የዓለም አትሌቲስ ከሚያካሂዳቸው ዓመታዊ ውድድሮች መካከል የቤት ውስጥ የዙር ውድድሮች ይጠቀሳሉ። የወርቅ፣ የብር እና የነሃስ ደረጃ የተሰጣቸው እነዚህ ውድድሮች በቻይና፣ አሜሪካ እና አውሮፓ 36 ከተሞች ይደረጋሉ።
ከፈረንጆቹ የመጀመሪያው ወር አንስቶ ለሶስት ወራት የሚዘልቀው ይህ ውድድር ከትናንት በስቲያ ምሽት በፈረንሳይ ሌቪን ከተማ ተካሂዷል።
ዛሬና ነገም በአውሮፓ ከተሞች በመም እና በሜዳ ላይ ተግባራት ቀጥለው ይደረጋሉ። የወርቅ ደረጃ ባገኘው የፈረንሳዩ ሌቪን ከተማ በተካሄደው ውድድር ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ደምቀው ታይተዋል። በምሽቱ ከተካሄዱ ውድድሮች ሁሉ እጅግ አጓጊ የነበረው የወንዶች 3ሺ ሜትር፤ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ብቃታቸውን ያስመሰከሩ ወጣት አትሌቶች የተገናኙበት መድረክ ነበር።
ኢትዮጵያዊያኑ አትሌቶች እርስ በእርሳቸው ከፍተኛ ፉክክር እንደሚያስተናግዱ በተጠበቀው መሰረት ቀልብ በሚስብ ትንቅንቅ ተከታትለው በመግባት ድሉን የግላቸው አድርገዋል። በዚህም የኦሊምፒክ 3ሺ ሜትር መሰናክል የብር ሜዳሊያ ባለቤቱ አትሌት ለሜቻ ግርማ የውድድር ዓመቱን በአሸናፊነት እንዲጀምር አስችሎታል።
አስደናቂ ፉክክር በታየበት ውድድር ለሜቻ ግርማ የርቀቱን የመጨረሻ መስመር 7:30.54 በሆነ ሰዓት ሲረግጥ የዓለም ክብረወሰንን ለመስበር የቀሩት ጥቂት ሰከንዶች ብቻ ነበሩ። ለአሸናፊነት ሲጠበቅ በ12ማይክሮ ሰከንዶች የተቀደመው ሌላኛው ብርቱ አትሌት ሰለሞን ባረጋ ደግሞ 7:30.66 በሆነ ሰዓት ሁለተኛ ሆኗል። ከቶኪዮ 2020 የኦሊምፒክ ድሉ በኋላ የተያዘውን የውድድር ዓመት በዚህ ርቀት ክብረወሰን በማሻሻል ለመጀመር ያቀደው ሰለሞን ባረጋ ሊሳካለት አልቻለም።
በ3ሺ ሜትር የዓለም ሁለተኛው ፈጣን ሰዓት ባለቤት እንዲሁም በቶኪዮ ኦሊምፒክ በ3ሺ ሜትር መሰናክል አራተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው ጌትነት ዋለም የሃገሩን ልጆች ተከትሎ 7:30.88 በሆነ ሰዓት ሶስተኛ ለመሆን ችሏል። በዚሁ ርቀት ሴቶች በተካሄደው ውድድርም ኢትዮጵያኑ አትሌቶች በተመሳሳይ ተከታትለው በመግባት ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ ይዘዋል።
በርቀቱ አሸናፊ የሆነችው አትሌት ዳዊት ስዩም ስትሆን፤ በቤት ውስጥ ቻምፒዮና ከአራት ዓመት በኋላ ወደ ድል መመለሷን የዓለም አትሌቲክስ አስታውሷል። አትሌቷ የገባችበት 8:23.24 የሆነ ሰዓትም የራሷ እና የስፍራው ምርጥ እንዲሁም በታሪክ ርቀቱ አራተኛው ፈጣን ሰዓት በሚል ተመዝግቦላታል።
አሯሯጮች በተሳተፉበትና ፈጣን በነበረው በዚህ ውድድር አትሌት እጅጋየሁ ታዬ በ3ሰከንድ ከ77 ማይክሮ ሰከንዶች ዘግይታ ስትገባ፤ ሌላኛዋ አትሌት ፋንቱ ወርቁ ደግሞ 8:38.15 በሆነ ሰዓት ሶስተኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ልትሆን ችላለች።
ሌላኛው ኢትዮጵያዊያን የተሳተፉበት ርቀት የአንድ ማይል ሲሆን፤ በሴቶች በኩል በተመሳሳይ አሸናፊነት ተጠናቋል። በኢትዮጵያዊቷ ፈጣን አትሌት ገንዘቤ ዲባባ የተያዘውን የርቀቱን የዓለም ክብረወሰን ለማሻሻል በምሽቱ ውድድር ላይ የተካፈለችው የ5ሺ ሜትር የኦሊምፒክ የነሃስ ሜዳሊያ ባለቤቷ ጉዳፍ ጸጋዬ ናት።
አትሌቷ በሰከንዶች ዘግይታ ፈጣን ሰዓት ባታስመዘግብም 4:21.72 በሆነ ሰዓት የሃገሯን ልጆች አስከትላ በመግባት ልትነግስ ችላለች። 4:25.30 የሆነ ሰዓት ያስመዘገበችው ወጣቷ አትሌት አክሱማዊት እምባዬ ሁለተኛ ስትሆን፤ ሂሩት መሸሻ እና ነጻነት ደስታ እስከ አራት ያለውን ስፍራ ተቆጣጥረዋል።
ወጣት አትሌቶች ጎልተው በታዩበት የሌቪኑ ምሽት በኢትዮጵያዊው አትሌት ሳሙኤል ተፈራ የተያዘው የ1500 ሜትር የዓለም ክብረወሰንም ሊሰበር ችሏል። ፈጣኑን ሰዓት ከእጁ ያስገባው ደግሞ ኖርዌያዊው የመካከለኛ ርቀት አትሌት ጃኮብ ኢገብሪትሰን ነው።
የ21 ዓመቱ ወጣት አትሌት ርቀቱን 3:30.60 በሆነ ሰዓት ያጠናቀቀ ሲሆን፤ ከቀድሞው ሰዓት የ44 ሰከንዶች ብልጫ አለው። የቀድሞው ፈጣን አትሌት ሳሙኤል 3:33.70 የሆነ ሰዓት በመሮጥ በሁለተኛነት ሲገባ፤ ስፔናዊው ኢግናሲዮ ፎንተስ 3:37.39 ሶስተኛው አትሌት ሆኗል።
በ2ሺ ሜትር በተካሄደው የወንዶች ውድድር ተሳታፊ የነበረው አትሌት ሳሙኤል ዘለቀም ባለድል ሊሆን ችሏል። አትሌቱ ከምርጥ አጨራረስ ጋር ኬንያዊውን አትሌት በማስከተል የበላይነቱን ወስዷል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን የካቲት 12 /2014