የ26 ዓመት ወጣት ናት። ተወልዳ ያደገችው አሶሳ ከተማ ሲሆን የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በአዲስ አበባ ከተማ ተከታትላለች።
የዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን ደግሞ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በመከታተል በኤሌክትሪካል ኢንጅነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪዋን አግኝታለች። ትምህርቷን አጠናቅቃ በተማረችበት የትምህርት ዘርፍ ሥራ ማግኘት በወቅቱ ፈተና ሆኖባታል።
ይሁንና ማንኛውንም ሥራ ለመሥራት ዝግጁ ነበረችና በአንድ የሶፍትዌር ኩባንያ በማርኬቲንግ ዘርፍ ለአንድ ዓመት ከስድስት ወራት አገልግላለች፡፡ ወጣቷ አጥብቃ በትምህርት የምታምን ናት፤ ማንኛውንም ችግር ለመፍታት ትምህርት ወሳኝ ነው የሚል መርህም አላት። ስለዚህ ማንኛውም ቢዝነስ በትምህርት መደገፍ ከቻለ ውጤታማ መሆን ይችላል ትላለች።
ባገኘችው አጋጣሚ ሁሉ ትምህርት መማር ያስደስታታል። በመሆኑም ከተማረችበት የትምህርት ዘርፍ ውጪ በሆነው የማርኬቲንግ ዘርፍ ተቀጥራ በምትሠራበት ወቅትም ሥራው በወረቀት መደገፍ አለበት የሚል አቋም ይዛ እየሠራች የማርኬቲንግ ትምህርቷን ተከታትላ ሁለተኛ ዲግሪዋን አግኝታለች፡፡ በኤሌክትሪካል ኢንጅነሪንግ እንዲሁም በማርኬቲንግ ትምህርት ዘርፍ ከመሥራት ባለፈ ምሩቅ የሆነችው የዛሬዋ እንግዳችን ወጣት ሰላማዊት ዓለሙ ትባላለች።
በሥራና በትምህርት የምታምነው ሰላማዊት በግሏ መሥራትን አስባ ከመደበኛው ትምህርት በተጨማሪ ተማሪዎችን ቤት ለቤት ማስጠናት የሚያስችል ፊደል ቲቶሪያል ኮንሰልት የተባለ ድርጅት አቋቁማለች። ሥራ በመቀጠር ብቻ ሳይሆን የራስንም ሥራ ፈጥሮ መሥራት ውጤታማ ያደርጋል ብላም ታስባለች። በዚሁ መሠረት የራሷን የግል ሥራ ወደመሥራቱ አዘነበለች። የፊደል ቱቶሪያል ኮንሰልት መሥራችና ሥራአስኪጅ ወጣት ሰላማዊት፤ የግል ሥራ መሥራትን ስታስብ ቀድሞ ወደ አዕምሮዋ የመጣው ተማሪዎችን ቤት ለቤት ማስጠናት ወይም በትምህርት ማገዝ የሚል ነው።
ለዚህ ደግሞ ምክንያቷ በአዳማ ዩኒቨርሲቲ የ4ኛ ዓመት ተማሪ በነበረችበት ወቅት በነበራት ትርፍ ጊዜ ቤት ለቤት በመዘዋወር ተማሪዎችን በማስጠናት ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዋን መመለስ በመቻሏ ነው። በወቅቱ አዋጭ ሥራ እንደነበር በመረዳቷ ትምህርቷን አጠናቅቃ አዲስ አበባ በግል ድርጅት ተቀጥራ በምትሠራበት ጊዜም ከሥራ ሰዓት ውጪ ቤት ለቤት ማስጠናትን ተጨማሪ ሥራ አድርጋ ቆይታለች፡፡ ከትምህርቷ ጎን ለጎን እንዲሁም በሥራ ላይ ተጨማሪ ሥራ አድርጋ የቆየችው ቤት ለቤት የማስጠናት ሥራን አጠናክራ በስፋት ብትሠራበት አዋጭና ተመራጭ እንደሆነ በማሰብ ዘርፉን ተቀላቀለች።
ሥራውን ለመሥራት ስትነሳ ታዲያ አንድ እሷ ብቻዋን ስትሠራ በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ ስድስት ተማሪዎች ነበሯት። ከዚያም በላይ አገልግሎቱን የሚፈልጉ ሰዎች እንደነበሩ አስተውላለች። በዚህ ጊዜ ታዲያ አገልግሎቱ በስፋት የሚፈለግ ከሆነ ሥራውም መስፋት አለበት የሚል ሀሳብ በማመንጨት በስፋት ወደ ሥራው መግባት ወሰነች።
ወደ ሥራው ለመግባት ስትወስን ታዲያ ‹‹ከአንድ ብርቱ ሁለት መድኃኒቱ›› እንዲሉ በሥራው መሳተፍ የሚችሉና ፍላጎት ያላቸውን አባላት ማሰባሰብ ቀዳሚ ሥራዋም ነበር፡፡ ሥራውን በስፋት ለመሥራት ያነሳሳት ከወላጆች በኩል ያለው ከፍተኛ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ቤት ለቤት በምታስጠናበት ወቅት ተማሪዎች ላይ ፈጠርኩት የምትለው በጎ ተጽዕኖ ጭምር መሆኑን ትናገራለች።
ሰላማዊት ተማሪዎች እገዛ ካገኙ ውጤታማ መሆን እና መድረስ የሚፈልጉበት ቦታ መድረስ ይችላሉ የሚል እምነት አላት። አንዳንድ ጊዜ እኩል መሄድ ያልቻሉ ልጆች ትንሽ እገዛ ሲያገኙ ውጤታማ ሆነው በማየቷም ከመደሰቷ ባለፈ ብዙዎች ጋር መድረስ እንዳለበትና በተያያዘም ሥራው ቢዝነስ ሆኖ ሲቀጥል የሚሰጠው ጠቀሜታ የጎላ ነው ብላም ታምናለች።
በተለይም በአገራችን ከአንድ በላይ ሥራ መሥራት የተለመደ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ የግል አስተማሪነት (አስጠኚ) ሥራ ደግሞ በአብዛኛው ከሥራ ሰዓት ውጪ የሚሠራ በመሆኑ ተጨማሪ ሥራን በማስለመድ በኩልም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው ነው የምትለው ወጣት ሰላማዊት፤ ማንኛውም ሰው ከሥራ ሲወጣ መሥራት የሚችለው ሥራ እንደመሆኑ ተጨማሪ ገቢ የማግኛ አንዱ መንገድም ነው ትላለች። እነዚህንና መሰል ጠቀሜታዎቹን ከግንዛቤ ማስገባት የቻለችው ሰላማዊት ታዲያ ‹‹ፊደል ቲቶሪያ›› የሚል ቤት ለቤት ተማሪዎችን ማስጠናት የሚችል ድርጅት መክፈቷም ለዚሁ ነው።
የቤት ለቤት የማስጠናት ሥራ በሥራ ላይ ያሉ ሰዎችም ሆኑ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መሥራት የሚችሉት ሥራ በመሆኑ ለበርካቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ያስችላል የምትለው ሰላማዊት፤ በሥራው መሳተፍ የሚችሉ የዲግሪ ምሩቃን የሆኑና በማንኛውም ዓይነት ሥራ ላይ የተሰማሩና ሥራ የሌላቸውም ቢሆኑ ማታ ላይ ወጥተው መሥራት እንዲችሉ እንዲሁም ተማሪዎችን ከዩኒቨርሲቲ በማሰባሰብ ሥራውን መሥራት እንዲችሉ የማመቻቸት ሥራ መሥራቷን ትናገራለች።
የትምህርት ዝግጅቷ ኤሌክትሪካል ኢንጅነሪንግ እንደመሆኑ ሥራውን ማሳለጥ የሚያስችል ቴክኖሎጂን በመጠቀም ፕላት ፎርም ቀርጻ ሥራዎቹ ሁሉ በዌብሳይት እንዲቀጥሉ አድርጋለች። ይህም ሲባል ፊደል ቲቶሪያል በሚለው የመረጃ መረብ በመጠቀም ማንም ሰው የሚፈልገውን አገልግሎት በቀላሉ ማግኘት እንዲችል ሆኗል። ሠራተኞቹ ሳይቀሩ የሰዓት ፊርማ መቆጣጠሪያን በዲጅታል ቴክኖሎጂው ተጠቅመው እንዲፈርሙ በማድረግ የወረቀት ሥራዎችን ማስቀረትም ችላለች።
አገልግሎቱን የሚፈልጉ ወላጆችም ዌብሳይቱን በመጠቀም በፊደል ቲቶሪያል ውስጥ ከሚገኙ 250 አስጠኚዎች መካከል ለልጁ የሚፈልገውን መምህር ከጾታው ጀምሮ ከዚህ ቀደም ባለው ልምድና ችሎታ እንዲሁም በሚፈልገው የትምህርት ዓይነት አስጠኚውን ከዌብሳይቱ ላይ መርጦ ማግኘት እንደሚችል ታስረዳለች። 250ዎቹ አስጠኚዎችም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ መሆናቸውን ወጣት ሰላማዊት ትናገራለች። ከፊደል ቲቶሪያል ጋር በጋራ እየሠሩ ያሉት 250 አስጠኚዎችም አመልክተው የተመዘገቡና ፈተና ተፈትነው ብቁ ናቸው ተብለው የተመረጡ ሲሆኑ ወላጆች ለልጆቻቸው የሚመርጧቸው አስጠኚዎችም ከእነዚሁ መካከል ነው። ስለዚህ ፊደል ቲቶሪያል ለወላጆች አማራጭ እያቀረበ የሚገኝ ድርጅት እንደመሆኑ ወላጆች የሚያቀርቡት ሀሳብ ካለም ያንን ሀሳባቸውን በመቀበል የሚፈልጉትን አገልግሎት ያቀርባል።
አገልግሎቱን በተሳካ መንገድ መስጠት እንዲቻልም አስጠኚዎች በየአካባቢው የሚገኙ መሆናቸው ትልቅ ጠቀሜታ አለው ትላለች፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ እያለች ጀምሮ ለትምህርት ልዩ ፍቅር ያላትና ትምህርትን አጥብቃ ትወድ ነበር። በተለይም ለሒሳብ፣ ለፊዚክስና ለኬሚስትሪ ትምህርቶች ታደላ እንደነበርና ቤት ለቤት እየተዘዋወረች ታስጠና የነበረውም የሳይንስ ትምህርቶችን እንደነበር ታስታውሳለች።
ትምህርት አስፈላጊ ነው ከሚሉ ሰዎች መካከል የምትመደብ እንደመሆኑም ማንኛውም ሥራ በትምህርት ቢደገፍ ውጤቱ ያማረና የሰመረ እንደሚሆን ታምናለች፡፡ በአሁኑ ወቅት በቴክኖሎጂ ታግዞ መሥራት ጊዜ፣ ጉልበትና ገንዘብን የሚቆጥብ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ቴክኖሎጂው ለሥራዋ በብዙ ያገዛት መሆኑን ትናገራለች። ለአብነትም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅት ተማሪዎች ቤት ሲቀሩ በተመሳሳይ ደግሞ ወደ ተማሪዎቹ ጋር መሄድ አስፈሪ የነበር በመሆኑ ቴክኖሎጂውን በመጠቀም በኦን ላይን የቤት ለቤት ትምህርት ትሰጥ ነበር።
በወቅቱ ብዙ ሰዎች በቤታቸው ኢንተርኔት ማስገባት በመቻላቸው ለዲጅታል ቴክኖሎጂው ቅርብ መሆን ቻሉ። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ‹‹ፊደል ቲቶሪያልን ዲጅታል ቴክኖሎጂን›› በመጠቀም በስፋት ተደራሽ ለማድረግ ጥሩ ዕድል መፍጠር እንደቻለ የምትናገረው ሰላማዊት፤ ከአስጠኚዎች ጋርም ሆነ ከወላጆች ጋር የሚኖረው ማንኛውም ዓይነት ግንኙነት ክፍያን ጨምሮ የሚከናወነው በዲጅታል ቴክኖሎጂ ነው ትላለች፡፡ አንድ አስጠኚ በአማካኝ ለአንድ ተማሪ እስከ ሁለት ሺ ብር የሚከፈለው ሲሆን አስጠኚው በሚችለው አቅም ሁለትም ሦስትም ተማሪ ሊይዝ ይችላል። አንድ ተማሪ ማጥናት ያለበት ለአንድ ሰዓት ቆይታ ያለው በሳምንት ሦስት ቀናት ብቻ ነው።
ተማሪዎች በክፍል ውስጥ ከተማሩት ትምህርት በተጨማሪ በቤታቸው መታገዝ ከቻሉ ውጤታማ መሆን ይችላሉ የምትለው ሰላማዊት፤ ድርጅቷን ወክላ በሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ላይ በነበረ ውድድር ትምህርትን ማገዝ በሚል ተሳታፊ እንደነበረች ታስታውሳለች። የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽንም አወዳድሮ ከመረጣቸው የተለያዩ ዘርፎች መካከል ከምርጥ 20ዎቹ መካከል 10ሩን መቀላቀል በመቻሏ የተለያዩ እገዛዎችን ከሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽኑ ማግኘት ችላለች። በተለያዩ ባለሙያዎች እገዛና ድጋፍ ከማግኘት ጀምሮ ሥራዋን ማስፋፋት የምትችልበትን የገንዘብ ድጋፍም አግኝታበታለች። ከዚህ በተጨማሪም በተለያዩ ሚዲያዎች ሥራዋን ማስተዋወቅ የምትችልበት ዕድል የተመቻቸ በመሆኑ ፊደል ቲቶሪያል በከተማ ውስጥ በስፋት ማስተዋወቅ ተችሏል ትላለች፡፡ ማህበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንጻር ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ እየሠራች መሆኑን የምትናገረው ሰላማዊት፤ ተማሪዎች በትምህርት ዓለም እያሉ የሥራ መንፈስን መለማመድ እንዲችሉ በማሰብ ከፊደል ቲቶሪያል ጋር በጋራ በመሆን በትርፍ ሰዓታቸው መሥራት እንዲችሉ በማመቻቸት ላይ ትገኛለች። ተማሪዎቹ ተማሪ እያሉ የሥራ ባህልን ከመልመድ ባለፈ ማህበረሰቡን አገልግለው ኢኮኖሚያቸውንም መደገፍ ያስችላቸዋል።
በመሆኑም እሷ በትምህርት ዘርፍ የጀመረችውን ተግባር ሌሎች ተቋማትም ልምድ ቢያደርጉት ተማሪዎቹ እራሳቸውን ከማብቃት ባለፈ ወደ ሥራ ዓለም ሲቀላቀሉ ውጤታማ መሆን ይችላሉ። ትምህርት ላይ እየሠራሁ እንደመሆኑ በተለያዩ መንግሥት ትምህርት ቤቶች ላይ በመዘዋወር ውጤታቸው ደከም ያሉ ተማሪዎች ፊደል ቲቶሪያል የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች እንዲጠቀሙ የማድረግ ሥራ እንሠራለን። በተለይም ከግማሽ በታች ውጤት የሚያመጡ ተማሪዎች ወላጆች ወጪ አውጥተው ማስጠናት ባይችሉም የተለያዩ የውጭ ድርጅቶችን በማፈላለግ እንዲያግዟቸው የማድረግ ሥራም እየሠራች ነው። በዚህም ማህበራዊ ኃላፊነትን መወጣት መቻሏን ወጣት ሰላማዊት ትናገራለች። በአሁኑ ወቅት ከ250 አስጠኚዎች በተጨማሪ ለ12 ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለችው ወጣት ሰላማዊት፤ በቀጣይም ሥራውን በማስፋፋት ከአዲስ አበባ ውጪ በሚገኙ የክልል ከተሞች የቲቶሪያል ትምህርትን የማስፋፋት ዕቅድ አላት።
በተጨማሪም በየክፍል ደረጃው የሚገኙ ተማሪዎችን በጥናት ወቅት በተለይም ብቻቸውን ሆነው በሚያጠኑበት ጊዜ ሊያግዛቸው የሚችል መርጃ መሣሪያዎችን በማዘጋጀት ለተማሪዎች ተደራሽ ለማድረግ በዝግጅት ላይ ትገኛለች፡፡ ተማሪዎች ከሚማሩት ትምህርት በተጨማሪ ሌሎች የዕውቀት ዘርፎችን በመከታተል ያላቸውን ዝንባሌ አውጥተው መጠቀም አስፈላጊ እንደሆነ የምታምነው ሰላማዊት፤ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ 80 በሚደርሱ የተለያዩ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ላይ የተለያዩ የጥያቄና መልስ ውድድሮችን በማድረግ ተማሪዎች ፍላጎታቸውን ማውጣት የሚችሉበት ዕድል በተለያየ ጊዜ ይፈጠራል። ውድድሩም በቀጣይ ተጠናክሮ የሚቀጥል በመሆኑ በተማሪዎችና በትምህርት ቤቶች መካከል ጠንካራ የሆነ የውድድርና የፉክክር መንፈስን መፍጠር የሚያስችል ነው።
‹‹ፊደል ቲቶሪያል›› ከአገር ውስጥ አልፎ በውጭ አገራትም አገልግሎት መስጠት የጀመረ ሲሆን ልጆቻቸውን አማርኛ ቋንቋ እና ግዕዝ የማስተማር ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ዌብሳይቱን በመጠቀም እየተቀላቀሉ መሆኑን ያመላከተችው ሰላማዊት በተለይም የኢትዮጵያን ቋንቋና ታሪክ በስፋት እያስተማሩ እንደሆነ ትናገራለች።
በቀጣይም ከአዲስ አበባ ከተማ ውጪ በሚገኙ በሁሉም የአገሪቷ ክልሎች ተመጣጣኝ በሆነ ክፍያ ተደራሽ ለመሆን ያላትን ዕቅድ በመግለጽ በተያያዘም ዘርፉ ሊስፋፋ የሚችልና ለበርካቶችም ተጨማሪ የሥራ ዕድል የሚፈጥር እንደሆነ ያላትን ሙሉ ዕምነት በመግለጽ ሀሳቧን ቋጭታለች።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን የካቲት 12 /2014