የያዝነው የካቲት ወር በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በተለይም በታሪክና ፖለቲካ ጉልህ ሚና አለው። ወሩ ከሚታወስባቸው መካከል የካቲት 12 የሰማዕታት ቀን፣ ዓድዋ እና የየካቲት 1066ቱ አብዮት በደማቁ የሚታወሱ ናቸው። ዓድዋንና የተቀሩትን በቀን በቀናቸው ስንደርስ እናስታውሳቸዋለን።
በ1888ዓ.ም በአድዋ ላይ በኢትዮጵያ ጀግኖች ዓለም አቀፍ ውርደትን የተከናነበው ጣሊያን ለ40 ዓመታት ያህል ያኔ የደረሰበት ሽንፈት ሲያንገበግበው ከኖረ በኋላ በ1928 ዓ.ም በቀሉን ሊወጣ ዳግም ወደ ኢትዮጵያ መጣ። ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያን ወረረ። ኢትዮጵያውያን ይህን ጠላት እንደ ቀድሞው ለማሳፈር ማይጨው ላይ ከፋሽስቱ ጦር ጋር ገጠሙ። ፋሽስቱ እስከ አፍንጫው ድረስ የታጠቀና በአለም አቀፍ ደረጃ የተከለከለ የመርዝ ጋዝ ይጠቀም ነበርና ኢትዮጵያንን በገዛ ሀገራቸው በግፍ ጨፍጭፎ ሀገሪቱን ወረረ።
እነሆ ከ85 ዓመታት በፊት በትናንትናዋ ቀን የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም እንዲህ ሆነ። ከጣሊያን ንጉሣዊ ቤተሰቦች አንድ ልዑል በመወለዱ በአዲስ አበባ ድል ያለ ድግስ ተዘጋጅቶ እንዲከበር በጀኔራል ግራዚያኒ ትዕዛዝ ተላለፈ። በዝግጅቱም በቀድሞው የገነተ ልዑል ቤተ መንግስት በአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ውስጥ የፋሽስቱ ባለሥልጣናት እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው ሁሉ እንዲገኙ ተደረገ።
በዚያም ላይ ትልቅ የደስታ ስጦታ መዘጋጀቱን ወጣቱ አብርሃም ደቦጭ ሰምቷል። አብርሃም ይህን መረጃ ለበጅሮንድ ለጥይበሉ ገብሬ፣ ለብላታ ዳዲ፣ ለቀኝአዝማች ወልደዮሃንስ፣ ለደጅአዝማች ወልደ አማኑኤል እና ሌሎች ኢትዮጵያውያን ጓደኞቹ ተናገረ። ጥሪው ከተደረገበት ቦታ ማንም ሰው መሄድ እንደሌለበትም አስታወቃቸው። ዳሩ ግን የፋሽስቱ እንዲህ በአገራቸው ላይ ደጋሽ እና ጋባዥ መሆን ያላንገበገባቸው ሆድ አደሮች ‹‹ዞር በል ወዲያ›› ብለውት ለመሄድ ወሰኑ።
አብርሃምም ስለጉዳዩ ለቅርብ ጓደኛው ለሞገስ አስገዶም ከነገረው በኋላ ምን ማድረግ እንዳለባቸው መከሩ። በዚች ታሪከኛ ቀን የካቲት 12 ከማንም ቀድመው ዝግጅቱ ላይ መገኘት እንዳለባቸውም ወሰኑ።
የጣሊያን ፋሽስት ጉዱን አላየ ሽር ጉድ ይላል። አብርሃም እና ሞገስም የሆዳቸውን በሆዳቸው ይዘውወደ ግብዣው ስፍራ ገቡ። ከታዳሚዎች መካከል ሞገስ አስገዶም እና አብርሃም ደቦጭ ድግሱ እሬት እሬት ብሏቸዋል፤ ያ ታላቅ ግቢ የፋሽስት ሶላቶ መፈንጫ መሆኑ አንገብግቧቸዋል፣ የአገር መደፈር አሟቸዋል።
ገዳይ ቢያረፋፍድ ሟች ይገሰግሳል ነውና ነገሩ ግራዚያኒ ከሚገባው በላይ ቅጡን ማጣቱ ያንገበገባቸው አብርሃም ደቦጭና ሞገስ አስግዶም ትዕግስታቸው አለቀ። በኪሳቸው ደብቀዋቸው የነበሩትን ቦንቦች መዥረጥ፣መዥረጥ አደረገው ግራዚያኒ ላይ ወረወሩ። ግራዚያኒም ወደቀ። ለህክምና እየተወሰደ ባለበት በስፍራው በተሰበሰበው ህዝብ ላይ ሁሉ እርምጃ እንዲወሰድ አዘዘ። ለአሸሸ ገዳሜ የታሰበው ያ ግቢ የዋይታ ሆነ።
ይህን ተከትሎም የጣሊያን ፋሽስቶች በእልህ እና በብስጭት በአዲስ አበባ ከሰላሳ ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያንን በግፍ ጨፈጨፉ። ህጻናት፣ ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ አዛውንቶች ሳይሉ ያገኙትን ሁሉ ገደሉ። ግድያውንም በጠመንጃ ብቻ ሳይሆን በአካፋ፣ በመጥረቢያና በመሳሰሉት ሁሉ ነው የፈጸሙት። ፋሽስቶች በህዝቡ መኖሪያ ቤቶች ላይ ቤንዚን በማርከፍከፍ ሲያጋዩ ሸሽተው የሚወጡትን በጥይት ጨረሷቸው። አዲስ አበባ በደም ጎርፍ ታጠበች፤ ጎዳናው ሁሉ አስከሬን በአስከሬን ሆነ፡፡
አብርሃም ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶምም በጎንደር አድርው ወደ ሱዳን እየሸሹ ሳሉ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ተገደሉ። የኢትዮጵያ ቆራጥ አርበኞች ግን ጣሊያንን ከአገራቸው ለማስወጣት ሴት ወንድ ሳይሉ በዱር በገደሉ መዋጋት ጀመሩ።
የሞገስ አስገዶምና የአብርሃም ደቦጭ ቁርጠኛ ውሳኔ ብዙ ጀግኖችን ለትግል አነሳሳ። አምስት አመታትን የወሰደው የኢትዮጵያውያን አርበኞች ትግል የጣሊያን ፋሽስት ጓዙን ጠቅልሎ ከኢትዮጵያ እንዲወጣ አደረገው። እነዚህ ጀግኖች አጥንታቸውን ከስክሰው ደማቸውን አፍስሰው እነሆ ኢትዮጵያን ብቸኛ አፍሪካዊት ነፃ አገር አደረጓት።
ጣሊያኖች በ1879 ዓ.ም ዶጋሌ ላይ፣ ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ ደግሞ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም አድዋ ላይ ውርደትን እንደተከናነቡት ሁሉ፣ ከአድዋው ድል ከ40 አመታት በኋላ ኢትዮጵያን ቅኝ ግዛታቸው ለማድረግ ያደረጉት ሙከራም በኢትዮጵያውያን ጀግኖች ከሸፈ።
ለእዚህ ድል መመዝገብ ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነው እንዲነሱ ባደረገው የየካቲት 12 የፋሽስት ጭፍጨፋ ለተሰዉ ኢትዮጵያውያን መታሰቢያ እንዲሆን ስድስት ኪሎ ላይ የካቲት 12 የሰማዕታት መታሰቢያ ሀውልት ተገነባ። በጭፍጨፋው ሕይወታቸውን ያጡ ዜጎችን ለመዘከር የካቲት 12 በብሔራዊ ደረጃ እንዲዘከር በ1934 ዓ.ም ታወጀ። በ1951 ዓ.ም ደግሞ አሁን የምናየው እና 28 ሜትር ርዝመት እንዳለው የሚነገረለት የሰማዕታት መታሰቢያ ሐውልት እንዲቆም ተደረገ።
ጽሁፉን ስናዘጋጅ ጳውሎስ ኞኞ ዳግማዊ አጤ ምኒልክ መጽሀፍና የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትና የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽንን በመረጃ ምንጭነት ተጠቁመናል፡፡
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን የካቲት 13/2014