ዓለማችን በውብ የተፈጥሮ ስጦታዎች የታደለች በውስጧ እልፍ ሚስጥር የያዘች ነች። በምድራችን ላይ ከማይታዩ ህዋሳት እስከ ግዙፋን ፍጥረታት፤ ከደቂቅ እፅዋት ጥቅጥቅ እስካለው ደን፤ ከምድረ በዳ እስከ ጥልቅና ሰፋፊ ውቅያኖሶችን በማካተት በአስደናቂ ስነ ምህዳር የታጀበች ነች።
ታዲያ የሰው ልጆች የሚኖርባቸው እነዚህ ክፍላተ ዓለማት እንደየፈርጃቸው ከእነዚህ የተፈጥሮ ፀጋዎች ውስጥ የየድርሻቸውን ይይዛሉ።
የሰው ልጆችም ከአንዱ አገር ወደሌላኛው ክፍል እየተዘዋወሩ የተፈጥሮ ስጦታዎችን ይመለከታሉ ያደንቃሉ። የቱሪዝም ዘርፍ ምድራችን ያደለችንን ፀጋዎች በሚገባ ማወቅ እንድንችል የሚያደርግ አንድ ዘርፍ እንደመሆኑ መጠን ከላይ ያነሳነውን “ተፈጥሮን” የማስተዋወቅ ስራን የምንሰራበት ነው።
ይህ ዘርፍ አያሌ የታሪክ፣ የባህል፣ የቅርስ እና ሌሎች ሃይማኖታዊና የማህበረሰብ እሳቤዎችን የሚያስተዋውቅ ሰፊ ፅንሰ ሃሳብ ጭምር ሲሆን “የተፈጥሮ” መታደሎችንም በሰዎች ሳይንሳዊ እሳቤ የመረዳት ልክ አዳዲስ እይታዎችና ሥርዓቶች እንዲኖረን ያደርጋል።
በተፈጥሮ ቱሪዝም ውስጥ የሰው ልጆች በራሳቸው አቅምና ፍላጎት ከፈለሰፉት ባህላዊና ታሪካዊ ሃብቶች በተለየ ከእኛ ያልሆኑ ይልቁንም “ልክ እንደ እኛው” ሁሉ የተፈጠሩ ግኡዝና ሕይወት ያላቸው አካላት ላይ ያተኩራል። የሰው ልጆችም መልክአ ምድሮችን፣ የዱር እንስሳትን፣ ውቅያኖሶችን ሌሎች መሰል ፍጥረቶችን የሚያውቁበት፣ መስተጋብር የሚፈጥሩበትና መንፈሳቸውን በጉብኝትና የሚያድሱበት ነው። ከተፈጥሮ ቱሪዝም ውስጥ በስፋት ትኩረትን የሚስበው “የዱር እንስሳትና አእዋፋት” የኑሮ ዘይቤና አፈጣጠር ነው።
የዓለማችን ጎብኚዎች ተመራማሪዎች ስለ እነዚህ በታላላቅና ሰፋፊ ደኖች፣ በረሃዎች እንዲሁም ሰማያት ላይ የሚንቀሳቀሱ ፍጥረታት መረዳትና ማወቅ በእጅጉ ይስባቸዋል። የቱሪዝም ዋንኛው አንቀሳቃሽ ኃይልም ናቸው። በዓለማችን ላይ እነዚህን ሃብቶች ተጠብቀው ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው እንዲኖሩ እጅግ ሰፋፊ ፓርኮችና ጥብቅ ቦታዎች ይገኛሉ።
ኢትዮጵያም በተመሳሳይ የእነዚህ ፓርኮች፣ ጥብቅ ቦታዎች ባለቤት ናት። አገሪቱ ያላትን የዱር እንስሳትና አእዋፋት ሃብቶች በበቂው አስተዋውቃ ተገቢውን ጥቅም አግኝታለች የሚል ድምዳሜ ላይ የሚያስደርስ መረጃዎች ባይኖርም፤ በውጭም ይሁን በአገር ውስጥ ጎብኚዎች፣ አጥኚዎችና ባለሙያዎች ዘንድ በቀዳሚነት ተመራጭ የሆነው ይሄው ሃብቷ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።
የተፈጥሮ ቱሪዝምን በተለይም “የዱር እንስሳት” መኖሪያ ፓርኮችን ለመጠበቅ እንዲሁም ሃብቶቹን ለማስጎብኘት በርካታ ጥረቶች እንደሚደረጉ ቢታወቅም ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ ህገወጥ እንቅስቃሴዎችም አሉ።
በዋናነትም በህግ ያልተፈቀደ አደንና የዱር እንስሳት ንግድ ተጠቃሽ ነው። አገራችን ኢትዮጵያም ሆነች ቀሪው ዓለም ህገወጥ አደንና ንግድን ለመከላከል ጠበቅ ያሉ ህጎችን ቢያወጡም በተደራጀ ረቂቅ ሰንሰለታማ የኮንትሮባንድ ንግድ ምክንያት ድርጊቱ ይፈፀማል። ይሄም ብርቅዬ እንስሳቶች እንዲመናመኑና እንዲጠፉ ከማድረጉም በላይ የቱሪዝም ዘርፉ እንዲዳከም አይነተኛ ምክንያት ነው።
በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ፓርኮችን፣ ጥብቅ ቦታዎችንና ከተፈጥሮ ጋር የተያያዙ የቱሪዝም ሃብቶችን እንዲጠብቅ፣ እንዲያለማና እንዲያስተዳድር በህግ ተግባርና ሃላፊነት የተሰጠው የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ነው። ከዚህ ከህገወጥ አደን ጋር በተያያዘም ድርጊቱን ለመከላከል በርካታ የቁጥጥር፣ ክትትልና ሌሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ያከናውናል።
የዱር እንስሳት ህገወጥ አደን እንዲቆም ከሚሰሩ ስራዎች ውስጥ ድንበር ተሻጋሪ ምክክሮችን፣ የቁጥጥር ስርዓት ዝርጋታና መሰል ተግባራትን ማከናወን ነው። ባሳለፍነው የካቲት 14 ቀንም ህገወጥ የዱር እንስሳት አደንን መከላከልና ከእርሱ ጋር ተያይዞ ስለሚደርሱ ጉዳቶች በተመለከተ አውደ ጥናት አካሂዶ ነበር። የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አመራሮች ከዚህ አደን ጋር የተያያዘ ርእሰ ጉዳይ ላይ መረጃዎችን ለዝግጅት ክፍላችን አድርሰዋል። አቶ ናቃቸው ብርሌው የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን የኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ ዳይሬክተር ናቸው።
አውደ ጥናቱን አስመልክቶ ሲናገሩም፤ ህገ-ወጥ የአቦ ሸማኔ አደንና ንግድን ለመከላከል በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ያለው የኢትዮጵያ፣ የመን እና ሱማሊያ የህግ ባለሙያዎችን ያሳተፈው አውደ ጥናት የአገራቱን የጋራ ትብብርና የህግ ማስከበር አቅም ይበልጥ የሚያጠናክረው እንደሆነ ይናገራሉ።
በአፍሪካ ቀንድና በመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢዎች በሕይወት ያሉ የአቦ ሸማኔ ግልገሎችን ሕገ-ወጥ የዱር እንስሳት ንግድን ለማስቆም የሕግ አስከባሪ አካላትን የክህሎት፣ የበይነ-ኤጀንሲዎች ትብብር መምሪያ ዝግጅት አቅም ማሳደግ ወሳኝ ጉዳይ ነው።ለዚህ ይረዳ ዘንድ የአቦ ሸማኔ ጥበቃ ፈንድ (CCF) አለማቀፍ የእንስሳት ደህንነት ፈንድ( IFAW) እና ሌጋል አትላስ(La) የዱር እንስሳት ጥበቃና የሕግ አስከባሪ ኃላፊዎች የአቅም ግንባታ አውደ ጥናት ከየካቲት 14-18 በአዲስ አበባ ኢትዮጵያ መካሄዱንም ይገልፃሉ።
“ከኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት፣ ከሱማሌ ክልላዊ መንግሥት፣ ከሶማሊያና ከየመን አገራት የተወጣጡ ተወካዮች በህገ-ወጥ የአቦ ሸማኔ ንግድን በህግ አግባብ መግታት (LICIT) የአቦ ሸማኔ ሕገ-ወጥ ንግድ የሕጋዊ መረጃ ልውውጥ ሥልጠና ተሳትፈዋል” ያሉት የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ፤ የኤል-አይ-ሲ-ይቲ ፕሮጀክት በሕገ-ወጥ የዱር እንስሳት ንግድ መከላከያ ፈንድ አማካኝነት ከዩ ኬ መንግሥት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ መዘጋጀቱን ገልፀዋል።
የሥልጠናው አውደ ጥናቱ በኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን (ኢዱጥባ) አስተናጋጅነት እና ድጋፍ መካሄዱንም ነው የተናገሩት። አውደ ጥናቱ በዱር እንስሳት ሕግ ማስከበር የፖሊሲና የኦፕሬሽን ጉዳዮች ላይ ትምህርትና ሥልጠና እንደሚሰጥ የገለፁት የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ፤ ይህም የዱር እንስሳት ሕጎችን ማጠናከርና ማጠቃለል፣ የዱር እንስሳት ልየታና የምርመራ ቴክኒኮችን፣ ብሔራዊ የጸረ ሕገወጥ ንግድ መርሃ ግብር ዝግጅትን እንደሚጨምር ነው የሚያስረዱት።
በዋነኝነት ትኩረቱ በሕገ-ወጥ የአቦ ሸማ ንግድ ላይ ሆኖ በጸረ ሕገ-ወጥ የዱር እንስሳት ዝርያዎችና የዱር እንስሳት ውጤቶች ሕገ-ወጥ ንግድ ዙሪያ በስፋት ጥቅም ላይ የሚውል የእውቀት ሽግግር የተደረገበት መሆኑን ጠቁመዋል።
“አውደ ጥናቱ በተሳታፊ አገሮች መካከል በዱር እንስሳት ላይ የሚፈጸሙ ህገ-ወጥ ተግባራትን ለመከላከል ግንኙነትና የመረጃ ልውውጥን ይበልጥ በማጠናከር የግንኙነትና የኔትወርክ መድረክ ሆኖ ያገለግላል” ያሉት አቶ ናቃቸው፤ ህገ-ወጥ አደን እንዲሁም የዱር እንስሳትና ውጤቶቻቸው ሕገ-ወጥ ዝውውር በመላው ዓለም ለሚገኙ የዱር እንስሳት ዝርያዎች መመናመን መንስኤዎች እና ዋና ስጋቶች እንደሆኑ ገልፀዋል።
የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ሕገ ወጥ ንግድ እንደ አቦ ሸማኔ እና መሰል የዱር እስሳት ዝርያዎችን ከምድረ ገጽ እንዲጠፉ የሚያደርግ ነው።በሕገ ወጥ የዱር እንስሳት ንግድ ከፍተኛ ስጋት ላይ ከወደቁት ዝርያዎች አንዱ አቦ ሸማኔ ነው።የአቦ ሸማኔ ጥበቃን የሚያግዘው የሲሲኤፍ ጥናት እንደሚያመለክተው ዓለም ባለፉት 100 አመታት ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑ አቦ ሸማኔዎችን አጥታለች።እስካሁን በዱር የሚገኙ ያደጉ አቦ ሸማኔዎች ብዛት ከ7 ሺህ 500 እንደማይበልጥ ጥናቱ ይጠቁማል።
ባለፉት ሁለት አስርት አመታት የሲሲኤፍ ተመራማሪዎች በሁለት ክልሎች መካከል ባሉት የአቦ ሸማኔ ግልገሎች ላይ ክትትል ሲያደርጉ ቆይተዋል፣ እ.ኤ.አ በ2010 እና በ2019 መካከል 300 የሚደርሱ የአቦ ሸማኔ ግልገሎች ከአፍሪካ ቀንድ መልክአ ምድር የህገ-ወጥ ዝውውር ሰለባ ሆነዋል።ግልገሎቹ በሰውና በዱር እንስሳት መካከል ባለው ግጭት እንዲሁም በቤት እንስሳት መልክ አላምዶ ቤት ውስጥ ለማኖር ፍላጎት ባላቸው ህገ ወጥ አዘዋዋሪዎች።
ከአፍሪካ ቀንድ ዕድሜያቸው ከፍ ያሉ አቦ ሸማኔዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ መመናመን ጋር ተያይዞ አስቸኳይ የመፍትሄ እርምጃ ካልተወሰደ ዝርያቸው በጥቂት አመታት ውስጥ ከአካባቢው እንደሚጠፋ የዱር እንስሳት ጥበቃ ተቆርቋሪዎች ያላቸውን ስጋት ይገልፃሉ። የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ ጉዳዩን አስመልክተው ሲገልፁ፤ ኢትዮጵያ ዋነኛዋ የምሥራቅ አፍሪካ የአቦ ሸማኔ መዳረሻ አገር ናት።
ይሁን እንጂ በሕገ ወጥ የዱር እንስሳት ንግድ ምክንያት በአገሪቱ ያሉ የአቦ ሸማኔ ዝርያዎች ቁጥር በእጅጉ እየቀነሰ መምጣቱ የሚያሳዩ ብዙ ምልክቶች አሉ። የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ሕገ ወጥ የዱር እንስሳት ንግድን ለመከላከልና የአቦ ሸማኔዎችን ሕይወት ለመታደግ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ በማንሳትም፤ ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ይህን ሕገ-ወጥ ተግባር ለመከላከል የባለድርሻ አካላት ቅንጅትና ትብብር ቅድሚያ የሚሰጠው እና አስፈላጊ በመሆኑ ይህን አውደ ጥናት በኢትዮጵያ ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።
የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ባሳለፍነው መስከረም ወር “ሲሲኤፍ፣ አይኤፍኤደብልዩ እና ኤልኤ” በሃርጌሳ ተመሳሳይ የአምስት ቀን ስልጠናዎችን ሰጥተው ነበር።
የሁለቱም አውደ ጥናቶች አላማ የተሳታፊዎችን የአካባቢና የዱር እንስሳት ሕጎች እውቀት በመጨመርና የተያዙ ግልገሎችን አያያዝና የቀልጣፋ የወንጀል ምርመራ ተግባራዊ ትምህርት በመስጠት ሕገ ወጥ የአቦ ሸማኔ አደን እና ሕገ ወጥ ንግድ እንቅስቃሴዎችን እንደሆነ ለማወቅ ችለናል። “በሕገ ወጥ መንገድ በተያዙ ዝርያዎች ልየታና በመከላከል ሥልጠና (ዲስራፕት) አማካኝነት አይኤፍኤደብልዩ የአቦ ሸማኔ ግልገሎችን ከጎሬያቸው ለቆዳቸው ለብርቅ እንስሳት ኢንዱስትሪ የሚሸጡ ድርጅቶችንና ግለሰቦችን ለመከላከል የሚፈጠሩ ኔትወርኮችን ያመቻቻል።
ይህን የመሳሰሉ አውደ ጥናቶች በሕግ አስከባሪ ኦፊሰሮች መካከል የግንኙነትና የመረጃ ልውውጥ ቀላል ኔትወርኮችን በመፍጠር ከዱር እንስሳት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የሚያሳልጡና ድንበር ዘለል ሕገ ወጥ የዱር እንስሳት እንቅስቃሴን ለመቀነስ መድረክ ሆነው ያገለግላሉ” ሲሉ የአይኤፍኤደብልዩ የዱር እንስሳት ወንጀል ዳይሬክተር ማት ሞርሌ ገልፀዋል።
የአቦ ሸማኔ ሕገ ወጥ ንግድ ዋና አንቀሳቃሽ ሞተር በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው የብርቅዬ እንስሳት የገበያ ፍላጎት ቢሆንም በመገኛ አገሮች ያለው የህግ አፈፃፀም ድክመት ሌላ መንስኤ መሆኑን የሚያነሱት ዳይሬክተሩ፤ የሰው እና የዱር እንስሳት ግጭት ከእነዚህ አዳኝ እንስሳት ጋር ተስማምቶ መኖርን አስቸጋሪ እንዳደረገው አንስተዋል። የአየር ንብረት ለውጥ በግብርናና በሰዎች ኑሮ ላይ ያስከተለው ተጽእኖም ችግሩን እንዳባባሰው አመላክተዋል።
በተመሳሳይ ጉዳዩን በማስመልከት “ሕገ ወጥ ንግድን ካስቆምን በኋላም በአፍሪካ ቀንድ የዱር አቦ ሸማኔዎች ጥበቃ ሥራችን ገና መጀመሩ ነው” ሲሉ የሲሲኤፍ መሥራችና ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሎሪ ማርከር ገልፀዋል።የኤልአይሲአይቲ ፕሮጀክት ለአመቻቸው ዕድል ምስጋናቸውን የገለፁት ዋና ዳይሬክተር ችግሩን ከመሰረቱ መለየት እንዳስቻላቸው እና አውደ ጥናቱ የአቦ ሸማኔ ዝርያዎችን ህልውና ለመታደግ ተስፋ ሰጪ ነው ” ብለዋል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን የካቲት 20 /2014