፍት ሻጮችና የተለያዩ የመንግሥት ተቋማት የተካፈሉበትና ከ11ሺህ በላይ ተማሪዎችና የሚመለከታቸው አካላት የጎበኙት) ወቅት በተለያዩ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እንደተነገረው ከሆነ የንባብ አስፈላጊነት ከዚህ በመለስ የሚባል አይደለም።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትን በመወከል የዩኒቨርሲቲው የፓርትነርሺፕና ምርምር አካዴሚክስ ዘርፍ አማካሪ ሐረገወይን አሰፋ (ፕሮፌሰር) “መጽሐፍ የሥነ ልቦና ግንባታን ከማነፅ ረገድ ወደር የሌለው ነው፣ አገራዊ ችግሮችንም ለመፍታት ንባብ ቁልፍ ነው፡፡ ለዚህም እንደ ’ንባብ ሳምንት’ ዓይነት ንቅናቄዎችን በመፍጠር፣ ማኅበረሰቡ የንባብ ባህልን እንዲያዳብር ማገዝ ያስፈልጋል” ማለታቸውን፤ እንዲሁም “የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሒሩት ካሳው (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ንባብ ንቁ ዜጋን ለመፍጠርና ትውልድን ለመገንባት ትልቅ ድርሻ ያለው በመሆኑም የንባብ ሳምንቱ በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች በይበልጥ መስፋፋት አለበት።” ያሉትን፤ “[…]ሁሉም ዜጎች ከንባብ ሳምንት ንቅናቄ በተጨማሪ አስገዳጅ ሕግ ማውጣት እንደሚያስፈልግ፣ ለዚህም ቢሮው ከሚመለከታቸው ጋር በመሆን፣ መጻሕፍትን ማንበብ የሚያስገድድ ሕግ እንደሚወጣ ጠቁመዋል፡፡ “ መባሉን ይዘን የአሁኑን ወቅት ስለ ንባብ ሲባል እየተደረገ ያለውን ንቅናቄ፤ በተለይም የዲላውን “የወጣት ተኮር ንባብ እና የምርምር ንቅናቄ መድረክ”ን ከማድነቅ፣ አድንቆም ተሳታፊ፤ በተቻለ መጠንም ደጋፊ ከመሆን ውጪ ሌላ አማራጭ የለምና ለ”ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል!!!” እጅ መስጠት የግድ ይሆናል።
የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አምባሳደር ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፣ ጥር 24 ቀን 2014 አ.ም ዩኒቨርሲቲው ከ106 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያስገነባውን ሁለ-ገብና ዘመናዊ ቤተ-መጻሕፍት ባስመረቀበት ወቅት እንደተናገሩት ከሆነ ወጣቱ በማህበራዊ ሚዲያው ጥገኝነት ስር ወድቋል። በመሆኑም ከዚህ መውጣት አለበት። ለዚህ መፍትሄው ደግሞ እውቀትና ክህሎትን ማዳበር ሲሆን፤ ይህም ሊሆን የሚችለው እንደዚህ አይነት ተቋማት (ቤተ-መጻሕፍት)ን በመገንባት ነው። አዎ፣ ርቆ ተቀብሯል ስንል በሌላ መንገድ ዜጎች ለ ‘በሬ ወለደ’ ወሬ እጅ ሰጥተዋል ማለታችን ነውና ዶክተሩ “ጥገኝነት ስር ወድቋል” ካሉት ጋር በአቻነት ሊቆም የሚችል አተያይ ነው።
ባለፈው አመት፣ ግንቦት ወር “መጻሕፍት ለዕውቀት ገበታ፤ መዛግብት ለዘመን ትውስታ” (መርሁ ለዘንድሮው ንቅናቄም አገልግሏል) በሚል መርህ (የንባብ ሳምንቱ የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብት እና ቤተ-መጻሕፍት ኤጀንሲ ከሀረሪ ክልል ቱሪዝም፣ ባህል እና ቅርስ ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር የተዘጋጀ) የተጀመረው የንባብ ሳምንት ከሀረሪ ክልል በተጨማሪ በሌሎች ክልሎችም እንደሚቀጥል የተገለፀው በሥራ ላይ እየዋለና ለውጦችም እየታዩበት እንደሆነ ግንዛቤ እየተያዘ ይገኛል። በዚሁ መሰረትም የብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት ኤጀንሲ ቃሉንም እያከበረ፤ በቃሉም እየተመራ ወደ 2014 ዓ.ም የተሸጋገረ ሲሆን፤ እነሆ 2014ንም በቃሉ መሰረት ተግባሩን ከእቅዱ በማጣጣም ከግማሽ በላይ አድርሶታል።
ኤጀንሲው በዚሁ አመት፣ በሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ከይርጋለም ከተማ 8 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የወረዳ ከተማ ከወንሾ ወረዳ አስተዳደር እና ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ጽ/ቤት ጋር በመተባበር ጥቅምት 2 ቀን 2014 ዓ.ም በወንሾ ከተማ የንባብ ሳምንት፣ ዐውደ-ርዕይ፣ ዐውደ ውይይት የሕዝብ ቤተ-መጻሕፍት ምረቃ መርሐ ግብር አካሒዷል፡፡ ይህም ሊመዘገብለት ይገባልና ይበል ያሰኛል።
ኤጀንሲው ለሕዝብ እና ለትምህርት ቤቶች ቤተ-መጻሕፍት የመጻሕፍት ልገሳ ለማድረግ በያዘው ዝግጅት ውስጥ ከተያዙት አንዷ የበንሳ ወረዳ ስትሆን ለበንሳ ወረዳ የሕዝብ ቤተ-መጻሕፍት ለመስጠት መጻሕፍቶችን በመያዝ ቢጓዝም የሕዝብ ቤተ-መጻሕፍት አለመኖሩን ከኤጀንሲው ድረ-ገፅ ከተገኘው የወቅቱ ዜና መረዳት ይቻላል። ኤጀንሲው ብቻውን የንባብ ባህልን ለማዳበር ይቻለዋል የሚል አስተያየት ተገቢ እንዳልሆነ፤ ይልቁንም ከቀበሌው፣ ወይንም ከትምህርት ቤት ጀምሮ እስከ ላይኛው የመንግስት መወዋቅር ድረስ ያሉት አካላት ኃላፊነትና ትብብር የሚያስፈልግ መሆኑን መረዳት ይቻላል። ኤጀንሲው ምን ቢጥርና ቢተጋ ቢያንስ ቤተ-መጻሕፍት እንኳን ከሌለ ምንም ማድረግ አይቻለውም ነው። ይህ እንግዲህ አንዱ ገጠመኝ ነው። (በብር 134,564.50 /አንድ መቶ ሠላሳ አራት ሺህ አምስት መቶ ስልሳ አራት ብር ከሃምሳ ሳንቲም/ በሆነ ወጪ ተገዝተው ለበንሳ የሕዝብ ቤተ-መጻሕፍት በስጦታ የተሰጡትን አንድ ሺህ መጻሕፍት ለግዜው የሕዝብ ቤተ-መጻሕፍት እስኪመቻች ድረስ ለቀዌና ጋጣ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡)
ኤጀንሲው እዚህ ድረስ ይሂድ እንጂ፣ በየደረጃው ያሉ አካላት ቢያንስ ቤተ-መጻሕፍት እንኳን መስራት ካልቻሉ የንባብ ባህል በራሱ እውን ሊሆን አይችልምና እዳው ገብስ አይደለም። የጋራ ጥረትና ግረትን የግድ ይላል። ከዚህ አኳያ የሚመለከታቸው የጌዴኦ ዞንና ዲላ ከተማ ኃላፊዎች ዞኑን የሚመጥን ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት ለመገንባት በመዝጊያ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ቃል መግባታቸውን ኃላፊነትን ከመወጣት አኳያ ሊመሰገኑ ይገባል ስንል የተበረከተላቸውን የመጻሕፍት ስጦታ የሚያስቀምጡበት ቤተ-መጻሕፍት አለማጣታቸውንም በመጥቀስ ነው።
ሕዳር 24 ቀን 2014 ይፋ በተደረገ አንድ ዜና እንደተገለፀው፣ ስንቅና ሌሎች ድጋፎችን ሳይጨምር፣ በጎንደር አካባቢ በጦርነቱ ለወደሙ ት/ቤቶች 4ሺህ 400 መጻሕፍት፣ በኦሮሚያ ክልል ለወደሙ ት/ቤቶች 4ሺህ 400 መጻሕፍት እና ለመከላከያ ሠራዊት 500 መጻሕፍት እና ምግብ ነክ እንዲሁም ለተፈናቃዮች የሚውሉ አልባሳት ከሠራተኛው ሲያሰባስብ በተጨማሪም ለመከላከያ ሠራዊት የ300ሺህ ብር የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን አስታውቋል፡፡ ይህም መልካም ተግባር ነውና ኤጀንሲው ጥሩ እየሄደ ነው ማለት ነው።
ኤጀንሲው (አንጋፋውና በ1936 ዓ.ም የተመሠረተው ብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት ኤጀንሲ (ወመዘክር)) ከሠላም የሕጻናት መንደር ጋር በመተበበር “ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል!!!” በሚል መሪ ቃል የንባብ ሳምንት፣ ዓለም አቀፍ የሕጻናት ቀን፣ የመጻሕፍት አውደ ርዕይና አውደ ውይይት መርሐ ግብር ማካሄዱንም (ኅዳር 25/2014 ዓ.ም)፤ ስለዚሁ፣ እየተነጋገርንበት ስላለው የተቋሙ የ2014 ዓ.ም ተግባርና እንቅስቃሴዎቹ ሲባል መገለፅ ይገባዋልና ይበል ያሰኛል ብንል ያስኬደናል። ግን ደግሞ፣ አሁንም ቢሆን ብቻውን የትም ሊደርስ እንደማይችል ሊታወቅ ይገባል። ከኤጀንሲው ለመንደሩ (ለሠላም ሕጻናት መንደር) የተዘጋጀው የሕጻናት የተረት መጻሕፍት፣ የመማሪያና ታሪክ እንዲሁም ልብ ወለዶች በቁጥር 1ሺህ 100፤ 85ሺህ ብር የፈጁ መጻሕፍት የተቋሙ መስራች ለሆኑት ለወ/ሮ ጸሐይ ሮስሊ አቶ ያሬድ ተፈራ ማበርከቱም ሊያስመሰግነው ግድ ይላል። የንባብ ባህል …. ሲባል ለሁሉም፣ በሁሉም ነውና የመንግስት የግል ሳይል መንቀሳቀሱም እንደዛው።
በቱሉ ዲምቱ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ስር አዲስ ለተመረቀው ኖኃተ ሰላም ቤተ-መጻሕፍት የተለያዩ ይዘት ያላቸው፣ በ45‚012 /አርባ አምስት ሺህ አስራ ሁለት ብር/ ወጪ የተገዙ 400 መጻሕፍት በስጦታ ያበረከተውም በዚሁ አመት ኅዳር ወር ላይ መሆኑን ልብ ስንል ኤጀንሲው አመቱን የንባብ ባህልን ርቆ ከተቀበረበት ማውጣት ተግባር ላይ እያዋለው ነው ማለት ይቻላልና ሁሉም ሊያግዘው ይገባል።
እንድገመው፣ በተለይ ርቆ የተቀበረው የንባብ ባህላችን ከተቀበረበት ተቆፍሮ ይወጣ ዘንድ እየተከፈለ ያለ መስዋዕትነት ነውና ከዚህ አኳያ ኤጀንሲው ሁሌም ቢፈከርለት አይበዛበትም እንላለን።
ሰሞኑን በደቡብ ክልል፣ ጌዴኦ ዞን፣ ዲላ ከተማ በተካሄደው ተመሳሳይ መድረክና ንቅናቄ ላይም የተደረገው ተመሳሳይ ተግባር ሲሆን፤ ኤጀንሲው በ800ሺህ ብር ወጪ የገዛቸውን ከስድስት ሺህ በላይ መጻሕፍት በዞኑ ስር ለሚገኙና ከትምህርት ቤቶች ጀምሮ ላሉ ተቋማት ማስረከቡም ከዚሁ ጋር በተደማሪነትና ተከታታይ ተግባርነት ሊመዘገብለትና ሊመሰገንበት የሚገባው ተግባሩ ነው ስንል ማዕከላችን የተስፋ ገብረ ሥላሴ “እውቀት እንዲስፋፋ፤ ድንቁርና ይጥፋ!!!” ነው።
“በቀን 500 ገጽ አንብብና ዕውቀት በሕይወትህ ላይ እንዴት እንደሚሰራ ታውቃለህ” የሚለውንና ሥራውን በሚጀምርበት አካባቢ በየቀኑ ከ600 እስከ 1000 ገጽ ያነብ የነበረውን አሜሪካዊው ቱጃር ዋረን ቡፌትንና መሰሎቹን ታሪክ ሹክ የሚለን፣ በአጠቃላይም “በዓለማችን ላይ በንባብ ምክንያት ሥራቸውንና ምኞታቸውን ያሸነፉ ሀብታሞች ጥቂቶች አይደሉም። በባለፀጋ ሰዎች ዙሪያ የተደረገ ጥናት እንደሚጠቁመው 1ሺህ 200 ሀብታሞች ከንባብ ጋር የተቆራኘ ምስክርነት ያላቸውም” ናቸው ሲል የሚናገረው የ”ታዛ”ው ዓለማየሁ ገበየሁ በአንድ የመጽሔቱ እትም ላይ እንዳሉት፤ ማንበብ:-
… ዓለምን ከአዲስ እይታ አንፃር እንድንመለከት ስለሚያደርግ ባለብዙ አይን ያደርገናል። አእምሮን በተለያዩ ሀሳቦች መመገብ የተለያዩ እሳቤዎች ተዳቅለው አዲስ መረጃ እንዲፈጠር ያደርጋል። ይህም ሥራ በፈጠራ እንዲታጀብ የራሱን ሚና ይጫወታል። ቲዮዶር ሩዝቬልት እንደሚለው ንባብ ንፁህ የምናብ ህክምና ነው። ራስን ጥሩ መጽሐፍ ውስጥ መዝፈቅ ምርጥ ፊልም እንደመመልከት ነው – ወደ አዲስ ዓለም ይዞ ይመነጠቃል። ጥሩ ጸሐፊና ንግግር አዋቂ ከማድረጉ በተጨማሪ የግባችንን አንካሴ ወደምንመኘው አቅጣጫ እንድንወረውር መደላድሉን ያመቻቻል። አንዳንድ ጊዜ ለአንዳንድ ነገሮች ልዩ አድናቆት አይኖረንም፤ ምክንያቱም ጉዳዩ ወይም ሁኔታው ምን ያህል አስደናቂ እንደሆነ መረጃው ወይም ዕውቀቱ ስለማይኖረን ነው። ንባብ በዙሪያችን ያሉትን ብቻ ሳይሆን አርቀንም ስለ ዓለም ያለን ዕውቀት እንዲሰፋ በዛው ልክ አድናቂ እንድንሆን ያደርጋል። ስለ ዓለም ብዙ ባወቅን ቁጥር ከተለያዩ ሰዎች ጋር በልበሙሉነት ውይይት ለማድረግ የሚያስችል ርዕሰ ጉዳይም ታጥቀናል ማለት ነው።
እውነቱ እንግዲህ ይህ ነው፤ ዓለማየሁ ገበየሁ በገለፁት ልክ እና በላይ።
በዲላው “የወጣት ተኮር ንባብ እና የምርምር ንቅናቄ መድረክ”ም የተለያዩ መጻሕፍት የቀረቡ ሲሆን፣ ትውልዱን በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙርያ ዕውቀት በማስጨበጥ የተሻለችና የተረጋጋች አገርን ለመፍጠር ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው በተለያዩ አካላት በስፋት ተገልጿል። ውይይት በተካሄደባቸው መድረኮች ሁሉ የተገኙ ተሳታፊዎችም “አነባለሁ”ን ቃል ገብተዋል። ከ10 በላይ የመጻሕፍት መደብሮች እስከ 50 በመቶ ድረስ የዘለቀ የመጻሕፍት ዋጋ ቅናሽን ይዘው የቀረቡ ሲሆን ገበያውም እጅግ የደራ እንደነበር በቦታው በመገኘት ለማየት ተችሏል። የኅብረተሰቡም “ይህ አይነቱ መድረክ እንዳይቀረጥ” አስተያየትን በቅርብና በስፋት ማየት የተቻለ ሲሆን በተለይ በዞኑና ከተማዋ አስተዳደር አካላት በኩል ተቀባይነት ያገኘ የሕዝብ አስተያየት መሆኑንም ንቅናቄውን አስመልክቶ በተካሄዱ ልዩ ልዩ ውይይቶች ላይ ከተነሱት ሀሳቦች መረዳት ተችሏል።
በአጠቃላይ የዲላው፣ “መጻሕፍት ለእውቀት ገበታ፤ መዛግብትና የጽሑፍ ቅርስች ለዘመን ትውስታ።” በሚል መሪ ቃል የተካሄደው “የወጣት ተኮር ንባብ እና የምርምር ንቅናቄ መድረክ” ጸሐፊ እምነት በጥሩ ሁኔታ ያለፈ ሲሆን ወደ ፊት በዚህና ሌሎች የዚሁ ጋዜጣ አምዶች ላይ ራሳቸውን የቻሉ የተለያዩ ጽሑፎች የሚወጡ መሆኑን ከወዲሁ መጠቆም ያስፈልጋል። ይህን የምናደርግበት አቢይ ምክንያት ደግሞ ይዘን ለተነሳነው “ርቆ የተቀበረውን የንባብ ባህል እንደገና . . . (ንባብና ማንነት፤ የአንድ ሰብዕና ሁለት ገጽታዎች)” ርእስ ተገዥ የመሆናችን፤ እንዲሁም፣ በሰሞኑ ዜናዎቻችን “የዞኑ አስተዳደር ተወካይ እና የዞኑ ትምህርት ጽ/ቤት የሆኑት አቶ ዘማች ክፍሌ እንደገለፁት ከሆነ [የወጣት ተኮር ንባብ እና የምርምር ንቅናቄ መድረክ] ወጣቱን አነቃቅቷል፤ የንባቡ ስሜቱን ቀስቅሷል፤ የመማርን መሰረታዊነት አስርጿል፤ የማንበብን የማይተካ ሚና በአግባቡ እንዲገነዘብ አድርጓል፡፡ መበልፀግ የሚቻለው በበለፀገ አእምሮ ነውና ይህን ከማስገንዘብ አንፃር መድረኩ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል።” ማለታቸውን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ነው። ቸር እንሰንብት።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን የካቲት 21 ቀን 2014 ዓ.ም