የ2024 የዳይመንድሊግ ውድድሮች አስራ አራት ከተሞችን አዳርሶ ከትናንት በስቲያ በብራሰልስ ፍፃሜውን አግኝቷል። የዳይመንድ ሊጉን አጠቃላይ አሸናፊ የሚለየውና ከፍተኛ ነጥብ መሰብሰብ የሚያስችለው የውድድሩ የመጨረሻ መዳረሻ ከተማ የሆነችው ብራሰልስም ባለፈው ዓርብና ቅዳሜ ምሽት በተለያዩ ርቀቶች ወሳኝ ፉክክሮችን አስተናግዳለች።
ዓርብ ምሽት በተካሄደው የወንዶች 5ሺ ሜትር ተጠባቂ ፉክክር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በፍፁም የበላይነት ሲያጠናቅቁ አትሌት በሪሁ አረጋዊ የ2024 ዳይመንድ ሊግ የርቀቱ አጠቃላይ አሸናፊ ሆኗል። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከአንድ እስከ ሦስት ያለውን ደረጃ ይዘው ባጠናቀቁበት ፉክክር የፓሪስ ኦሊምፒክ የ10ሺ ሜትር የብር ሜዳሊያ አሸናፊው በሪሁ አረጋዊ በድንቅ ብቃት 12:43.66 ሰዓት በቀዳሚነት አጠናቋል። ይህም የዳይመንድ ሊግ ውድድር ጎልደን ሊግን ተክቶ እኤአ ከ2010 አንስቶ መካሄድ ከጀመረ ወዲህ 18ኛው ኢትዮጵያዊ አሸናፊ ያደረገው ሲሆን የአልማዝ ዋንጫ እና የ30 ሺ ዶላር ተሸላሚ ሆኗል። በሪሁ 2021 ላይ የ5ሺ ሜትር አጠቃላይ የዳይመንድሊግ አሸናፊ እንደነበረ የሚታወስ ሲሆን፣ ከእሱ በኋላ በርቀቱ አጠቃላይ የዳይመንድሊግ አሸናፊ የሆነ ኢትዮጵያዊ አትሌት የለም።
በውድድር ዓመቱ የዳይመንድሊግ ፉክክሮች በተለያዩ ከተሞች በድንቅ ብቃት እያሸነፈና ፈጣን ሰዓት እያስመዘገበ የተጓዘው አትሌት ሐጎስ ገብረሕይወት ብራሰልስ ላይ በበሪሁ የበላይነት ተወስዶበታል። በዚህም 12:44.25 ሁለተኛ ሆኖ አጠናቋል። ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ጥላሁን ኃይሌ በ12:45.63 ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን ፈፅሟል። ውጤቱን ተከትሎ ሐጎስ ገብረሕይወት የ12 ሺ ዶላር እንዲሁም ጥላሁን ኃይሌ የ7 ሺ ዶላር ተሸላሚ ሲሆኑ አምስተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ዮሚፍ ቀጄልቻ የ2500 ዶላር አሸናፊ ሆኗል።
በወንዶች 3 ሺ ሜትር መሰናክል ጌትነት ዋለ እና ሳሙኤል ፍሬው የ7ኛ እና 8ኛ ደረጃን ይዘው በማጠናቀቅ የ1,500 እና 1,000 ዶላር ተሸላሚ ሆነዋል። በዚህ ውድድር ኬንያዊው አሞስ ሳሬም ሲያሸንፍ የኦሊምፒክና የዓለም ሻምፒዮኑ ሞሮኳዊው ሶፊያን ኢል ባካሊ ሁለተኛ ደረጃን አግኝቷል::
በሴቶች 800 ሜትር ደግሞ ሀብታም ዓለሙ በ1:59.81 የ6ኛ ደረጃን ይዛ በማጠናቀቅ የ2 ሺህ ዶላር አሸናፊ ሆናለች። ኬንያዊቷ ሜሪ ሙራ ደግሞ የርቀቱ አሸናፊ ሆናለች። በ1500 ሜትር ኖርዌዢያዊው የኦሊምፒክ ሻምፒዮን ጃኮብ ኢንግሪስተን ሲያሸንፍ ኬንያዊ ቼሪዮት ሁለተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል::
በብራስልስ ዳይመንድ ሊግ የሁለተኛ ቀን ውሎ ተጠባቂ ከነበሩት ውድድሮች የ5ሺሜትር ሴቶች አንዱ ሲሆን 12 ኢትዮጵያውያን ተሳትፈዋል። 9ኙ ውድድራቸውን ሲያጠናቅቁ ሦስቱ አቋርጠዋል:: በውድድሩም ከ2ኛ እስከ 4ኛ ያለውን ደረጃ ይዘው ፈጽመዋል::
የርቀቱ የዓለም ከ20 አመት በታች የክብረወሰን ባለቤት አትሌት መዲና ኢሳ በተጠባቂዋ አትሌት ቢያትሪስ ቺቤት በ11 ሰከንዶች ያህል ተቀድማ 2ኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቃለች። ሌላዋ ኢትዮጵያዊት ፎቴን ተስፋዬ 3ኛ ሆና ስታጠናቅቅ እጅጋየሁ ታዬ 4ኛ ሆና አጠናቃለች:: መልክናት ውዱ 7ኛ፤ ጽጌ ገብረሰላማ 9ኛ ደረጃን ሲይዙ በላይነሽ ፋንታዬ ውድድሩን ሳታጠናቅቅ ቀርታለች::
በተመሳሳይ 1500ሜ ሴቶች በአትሌት ድርቤ ወልተጂ እና ፌዝ ኪፕዬጎ መካከል ማራኪ የመሸናነፍ ፉክክር የታየ ሲሆን በማይክሮ ሰከንዶች ልዩነት ኪፕዬጎ ቀዳሚ በመሆን አሸንፋለች:: 3፡54፡75 አሸናፊዋ ርቀቱን የሸፈነችበት ሲሆን የውድድሩ አዲስ ክብረወሰን ሆኖ ተመዝግቧል:: ጠንካራዋ አትሌት ድርቤ በበኩሏ 2ኛ ሆና ስታጠናቅ 3፡55፡25 ሰዓት አስመዝግባለች። አውስትራሊያዋ ተወዳዳሪ ሀል ጄሺካ 3ኛ ወጥታለች:: ፍሬወይኒ ኃይሉ 4ኛ፤ ብርቄ ሀየሎም 8ኛ እንዲሁም ወርቅነሽ መሰለ 10ኛ ደረጃ በመያዝ አጠናቀዋል ::
በ3ሺ ሜትር ሴቶች መሰናክል ኢትዮጵያን በብቸኝነት የወከለችው አትሌት ሎሚ ሙለታ 10ኛ ወጥታለች:: በውድድሩ የኬንያ፤ ባሕሬን እና ዩጋንዳ አትሌቶች በቅደም ተከተል ከ1ኛ አስከ 3ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ አሸናፊ ሆነዋል::
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን መስከረም 6 ቀን 2017 ዓ.ም