የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተከሰተ ወዲህ አገራት ቫይረሱን ለመከላከል የሚያግዙ ክትባቶችን ለማግኘት ሲሯሯጡ ቆይተዋል፡፡
ይህም ተሳክቶላቸው ቫይረሱን ሙሉ በሙሉ የመከላከል ብቃት ያለው ክትባት ባያገኙም ከ90 በመቶ በላይ የመከላከል አቅም ያላቸውን አዳዲስ ክትባቶችን በምርምር አግኝተዋል፡፡ ክትባቶቹ በዓለምአቀፍ ደረጃ ለዜጎች ተሰራጭተውም ውጤታማ ሆነዋል፡፡
ኢትዮጵያም ቀደም ሲል ኮቫክስ በተሰኘው ዓለምአቀፍ የክትባት ጥምረት አማካኝነት ለመጀመሪያ ጊዜ 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶዝ የአስትራዜኒካ ክትባቶችን አስገብታ ለቫይረሱ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንዲከተቡ ተደርጓል፡፡
በሂደት ደግሞ ሲኖፋርምና ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን የተሰኙ ክትባቶችን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት በየደረጃው ያሉና ለቫይረሱ ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንዲከተቡ ተደርጓል፡፡ በቅርቡ ደግሞ ፋይዘር የተሰኘ ተጨማሪ ክትባት ወደ አገር ውስጥ ገብቶ ዕድሜያቸው አስራ ሁለትና ከዚያ በላይ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች በዘመቻ ተሰጥቷል፡፡ ከዚህ ውጪ በ2014 በጀት አመት በዘመቻ ብቻ ከ5 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎችን መከተብ ተችሏል፡፡ እስካሁን ባለው ሂደትም የዘመቻውን ጨምሮ ባጠቃላይ 10 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ክትባት አግኝተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ጤና ሚኒስቴር ከ20 እስከ 30 ሚሊዮን የሚጠጉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በክትባት ተደራሽ ለማድረግ ሁለተኛ ዙር የክትባት ዘመቻ መርሃግብር ከሰሞኑ አስጀምሯል፡፡
በጤና ሚኒስቴር የብሔራዊ ክትባት ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ዮሐንስ ላቀው እንደሚሉት ቀደም ሲል የኮቪድ-19 ክትባት በጤና ተቋማትና በተለያዩ ጊዜያዊ የክትባት ጣቢያዎች ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ በኋላ ላይ ደግሞ የመጀመሪያው ዙር ክትባት ዘመቻ በ2014 ዓ.ም በኅዳር ወር መጨረሻና ታኅሣሥ ወር መጀመሪያ ላይ ተከናውኗል፡ ፡ በዚህ ዘመቻም ከ5 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ተከትበዋል፡፡ ከዘመቻው በፊት የተከተቡትን ሰዎች ሲጨምር ደግሞ ቁጥሩ 10 ሚሊዮን ይደርሳል፡፡
በመጀመሪያው ዙር ዘመቻ በሁለት ሳምንታት ውስጥ 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ያህል ሕዝብ መከተብ የተቻለ ሲሆን በአጭር ጊዜ ይህን ያህል ሕዝብ መከተብ የተቻለውም በርካታ የቅስቀሳ ሥራዎችን በመስራት፣ በርካታ ከታቢ ባለሞያዎችን በማሰማራት፣ ብዙ ሴክተሮችን በማሳተፍና ብዛት ያላቸው ክትባቶችን እስከታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል ተደራሽ በማድረግ ነው፡፡
በዚህም ትልቅ ውጤት ማስመዘገብ ከመቻሉም በላይ በአፍሪካም በዘመቻ መልክ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ የተከተበበት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ እንደ አስተባባሪው ገለፃ የሁለተኛው ዙር የኮቪድ19 የክትባት ዘመቻ ከየካቲት 7 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ እየተሰጠ ሲሆን የተሰራጨውን ጨምሮ 30 ሚሊዮን የሚጠጋ ክትባት ተዘጋጅቷል፡፡ 20 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎችን በክትባቱ ተደራሽ ለማድረግም ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡
በኅብረተሰቡ በኩል የመከተብ ፍላጎት እያደገ በሄደ ቁጥር ደግሞ ከዚህም በላይ ለመከተብ እቅድ ተይዟል፡፡ በዚህ የክትባት ዘመቻ ዕድሜያቸው ከ12 ዓመት በላይ የሆኑ፣ ከዚህ ቀደም ክትባቱን ያልወሰዱ፣ የመጀመሪያውን ክትባት ወስደው ሁለተኛውን በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ፣ ከዚህ በፊት ሙሉ የኮቪድ ክትባት ወስደው ስድስት ወር የሞላቸውና አሁን ላይ የማጠናከሪያ ክትባት /booster dose/ መውሰድ የሚፈለጉ ክትባት ይወስዳሉ፡፡ የክትባት ዘመቻው በአንድና በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅ እየተሠራ የሚገኝ ሲሆን በጤና ሚኒስቴር በኩል ከየካቲት ሰባት እስከ ሃያ አንድ መርሃ ግብር ተይዞለታል፡፡
ይሁንና ክልሎች እንደራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ ክትባቱን በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ እንዲያከናውኑ መመሪያ ተላልፏል፡፡ ክትባቱም በጤና ጣቢያዎችና በጊዜያዊ የክትባት መስጫ ጣቢያዎች ይሰጣል፡፡ እስካሁን አራት የሚሆኑ ክትባቶች ወደ አገር ውስጥ የገቡ መሆናቸው የሚታወቅ ሲሆን በዚህ ዘመቻም የጆንሰን ኤንድ ጆንሰን፣ ፋይዘርና ሲኖፋርም ክትባቶች ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡ በሂደት ደግሞ ሌሎች ክትባቶች ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ የሚሰራጩ ይሆናል፡፡
አስተባባሪው እንደሚሉት ከዚህ በፊት ክትባቱን የክትባት ዘመቻውን ለሁለንተናዊ ደህንነት ላለመውሰድ ማንገራገርና አለመፈለግን ጨምሮ ሌሎች ችግሮች ከኅብረተሰቡ በኩል ይታዩ ነበር፡፡ አብዛኛው ሰውም ቫይረሱን እየፈራው አይደለም፡፡ እውነታው ግን ሰዎች በየጊዜው በቫይረሱ እየተያዙና እየሞቱ እንደሆነ ሪፖርቶች ያሳያሉ፡፡ አንድ የቤተሰብ አባል በቫይረሱ ምክንያት በሞተ ቁጥር ደግሞ በቀሪው ቤተሰብ ላይ የሚደርሰው ሁለንተናዊ ጉዳት በግልፅ እየታየ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ኅብረተሰቡ ኮቪድን አቅልሎ ማየት የለበትም፡፡
ቫይረሱ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊም ሆነ በፖለቲካው መስክ እያመጣ ያለው ቀውስ ቀላል ባለመሆኑ በመፍትሄው ላይ በጋራ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ጤና ሚኒስቴር ያወጣቸው መመሪያዎችን ሁሉ መተግበር በተለይ ደግሞ መከተብ፣ ማህበራዊ ርቀትን መጠበቅ፣ የአፍና አፍንጫ ጭምብሎችን መልበስና የእጆችን ንፅህና መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ በርካታ መዘናጋቶች ባሉበት በዚህ ጊዜ ደግሞ የኮቪድ19 ክትባቱን መውሰድ ደግሞ እጅግ ጠቃሚ በመሆኑ ኅብረተሰቡ ክትባቱን በመወሰድ ራሱንና ቤተሰቡን ከቫይረሱ መከላከል ይጠበቅበታል፡፡ ይህ የዘመቻ ክትባት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ሲሆን በቅድሚያ ተጠቃሚ የሚሆነው ተከታቢው ነው፡፡
በመቀጠል ግን የእያንዳንዱ ግለሰብ በተከተበ ቁጥር በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለው የቫይረሱ ስርጭት መጠን ስለሚቀንስ ወረርሽኙን በመግታት ረገድ ጉልህ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡ ብዙ ሰው ባልተከተበ ቁጥር ሊከሰት የሚችለውን አዳዲስ የኮቪድ-19 ቫይረስ ዝርያዎች እንዳይፈጠሩ በማድረግ ረገድም ሚናው የጎላ ነው፡ ፡ የክትባት ዘመቻው ከጤና ጥቅም ባለፈ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥቅሞችንም ይዞ ይመጣል፡፡
ኮቪድ-19 ዓለምአቀፍ ስጋት ሆኖ ከቀጠለና አሁንም ሰዎችን እየገደለ ከሄደ በቀጣይ በጤና ሚኒስቴር በኩል ቫይረሱን የመከላከል ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ የክትባት ዘመቻዎቹም በቁጥርም በስፋትም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ሌሎችም ሥራዎች በተመሳሳይ ይሠራሉ፡፡
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን የካቲት 12 /2014