የ2022 የዓለም የቤት ውስጥ የዙር ውድድሮች በተለያዩ የዓለማችን ከተሞች በተያዘላቸው መርሃ ግብር መሰረት ቀጥለዋል። ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም በእነዚህ ውድድሮች በተለያዩ ርቀቶች በሚደረጉ ፉክክሮች ተከታትለው በመግባት ማንጸባረቃቸውን ቀጥለዋል።
ባለፈው ሐሙስ ምሽት በፈረንሳይ ሌቪን በተካሄደው የአንድ ማይል ውድድር አሸናፊ የነበረችው ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ ከትናንት በስቲያ ምሽት በፖላንድ ቶረን በተካሄደው የ 1500 ሜትር ውድድርም ባለ ድል ሆናለች። የቶኪዮ ኦሊምፒክ የ5ሺ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊዋ ጉዳፍ በቶረን ያደረገችውን ውድድር ከመጀመሪያ አንስታ ተፎካካሪዎቿን በሰፊ ርቀት በመምራት የርቀቱን የዓለም ክብረወሰን ለመስበር ትልቅ ትግል አድርጋለች።
ጥረቷ ግን የዓለም ክብረወሰንን ለማሻሻል በቂ አልነበረም። በመጨረሻ ግን ውድድሩን ያጠናቀቀችበት 3:54:77 ሰአት የዓመቱ ፈጣን ሰአት ሆኖ ተመዝግቧል። ይህ ሰአት የዓመቱ ፈጣን ከመሆኑ በተጨማሪም ጉዳፍ ባለፈው ዓመት ሌቪን ላይ ራሷ ካስመዘገበችው የርቀቱ የዓለም ክብረወሰን( 3:53:09) በጥቂት ማይክሮ ሰከንዶች የዘገየ የምን ጊዜም ሁለተኛው ፈጣን ሰአትና የቦታው ክብረወሰን ሆኖ ተመዝግቧል።
‹‹እቅዴ የነበረው ባለፈው የሌቪን ውድድር የአንድ ማይል ክብረወሰን ማሻሻል ነበር፣ ይሁን እንጂ ዛሬ በቶረን ሁለተኛውን ፈጣን ሰአት በሌላ ርቀት በማስመዝገቤ ደስተኛ ነኝ፣ የማይል ክብረወሰንን ለማሻሻል በጥሩ አቋም ላይ እንደምገኝ እርግጠኛ ነበርኩ፣ ያ ቀን ግን ለእኔ ጥሩ አልነበረም›› በማለት ጉዳፍ ከውድድሩ በኋላ አስተያየት ሰጥታለች። ጉዳፍን ተከትለው ሌሎቹ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ለምለም ኃይሉ በ4:02.25፣ ፍሬወይኒ ኃይሉ በ4:02.50 ፣ ሐብታም አለሙ በ4:02.52፣ ሒሩት መሸሻ በ4:03.22 ሰአት እስከ 5ኛ ያለውን ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል።
ከሴቶቹ 1500 ሜትር ውድድር ቀደም ብሎ የተካሄደው የወንዶች 3ሺ ሜትር ውድድር ትልቅ ትኩረት የተሰጠው ነበር። በዚህ ውድድር ኢትዮጵያውያኑ የኦሊምፒክ የ10ሺ ሜትር ቻምፒዮን ሰለሞን ባረጋ፣ የ3ሺ ሜትር መሰናክል የብር ሜዳሊያ አሸናፊው ለሜቻ ግርማና የርቀቱ የዳይመንድሊግ አሸናፊ ጌትነት ዋለ ተሳታፊ መሆናቸው ፉክክሩን ተጠባቂ አድርጎታል።
በተለይም እነዚህ አትሌቶች ከሳምንት በፊት በሌቪን በተመሳሳይ ርቀት አስደናቂ ፉክክር አድርገው ከአንድ እስከ ሶስት ማጠናቀቃቸው በቶረን የሚያደርጉትን ፉክክር የበለጠ ተጠባቂ አድርጎታል። ሆኖም አትሌቶቹ ፈጣን ሰአት ለማስመዝገብ ጥረት ከማድረግ ይልቅ እርስ በርስ መሸናነፍ ላይ ትኩረት በማድረጋቸው የተሻለ ሰአት በውድድሩ ሊመዘገብ አልቻለም።
ሌቪን ላይ እስከ ውድድሩ መጨረሻ ድንቅ ፉክክር አድርገው በአጨራረስ ብቃት አሸናፊ የሆነው አትሌት ለሜቻ ግርማ በቶረንም ተመሳሳይ ድል አስመዝግቧል። በሌቪኑ ውድድር ለሜቻን ፈትኖት የነበረው ሰለሞን ባረጋ ቶረን ላይም ተመሳሳይ ብቃቱን አሳይቷል። ያም ሆኖ በርቀቱ የተሻለ ልምድና ብቃት ያለው ለሜቻ ግርማ የኦሊምፒክ ቻምፒዮኑን ሰለሞን በአንድ ሳምንት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ሊያሸንፈው ችሏል።
ለሜቻ በውድድሩ መጨረሻ ያሳየው አስደናቂ የአጨራረስ ብቃት በ7:31.09 ሰአት ቀዳሚ ሆኖ እንዲያጠናቅቅ ሲያደርገው፣ በሌቪን የደረሰበትን ሽንፈት ለማካካስ የቻለውን ሁሉ ያደረገው ሰለሞን በ7:31:39 ሁለተኛ ሆኖ አጠናቋል። ኬንያዊው አትሌት ጃኮፕ ክሮፕ በ7:31.90 ሰአት ሶስተኛ ሆኖ አጠናቋል። በሌቪኑ ውድድር ለሜቻና ሰለሞንን ተከትሎ ሶስተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው ጌትነት ዋለ ቶረን ላይ ተመሳሳይ ውጤት ለማስመዝገብ ጥረት ቢያደርግም በስተመጨረሻ በኬንያዊው አትሌት ተቀድሞ በ7:32.50 ሰአት አራተኛ ሆኖ አጠናቋል። ሌሎቹ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አድሃነ ካሳይ በ7:49.13 ሰባተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ ሀፍቱ ተክሉ በ7:52.10 ሰአት ዘጠነኛ ደረጃን ይዞ ውድድሩን ፈጽሟል።
በ800 ሜትር ጠንካራ ፉክክር ያደረገችው ትዕግስት ግርማ ከአሸናፊዋ ካትሪዮን ቢሴት በ0.03 ሰኮንድ ብቻ በመዘግየት በሶስተኝነት አጠናቃለች። ወርቅነሽ መሰለ ደግሞ በ2:05.34 ሰአት አምስተኛ ሆና ፈጽማለች።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን የካቲት 17/2014