የየካቲት ወር ተጋምሷል። ፀሃይዋ እንዲህ እንደዛሬው ያለቅጥ የምታሳርር ሆናለች። በተለይ በየካቲት 26 ቀን 1982 ዓ.ም ቀትር ሰባት ሰዓት ላይ የፀሃይዋ መክረር በፈጣሪ ሳይሆን በሰው የታዘዘች እስኪመስል ድረስ ጭካኔዋ በርትቷል።
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ባሶና ወራና ወረዳ መጥቆሪያ ቀበሌ ላይ እየወረደ ያለው ፀሃይ ደግሞ በቀበሌዎቹ ነዋሪዎች ዘንድ የሚዘነጋ አይደለም። የፀሃይዋ ሙቀት ሳይሆን ክረት የአባውን የረጋ ደም ለማስታወስ ያስገድዳል። ጭር ብሏል። ሁሉም በየቤቱ ቢሆንም አንዳንዶች በቤታቸው በር ላይ የፀሃይዋን መክረር እያዩ ይገረማሉ።ገሚሱ በየቤቱ ቡና አፍልቶ ምሳውን ይበላል።
ከመበተን በፊት
በልጆች ሃብት የታደሉት ወላጆች፤ ከ12 ልጆቻቸው ጋር ቁርስ እና እራት ብቻ ሳይሆን ምሳንም አብረው ይመገባሉ።እንደውም ምሳ ላይ በጋራ መመገብ ልማዳቸው አድርገውታል።እናት እና አባት እንደሌሎች ወላጆች በልጅ ብቻ ሳይሆን በሃብትም የተትረፈረፉ ናቸው።
ጎተራቸው ሙሉ ነው። ፍቅራቸው ይለያል።ባልና ሚስት ፍቅራቸው የተለየ ከመሆኑም በተጨማሪ፤ አኗኗራቸው እንደሰለጠነ ሰው ልጅን የሚያቀርብ እና ሁሉንም በፍቅር አንድ የሚያደርግ ነበር። አባት ልጅን፤ አባት እናትን ሁሉንም ያጎርሳል።እናትም በተመሳሳይ መልኩ ልጆቿን ታጎርሳለች።
በመጎራረስ ይጠግባሉ። ለፍተው ይሠራሉ። ጠግበው ይበላሉ።ይህንን የአካባቢው ሰው በደንብ ያውቃል። በልተው ጠጥተው ደግሞ እየተሳሳቁ ትንሽ ቆይተው ሁሉም እንደየ አቅሙ ወደየሥራው ይቀጥላል።
የካቲት 26 ቀን 1982 ዓ.ም
ከሰላሳ ሁለት ዓመት በፊት በየካቲት 26 ከቀኑ ሰባት ሰዓት አካባቢ ቤተሰቡ ምሳውን እንደልማዱ እየተጎራረሰ በመብላት ላይ ነው።አንዱ ሌላውን እያጎረሰ ሁሉም በደስታ ጣፍጦት ይመገባል።በልጅም በንብረትም የተባረኩት ወላጆች ቀትር ሠባት ሰዓት ላይ አገር አማን ብለው ምሳቸውን ሲበሉ፤ በልጅ መባረካቸው እና በሃብት የተትረፈረፈ ኑሮን መምራታቸው የሚያስቀናቸው አረመኔዎች ተባብረው፤ ሁሉንም ባዶ ለማድረግ ቋምጠው ግፍ እንደሚፈፅሙባቸው አልጠረጠሩም ነበር፡፡
ነገር ግን ምን ዋጋ አለው? ሁሉንም መና ያስቀረ ጥፋት ብቻ ሳይሆን ትልቅ ግፍ ተፈፀመ።ወላጆች እንደጉም ተነው የሚጠፉበት፤ ልጆችም የሚበተኑበት ክፉ ቀን ገጠመ። ቀኑን እንኳን ግፉን የተፈፀመበት ቤተሰብ ቀርቶ የቀበሌው ነዋሪ አይዘነጋውም። በቤተሰቡ ላይ ትልቅ መዓት ዘነበ።
በዕለቱ የምሣ ሰዓት ላይ በስድስት ግለሰቦች መሰሪነት ሊበተን ተቃርቦ የነበረው ቤተሰብ በልጆች ሳቅና ደስታ የሞቀ የደመቀ ነበር።ሆኖም ሰብሰብ ብለው ምሳ ይበሉ የነበሩ የቤተሰብ አባላትን ለማጥፋት፤ አሲረው ያሰፈሰፉት ወንጀል ፈፃሚዎች፤ ስድስት ሆነው እሳት ለብሰው እሳት ጎርሰው መሳሪያ ይዘው መንደሩን እያቆራረጡ ወደ ቤተሰቡ አባላት ገሰግሱ።የሥድስቱ ሰዎች መሳሪያ አያያዝ እና አረማመድ የአካባቢውን ነዋሪዎች በእጅጉ አደናገጠ፡፡
‹‹ተዉ እባካችሁ›› ያላቸው አልነበረም።ይልቁኑ ሁሉም በፍራቻ ፀሃዩ አሽሽቶት በቤቱ ደጃፍ የቆመ እና የተቀመጠው ሁሉ ወደየቤቱ ገብቶ ተሰገሰገ። አብረው ማዕድ በመቋደስ ላይ የነበሩት የቤተሰብ አባላት ከደጅ አባወራውን ውጣ የሚለውን ድምፅ ሲሰሙ ተደናገጡ።ልጆቹ ሁሉም ተበታተኑ።
እናት ከማዕዱ ፊት ለፊት በድንጋጤ ደርቃ ቆማ ቀረች።አባወራው በመስኮት ተመለከተ።ስድስት ሰዎች መሳሪያ ይዘው በራቸው ላይ በተጠንቀቅ አቀባብለው ቆመዋል። ከ14ቱ የቤተሰብ ዓባላት መካከል ሁለቱ ማለትም የ16 ዓመት ልጅ የነበረው ወጣት እና አባወራው በጓሮ ወደደጅ መሮጥ ጀመሩ።
ገዳዮች ቤት ገብተው፤ እናትን በያዙት ጠመንጃ ገደሉ።ልጆቹ አልጮሁም፤ ልጆች ናቸውና ፍርሃት አንዘፈዘፋቸው። የጎጆውን ግድግዳ ተደግፈው የእናታቸውን መሞት እያዩ እንባቸውን አፈሰሱ። ስድስቱ ነፍሰ ገዳዮች ተከፋፈሉ። ግማሾቹ በጓሮ በር ወጥተው አባወራውን እና ልጁን ማሳደድ ያዙ።ግማሾቹ በፊት ለፊት በር ወጥተው ሰፈሩን ቃኙ፡፡
አባት እና ልጅ ወደ ጥሻ ሮጡ።ገላጋይ አልነበረም።ሁሉም በቤቱ ተሸሽጓል።አባት እና ልጅ ብዙ ሮጡ። አገር ሰላም ብለው ምሳቸውን ሲበሉ የነበሩት አባትና ልጅ የተፈጠረውን ለማመን ከብዷቸዋል። ፀሃዩ ከሯል። አባት እያለከለኩ ከዛ በላይ ሮጠው ማምለጥ አልቻሉም። ልጃቸውን ‹‹አምልጥ ሩጥ›› አሉት።
ልጅ ሮጠ፤ በደንብ የተተበተበ ጥሻ አገኘ፤ እርሱም ደክሞት ነበር።አጎንብሶ ተደብቆ ማየት ጀመረ። ነፍሰ ገዳዮቹ ወደ አባቱ ቀርበዋል።
አባቱን ማዳን አልቻለም።እርሳቸውም ደርሰው መደበቅ አቃታቸው። ዓይኑ እያየ አባቱ ላይ መሳሪያ ተተኮሰ። ልጅ ተደብቆ አፉን በሁለቱም እጆቹ አፍኖ እንባው እየወረደ ትንፋሹን ዋጠ። ነፍሰ ገዳዮቹ በጭካኔ በጥይት አባወራውን ደብድበው ከገደሉ በኋላ፤ እንደሞተ ሲያረጋግጡ ተመለሱ።
ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት…
ልጅ እንደማይመለሱ ሲያረጋግጥ ወደ አባቱ ሬሳ ተጠጋ፤ የአባቱ ሬሳ በደም ተጨማልቋል። የፀሃዩ መክረር ደማቸውን አድርቆታል። ጭንቅላታቸውን ቀና አድርጎ ድንጋይ አንተርሶ ተንሰቀሰቀ፤ የደረሰለት አልነበረም። ሁሉም ፈርቶ ቤቱ ተሸሽጓል። በደም የተጨማለቀ የአባቱን ሬሳ ታቅፎ ፊታቸውን በእንባው አጠበ። ወንድም እህቶቹ በበኩላቸው ነፍሰ ገዳዮቹ ከቤት ሲወጡ እነሱም ከቤት ወጥተው የሚያስጠጋቸው ጎረቤት ፈለጉ።‹‹ኑ ግቡ›› ያላቸው አልነበረም።
ነፍሰ ገዳዮቹ ተመለሱ የ12 ልጆች ወላጆች የሆኑትን እናትና አባት በጥይት ደብድበው ከገደሉ በኋላ ፤ መኖሪያ ቤታቸውን እና ከ200 ኩንታል በላይ የሚሆነውን ዕህል በዕሳት አጋይተው ሁለት በሬዎችን እየነዱ ከአካባቢው ተሰወሩ። ቀና አድርጎ ድንጋይ ያንተራሳቸው፤ የ16 ዓመት ልጅ አስክሬኑን ብቻውን ማንቀሳቀስ አልቻለም።አስክሬናቸውን በቅጠል ሸፈናቸው፡፡
የለቅሶ ሥነ-ስርዓት
ወትሮ በአካባቢው ወግ እና ባህል መሠረት ዘመድ ይሰበሰባል።ነዋሪው ይጠራራል። ለቀስተኛው ተላቅሶ፤ የሞተውን ቀብሮ ይስተናገዳል። ለዚህ ቤተሰብ ግን ይህ አልሆነም። የሚለቀስበት ቤት የለም።
አባትና እናታቸውን በሞት፤ ንብረታቸውን በእሳት የተነጠቁት 12ቱ ልጆች ቀኑ ጨለማ ሆነባቸው፤ ሃዘናቸውን የሚቀመጡበት እንግዳ የሚያስተናግዱበት ቤት አጡ። የተወሰኑ ሰዎች ተገኝተው ወላጆች ተቀበሩ። ከ14ቱ የቤተሰብ አባላት መካከል የ2ቱ አባላት መቀነስ ሙሉ ለሙሉ ቤቱን ከመሠረቱ ናደው።
ለሟች ወላጆች እንደአካባቢው ባህል 40 እና 80 አልወጣም። ቁርባን አልተፈፀመም። ልጆቹ ገዳዮቹን ስለሚያውቋቸው ክስ ለመመስረት ቢፈልጉም ‹‹ሂዱ ከዚ›› ተባሉ። በተለያየ መልኩ ደጋግመው ቢጠቁሙባቸውምእየታሠሩ መልሰው ተፈቱ፡፡
መጠጊያ ፍለጋ
አሁን ከእርሻ መሬት በቀር የቀረላቸው ምንም አልነበረም። ሊያኖራቸው የሚችል ቤትም ሆነ ንብረት የለም። ገዳዮቹን በመፍራት የአካባቢው ነዋሪዎችም ልጆቹን ለማስጠጋት ፈቃደኛ አልሆኑም። ‹‹እነርሱ ሽፍቶች ናቸው ታስፈጁናላችሁ›› ብለው ሁሉም አናስጠጋ አሏቸው።
ልጆች የሚያስጠጋቸው ባለማግኘታቸው ያ በፍቅር የተሞላ ቤተሰብ የግድ ተበታተነ። የተወሰኑት ደብረብርሃን ሕፃናት ማሳደጊያ ሲገቡ የተቀሩት ተሰደዱ። ወደ ደብረብርሃን ቢሄዱም ገዳዮች ቆይተው በድጋሚ አድገው ይበቀሉናል ብለው በመስጋታቸው ያሳድዷዋቸው ያዙ።
የልጅነት ጊዜያቸው የደስታ ትዝታ ወላጆቻቸው ላይ በተፈፀመ ዘግናኝ ድርጊት ሙሉ ለሙሉ በሃዘን እና በጨለማ ተተካ።የማይረሳ የተደፈነ ታሪክ ሆኖ ሁለት አስርት ዓመታት ተቆጠሩ።
ምርመራ
ቀናት በቀናት እየተፈራረቁ በ2007 ዓ.ም በግፍ የወላጆቻቸውን ህይወት የተነጠቁ ልጆች ከ24 ዓመታት በኋላ ፍትህ የሚያገኙበት ጊዜ ደረሰ። ጉዳዩን የሰማው ፖሊስ ሠነድ ማገላበጥ ጀመረ።
በአዲስ መልክ የምርመራ ቡድን ተዋቅሮ፤ ምርመራ ተጀመረ።በሚስጥር መረጃ ተሰባሰበ። ድርጊቱ ሲፈፀም እነማን ነበሩ? የሚለው ተጣርቶ ምርመራው ቀጠለ። ሰዎቹ አሉ የተባለበት ቦታ ላይ የመያዣ ትዕዛዝ ተላለፈ። ነገር ግን ተጠርጣሪዎቹ ስምና አድራሻቸውን ቀይረው ተሰውረዋል።
ይህ ምርመራውን ፈታኝ አደረገው፤ የጊዜው መርዘም ደግሞ ድርጊቱን የፈፀሙ ከፊሎቹ 60፤ አንዳንዶቹ ደግሞ 70 ዓመት የሞላቸው መሆኑና ወንጀሉ ከተፈፀመ 24 ዓመታት ማለፉ ምርመራውን የበለጠ አወሳሰበው። ብዙዎቹ የወንጀሉ ተሳታፊዎች ደግሞ መኖሪያቸው አዲስ አበባ ነበር፡፡
ጥቅምት 17 ቀን 2007 ዓ.ም ከለሊቱ 10 ሰዓት በድቅድቅ ጨለማ አዲስ አበባ ገርጂ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን የመቃብር ስፍራ ላይ የምርመራ ቡድኑ ተገኝቷል። የሙታኑን መንደር አስፈሪ ዝምታ ውጦታል። የቡድኑ በዛ አካባቢ የመገኘት ምክንያት ዋናው ተጠርጣሪ የቤተሰብ አባል የሞተበት በመሆኑ ሃውልት ምረቃ ላይ ይገኛል ተብሎ ስለተገመተ ነበር። ነገር ግን እንደተገመተው አልሆነም።
በዛ ባይያዝም በአዲስ አበባ በመኖሪያ ቤቱ ተያዘ።ዋናው ተጠርጣሪ ከተያዘ በኋላ ሌሎቹን ማፈላለግ ተጀመረ።በመጨረሻ የምርመራ ቡድኑ ቀስ በቀስ ስድስቱንም ተጠርጣሪዎች በቁጥጥሩ ስር አዋለ።
ውሳኔ…
ግንቦት 5 ቀን 2007 ዓ.ም በዋለው የሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ችሎት ስድስቱም ግለሰቦች ጥፋተኛ ሆነው መገኘታቸውን አረጋግጦ ውሳኔ አስተላለፈ።ዕድሜያቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት እያንዳንዳቸው የአሥራ አራት ዓመት እስራት ይገባቸዋል ሲል ከ24 ዓመታት በኋላ ፈርድ ሰጠ።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን የካቲት 19 /2014