አምቦ ወደ ከተማነት ለማደግ ዳዴ የጀመረችበት አካባቢ መሆኑ የሚነገርለትና ከተማዋ ዋነኛ እንቅስቃሴዋን ትከውንበት የነበረው ቀበሌ ስድስት አካባቢ ዛሬ ጊዜ ጥሎታል። በእጅጉ ተጠጋግተው ከእርጅና ጋር በሚገፋፉ ቤቶች ተከብቦ ይታያል። አካባቢውን ጊዜ «አረጀህ አፈጀህ» ይበለው እንጂ ከልጅነት እስከ ወጣትነት፤ ከወጣትነትም እስከ አዋቂነት የተጓዙ እድሜ ጠገብ ነዋሪዎችን በጉያው ሸሽጎ ያኖራል። ታድያ በዚህ አካባቢ ነዋሪ ስለሆኑት ስለ እናት ሊኩ ዑመር የሰማነው ታሪክ መኖሪያ ቤታቸው እንድንገኝ አስገድዶናል። እናት ሊኩ ዑመር ከሁለት ልጆቻቸው ጋር በመሆን ባለ አንድ ክፍል በሆነችው ቤታቸው ውስጥ ኑሯቸውን ለማሸነፍ ይተጋሉ።
የተጫናቸው እርጅና፣ የሚታገላቸው የኑሮን ክብደት ሚዛን በቀይ ዳማ የፊት ገጽታቸው ላይ ፍንትው ብሎ ይነበባል። በቤታቸው ግድግዳ ላይ የተሰቀሉት ፎቶ ግራፎች ግን ከዚህ በተቃራኒ ያለፈን ታሪክ ይናገራሉ። የእናት ሊኩ ቤተሰብ እንዲህ እንደ ዛሬው በአንድ ክፍል ቤት ያልተወሰነ ጥሩ ኑሮን ያጣጣመ ስለመሆኑ በአሮጌው ግድግዳ ላይ የተንጠለጠለው ፎቶ ምስክር ነው።
እርሳቸውም ሆኑ ሙሉ የቤተሰቡ አባላት በችግር ደጃፍ ያላለፉ፤ በስንክሳር ያልተፈተኑ ይመስላል። እይታዬ ከግድግዳው መቅረቱ የገባቸው እናት ሊኩ ባለቤታቸውና ልጆቻቸው መሆናቸውን ጥያቄዬን ሳይሹ ይነግሩኝ ጀመር። ትናንሽ አይኖቻቸውን ጨፈን ገለጥ በማድረግ ከራሳቸው ውጪ ሌላው በቅጡ የማያውቀውን የህይወት ጉዟቸውን መለስ ብለው ለማስታወስ ሞከሩ። «ትውልድና እድገቴ አምቦ ከተማ ነው።
የልጅነት ጨዋታ፣ የትምህርት ቤት ቆይታ፣ የወጣትነት ትኩስ ጊዜን በትውልድ መንደሬ ነበር ያሳለፍኩት። የህይወትን «ሀ…ሁ» በዚህችው ከተማ ተምሬያለሁ። የህይወቴ የልጅነት ምዕራፍ ተዘግቶ ወደ ወጣትነት የተሸጋገርኩትም በዚሁ ከተማ ነበር። የወጣትነት አፍላ የፍቅር እፍታንም በዚህችው የትውልድ መንደሬ በማጣጣም ትዳር ወደሚባለው ሰፊው የህይወት ባህር መግባት ችያለው» ይላሉ እናት ሊኩ ሀዘን በከበበውና ተስፋ በመቁረጥ ስሜት። የትዳርን ጣዕም ወደማጣጣሙ የተሸጋገረው የህይወት ጉዟቸው ከአጋራቸው ጋር በመሆን በወጉ ባማረና በደመቀ ሳሎን፤ በፍቅር በተሞላ መኝታ ቤት ቅዝቃዜ ሳይጎበኘው ዓመታትን መጓዝ ችለዋል።
ረጅሙ የትዳር ጉዞ እንዲያው ዝምና ዝግ ያለ አልነበረም። በአነስተኛ መንደር፤ በአነስተኛ ጎጆ ውስጥ የሚጓዝ ቢመስልም አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ በመባባል በጥልቅ ፍቅር የተመሰረተና ለጎረቤትና ለአካባቢው ነዋሪዎች ሁሉ ምሳሌ መሆን የቻለ ትዳር ነበር። ከዓመታት ቆይታ በኋላም ይሄን ቤተሰብ ወደ ሌላ የታሪክ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ክስተት ተፈጠረ። የቤተሰቡን ቁጥር ከሁለት ወደ አራት ከፍ የሚያደርጉ ልጆች በተከታታይ ቤተሰቡን ጎበኙት። የመጀመሪያዋ ሴት ልጅ ቤተሰቡን ወደ አዲስ ምዕራፍ ስታሸጋግር፤ ከዓመት በኋላም የተከተለው ወንድ ልጅም ለቤተሰቡ ጥልቅ የሆነ ደስታን ይዞ ተቀላቀለ። በሊኩ ቤተሰብ ውስጥ የነገሰው ፍቅርና መተሳሰብ መንጎዱን ቀጠለ። ከጊዜ በኋላ ግን የቤተሰቡ ደስታ ደፍርሶ በሀዘን ተተካ።
ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ከቤት ውጭ ደፋ ቀና በማለት የቤተሰቡን ኑሮ በኢኮኖሚ ይደግፉ የነበሩት የእናት ሊኩ ባለቤት በአጭር ጊዜ ህመም ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን ነበር። የባለቤታቸውን ሞት ተከትሎም የእናት ሊኩና የሁለት ልጆቻቸውን ህይወት ችግር ጎበኘው። ባለቤታቸው በሚሰሩት ስራ ይተዳደር የነበረ በመሆኑ የቤተሰቡ ሙሉ ኃላፊነት በእናት ሊኩ ጫንቃ ላይ ወደቀ። በዚህም የበዛ ሀዘን፣ ህመም፣ ችግር፣ ዕድሜ፣ አቅም ማጣት ተፈራረቁባቸው። በዚሁ ምክንያትም የቤተሰቡ ህልውና ፈተና ውስጥ ገባ። ችግሩ ቀጥሎ ሁለት ልጆቻቸው ከዕውቀት ገበታ ሊስተጓጎሉ ሆነ። ትምህርታቸውን ያልጨረሱ እነዚህን ታዳጊዎች ይዞ የቤት ኪራይ መክፈል፣ የትምህርት ቁሳቁሶችን አሟልቶ ማስተማርና የዕለት ጉርስ የዓመት ልብስ ማሟላት በእጅጉ ፈታኝ ቢሆንም እጅ አልሰጥም በማለት ሲንገዳገዱ ቆይተዋል። ይሁን እንጂ ተደራርቦ የመጣውን ችግርና ፈተና መቋቋም ባለመቻላቸው ተረቱ። የቤተሰቡ ሰቆቃ ከዕለት ወደ ዕለት ሽግግሩን ቀጠለ። «አታምጣ ስለው አምጥቶ…» እንዲሉ አበው፤ ከመኖር ወደ አለመኖር ተሸጋገረ፡፡
ቤት ውስጥ የሚላስ የሚቀመስ እስከ መጥፋት ደረሰ። ራስን ችሎ ከመኖር የሰው እጅ ማየትና ምፅዋት መጠበቅ የግድ ሆነ። የቤት ኪራይ የመክፈል አቅምም ተሟጠጠና ህይወት ወደ ጎዳና ተሸጋገረ። እናትም «እኔ የህይወት ሰቆቃን ባለ እዳ ሆኜ ልግፋ እንጂ፤እነርሱ ምን በወጣቸው» በማለት ታዳጊዎቹን ለቅርብ ዘመዶቻቸው አከፋፈሉ። ዘመድ አዝማዱ ፊቱን ኮሶ ቢያስመስልባቸውም፤ገጹን አጨማዶ በድምጽ አልባ ንግግር ቢያባርራቸውም ልጆቹን መቀበላቸው ትልቅ እረፍት እንዲሰማቸው ያደረገ እንደነበር ዛሬም ድረስ በተደበቀ ፈገግታ ታጅበው ያስታውሱታል። ቅዠት የሚመስለውን ትናንትን ማስታወሳ ቸውን ቀጥለዋል። «በዚህ እድሜ ጎዳና ወጥቶ ለልመና እጅ መዘርጋትን ማሰቡ ከባድ ቢመስልም፤የህይወት አንዱ አጋጣሚ ሆነና ለመኖር ተገደድኩኝ። ለዓመታት ከዚሁ ውጣ ውረድ ጋር ትግል በማድረግ ቅዠት የሚመስል ኑሮን ኖሬያለው።
እድሜ ለኡቡንቱ ይህ ቤተሰብ የህይወት ፈተናና ውጣ ውረድ የበዛበትን ትናንትና አልፎ ዛሬ በአዲስ ምዕራፍ ተተክቷል። ከባለቤቴ ሞት ማግስት የነበረው ችግር እጆቼን ለልመና እስከመዘርጋት የወረደው የህይወት ጉዞዬ እንደ ህልም ይታየኛል። ዛሬ ቀኑ አዲስ ሆኗል፤ህይወትም እንደዛው» ሲሉ በውጣ ውረድ የተሞላውን ትናንትን ይገልጹታል። ዛሬ ግን ህይወት በአዲስ ምዕራፍና ጎዳና ጉዞዋን ቀጥላለች። ‹‹ታዲያ የትናንቱ ሰቆቃና የበዛ ችግር አልፎ የዛሬው አዲስ የህይወት ምዕራፍ ጉዞ እንዴት፣ መችና በምን አጋጣሚ ተቀየረ?›› ስንል ባለታሪኳን እናት ሊኩን ጠየቅን። እናት ሊኩም፤ መሰረቱን በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ካደረገው «ኡቡንቱ» ቤተሰብ አቀፍ የልጆች ድጋፍ መስጫ የበጎ አድራጎት ድርጅት ምስጋና ይግባውና ከሞተ ተስፋ ጎትቶ አወጣኝ፤አለቀለት አበቃለት የተባለውን የሰቆቃ ሕይወቴን ቆሻሻ አራግፎ በአዲስ ምዕራፍ ሕይወቴን እንድመራ አደረገኝ›› በማለት አጫወቱን። እናት ሊኩ ይሄንኑ አጋጣሚ ለመናገር የተሰናዱት አፋቸው ቃላት ለማፍለቅ ሲዳዳው ስሜታቸው አቅጣጫውን ቀየረ። ከትናንሽ አይኖቻቸው የሚፈልቅ ዕንባ ያለማቋረጥ ችግር በሰለጠነበት ፊታቸው ላይ ይንዠቀዠቅ ጀመር። የእንባቸው ከረጢት የተቀደደ ይመስል ለመቆጣጠር አለመቻላቸው የአንደበታቸውን ቃላት አመንጪነት ገድቦት ቆየ። የተረበሸው መንፈሳቸው እስኪረጋጋ ድረስ ደቂቃዎች ነጎዱ። ከደቂቃዎች በኋላም ወደቀድሞው ስሜት በከፊል ተመልሰው እንዲህ ሲሉ ያስታውሱ ጀመር።
«መሰረቱን በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ካደረገው ‘ኡቡንቱ’ቤተሰብ አቀፍ የልጆች ድጋፍ መስጫ የበጎ አድራጎት ድርጅት ጋር በቅርብ የማውቀው ሰው ነበር ያገናኘኝ። ቆሎ ሸጬ ልጆቼን ለመመገብ የማደርገውን ጥረትና ያለሁበትን ሁኔታ እንዲሁም አጠቃላይ የህይወቴን ውጣ ውረድ በመረዳት ከኡቡንቱ መስራች ከሆኑት አቶ ሰለሞን ጋር አገናኙኝ። በርከት በማለት የምኖርበት ቤት ድረስ በመምጣት የኑሮዬን ሁኔታም ተመለከቱ። ተቋሙ የሚያደርገውን ድጋፍ በመግለጽም የኡቡንቱ ቤተሰብ በመሆን ድጋፍ እንደሚያደርጉልኝ ቃል በመግባት ተመልሰው ሄዱ›› ይላሉ። ከኡቡንቱ ጋር ከዓመት በፊት በዚህ ሁኔታ የተገናኘው የሊኩ ቤተሰብ የተለያዩ የቁሳቁስ ድጋፎችን በማግኘት መልሶ ወደ መቋቋም ተግባር ተሸጋገረ። የቤተሰቡን ተስፋ ዳግም የማለምለም ተግባሩ ደግሞ ገንዘብ በመስጠት ላይ የተንጠለጠለ ሳይሆን መስራት በሚፈልጉት የስራ መስክ ላይ አንዲሰማሩና ለዚህም መነሻ ገንዘብ በመስጠት ራሳቸውን እንዲችሉ በማድረግ ተጀመረ። የሊኩ ቤተሰብ ያላቸውን የመስራት ፍላጎት መሰረት በማድረግ መነገጃ የሚሆን አምስት ሺህ ብር በመስጠት ካለባቸው የኢኮኖሚ ችግርና ሰቆቃ እንዲላቀቁ ጅምር ስራ ተከናወነ። በኡቡንቱ ድጋፍ በህይወት ህመም ድርብርቦሽ ስንኩል ሆኖ የኖረው ቤተሰብ ዳግም ለመሰብሰብ ቻለ።
ከኡቡንቱ ባገኙት የአምስት ሺህ ብር መቋቋሚያ ቀን ቀን ጉልት በመቸርቸር፤አመሻሽ ላይ ቆሎና ሌሎች አዝዕርቶችን ቆልተው በመሸጥ የቤተሰቡን ዳግም ትንሳኤ ለማብሰር መታተር ጀመሩ። የመጀመሪያ ልጃቸውም በሌላኛው ጫፍ የቤተሰቡን ችግር ለመጋራት ባደረገችው ጥረት ወደውጭ በመሄድ መስራትን አማራጭ በማድረግ ወደ አረብ ሀገር ለመጓዝ በመንግስት የተዘጋጀላትን የሁለት ወራት ስልጠና እየወሰደች ትገኛለች። እናት ሊኩ ስለ ሴት ልጃቸው የአረብ ሀገር ጉዞ ሲናገሩ፣ «በሀገርሽ ሰርተሽ መለወጥ ትችያለሽ ብለን ብንመክራትም፤ ‘የለም ሀርሜ ኮ የተወሰነ ዓመት ዓረብ ሀገር ሰርቼ በችግር ማዕበል የተናወጠውን ቤተሰብ እንዲረጋ አደርገዋለው’ አለችኝ፡፡
በዚህም ሀሳቧን መግፋት አልቻልኩም» በማለት ይናገራሉ። የኡቡንቱን ውለታ ተናገረው የማይጠግቡት እናት፣ ልጃቸው ለዚሁ ጉዳይ አዲስ አበባ የምትመላለስበትና ሌሎች ወጪዎችን የምትሸፍነው ድርጅቱ በከፈተላቸው የሂሳብ ደብተር ላይ ባጠራቀሙት ገንዘብ መሆኑንም በደስታ ይናገራሉ። ተቋሙ በዚህ ቤተሰብ ላይ እየሰራ ያለው መልካም ስራ ለትንሹ ልጃቸውም ተደራሽ ሆኗል። ወንድ ልጃቸው በአሁኑ ወቅት ዩኒቨርሲቲው በር ላይ ሊስትሮ እንዲሰራ ቦታ ተመቻችቶለት እየሰራ የሚገኝ ሲሆን፤በቀጣይም ሌሎች ድጋፎች እንደሚደረግላቸውና ሸብቦ የያዛቸውን የቤት ችግርምእንደሚቀረፍላቸው ተስፋ በማድረግ ሀሳባቸውን ይቋጫሉ። ይህ መሰረቱን በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ያደረገው «ኡቡንቱ» ቤተሰብ አቀፍ የልጆች ድጋፍ መስጫ የበጎ አድራጎት ድርጅት እንደ እናት ሊኩ ቤተሰብ ሁሉ 135 ቤተሰቦችን በማቀፍ ድጋፍ እየሰጠ የሚገኝ ግብረ ሰናይ ደርጅት ነው። በዚህ ድርጅትም የተመሳሳይ ታሪክ ባለቤት የሆኑ አብዛኛዎቹ ቤተሰቦች በእናት ብቻ የሚተዳደሩ ናቸው። ለእነዚህ ቤተሰቦች አምስት ሺህ ብር ለመስሪያ የሚሆን መነሻ ገንዘብ በመስጠት ለማቋቋም ጥረት ይደረጋል። ከዚህ በተጨማሪም የሚያስፈልጉ አልባሳት እንደ ብርድ ልብስ፣ አንሶላና የመማሪያ ቁሳቁሶችን ድጋፍ እያደረገ የሚገኝ ድርጅት ነው። በአምቦ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የኡቡንቱ ቤተሰብአቀፍ የልጆችድጋፍ ሰጪ ድርጅት መስራችና ኃላፊ አቶ ሰለሞን አለሙ ስለ ድርጅቱ እንዲህ ይላ፡፡
የሚከተለውን ብለዋል። «ኡቡንቱ» አንዱ እያዘነ እንዴት ሌላው ደስተኛ ይሆናል የሚል ትርጓሜ አለው፡፡ በድህነት ምክንያት ልጆቻቸውን ማስተማር ያልቻሉ ቤተሰቦችን የመደገፍ ዓላማን በመሰነቅ በ12 የዩኒቨርሲቲው መምህራን ከአራት ዓመት በፊት የተመሰረተና በአሁኑ ወቅት 360 አባላትን አቅፎ የሚንቀሳቀስ በሀገር አቀፍ ደረጃ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ የተቋቋመ ቀዳሚው የበጎ አድራጎት ድርጅት ነው››። እንደ አቶ ሰለሞን ማብራሪያ፣ ድርጅቱ በየዓመቱ ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን እየረዳ አራት ዓመታትን አስቆጥሯል። በመጀመሪያው ዙር 26፣ በሁለተኛው ዙር 27፣ በሶስተኛው ዙር 39 እንዲሁም በአራተኛው ዙር 43 ቤተሰቦችን ተቀብሎ ሲያግዛቸው ቆይቷል። ለእነዚህ ቤተሰቦች አምስት ሺህ ብር ለስራ መነሻ የሚሆን ገንዘብ በመስጠት እንዲቋቋሙ የሚደረግ ሲሆን፤ በተጨማሪም አስፈላጊ የሆኑ አልባሳት እንደ ብርድ ልብስ፣ አንሶላና የመማሪያ ቁሳቁሶችንም በማቅረብ ድጋፍ ያደርጋል። ኡቡንቱ በቀጣይም ችግረኛ የሆኑ ቤተሰቦችን በዘላቂነት ለመርዳት ሰፊ ዕቅድ እንደያዘ የተናገሩት አቶሰለሞን፣ የቤተሰቦቹን መሰረታዊ ችግር በመረዳት «ኡቡንቱ ቪሌጅ»በሚል ስያሜ በአነስተኛ ወጪ ለ100 ቤተሰቦችየ መኖሪያ ቤት ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል። በመሆኑም ከተማ አስተዳደሩ መሬት እንዲሰጣቸው ጥያቄ አቅርበው በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ሰለሞን አጋር ድርጅቶችንና የዩኒቨርሲቲውንማህበረሰብ በማሳተፍ በቀጣይ ዓመት የቤቱን ግንባታ አጠናቅቀው ለማስረከብ እየሰሩ መሆናቸውን በመግለፅ ሀሳባቸውን ቋጭተዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 4/2011