ሕይወት በመስጠት ሂደት ሕይወት እንዳይቀጠፍ በሚለው ፅንሰ ሃሳብ መሰረት እናቶች በተለይ በእርግዝና እና በወሊድ ጊዜ ተገቢውን የጤና እንክብካቤ ማግኘት እንዳለባቸው ምንም የሚያጠያቅ ጉዳይ አይደለም።
ሆኖም ዛሬም በየዕለቱ ከወሊድ ጋር በተያያዘ በርካታ እናቶች ይሞታሉ።አዳዲስ ጨቅላዎችም ሕይወታቸው አልፎ ይወለዳሉ።ከዚህ አንፃር ብዙ ስራዎች እንደሚቀሩ የዘርፉ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ። በአዲስ አበባ ከተማ ለረጅም ዓመታት የእናቶች የወሊድ አገልግሎት ሲሰጡ ከቆዩ ሆስፒታሎች ውስጥ አንዱ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ ነው።
ሆስፒታሉ በተለይ ከመላው አዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ ጤና ጣቢያዎች በሪፈር ለሚመጡ እናቶች የወሊድ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል።ከአዲስ አበባ ከተማ በዘለለ በዙሪያዋ በተለይ ደግሞ ከቡራዩና አካባቢው ለሚመጡ እናቶችም አገልግሎት በመስጠት በወሊድ ምክንያት ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን በመቅረፍ የበኩሉን ሚና ተጫውቷል።
ከዚህ ባለፈ ሆስፒታሉ የቀዶ ህክምና የወሊድ አገልግሎትን በአቅራቢያው በሚገኙት የኮልፌና የፈለገ መለስ ጤና ጣቢያዎች ውስጥ በማስፋት እናቶች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችሏል።
ከቅርብ ግዜ ወዲህ ደግሞ በሆስፒታሉ የሚታየውን የቀዶ ህክምና ወሊድ አገልግሎት ጫና ለመቀነስ በተለይ እናቶች በአቅራቢያቸው በቀዶ ህክምና የወሊድ አገልግሎት እንዲያገኙ አገልግሎቱ ቡራዩ አካባቢ የሚሰጥበትን ሁኔታ አመቻችቷል። ዶክተር ማራማዊት አስፋው በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ የሜዲካል ስኩል ዲን ናቸው።እርሳቸው እንደሚሉት በጤና ጣቢያ በቀዶ ህክምና የማዋለድ አገልግሎቱ ከተጀመረ ስድስት አመታትን አስቆጥሯል።
ይህም አገልግሎት የተጀመረው በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል አቅራቢያ ባሉት የኮልፌና ፈለገ መለስ ጤና ጣቢያዎች ውስጥ ነው።ዋነኛ አላማውም ጤና ጣቢያዎቹን በቀዶ ህክምና የወሊድ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማብቃት ነበር።
በዚህም እንዲህ አይነቱን የወሊድ አገልግሎት በጤና ጣቢያዎቹ ውስጥ እንዲሰጥ ለማስቻል የጤና ጣቢያዎቹን ህንፃዎች ከማስተካከልና ለዚሁ አገልግሎት አመቺ እንዲሆኑ ከማስቻል ጀምሮ የህክምና መሳሪያዎችን የማስገባት ስራዎች ተሰርተዋል።
በኮልፌ ጤና ጣቢያ የቀዶ ህክምና የወሊድ አገልግሎት ሲጀመር የቀዶ ህክምና ባለሙያዎቹ ሙሉ በሙሉ ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የተመደቡና በስፔሻሊቲ ትምህርት ስልጠና ላይ ያሉ ነበሩ።ሆኖም በፈለገ መለስ ጤና ጣቢያ ህንፃው እንዲደራጅ በማድረግ ከጳውሎስ ሆስፒታል ጋር በመሆን የጤና መኮንኖች ገብተው አገልግሎቱን እንዲሰጡ ተደርጓል። አገልግሎቱ ወደ ቡራዩ እንዲሰፋ የተደረገው ግን በቅርቡ ነው።
በቅርቡ ቡራዩ ላይ በተጀመረው የቀዶ ህክምና ወሊድ አገልግሎት አነስተኛ ቁጥር ያላቸው እናቶች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ነበሩ። ይሁንና በዚህ በጀት ዓመት በስድስት ወራት ውስጥ 600 የሚሆኑ እናቶች በቀዶ ህክምና / caesarean section /እንዲወልዱ ተደርጓል።በኮልፌና በፈለገ መለስ ጤና ጣቢያዎች ደግሞ ቁጥራቸው ከ200 እስከ 250 የሚሆኑ እናቶች በየወሩ በቀዶ ህክምና ወልደዋል።
ይህ ቁጥር ግን አገልግሎቱን ፈልገው በምጥ የተገላገሉ እናቶችንም ይጨምራል። እንደ ዶክተር ማራማዊት ገለፃ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የሪፈራል ሆስፒታል እንደመሆኑ ከተመደቡለት ጤና ጣቢያዎች የሚመጡ እናቶችን ተቀብሎ ያስተናግድ ነበር።እነዚህ እናቶች ቀላልና እዛው በጤና ጣቢያዎች መስተናገድ የሚችሉ ሆኖ ነገር ግን ሆስፒታል እስከሚደርሱ ድረስ ልዩ ልዩ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል።
በተለይ ደግሞ በሆስፒታሉ አቅራቢያ ከሚገኙት ኮልፌና ፈለገ መለስ ጤና ጣቢያዎች በተለየ ከቡራዩ አካባቢ የሚመጡ እናቶች ረጅም መንገድ ይጓዛሉ። በዚህ ሂደትም የመንገድ መዘጋት ሊያጋጥማቸው ይችላል።በዚህም አንዳንዴ ምጥ ላይ የሚከሰቱ ችግሮች ጊዜ የማይሰጡ ሊሆኑ ይችላሉ።
ከዚህ አኳያ እናቶቹ የተለያዩ የጤና ችግሮች ሊያጋጥማቸው ይችላል።የእነርሱም ሆነ የልጃቸው የመኖር እድልም አደጋ ላይ ይወድቃል። ሆኖም እናቶች ባሉበት አካባቢ ተጓዳኝ የህክምናና የቀዶ ህክምና ወሊድ አገልግሎቱን እንዲያገኙ መደረጉ ብዙ ሳይንገላቱ እንዲወልዱ ያስችላቸዋል። እነዚህ ተቋማት በቀዶ ህክምና እናቶችን ማዋለድ ጀምረዋል ማለት ግን ሁሉንም ነገር ይሰራሉ ማለት አይደለም።
ሁሉም አገልግሎት ማዋለድ ቢሆንም ተጨማሪ ተጓዳኝ ችግሮች ያሉባቸው፣ የምጡ ጊዜ ያልደረሰ ከሆነ፣ ተጨማሪ እንክብካቤ ለልጁም ለእናቲቱም አስፈላጊ ሲሆን ወደ ሆስፒታሉ መጥተው እንዲገለገሉ ይደረጋል።ቀለል ያሉ ችግሮችና አነስተኛ የቀዶ ህክምና የሚጠይቁ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ግን እዛው በጤና ጣቢያዎቹ ውስጥ እንዲጠቀሙ ይደረጋል።
ይህም እናቶች ለከፋ እንግልት እንዳይዳረጉ ረድቷል። የቀዶ ህክምና ወሊድ አገልግሎቱ መጀመሩ እናቶች በራሳቸው ጤና ጣቢያዎች ላይ ሄደው የመገልገል ፍላጎታቸው እንዲጨምር አድርጓል።ቀዶ ህክምናው ብቻ ሳይሆን የሚያገኙት ተጨማሪ የህክምና አገልግሎት ጥራትንም በአንድ ደረጃ የማሻሻል እድል ፈጥሯል።
እናቶች ከመጀመሪያውኑ ችግር ቢያጋጥማቸውም ባያጋጥማቸውም ወደ ተቋማቱ ሄደው የመታየትና የመታከም እድላቸውንም አስፍቷል። ለውጥ ስለመምጣቱ ትክክለኛ ጥናት የሚያስፈልገው ቢሆንም አሁን ባለው ሁኔታ በጳውሎስ ሆስፒታል በአንድ ወር ውስጥ በመገኘት የሚወልዱ እናቶች ወደ 1 ሺ አካባቢ ይደርስ ነበር።
ነገር ግን ሆስፒታሉ ለእናቶች ማግኘት ያለባቸውን ጥራት ያለው የህክምናና የወሊድ አገልግሎት ለመስጠት ሲቸገር ቆይቷል።ሆኖም አገልግሎቱ ወደ ጤና ጣቢያዎች እንዲወርድ ከተደረገ በኋላ ቁጥሩ ወደ 600 መውረድ ችሏል።ሆስፒታሉ ያለበትን የቀዶ ህክምና ወሊድ አገልግሎት ጫናም አቃሏል።
የአገልግሎቱ ጥራቱንም አሳድጓል። ዶክተር ማራማዊት እንደሚገልፁት የቀዶ ህክምና ወሊድ አገልግሎቱ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታልን ጨምሮ በተለያዩ ሆስፒታሎች የራሳቸውን ጤና ጣቢያ ይዘው የማብቃት ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ።እናቶች ወደ እነዚህ ተቋማት መጥተው ሲገለገሉም አገልግሎቱን በጥራት ለመስጠት ያስችላል።ከዚህ አኳያ ይህ አገልግሎት በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ብቻ የተጀመረ አይደለም።በከተማና ክልል ጤና ቢሮዎችም ተመሳሳይ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛል።
በቀጣይም አስካሁን እየተሰጠ ያለው አገልግሎት ምን ያህል ለውጥ እንዳመጣ በሚገባ በማጥናት አገልግሎቱን የማስፋት ስራዎች ይከናወናሉ።በተለይ ስራው በጤና ቢሮ በኩል ቢሰራ የአገልግሎቱን ተደራሽነት ከዚህም በላይ ማስፋት ይቻላል።
እ.ኤ.አ በ2019 በተሰራው የስነ ህዝብና ጤና ዳሰሳ ጥናት በኢትዮጵያ 51 ነጥብ 4 ከመቶ ያህሉ እናቶች በቤት የሚወልዱ፣ 49 ነጥብ 8 ከመቶ ያህሉ በባለሙያ ተደግፈው የሚወልዱ እንዲሁም 13 ነጥብ 4 ከመቶ ያህሉ ያለባለሙያ እገዛ በራሳቸው የሚወልዱ መሆኑን ያሳያል።
አዲስ ዘመን የካቲት 19 /2014