
በሰሜናዊ ምሥራቃዊ አርካም ክልል አማፂያን ባደረሱት ጥቃት ስምንት ወታደሮቹ መገደላቸውን እና አምስቱ እንደጠፉ የማሊ ጦር አስታወቀ።
ግጭቱ የተከሰተው ፈረንሳይ እና አጋሮቿ ጦራቸውን ከማሊ እናስወጣለን ካሉ ከቀናት በኋላ ነው።
ከሰሞኑ ለተፈፀመው ጥቃት ምላሽም የማሊ አየር ኃይል 57 ታጣቂዎችን መግደሉን ጦሩ በመግለጫው አክሏል።
ወታደሮቹ የአማፂያን መደበቂያ ቦታዎችን ሲያፈነፍኑ በነበረበት ወቅት «ማንነታቸው ባልታወቁ የታጠቁ ሰዎች» እንደተተኮሰባቸውና እንደሞቱም ተነግሯል።
የፈረንሳይ ወታደሮች ከአገሪቱ እንዲወጡ ከተደረገ በኋላ እንዲሁም በቀጣናው የሩሲያ ቅጥረኞች መሰማራት በማሊ የጸጥታ ሁኔታ ላይ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ስጋት ጭሯል።
በዚህ ሳምንት ብቻ፣ እስላማዊ መንግሥትን ጨምሮ ተቀናቃኝ እስላማዊ ቡድኖች በሚንቀሳቀሱበት አርካም ክልል 40 ንፁሃን ዜጎች መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
ማሊ ለዓመታት ከጂሃዲስቶች ጋር ስትታገል ቆይታለች። ከዚህ ጋር ተያይዞም በአውሮፓውያኑ 2020 ፕሬዚዳንት ኢብራሂም ቡባካር ኬይታ ከፍተኛ ተቃውሞ የተነሳባቸው ሲሆን ይህንንም ተከትሎ የአገሪቱን ጸጥታ እናስከብራለን በሚልም መፈንቅለ መንግሥት ተካሂዶባቸዋል።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የአገሪቱ አዲስ ወታደራዊ አመራሮች ከቀድሞ ቅኝ ገዢዋ ፈረንሳይ ጋር አለመግባባቶች ተፈጥሯል።
በዚህ አመት ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ የተደረሰውን ስምምነት በመሻር እና የፈረንሳይ አምባሳደርም ሲቃወሙ ማባረራቸው ይታወሳል።
ጂሃዲስቶችን ለ10 ዓመታት ያህል ስትዋጋ የነበረችውን ፈረንሣይ ሁሉንም ወታደሮቿን እንድታስወጣ ማሊ ትዕዛዝ ሰጥታለች።
በሌሎች ምዕራባውያን አገራት ወታደሮች የተጠናከረው የማሊ ጥምር ተልዕኮ ወይም ታኩባ ግብረ ኃይል በአሁኑ ወቅት ድንበሩን አቋርጦ ወደ ኒጀር በመጓዝ አሁን ካለው የጦር ሰፈር በቅርብ ርቀት ላይ ሆኖ ይቆያል።
የኒጀር ፕሬዚዳንት አርብ ዕለት እንዳሉት የፈረንሳይ ጦር እና አጋሮቻቸው ከማሊ መውጣታቸውን ተከትሎ የአገሪቱ ድንበሮች ለጂሃዲስት ታጣቂዎች እንቅስቃሴ የበለጠ ተጋላጭ ይሆናሉ።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የኒጀር ፕሬዚዳንትና ሌሎች የምዕራብ አፍሪካ መሪዎች የፈረንሳይ ጦር ከማሊ መውጣቱን በተመለከተ ይፋ ከማድረጉ በፊት ከፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር የተገናኙ ሲሆን በውይይታቸውም ወታደሮቹ ወደ ቀጣናው አገራት እንዲዘዋወሩ ተስማምተዋል።
ምንጭ ቢቢሲ
አዲስ ዘመን የካቲት 14 ቀን 2014 ዓ.ም